Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

በጥረት የማይወጣ አቀበት የለም

0 255

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

በጥረት የማይወጣ አቀበት የለም

                                                    ቶሎሳ ኡርጌሳ

ከመሰንበቻው የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስትርና የብሔራዊ ደህንነት ምክር ቤት ፀሐፊ አቶ ሲራጅ ፈጌሳ በተለይ በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች የድንበር አካባቢ ተፈጥሮ የነበረው አለመረጋጋትን ለመፍታት መንግስት በወሰደው ርምጃ ላይ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተው ነበር። እርሳቸው እንደገለፁት፤ በአሁኑ ወቅት በእነዚህ አካባቢዎች ሁኔታዎች ተለውጠዋል።

መንግስት በወሰደው ርምጃ የሁለቱም ክልሎች ታጣቂዎች ሚሊሽያዎች ከድንበር አካባቢ እንዲርቁ ተደርጓል፤ ከሁለቱም ክልሎች የተፈናቀሉ ወገኖችን የማቋቋም ስራ ተጀምሯል። እንዲሁም ወደ ነበሩበት መመለስ የሚፈልጉ ተፈናቃዩችን የመመለስና ፍላጎት የሌላቸውን ባሉበት የማቋቋም ስራ እየተከናወነ ነው። የዚህ ድምር ውጤትም የህብረተሰቡ መንፈስ እየተረጋጋ እንዲሆን ማድረግ ተችሏል።

እንዲሁም በአሁኑ ወቅት በሁለቱም አካባቢዎች አንፃራዊ ሰላም መስፈን ችሏል። ይህ አንራፃዊ ሰላምም በመንግስትና በሁለቱም ክልሎች ህዝብና መንግስታት ጥረት የተገኘ ጥረት ነው። ይህም ምንም ዓይነት ችግር ቢኖር በመተጋገዝ ላይ በተመሰረተ ጥረት የማይወጣ አቀበት የሌለ መሆኑን የሚያሳይ ይመስለኛል።

እንደሚታወቀው መንገስትና ህዝብ በጋራ ከጣሩ የማይወጡት አቀበት፣ የማይወርዱት ቁልቁለትና የማይሻገሩት ጅረት የለም። በተለይም ሰላምንና መረጋጋትን ለማምጣት ሲባል የአንድ ሀገር ህዝብ ከሚመራው መንግስት ጋር ተጣምሮ በሀገራዊ ስሜት ጊዜያዊ ችግሮችን መፍታት ከቻለ ሀገሩን በአስተማማኝ ሰላምና ዘላቂ የልማት ጎዳና እንድትጓዝ ማድረጉ አይቀርም። ይህን እውነታ በተገቢው መንገድ ለመግለፅ የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ላለፉት 26 ዓመታት ያስገኟቸውን ስኬቶች በመጠኑ ማውሳት የሚቻል ይመስለኛል።

እንደሚታወቀው ምንም እንኳን አልፎ አልፎ ጊዜያዊ ግጭቶች ቢኖሩም፤ የተለያየ እምነትና የአኗኗር ዘይቤን የሚከተሉ የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች በመግባባትና በመረዳዳት መንፈስ አብሮ በመኖር በዓለም የሚታወቁበት የመቻቻል ባህልም ከመቼውም በላቀ ሁኔታ እየዳበረ ይገኛል። እነዚህ ታሪካዊ፣ ባህላዊና መንፈሳዊ የጋራ እሴቶቻችን ለሀገራችን ተጨማሪ ክብርና ሞገስ ከማላበስ አልፎ ለፈጣን ልማት ስራዎቻችን የበኩላቸውን ድርሻ ማበርከት የቻሉ ናቸው።

የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ከሀገራቸው ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ህይወት ተገልለውና ተረስተው በባይተዋርነት ለመኖር የተገደዱበት አድሎአዊና ፍትህ አልባ ሁኔታ ሙሉ ለሙሉ ተቀይሮ ዜጎች በማንኛውም ሀገራዊ ጉዳይ ውስጥ እኩል ተሳታፊ የመሆን ዕድልን ተጎናጽፈዋል።  

ይህን ዕድል በተጨባጭ ስራ ላይ በማዋል የሀገራችንና የህዝባችን የማደግና የመበልጸግ ተስፋን በእጅጉ አለምልመዋል። መላው ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች በመብቶቻቸው እየተገለገሉና ዘላቂ ጥቅሞቻቸውን እያስከበሩ በፈጣን ልማትና በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ አቅጣጫ ላይ የተያያዙት ፈጣን የዕድገት ጉዞም እንዲሰምር አድርገዋል። ይህ ሁለንተናዊ የዕድገት ጉዞ ገና በለጋ ዕድሜው ብቻ የበርካታ አፍሪካዊ ወንድሞቻችንን ቀልብ ከመሳብ አልፎ፤ በአርአያነት እንዲጠቀስና በሞዴልነትም እንዲወሰድ ማድረግ ችለዋል።

ርግጥ ለአፍሪካውያን ወንድሞቻችን አርአያና መኩሪያ የሆነው የሀገራችን ህዝቦች የሚከተሉት ዕድገት ብቻ አይደለም። ለዕድገቱ ያበቃን የምንከተለውና በህገ መንግስቱ አማካኝነት እውን የሆነው ፌዴራላዊ ስርዓታችንም የህዝቦች መፈቃቀድና በጋራ የመኖር መቻቻላችነም የራሱን አስተዋጽኦ አበርክቷል። ይህ አብነታዊ የፖለቲካ ስርዓት በርካታ ቁጥር፣ ባህልና ቋንቋ ብሎም ትውፊቶች ያላቸው ህዝቦች እንደምን ተከባብረውና ተፈቃቅረው መኖር እንደሚችሉ ማሳያ ሆኗል።

ለነገሩ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ረጅሙንና አስቸጋሪውን የትግል ምዕራፍ በድል አድራጊነት በቋጩ ማግስት በጋራ ተወያይተውና አምነው ያፀደቁት ህገ መንግስት የዘመናት ጥያቄዎቻቸውን ሙሉ ለሙሉ የመለሰ ከመሆኑም ባሻገር፤ በቀጣይ ለሚያካሄዷቸው የጋራ አጀንዳዎች ዘላቂነትና ውጤታማነት ዋስትና የሰጠ ነው።

በሀገራችን እውን የሆነው ፌዴራላዊ የመንግስት ስርዓት አወቃቀር ለሀገራችንና ለህዝባችን አንድነት፣ ሰላምና ዕድገት መጠናከር ወሳኝ አስተዋጽኦ አበርክቷል። የዚህ አዲስ ስርዓት ግንባታ ሂደት በተጨባጭ ተፈትኖ ፍቱንነቱ የተረጋገጠ ነው። የተገነባው ፌዴራላዊ ስርዓት በሀገራችን ላይ አንዣቦ የነበረውን የመበታተን አደጋ ያስወገደና በእኩልነትና በመፈቃቀድ ላይ ለተመሰረተ ከብረት የጠነከረ የህዝቦች አንድነት ዘላቂ ዋስትናን አስገኝቷል። ይህ የሆነው በ26 ዓመታት ውስጥ መንግስትና ህዝብ ተባብረው ስለሰሩ ነው። ዛሬም ይህ ጥምረት መጠናከር ይኖርበታል። በበኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች ለተፈናቀሉ ወገኖች መንግስትና ህዝቡ ያደረጉት ጥረት መገለጫ ነው።

ርግጥ በአንድ ሀገር ውስጥ ሰላምንና መረጋጋትን ለማምጣት የሁለቱ ጥምረት ተኪ አይገኝለትም። የኢትዮጵያ ህዝቦች ላለፉት 26 ዓመታት በራሳቸውና በመንግስት ጥረት እውን ያደረጉት አስማማኝና ዘላቂ የሰላም ቁመና ታጅበውም ህዳሴያቸውን ዕውን ለማድረግ እጅ ለእጅ ተያይዘው ቆመዋል። በሰላማቸውና በመረጋጋታቸው ከፍታቸውን ለማረጋገጥ ዝግጁ ናቸው። ይህን ዝግጁነታቸውን ትናንትም ይሁን ዛሬ እያረጋገጡ ነው።

በአሁኑ ወቅት በአንዳንድ አካባቢዎች የሚስተዋሉትን የሰላምና የመረጋጋት ችግሮችን በዘላቂነት ለመቅረፍ ከመንግስት ጋር ተባብረው በመስራት ላይ ይገኛሉ። ርግጥ በየትኛውም ሀገር ውስጥ እውን እንዲሆን የሚፈለግ ሰላም ያለ ህዝቡ ተሳትፎ ምንም ዓይነት ውጤት ሊያመጣ አይችልም። የሰላም ዋጋን ዋነኛ መዛኙ ኃይል ህዝብ ነው። ህዝብ ጥቅሙን የማያውቀው ሰላም እውን ሊሆን አይችልም።

ርግጥም ለአንድ ሀገር ልማትና ዕድገት ሰላም ከምንም በላይ የገዘፈ ዋጋ ያለው መሆኑ አያጠያይቅም። እንደ እውነቱ ከሆነ የሰላም ዋጋ በምንም ዓይነት ምድራዊ ዋጋ የሚለካ አይመስለኝም። ሰላም የሚተመንበት አሊያም የሚሰፈርበት ልኬት አለው ሊባል የሚችልም አይመስለኝም። ከግለሰብ የነገ ማንነት ህልም ጀምሮ እስከ የሀገር ህዳሴ ዕውን መሆን ድረስ ሰላም ዋጋው እጅግ የገዘፈ ነው።

በየትኛውም ሀገር ውስጥ ዜጎች መብትና ግዴታዎቻቸውን ሲያውቁና ሌላውን ለማስተማርና ለመደገፍ ሲነሳሱ ሰላም ይረጋገጣል። ልማትና ዕድገትም ይደረጃሉ፤ ዴሞክራሲያዊ እሴቶችም በዚያው መጠን እያበቡ ይሄዳሉ። ይህ ህዝብ የሀገርን ሰላምና ደህንነት መጠበቅ የመንግስት ብቻ አለመሆኑን የተገነዘበ ነው።

ህዝቡ በያለበት ሆኖ ሰላሙን ከጠበቀ ሰላምን ለማደፍረስ የሚሮጥ የትኛውም ሃይል አቅም ሊኖረው አይችልም። የሰላምን ምንነት የሚገነዘብ ህዝብ ውስጥ ፀረ ሰላምነትን ማንገስ አይቻልም። ህዝብ የሚጠቀምባቸውን ማንኛውንም ዓይነት ንብረቶችንና የግለሰቦችን ሃብት ለማውደም አይበቃም፤ ይጠብቃቸዋል እንጂ። ይህ የህዝብ ሚና በቅርብ ጊዜው የኦሮሚያና የኢትዮጵያ ሶማሌ ጊዜያዊ ግጭት በመፍትሔነት ሲተገበር ተመልክተናል። ህዝቡ ማንኛውንም ዜጋ የመደገፍና ችግሩን የመጋራት የቀየ እሴት ያለው መሆኑን አስመስሯል። ይህ ከመንግስት ጋር የሚያደርገው ሁለንተናዊ ጥረት የሚፈጠሩ አቀበቶች መውጫ በመሆኑ ነገም ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል።

  

  

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy