Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

በዳበረ ልምድና በተሟላ ኢትዮጵያዊነት ችግሮች ሲፈቱ

0 384

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

በዳበረ ልምድና በተሟላ ኢትዮጵያዊነት ችግሮች ሲፈቱ

ዮናስ

የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የዛሬ ሁለት አመት ግድም ከነሃሴ 10-15/2008 ዓ.ም ድረስ ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ ያለፉትን አስራ አምስት ዓመታት የለውጥ ጉዞ በመገምገም በአንድ በኩል በእስካሁኑ ትግል የተመዘገቡ ውጤቶችን አጠናክሮ ለመቀጠል፣ በሌላ በኩል ደግሞ ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ ስርዓቱን የሚፈታተኑ ችግሮችን በመቅረፍ የህዝብ መብትና ተጠቃሚነትን ለማጎልበት የሚያስችሉ ውሳኔዎችን አሳልፎ የነበረ መሆኑ ይታወሳል፡፡ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው በድርጅቱ የቀረበውን የአስራ አምስት ዓመታት የለውጥ ሂደት የሚመለከት የግምገማ ሃሳብ መነሻ በማድረግ በዚህ ሂደት በአገራችን የተመዘገቡ አዎንታዊ ለውጦችና በተጨባጭ የሚታዩ ድክመቶችን በዝርዝር ገምግሞ የነበረ መሆኑም በተመሳሳይ፡፡

በዚህ ግምገማ በአገራችን ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ህገ መንግስታዊ ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ስርዓት ግንባታ በመካሄድ ላይ መሆኑ፤የዴሞክራሲያዊ ፖለቲካዊ ስርዓት ግንባታ ሂደት የዜጎችና የልዩ ልዩ ማህበረሰቦች የፖለቲካ መብቶች ህጋዊ እውቅናና ዋስትና አግኝተው መከበራቸውን፤ የብሄር ብሄረሰቦችን ማንነት ያስከበረ አዲስ ዓይነት ፌደራላዊ የእኩልነት ስርዓት መገንባቱ፤ የሃይማኖት እኩልነት ተከብሮ መንግስትና ሃይማኖት መነጣጠላቸው፤ የዜጎችና የመላው ህዝብ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዲከበሩ ቅድሚያ ሰጥቶ የተጀመረው የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ህዝብ የሚጠቀምበት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ስርዓት በመገንባት ረገድ ረጅም ርቀት መጓዝ የተቻለ መሆኑ ተመልክቷል፡፡

ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ይህን መነሻ በማድረግ ባካሄደው ግምገማ በአሁኑ ጊዜ ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓቱን ከሚፈታተኑት ችግሮች መካከል አንዱ የመንግስት ስልጣን የህዝብን ኑሮ ለማሻሻልና አገራዊ ለውጡን ለማስቀጠል እንዲሆን ከማድረግ ይልቅ የግል ኑሮ መሰረት አድርጎ የመመልከትና በአንዳንዶችም ዘንድ የግል ጥቅም ከማስቀደም ጋር የተያያዘ እንደሆነ ማረጋገጡንም ገልጦልን የነበረ መሆኑ ይታወሳል፡፡ አገራዊ ለውጡ በስኬት ሲጓዝ የቆየው መንግስታዊ ስልጣንን ለህዝብ ጥቅም ማስከበሪያ ማድረግ በመቻሉ የሆነውን ያህል ይህ ስልጣን ያለአግባብ ለመጠቀም ለሚሹ ግለሰቦች በመሳሪያነት ማገልገል ሲጀምር የተጀመረው ልማት መደነቃቀፉና መልካም አስተዳደርም መጥፋቱ በተመሳሳይ በግምገማ ውጤቱ ተመልክቷል፡፡ ከዚህ በመነሳት ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ደረጃውና መጠኑ ምንም ይሁን ምን የመንግስት ስልጣንን ያለአግባብ ለግል ኑሮ መሰረት ለማድረግ የሚታየው ዝንባሌና ስህተት መታረምና መገታት እንዳለበት፣ ይህን ለማድረግ የሚያስችል ተጨማሪ እርምጃም መውሰድ እንዳለበት ወስኖ የነበረ መሆኑም ይታወሳል፡፡ ዝንባሌው በሚታይባቸው ቦታዎች ሁሉ በአግባቡ እየተፈተሸ እንዲስተካከልና የድርጅቱን ጥራትና ጥንካሬ ተጠብቆ እንዲቀጥል አስፈላጊ የሆነው ርምጃ ሁሉ እንዲወሰድ ሲወስንም፤ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው በዚህ ረገድ ከራሱ ጀምሮ የሚታዩ የጥገኝነት አስተሳሰቦችና መገለጫ የሆኑትን ጠባብነትና ትምክህተኝነትነ እንዲሁም የጥገኝነት ተግባራትን በጥብቅ በመታገል ይህ አዝማሚያ እንዲገታ ለማድረግ የሚያስችሉ ዝርዝር ዕቅዶችም ማዘጋጀቱንም ገልጾ መላው ህዝብ ከጎኑ እንዲሰለፍ ጠይቋል።

ያም ሆኖ ግን ችግሮች ከጊዜ ወደጊዜ እየተባባሱ እስካሁን ከመዝለቃቸውም በላይ ደም አፋሳሽ ግጭቶች ገጥመውናል።ይህን ለማረቅም ላለፉት አስራ ስምንት ቀናት ስራ አስፈጻሚው ሲወያይ ከርሟል። ከቀናቱ መርዘምና ምስቅልቅሉ ላሳለፍነው ሁለት አመታት መቀጠሉ ደግሞ ተስፋ ቆራጩን ህዝብ አበራክቶታል።ስለሆነም የድርጅቱን ያለፉ ተሞክሮዎች መቃኘት ወይ ወደተስፋ ይመራናል።ወይ ተስፋ ያሳጣናል። ስለሆነም ከ 1992ዓም ኢህአዴግን ጠንቅቆ ለመረዳት ይበጃል።

በ1992 ዓ.ም ምርጫ ቀላል የማይባል አዲስ አበባ ህዝብ ድምፁን ለኢህአዴግ ነፍጎት የነበረ መሆኑ የነገሮች ሁሉ መነሻና የሚስጥሩ መጀመሪያ ነው፡፡ ይህ የተፈጠረው ደግሞ ሃገሪቱ በጦርነት ውስጥ እያለች መሆኑ የቅሬታውን መጠን ያሳያል፡፡ ከዚያም ድርጅቱ “ንቅዘት አጋጥሞኝ ነበር፤ ራሴን እያደስኩ ነው” ሲል ምልዓተ ሕዝቡ ሞቅ ባለ ስሜት ተቀብሎት የነበረ መሆኑም እዚህ ጋር ሊታወስ ይገባል፡፡

የድርጅቱ አባላት ሁኔታ ደግሞ ከዚህም የላቀ ነበር፡፡ ድርጅታቸው ከማንጎላጀት አልፎ የነበረውን ሽታ እያጣ መምጣቱ ሁሉንም በያለበት አብሰልስሏል፡፡ የተሟሟቀ የትግል መድረክ እንደቀድሞው አለመኖሩና ሀሜት መስፈኑን ሁሉንም በየአካባቢው ያነጋገረ  ጉዳይ ነበር፡፡ ጦርነቱ የሁሉንም ቀልብ ስቦ ትኩረትን የሚለውጥ ሁኔታ ተፈጥሮ ከቆየ በኋላ እንደገና ሲሰክን የውጥረት ስሜቱ ከፍ ባለ ደረጃ እንደገና ነገሰ፡፡ በድርጅቱ ከፍተኛ አመራር መካከል የሚካሄደው ትግል በአብዮታዊው ኃይል የበላይነት እየተመራ ወደ አባሉ ሲደርስ የበለጠ መሰረቱን አሰፋና ዳር እስከ ዳር ንቅናቄን ፈጠረ፡፡ ድርጅቱ በከፍተኛ የለውጥ ፍላጎት ንዝረት ተናወጠ፡፡ በአሸናፊነት የወጣው የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ኃይል አጠቃላይ ሂደቱንና የለውጥ ፍላጎቱን ያገናዘበ መወያያ ፅሁፍ በማዘጋጀት የለውጥ ፍላጎቱ በትክክለኛ መስመር እንዲመራና ወደ አንድ ግብ የሚያደርስ ማድረግ ቻለ፡፡ በፅሁፉ ላይ የተካሄደው ሰፊ ውይይትና ክርክር በከፍተኛ ስሜት የተሞላውን አባል በአንድ ማዕቀፍ መግባባት ለመፍጠር አስቻለ፡፡

ይህንን ተከትሎ መስከረም 1994 ዓ.ም የተካሄደው የኢህአዴግ 4ኛ ድርጅታዊ ጉባኤ የተሃድሶውን መስመር በግልፅ የሚያመለክቱ ውሳኔዎችን አሳለፈ፡፡ ይህ ታሪካዊ ጉባኤ ለድርጅቱ አባላት ብቻ ሳይሆን ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የአዲስ ዓመት ስጦታ የሆኑ አዲስ ውሳኔዎችን ያሳለፈ ነበር፡፡  

ተሃድሶው ሀገራዊ አጀንዳ ሆኖ ይፋ ከተደረገ በኋላ ይዘቱ አንድ ድርጅት ወይም ኢህአዴግን ማደስ ብቻ ሳይሆን ሀገርን ከጥፋትና ከትርምስ የማዳን ጉዳይ መሆኑ ግልፅ ሆነ፡፡ የመጀመሪያውና ዓብዩ ተግባር በንቅዘት መንገድ ረዥም ርቀት ተጉዞ የነበረውን ድርጅት ወደ መሰረታዊው አብዮታዊና ዴሞክራሲያዊ መመለስና የነገ ፓርቲ እንዲሆን በአዲስ መስመር ላይ እንደገና መልሶ መገንባት ነበር፡፡ ይኼ የቀናት ወይም የሳምንታት ተግባር አይደለም፡፡ በተራዘመ ጊዜ የተከናወነና ተከታታይ ተግባራትን የያዘ ሂደት ነበር፡፡ ለዓመታት ወደፊት መጓዝ ብቻ ሳይሆን ማሰብ ተስኖት ቆሞ ለባጀ ድርጅት ሀገሪቱ የምትመራበትን ቀጣይ ጎዳና መቀየስ ቀላል ተግባር አልነበረም፡፡  

ኢህአዴግ “ጥገኛ ዝቅጠት፣ ንቅዘት ወዘተ” እያለ የጠራውና የድርጅቱ ቁልፍ ችግር እና የስርአቱ አደጋ ብሎ የገመገመው የኪራይ ሰብሳቢነት ወይም ያለአግባብ የመጠቀም አመለካከትና ተግባር ነው፡፡ ይህ የውስጥ ድርጅትን ዴሞክራሲ በአጠቃላይም የዴሞክራሲን መፋዘዝና የመተጋገል እጦትን ለም መሬት አድርጎ የሚፋፋው የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ተግባር የፖለቲካል ኢኮኖሚ መሰረት እንዳለውም ተለይቶ ወጥቷል፡፡

ሌላው የተሃድሶ መስመር ዓብይ ይዘት በየደረጃው ያለውን አመራርና ፈፃሚ የሕዝባዊነት አመለካከት እና የማስፈፀም አቅም መገንባት ነበር፡፡ የድርጅቱ ሕዝባዊነት ዋና መገለጫ ለሕዝብ ጥቅም ቅድሚያ መስጠት፣ የሕዝብን ጥቅም መሰረት አድርጎ መወሰን፣ ለዚህም አስፈላጊውን መስዋዕትነት መክፈል ነው፡፡ ሕዝብን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተገነባ ባለው የነፃ ገበያ ስርዓት አመራሩ /እንዲሁም ፈፃሚው/ ራሱን አገልጋይ በማድረግ ኃብት ያለው አርሶ አደር እንዲሁም ሀገራዊ ባለኃብት መፍጠር ተልዕኮ አድርጎ ሲሰራ በአቋራጭ ለመክበር አደጋ እንደሚጋለጥ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ ባለችው ስልጣን፣ ኃላፊነትና ሙያ ለኪራይ ሰብሳቢነት የመዳረግ ዕድሉ እጅጉን ሰፊ ነው፡፡ ይህንን መግታት የሚችለው ሕዝባዊነቱንና የዓላማ ፅናቱን የሙጥኝ በማለት ብቻ በመሆኑ ተሃድሶው የአመለካከት ጥራትና ግንባታ ላይ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቷል፡፡ ሌላው ከአመራርና ከፈፃሚ አኳያ የነበረው ቁልፍ ችግር የአቅም እጥረት መሆኑም ግልፅ ስለ ነበር የአቅም ግንባታ ስራው አብሮ የትኩረት አቅጣጫ ሆኖ ተለየ፡፡ ከግለሰቦች አቅም ግንባታ ባሻገር አሰራሮችንና አደረጃጀቶችን ምቹና ዘመናዊ ማድረግ እንደዚሁ የተሃድሶው አካል ነበር፡፡ በሲቪል ሰርቪስና በፍትህ ስርአቱ ላይ ሪፎርም ማድረግ የማስፈፀሚያ አቅጣጫ ሆነ፡፡

የተሃድሶ መስመሩ አንጥሮ ያወጣው ሌላው ጉዳይ ዴሞክራሲ የሕልውናና የልማት አጀንዳ መሆኑ ላይ ሀገራዊ መግባባት እንዲፈጠር ማድረግ ነው፡፡ የብዝሃነት ምድር በሆነችውና ልማቷ በሕዝቦቿ በጎ ፈቃድና ፍላጎታቸው በሚያፈሱት ጉልበት ላይ በተመሰረተው ኢትዮጵያ ዴሞክራሲ የሕልውና ጉዳይ መሆኑ ያለማቅማማት እንዲታመን ተወሰነ፡፡ የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች መብትና እኩልነት መረጋጥ፣ የቡድንና የግለሰብ መብቶች የሚከበሩበት ሕገ-መንግስታዊ ስርዓት ከልባዊ ዴሞክራሲ ውጪ ዕውን መሆን እንደማይችል ተሃድሶው አድምቆ አሰመረበት፡፡ የሀገራችን ዴሞክራሲ ለፕሮሲጀር ሳይሆን ከልባዊነትና ከሕዝባዊ ወገንተኝነት የሚመነጭ፣ ለሕዝብ ጥቅም የሚቆም እርግጠኛ ዴሞክራሲ መሆኑና ሊሆንም እንደሚገባው በግልፅ ተቀመጠ፡፡

በዚሁ አግባብ እነዚህ መሰረታዊ የተሃድሶ አቅጣጫዎች ግልፅ ፖሊሲ ተቀርፆላቸው የማስፈፀሚያ ስትራቴጂና ስልት ተነድፎላቸው መንግስታዊ ሰነድ ሆነው እንዲወጡ ተደርጓል፡፡ ሰነዶቹ በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢና የሕብረተሰብ ክፍል ዘንድ ተበትነው የጋራ ማጣቀሻ እንዲሆኑ ተደረገ፡፡ በዚህ መልኩ ነው የተሃድሶ መስመር ሀገራዊ መሰረት ሆኖ የተዘረጋው፡፡ በምልዓተ ሕዝቡ ተሳትፎ ፈጣን፣ ፍትሃዊ እና ሁሉንም በየደረጃው ተጠቃሚ የሚያደርግ ልማትን ማረጋገጥ ዓላማ ያደረገው የተሃድሶ መስመር ሀገራችንን ከጥፋትና ከትርምስ የሚታደገው ይኸው ፈጣን ልማት ብቻ መሆኑን ይፋ በማድረግ የተጀመረው ንቅናቄ ገና ብዙም ሳይጓዝና በውጤት ሳይታጀብ ምርጫ 97 ሌላ ጣጣ ይዞ መጣ።  

የተሃድሶው መስመር ችግሮች ተለይተው፣ መፍትሄዎች ተቀምጠው፣ አቅጣጫዎች ተመርጠው እንቅስቃሴ በተጀመረበት ወቅት መባቻ የመጣው ምርጫ 97 ሁሉም ወገኖች ለየዓላማቸው መሳካት ዓይነተኛ አውድ ነው ብለው ያሰቡት ታሪካዊ ክስተት ነበር፡፡ በገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ በኩል በተሃድሶ መንፈስ የተጋጋለ ስሜት የነበረበት ልባዊ የሆነ ዴሞክራሲ ከምንጊዜውም የላቀ እንከን አልባ፣ ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ ለማካሄድ የተቆረጠበት ጊዜ ነበር፡፡ ይህንን ጠንቅቆ የተረዳው የተቃዋሚው ጎራ ወለል ብሎ በተከፈተው ዴሞክራሲያዊ መድረክ የሞት ሽረት ትግል ለማካሄድ ቆርጦ የተነሳበትም ጊዜ ነበር፡፡ ተቃዋሚው ጎራ ይህ ምዕራፍ ህልውናውን የሚወስን ዓይነተኛ ምዕራፍ መሆኑን በሚገባ ተረድቷል፡፡ኢህአዴግ የጀመረው የተሃድሶ መስመር ጊዜ ወስዶ ከተተገበረና እየተንደረደረ ያለው የተሃድሶ ጊዜ ወደ ፍጥነት ከገባ እንደማይደርስበትና ህልውናው እንደሚያከትም በሚገባ ተገንዝቧል፡፡ ሕዝቡ ዘንድ የተከማቸው ቅሬታ ጥቅም ላይ ሊውል የሚችልበት አሁንና አሁን ብቻ መሆኑን የተረዳው ተቀዋሚ ምርጫ 97ን የህልውና ጉዳይ አድርጎ ተነሳ፡፡

ኢህኤዴግ ቀደም ብሎ ይፋ ያደረገው የምርጫ ስነ-ምግባር መመሪያ በከፍተኛ ደረጃ ጥቅም ላይ ዋለ፡፡ በገዢው ፓርቲ በኩል ምርጫው ያለአንዳች እንከን እንዲከናወን፣ አባላቱና ደጋፊዎች ከሀምሳ በላይ ተጉዘው እንዲሰሩ ንቅናቄ የፈጠረበት ሲሆን ተቃዋሚው ኃይል ደግሞ እንደፈለገው ሕገ-ወጥ ተግባራትን ጭምር እንዲያከናውን ያነሳሳው በዚሁ መሰረት ሁለቱም ወገን በየፊናው ሰፊ እንቅስቃሴ ማድረግ የጀመረበት ታሪካዊ ሰነድ ነው፡፡ ከዚህ በመነሳት ሁሉም በየጎራው ወደ እንቅስቃሴ ሲገባ የተለያዩ ገፅታዎች ታይተዋል፡፡

ሕገ-መንግስታዊውን ስርዓት አጥብቀው የሚጠሉት አክራሪ ፅንፈኞች በተለያየ ምክንያት ከስርዓቱ ጋር የተቃቃረውን በሙሉ ከጎናቸው ለማሰለፍ ተንቀሳቀሱ፡፡ በብሄር ብሄረሰቦች መብት መከበር ላይ የተመሰረተው ፌዴራላዊ የፖለቲካ ስርዓት ኢትዮጵያን የሚያጠፋና እያጠፋ ያለ ነው ብለው የሚያምኑት ፅንፍ የወጣ የትምክህት አመለካከት ያላቸው ወገኖች በአንድ በኩል፤ አገሪቱን ለመበታተንና በየብሄራቸው የጠባብ ቡድናቸውን ለማረጋገጥ ከተቻለ በሀገር አቀፍ ደረጃም አምባገነንነታቸውን ለመጫን የሚያልሙ ጠባቦች በሌላ በኩል ለመጨረሻው ፍልሚያ ተሰለፉ፡፡ እነዚህ እርስ በርስ ቢነካኩ እሳት የሚጭሩ ፅንፍና ፅንፍ የቆሙ ተቃራኒ አቋም ያላቸው ኃይሎች ሕገ-መንግስታዊውን ስርዓት በመናድ የጋራ ተልዕኮ ጎን ለጎን ተሰለፉ፡፡ ባለፈው ስርአት ከከፍተኛ እስከ ዝቅተኛ አመራር የተሳተፉ በአንድ ወይም በሌላ መንገድ የጥቅም ተጋሪ የነበሩ ሁሉ በነዚህ ዙሪያ ተሰባሰቡ፡፡ የተሃድሶው ሂደት በየደረጃው ያንጠባጠባቸውና በተለያየ ምክንያት ከስርአቱ ጋር ሲሰሩ ቆይተው መንገድ ላይ የቀሩትና ተገፍተው የወጡትም የዚሁ ጎራ አጃቢ ሆነው ተቀላቀሉ፡፡ እንደዚህ እያለ የስብስቡን ቁጥር ያሰፋው የተቃዋሚ ጎራ  እጅጉን ነፃ በሆነው ዴሞክራሲያዊ የምርጫ መድረክ ሕገ-ወጥነትንና ሕጋዊነትን ያደባለቀ ቅስቀሳውን በሰፊው ተያያዘው፡፡ በወቅቱ በሁሉም ዘንድ እንደተስተዋለው የቅስቀሳቸው መነሻም መድረሻም ገዥውን ፓርቲ ማብጠልጠል እና ማብጠልጠል ብቻ ነበር፡፡

የሕዝቡን ሁኔታ ስንመለከት ደግሞ በአዲሱ ሕገ-መንግስታዊ ስርዓት መብትና ጥቅሙ የተጠበቀለት ምልአተ ህዝብ እንዳለ ሆኖ በየህብረተሰብ ክፍሉ የየራሱ ቅሬታና ብሶት የነበረውም ብዙ ነበር፡፡ በተሃድሶ የተቀመጠውን አርሶ አደሩን በሙሉ አቅም ወደ ስራ ማስገባትና ቴክኖሎጂዎችን እንዲጠቀም በማስቻል ምርታማነቱን አሳድጎ ፍላጎቱ እንዲያድግ የማድረግ አቅጣጫን ለማስፈፀም ሲባል ያለፈቃዱና ሳያምንበት ለማሰማራት በአንዳንድ አካባቢዎች የተደረገው ፀረ-ዴሞክራሲያዊ አዝማሚያ ያስከፋው አርሶ አደር ቁጥር ቀላል አልነበረም፡፡ ከማዳበሪያ ዋጋ ጭማሪና ብድርን የመመለስ ችግር ሌላ የብሶት ምክንያት ነበር፡፡ በየአካባቢው የሚታዩ ሌሎች የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ተጨምረው ለቅሬታ የተጋለጠው የገጠር አካባቢ ሕዝብ ትንሽ አልነበረም፡፡ የተሃድሶው እንቅስቃሴ ከዝግጅት ያለፈ ተግባራዊ ክንውኖች ገና ብዙ ያልተፈፀመበት እንደመሆኑ “ገዥው ፓርቲ ብሶታችንን እያዳመጠ አይደለም፣ ምላሽና መፍትሄ አልሰጠንም” የሚለው ቅሬታ ሰፋ ባሉ የገጠር አካባቢዎች ተስተውሏል፡፡

በከተሞች ደግሞ ከዚህም የባሰ ሁኔታ በኢህአዴግ ላይ ተስፋ የመቁረጥ አዝማሚያ ታይቷል፡፡ “ኢህአዴግ ለገጠሩ እንጂ ለከተማው ቁብ የለውም” የሚል አስተሳሰብ በከተሞች ጎልቶ መታየት ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡ የትምክህትና የጥበት ኃይሎች መናኸሪያ ሆኖ የቆየው የትምህርት ስርዓት እና የትምህርት ቤት አካባቢ ወጣቱን እንኳን በችግሮች ትንታኔ አፈታት ላይ በባለቤትነት ስሜት እንዲሳተፍ ማድረግ ቀርቶ ወደ ተንጋደደ አቅጣጫ እንዲያመራ ሲገፋ የነበረ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የብሶተኝነት ስሜቱ እንዲባባስ ሲያደርግ የቆየ ነበር፡፡ የስራ አጥነት ችግሩም ሌላ የቅሬታ ዓይነተኛ ምንጭ ነው፡፡

እነዚህ በርካታ ችግሮች ድርጅቱ በተሃድሶ በገመገመው የማንጎላጀት ዓመታት የተፈጠሩና እየተከማቹ የመጡ ናቸው፡፡ በጥበትና በትምክህት ፅንፎች የተወጠረው የተቃውሞ ጎራ እነዚህን ቅሬታዎች ማባባስ፣ ማራገብና ማግለብለብ ዓይነተኛ ተግባሩ ሆኖ ተሰማራ፡፡በዚህ መሰረት ዓይነተኛ ዓላማው ብሶት መቀስቀስ፣ ስሜት ማጋጋል እና ሕዝብን ለሁከትና ለብጥብጥ ማነሳሳት የሆነ የምርጫ ቅስቀሳ ውስጥ ገቡ፡፡ ውዥንብር መንዛት፣ የመንግስት ህልውና ጥርጣሬ ላይ እንዲወድቅ የሚጋብዙ ሕገ-ወጥ ተግባትን መፈፀም፣ የዘረኝነት ጉትጎታዎች ወዘተ በምርጫ ቅስቀሳ ሽፋን ተከናወኑ፡፡

“የተሃድሶ መስመር እየተንደረደረ በነበረበት ሁኔታ ጊዜ አግኝቶ ከተፈፀመ ህልውናችን ያከትማል” በሚል ስሌት ለሞት ሽረት ትግል የተሰማራው ፅንፈኛ ተቃዋሚ ኃይል የፈለገው ባይሳካለትም ያሰበው እውነት መሆኑን ግን የሚያረጋግጡ ዓመታት ተከታትለው መጡ፡፡ ስርዓቱን ለመናድ በአንድ ግንባር የተሰለፉት ተቃራኒ ኃይሎች ተቃርኖና እሳትና ጭድነትም በእነዚሁ ተከታይ ጊዜያት ታየ፡፡ የፅንፈኛው ተቃዋሚ ጎራ እርስ በርስ መወነጃጀልና መባላት በተመሳሳይ መስመር በተሰለፉት ውስጥም ጭምር ተከሰተ፡፡ የትምክህትና የጥበት ኃይሉም መፋለም ብቻ ሳይሆን በትምክህት ጎራ ስር ተሰብስበው የነበሩ የተለያዩ ቡድኖችና ግለሰቦች በማያባራ ሽኩቻና ትርምስ ውስጥ ገብተው ብዙ የተወራለት ቅንጅታቸው እንደ ገል ፈራረሰ፡፡  

በገዥው ፓርቲ በኩል የተደረሰበት ድምዳሜ ደግሞ “ፈጥነን በመሮጥ ካላመለጥነው ደርሶ ይፈረካክሰናል ያልነው ናዳ ማሳያ ነው” የሚል ነበር፡፡ ተቃዋሚዎች እዚህ ውስጥ ምንም ሚና እንደሌላቸው የሕዝቡ የፈጣን ልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄ መገለጫ መሆኑ ነበር በገዥው ፓርቲ በኩል የተገመገመው፡፡ ሕዝቡ ኢህአዴግ ላይ ያለውን ቅሬታ ዴሞክራሲያዊ በሆነ አግባብ መግለፁ ድርጅቱ የታገለለት ዓላማ ፍሬ ማፈራቱን ያመለከተ መሆኑ በአወንታዊነት ተገመገመ፡፡

የተጀማመሩ የልማት ስራዎች  ፍላጎት  መጨመራቸውና ሕዝቡ የማያቋርጥ የፍላጎት አዙሪት ውስጥ ሲገባ ይህን የሚመጥን ፈጣን ሁሉንም በየደረጃው ተጠቃሚ የሚያደረግ ልማትን ማረጋገጥ ከፊት ለፊት የሚጠብቀው ፈተና መሆኑን ድርጅቱ በስፋት ገመገመ፡፡ ይህን ተከትሎ የጠራ አቅጣጫ መንደፍ ፈጣን ልማት ያረጋገጡ ሀገሮችን ልምድ መቀመርና የተሃድሶውን መስመር ማጥራት መሠረታዊ ጉዳይ መሆኑ ተሰመረበት፡፡  የተሃድሶውን መስመር ከማጠናከርና ከማጥራቱ ጐን ለጐን የተጀመሩ የልማት ስራዎችን በከፍተኛ ደረጃ ማስፈፀም ርብርብ የሚሻ ጉዳይ መሆኑ ስምምነት ላይ ተደርሶ ወደ ስራ ተገባ፡፡ በተለይ የድርጅቱ ከፍተኛ አመራር የተሃድሶውን መስመር የሚያጠናክሩና የሚያጠሩ የልምድ ቅመራ ስራውን በከፍተኛ ደረጃ አጠናክሮ ቀጠለ፡፡ የህዳሴው መስመር አሸናፊ ሆኖ ከወጣበት ካለፉት አመታት ወዲህ ባሉት ዓመታት የልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መንግስቱ በልማትና በመልካም አስተዳደር እቅዶችን ነድፎ በህዝብ ተሳትፎ ተፈፃሚ በማድረጉ በየመስኩ ለሌሎች አገሮችም ተሞክሮ ሲሆን እድገት በተከታታይ በማስመዝገብ ድህነትን መቀነስና በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ እድገት ማስመዝገብ ተችሏል።

አሁን የተፈጠረውን ችግር ይልቁንም የኪራይ ሰብሳቢነት አደጋና እየሰፋ የመጣውን የህዝብ ጥያቄ በዚሁና ከላይ በተመለከትነው ተሞክሮ ተመርቶ መመለስና ማስወገድ የሚጠበቅበት ሲሆን፤ ለዚህም በዳበረ ልምድና በተሟላ የኢትዮጵያዊነት ስነ-ልቦናዊ፤ እንዲሁም ፖለቲካዊ የመስመር እምነት ላይ መመስረት አለበት።  ከአንድ ህዝባዊ ወገንተኝነት ካለው ተራማጅ ፓርቲም ሆነ ይመለከተኛል ከሚል ወገን የሚጠበቀውም ይኸው ነው።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy