Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

…ባለቤቶች አሉ!

0 359

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

…ባለቤቶች አሉ!

ዳዊት ምትኩ

በአንዳንድ ወገኖች የፌዴራል ሥርዓቱ የኢህአዴግ እንደሆነ የሚሰጡ አስተያየቶች አግራሞትን የሚያጭሩ ናቸው። የሥርዓቱ ባለቤቶች የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች እንጂ ኢህአዴግ አይደለም። አምባገነኑን የደርግ ስርዓት ታግለው የጣሉትና አዲሲቷን ኢትዮጵያ የፈጠሩት መላው የአገራችን ህዝቦች እንጂ አንድ ድርጅት ሊሆን አይችልም።

ትግሉ የመላው ህዝብ እንጂ የአንድ ድርጅት ጉዳይ አይደለም።  ህዝቡ ኢህአዴግን ፈጠረው እንጂ፤ ኢህአዴግ ህዝቡን አልፈጠረውም። እርግጥ ኢህአዴግ የህዝቡን የለውጥ ትግል መርቶ ለድል አብቅቷል። ይህ የሚካድ እውነታ አይደለም። የድሉ ባለቤት ግን ኢህአዴግ ሳይሆን የዘመናት ጥያቄዎቹን አንግቦ ለለውጥ የተሰለፈው መላው የአገራችን ህዝብ ነው። ይህም በአንዳንድ ወገኖች የሚቀነቀነውና ‘ሥርዓቱ የኢህአዴግ ነው’ የሚለው ሃሳብ መሰረተ ቢስ መሆኑን ለመገንዘብ አይከብድም።  

እርግጥ የህገ- መንግስቱ ባለቤት ገዥው ፓርቲ አይደለም። ምከንያቱም ዋነኛው ባለቤቶች መላው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ናቸውና። ለዚህም ህገ- መንግስቱ በመግቢያው ላይ “እኛ የኢትዮጱያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች… በራሳችን ፈቃድ ላይ የተመሰረተ አንድ የፖለቲካ ማህበረሰብ በጋራ ለመገንባት ቆርጠን በመነሳት…ህገ- መንግስቱን በተወካዮቻችን አማካኝነት አፅድቀነዋል” የሚለውን አባባል መጥቀስ የሚቻል ይመስለኛል።

ለነገሩ እዚህ ላይ ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ አሁን በስራ ላይ ላለው ህገ- መንግስትና ህገ-መንግስታዊ ስርዓት እውን መሆን መታገሉ፤ ማታገሉና በሂደቱም መስዋዕትነት መክፈሉ የሚካድ አይደለም። በዚህም ኢትዮጵያንና ህዝቦቿን ከአምባገነኑ ፀረ- ዴሞክራሲያዊ ስርዓት የአፈና አገዛዝ አላቋል። በሀገራችን የፀረ- ዴሞክራሲ ኢኮኖሚያዊ መሰረትን ንዷል፣ የብሔራዊ ጭቆናን ተቋማዊና መዋቅራዊ እንዲሁም ድርጅታዊና ርእዮተ ዓለማዊ መሰረቶች ከመሰረታቸው እንዲመነገሉ  አድርጓል።

ከዚህ በተጨማሪ፤ የግልና የቡድን መብቶችን ያጣመረ ዴሞክራሲን መገንባት ችሏል። እነዚህና ሌሎች ዓለም አቀፍ የዴሞክራሲያዊና የሰብአዊ መብት እምነቶች ለህዝብ ቀርበው እስከ ታች ድረስ የወረደ ሰፊ ውይይት ተካሂዶባቸው ማሻሻያ ከተደረገባቸው በኋላ፤ በህገ- መንግስትነት እንዲፀድቁና ህዝቡ “የእኔ ናቸው” ብሎ እንዲቀበላቸው አድርጓል።

ይህም ዴሞክራሲያዊው ስርዓት እንዲፈጠር ገዥው ፓርቲ የመሪነት ሚናውን በብቃት ቢወጣም፤ በስተመጨረሻም የህገ- መንግስቱ ባለቤት ህዝቡ መሆኑን በግልፅ የሚያስረዳ ዕውነታ ይመስለኛል። ይህን የባለቤትነት መብት ማንም ሊሽረው አይችልም።

ለህገ መንግስቱ መሰረት በሚካሄዱ ምርጫዎች ህዝቡ ድምፅ የሚሰጠው ህገ- መንግስቱን ለሚንከባከብለትና ለሚጠብቀው ኃይል መሆኑ ለአምስት ለተከታታይ የምርጫ ጊዜያት ታይቷል። ይህም የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች አምነውበትና ተስማምተውበት ያፀደቁትን ዴሞክራሲያዊ ህገ- መንግስት የትኛውም ኃይል እንዲነካባቸው የማይፈልጉ መሆኑን የሚያሳይ ሃቅ ነው።

ከህገ- መንግስቱ ውስጥ አንቀፆችን መሰረዝም ይሁን ማሻሻል የሚችሉት የሀገራችን ህዝቦች ወይም ስልጣናቸውን በውክልና በመስጠት የመረጡት አካል እንጂ የትኛውም አካል አለመሆኑን መገንዘብ የሚገባ ይመስለኛል። ከዚህ በተጨማሪም የህገ መንግስቱን ምሶሶዎች ማፍረስ የሚቻል አይመስለኝም።

የህገ-መንግስቱ ምሶሶዎች ተብለው በመሰረታዊነት ከሚጠቀሱት ውስጥ፤ የመንግስትና የሃይማኖት መለያየት፣ የቡድንና የግለሰብ መብቶች የተከበሩበት ዴሞክራሲያዊ ፌዴራላዊ ስርዓት፣ ራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት፣ የነፃ ገበያ መርህና በዚሁ ማዕቀፍ የመሬት አስተዳደር  በመንግስትና በህዝብ ስር እንዲሆን ማድረግ የሚሉት ዋነኛዎቹ ናቸው።

እነዚህን የህገ-መንግስቱን የማዕዘን ድንጋዩች መቃወም አሊያም ከህገ-መንግስቱ ውስጥ እንዲወጡ ማለም ማለት፤ እንደ አፄው ስርዓት ወቅት “ስዩመ-እግዚሐብሔር” እየተባለ መንግስትና ሃይማኖት አንድ እንዲሆኑ መመኘት፣ የቡድንና የግለሰብ መብቶችን የሚጨፈልቁት ያለፉት ፊውዳላዊና አምባገነናዊ ፀረ-ዴሞክራሲያዊ ስርዓቶች ተመልሰው እንዲመጡ መሻት፣ የሌሎች ፍላጎቶችን ለማሟላት ሲባል የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብቶችን እንዲታፈኑ መፍቀድ አሊያም ያለፈውን የሶሻሊስት ስርዓትን በመናፈቅ የነፃ ገበያ ስርዓት መርህ እንዳይኖር መፈለግ እንዲሁም የአርሶ አደሩን መሬት በመሸጥና በመለወጥ ጭሰኛ ሆኖ እንዲቀር መፈለግ ማለት ነው።

እነዚህን ፍፁም ፀረ-ዴሞክራሲያዊና ፀረ-ልማታዊ አስተሳሰቦችን ጫንቃው ላይ ጭኖ ለመሸከም የሚፈቅድ ማህበረሰብ በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖር አይመስለኝም። የለምም።

የሀገራችን ህዝቦች እነዚህን ፀረ-ዴሞክራሲያዊና ኢ-ልማታዊ እሳቤዎችን አምርሮ የሚጠላቸውና ከጫንቃው ላይም እንዲወገዱ በፅናት የታገላቸው ናቸው። በመሆኑም እነዚህን ያለፉ ስርዓቶች ተግባራትን ማለም ህገ-መንግስቱን ዕውን ለማድረግ ውድ ህይወቱን ከከፈለው የሀገራችን ህዝብ ጋር መጋጨት ይመስለኛል።

የኢትዮጵያ ህዝቦች የህገ-መንግስቱ ምሶሶዎች በሌሉበት ሁኔታ ውስጥ መኖርን በምንም መንገድ ሊፈቅዱት አይችሉም። ከሁሉም በላይ ደግሞ በህገ-መንግስታዊ ዓመታት የዴሞክራሲ ትሩፋቶችን በሚገባ ማጣጣማቸው፣ የጀመሩት ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ እንዲያድግላቸውና እንዲመነደግላቸው ይፈልጋሉ።

እናም ዳግም ተመልሰው በኢ-ሰብዓዊና አምባገነናዊ ስርዓቶች ውስጥ መዳከርን አይመኙም፤ ሊያስቡትም የሚፈልጉ አይመስለኝም። እናም በርካታ መስዕዋትነት የከፈሉበትንና የቃል ኪዳን ሰነዳቸው የሆነውን ህገ-መንግስት እንደ ዓይናቸው ብሌን ይንከባከቡታል።

ህገ-መንግስቱ በራሳቸው የደም ጠብታ የፃፉት የጋራ ሰምምነት ሰነዳቸው በመሆኑም፤ አንዳንድ ወገኖች ህገ የስርዓቱ መሰረት የሆነውን ህገ መንግሰት የአንድ ድርጅት ንብረት አደርገው እንዲቆጥሩት እድል ሊሰጡ አይችሉም።  

ሥርዓቱ የህዝቦች ትግል ውጤት ነው። በሥርዓቱ ውስጥ ቀዳሚዎቹ የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዘቦች እንጂ ድርጅት አይደለም። አሁንም ቢሆን ኢህአዴግ በህዝቦች ትግል ውስጥ የመሪነት ሚና ያለው መሆኑ የማይካድ ቢሆንም፤ የመሪነት ሚናውን የተወጣውና የሚወጣው ህዝቡን በቀዳሚነት አሰልፎ ነው።

አንድ ህዝባዊ ድርጅት ሲቋቋም መነሻው ህዝብ እንጂ ደርጅት አይደለም። ህዝብ የሌለው ድርጅት ከቶ ለማን ይታገል ይሆን?…ለማንም። ህዝብ የተቆጣበት ምክንያት ይኖራል። ያንን ህዝባዊ ቁጣ በህዝቡ ስም የሚያስተባብር ድርጅት ይፈጠራል። ትግሉንም በህዝብ ቀዳሚነት ይጀምራል። ኢህአዴግ የተፈጠረው በዚህ ሂደት ነው። በመሆኑም ሥርዓተቱን የኢህአዴግ ነው የሚያስብል ነገር የለውም።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy