ተጠቅሞ የመጣል ፖለቲካ
ዘአማን በላይ
የኤርትራ መንግስት የሚከተለው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ የከሰረና ወላዋይ ባህሪውን የሚያረጋግጥ ነው። የኤርትራው ብቸኛ አምባገነን መሪ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በግብፅ ያደረጉት ጉብኝት ወትሮም “ጠብ ያለሽ በዳቦ” ለሚሉት ግለሰብ ደስታን የፈጠረላቸው ይመስላል። ምንም ዓይነት የዲፕሎማሲ መርህ ለሌላቸው ለእኚህ ግለሰብ አዲስ የገንዘብ ማግኛ መንገድም ሆኖላቸዋል። ሰሞኑን አልጀዚራ ቴሌቪዥን የፕሬዚዳንቱን የካይሮ ጉብኝት አስመልክቶ የጉድኝቱን እውነታ በመሄሱ ሳቢያ አቶ አሳያስ “የአልጀዚራ ጡሩንባ ምንም ዓይነት ለውጥ አያመጣም” ማለታቸው ትናንት በፍቅር ሲከንፉላት የነበረችውን ኳታር በማጣጣል ፊታቸውን ወደ ሌሎች ሀገራት ማዞራቸውን ያረጋገጡበት ክስተት ሆኗል።
ርግጥ በምስራቅ አፍሪካ ውስጥ እንደ ኤርትራ “የፔንዱለም” ፖለቲካን የሚጠቀም ሀገር የለም። ቀደም ባሉት ጊዜያት ኤርትራ ከኳታር፣ ከኢራን፣ ከሱዳን ጋር የሞቀ ግንኙነት ነበራት። ኋላ ላይ ግን የአስመራው አስተዳደር “ለከፈለን ሁሉ እንሰራለን” በማለት ፊቱን ወደ ገንዘብ ለጋሽ ሀገራት አዙሯል። ይህ ሁኔታም የኤርትራው መንግስት የተለመደውን የተጠቅሞ መጣል (use and throw) ፖለቲካን በመጠቀም በውጭ ጉንኙነቱ በኩል ከየትኛውም ሀገር ጋር በመርህ ላይ የተመሰረተ ግንኙነት እንደሌለው ማረጋገጫ ነው።
የአስመራው አስተዳደር ፊቱን ጊዜያዊ ጥቅም ወደ ሚያስገኝላቸው ሀገራት ብቻ የሚያዞር ነው። ከሀገራት ጋር የሚደረግ የግንኙነት ፖሊሲ፣ የጎረቤት ሀገራት አመኔታ፣ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት…ወዘተ የሚሉ ጉዳዩች በአስተዳደሩ ውስጥ ከቶም ቦታ የላቸውም። የኤርትራ መንግስት ገንዘብ እስካገኘ ድረስ ቀጣናውን ከማተራመስና ከማናጋት ወደ ኋላ የሚል አይደለም። ሻዕቢያ በቀጣናው ላይ የራሳቸው ፍላጎት ካላቸው ሀገራት ጋር በመርህ አልባ ጉድኝት እየተመራ ዛሬ ድረስ የዘለቀ ነው። በእኔ እምነት ይህ የአስመራው አስተዳደር ሁኔታ የቅርብ ክትትል ሊደረግበት የሚገባ ይመስለኛል።
የአቶ ኢሳያስ መንግስት ወጥ አቋም የሌለው በመሆኑ መርህን ሳይሆን ጥቅም ወዳለበት ቦታ ይሮጣል። የትም ቢሆን ጊዜያዊ የጥገኝነት ሱሱን እስከተወጣለት ድረስ ከማንም ጋር ሽርክ ይሆናል። ሰይጣንም ከቀይ ባህር ወጥቶ ‘አብረን እንስራ’ ቢለውም የሁከት ፅዋውን አንስቶ “ቺርስ” ብሎ ስምምነቱን የሚገልፅ ይመስለኛል። በአጭሩ ሻዕቢያ ለሰጠው ሁሉ አፋሽ አጎንባሽ ነው ማለት ይቻላል።
የኤርትራ መንግስት ቀደም ሲል ከኳታር መንግስት ጋር የነበረውን ግንኙነት ዛሬ ላይ የሚያስታውሰው አይመስልም። ኧረ እንዲያውም ከአዕምሮው ጓዳ ፍቆ ሳያወጣው የቀረ አይመስለኝም። ግና ታሪክ ነውና የፕሬዚዳንት ኢሳያስ መንግስትና የኳታርን ግንኙነት መናገር የግድ ይለኛል። ይህን የምልበት ምክንያት የኤርትራ መንግስት ሰናይ ስብዕና ያለው ሆኖ ሲያበቃ፤ እኔ በመጥፎነቱ እየሳልኩት አይደለም። በሌላው ዘውግም ጥፋቱን በመቀባባት የምሸፍንለት አይደለሁም። የነበረውንና ያለውን ዕውነታ በመረጃ እያስደገፍኩ ብቻ ነው የምገልፀው። ሲጀመር የአስመራው አስተዳደር ምንም ዓይነት ሰናይ ምግባር የለውም እንጂ ቢኖረው እዚህ ላይ ማስፈሬም አይቀርም ነበር።
ግና ትናንት ከዶሃ መንግስት ጋር የፍቅር ታንኳን እየቀዘፈ እፍ…ክንፍ ሲል የነበረው ሻዕቢያ፣ ዛሬ ደግሞ አዲስ ለምድ ለብሶ ከሳዑዲ አረቢያ፣ ከተባበሩት አረብ ኢምሬትስና ከግብፅ ጋር የ“አንለያይም” ነጠላ ዜማን እያቀነቀነ ነው። “ቤቴ ቤታችሁ ነው” በማለት የጦር ሰፈር ሰጥቶ “አሸሼ ገዳሜ…መቼ ነው ቅዳሜ” እያለም ነው።
ትናንት የኳታር መንግስት ኤርትራ የራስ ዱሜራን አካባቢዎች ስትወር ገንዘብ ተቀብሎ ቦታውን “በሰላም አስከባሪነት” ለኳታር እንዳልሰጠ፣ ትናንት የአልጀዚራ ጋዜጠኞችን ጓዳው ድረስ አስገብቶ እንዳልጋበዘ ዛሬ ላይ “ጡሩንባዎች” ማለቱ የሻዕቢያን ተጠቅሞ የመጣል ፖለቲካ ማሳያ ነው። ዛሬም ወገቡን ሸብ አድርጎ የምስራቅ አፍሪካ ቀጣናን በሁከት ለማተራመስ የነገር አንቴናውን እያንቀሳቀሰ ነው።
ሻዕቢያ ከትርምስ ውጭ አንዴም ቢሆን ለምስራቅ አፍሪካ ሰላምና መረጋጋት የሰራበትን ወቅት አላስታውስም። ባለፉት ጊዜያት ጦረኝነትን እንደ አንድ የመታወቂያ መንገድ በመውሰድ፤ በመጀመሪያ በሃኒሽ ደሴት ጉዳይ የመንን የወረረ፣ ሱዳን ውስጥ “የቤጃ እንቅስቃሴ” የሚያካሂዱ አማጺዎችን የደገፈና በማስፈራራት ፖሊሲ ሲሞክር የነበረ፣ የሀገራችንንም ባድመንና አካባቢውን በእብሪት የወረረና ሀገሪቱ በጦርነት ስትታመስ ወደ 400 የሚጠጉ ወታደሮቹን በአንድ ወገን አሰልፎ በጣልቃ ገብነት የተዋጋ እንዲሁም የጂቡቲን የራስ ዱሜራ ኮረብታዎችንና ሃይቆችን ወርሮ አልለቅም ያለ መንግስት ነው። ያለ አንዳች ይሉኝታ በአዲሲቷ ደቡብ ሱዳን ጉዳይም የትንኮሳ እጁን ያስገባ ነው። ይህ ሁኔታም በአፍሪካ ህብረትና በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የሚታወቅ ብቻ ሳይሆን፤ የመንግስታቱ ድርጅት ከአንዴም ሁለቴ ማዕቀብ እንዲጥልበት ምክንያት የሆነበት ነው።
ባለፉት ጊዜያት የኤርትራ መንግስት በቀጣናው ላይ የወሰዳቸው አፍራሽ የትርምስ ርምጃዎች በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ የተሳኩ አይደሉም—ምስጋና ለሰላምወዳድ ሃይሎች ይሁንና። እንደሚታወቀው የኤርትራ መንግስት ወርሯት የነበረችው የመን ጉዳዩን ወደ ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት ወስዳ ሃኒሽ ደሴትን ማስመለስ ችላለች።
ሱዳንም ብቅ…ጥልም የሚል የዲፕሎማሲ መንገድን ከኤርትራ ጋር ስታከናውን ቆይታለች። መረጃዎች እንደሚጠቁሙት በሱዳንና በኤርትራ መካከል የነበረው ግንኙነት አርኪ አልነበረም። ምንም እንኳን ኢሳያስ አፈወርቂ ካርቱም፣ ሐሰን አልበሽር አስመራ በየጊዜው እየተገናኙ ቢወያዩም ግንኙነታቸው አጥጋቢ ነበር የሚባል አይደለም።
ይሁንና ሁለቱ ሀገራት የተሳሰረ ግንኙነት አልነበራቸውም ማለት አይቻልም—የዛሬን አያድርገውና። ዛሬ ግብፅ ጦሯን ኤርትራ ላይ ማስፈሯ እንደተሰማ፤ ሱዳን ከኤርትራ ጋር የሚያዋስናትን ድንበሯን ጥርቅም አድርጋ መዝጋቷን ሪፖርቶች ገልፀዋል። ምክንያቷ ደግሞ “ሀገሬን የሚያጠቃ ሃይል በድንበሩ በኩል እንደሚመጣብኝ መረጃ ደርሶኛል” የሚል ነው። እንግዲህ ኤርትራና ሱዳን ዘለግ ያለ ድንበር የሚጋሩና ህዝባቸውም በታሪካዊ ሁኔታ የተዛመደ ሆኖ ሲያበቃ፤ በአቶ ኢሳያስ አፈወርቂ ጥገኛ ባህሪ ምክንያት ኤርትራ ዛሬ የሱዳን የስጋት ምንጭ ሆናለች።
ግብፅና ሱዳን ቀደም ሲል ድንበራቸው ላይ በምትገኘው ትንሽዬ ደሴት ሳቢያ እሰጥ- አገባ ውስጥ ነበሩ። ከዚያም በኋላ ሱዳኖች ኢትዮጵያ በፍትሃዊነትና በጋራ ተጠቃሚነት የምትገነባው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሚያስገኝላቸውን ዘርፈ-ብዙ ጥቅሞች በማየት የግድቡ ደጋፊ መሆናቸው “ታሪካዊ የውሃ ሃብታችን አይነካም” በማለት በሰለጠነው 21ኛው ክፍለ ዘመን የቅኝ ገዥዎች ውሎችን የሙጥኝ ያሉት ግብፆችን እንዳናደዳቸው መረጃዎች ያስረዳሉ።
ምን ይህ ብቻ። ሱዳኖች ግንኙነታቸውን ከኢራን ጋር ማጥበቃቸው፣ በተለይም የቱርክ ፕሬዚዳንት ረሲፕ ጣይብ ኤርዶጋን ከመሰንበቻው ሱዳንን ሲጎበኙ በአሸባሪነትና በወታደራዊ ጉዳዩች ተባብረው ለመስራት ሲፈራረሙ፤ የአረቡ ዓለም ተወካይ ነኝ የምትለው ግብፅ ደስተኛ አልነበረችም። በዚህም በካርቱምና በካይሮ መካከል ውጥረት እንዲከሰት ምክንያት ሆኗል። እናም አንዳንድ ተንታኞች እንደሚገልፁት፤ የግብፅ መንግስት ጦሩን ኤርትራ ላይ አስፍሯል። ታዲያ ይህን ሁኔታ ያጤኑት አቶ ኢሳያስ አፈወርቂ ወደ ካይሮ ሄደው ከፕሬዚዳንት አልሲሲ ጋር በመወያየት የተለመደውን “ገንዘብ ከሰጣቸሁኝ ምንም ነገር እሰጣችኋለሁ” ብለው ወደ ሀገራቸው ተመልሰዋል።
በአንድ ወቅት አሜሪካዊው ተመራማሪ ዳን ኮኔል እንዳለው ኤርትራ ውስጥ ጦርነት ንግድ ነው። እናም ሁሌም ጦርነት ባለበት ቦታ ሁሉ የማይጠፋው የአቶ ኢሳያስ መንግስት በአሁኑ ወቅት እነ ግብፅ ከሚገኙበት የመካከለኛው ምስራቅ የፖለቲካ ትኩሳት ተሳታፊ ሆኗል። እነዚህ ሀገራት ወደብ ከመግዛት ጀምሮ ጥሬ ብር ለአቶ ኢሳያስ በማስታቀፋቸው ከሀገራቱ ጋር እጅና ጓንት መሆንን መርጧል።
ርግጥም ዛሬ አቶ ኢሳያስና አስተዳደራቸው ፊታቸውን አዙረው ሀገራቱ ሲያስነጥሳቸው መሃረብ ይዘው በመቅረብ ‘እኔን!…እኔን!’ ባይ ሆነዋል። የካይሮው ጉብኝታቸው የእነ ግብፅን ፍላጎት ተከፍሏቸው ለማሟላት የተደረገ መሆኑን ለመገመት ነብይ መሆንን አይጠይቅም—ግልፅ ነውና። የመካከለኛው ምስራቅ ፖለቲካ ወደ ምስራቅ አፍሪካ እንዲሳብና በተለይ የግብፅ ጥቅሞችን ለማስፈፀም የተሰለፉ ናቸው። አቶ ኢሳያስ ያለ መርህ ለሰጣቸው ሁሉ አፋሽ አጎንባሽ በመሆናቸው የእነ ግብፅ ፍላጎት የመጫወቻ ካርታ ሆነዋል።
በአሁኑ ወቅት ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ፣ አፍሪካ ህብረትና የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) በመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት መካከል የተፈጠረው የፖለቲካ ውዝግብ በውይይት እንዲፈታ ጥሪ እያቀረቡ ባሉበት ወቅት፤ የፕሬዚዳንት ኢሳያስ አስተዳደር የአንድ ጎራ ዘማሪ ሆኖ መታየቱ ሻዕቢያ ዛሬም ከሁከትና ከብጥብጥ ለማትረፍ ያለውን ፍላጎት ፍንትው አድርጎ ያሳያል። ምን ያህል ጥሬ በሆነ የፖለቲካ መንገድ ላይ እንደሚጓዝ፣ ለዓለም አቀፉና ለአፍሪካ ህብረት ሚዛናዊና ሰላም ወዳድ ፍላጎቶች የማይገዛ መንግስት መሆኑን የሚያሳይ ይመስለኛል።
የኤርትራ መንግስት በፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ አምባገነናዊ አመራር የሚመራ በመሆኑ ሁሉም ነገሮች በእርሳቸው ፍላጎት ብቻ የሚቃኝ ነው። ተደጋግሞ እንደሚገለፀው እርሳቸው የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ቢሆኑም የሁሉም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችን ስራ ወክለው በቀጥታ ትዕዛዝ የሚሰጡ ናቸው። ምናልባትም የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይና የመከላከያ ሚኒስትሮች ሳያውቁት እርሳቸው ድንገት በጎረቤት ሀገር ላይ ወረራ እንዲፈፀም የበታች ሹማምንቶችን ሊያዙ ይችላሉ። ይህ ምንም ማለት አይደለም። በአስመራው ቤተ መንግስት ውስጥ የተለመደ አሰራር ነው።
እናም አቶ ኢሳያስ ተጠቅሞ የመጣል ፖሊሲያቸውንና ገንዘብ በማገኘት ጎረቤቶቻቸው ላይ የሚታዘዙትን ሁሉ ከመፈፀም ወደ ኋላ የማይሉትን ሰውዬ በንቃት መጠበቅ ያስፈልጋል። ምክንያቱም “ነገ እንዲህ ሊያደርጉ ይችላሉ” ተብሎ መገመት ስለማይቻል ነው። እናም በእኔ እምነት ሱዳን ከእርሳቸው ጋር የሚያዋስናትን ድንበር ጥርቅም አድርጋ መዝጋቷ ትክክለኛ ውሳኔ ነው። ምንም እንኳን ሻዕቢያ ሊከተለው የሚችለውን ቅጣት ጠንቅቆ ስለሚያውቅ ኢትዮጵያን ደፍሮ አንድ ነገር ያደርጋል ተብሎ ባይታሰብም ቅሉ፤ የኢፌዴሪ መንግስት በተለይ በድንበር አካባቢዎች የቅርብ ክትትልና ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርበታል ብዬ አስባለሁ።