Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ትክክል! የአገር ጉዳይ ቀድሟል

0 408

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ትክክል! የአገር ጉዳይ ቀድሟል

                                                       ደስታ ኃይሉ

በአንዳንድ አካባቢዎች ቀደም ሲል ግጭቶች ቢከሰቱም ኢህአዴግ እንደ ድርጅት ግጭቶችን ለማስወገድ በመግለጫው ላይ በመስማማቱ ለግጭቶች መፍጠር ምክንያት የሆኑ ጉዳዩችን እንደሚዘጋ ገልጿል። አሁን በምንገኝበት ሁኔታ በርካታ አካባቢዎች ወደ ሰላማዊ ሁኔታ ተመልሰዋል። ይህም አገራዊ አንድነት እንዲጠናከር በር የሚከፍት ነው። ኢህአዴግ የያዘው ይህ ግጭቶችን የመፍታት ቁርጠኛ አቋም አገርን እንደ አገር ሊያቆምና ከነበርንበት ለግጭት ምቹ የሆነ ሁኔታ ሊያወጣን የሚችል መሆኑ ግልፅ ነው።

እንደሚታወቀው ሁሉ ኢህአዴግ በመግለጫው “በአገራችን የሚታዩ የቆዩና ወቅታዊ ችግሮችን ከነዝርዘር መገለጫቸው በመለየት በመንስኤና መፍትሄዎቻቸው ላይ መክሮ የሃሳብ አንድነትና መተማመን ፈጥሯል። ችግሮቹን በመቅረፍ በእስካሁን ትግላችን የተመዘገቡ መልካም ውጤቶችን አስጠብቆ ለማስቀጠል የሚያስችል ቁርጠኝነትና ጠንካራ መግባባትን አረጋግጦ ወጥቷል” በማለት ግጭቶቹን ለመፍታት ያለውን የማያወላዳ አቋም ይፋ አድርጓል። የዚህ አባባል ምክንያት ግልፅ ይመስለኛል። ይኸውም ኢህአዴግ ትናንትም ይሁን ዛሬ ግጭትንና መንስኤዎቹን የሚሸከም ትከሻ የሌለው መሆኑ ነው።

ኢህአዴግ የግጭት መንስኤ የሆኑትን ጥበትን፣ ትምክህትንና ኪራይ ሰብሳቢነትን የሚሸከም ታሪክ የለውም። አገራችን ውስጥ ያሉት የጠባብነት፣ የትምክህተኝነትና እነርሱን ተከትለው ሊመጡ የሚችሉ የመንግስት ስልጣንን ለግል ኑሮ መገልገያነት የማዋል ፍላጎትና ተግባር መኖሩ ግልፅ ነው።

እነዚህ ችግሮች ካለፉት ስርዓቶች ሲንከባለሉ የመጡና እዚህ ሀገር ውስጥ ላለፉት 26 ዓመታት የተገኙት የልማት ትሩፋቶች የፈጠሯቸው አውዶች በመሆናቸው በአንድ ጀንበር ሊወገዱ የሚችሉ አይመስሉኝም። ሆኖም ችግሮቹ ገዥ እንዳይሆኑና የሚፈጥሩትን ተፅዕኖ እጅግ አነስተኛ ማድረግ ይቻላል። በእኔ እምነት ኢህአዴግ ከህዝቡ ጋር በመሆን ይህን ማድረግ ይችላል። ለዚህም ይመስለኛል በተለያዩ ወቅቶች በጥልቀት በመታደስ ተግዳሮቶቹን መፍታት እንደሚችል እየገለፀ የሚገኘው።

እረግጥ ኢህአዴግ “እታደሳለሁ” ካለ ይታደሳል። ይህንንም በተለይም የዛሬ 16 ዓመት ገደማ አሳይቶናል። በዚያ የተሃድሶ ወቅት በተከተላቸው ትክክለኛ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ሀገራችንን የልማት ተምሳሌት አድርጓል።

የኢህአዴግን መስመር ዛሬ አፍሪካዊ ወንድሞቻችን እንደ “ሞዴል” እየወሰዱት ነው። ድርጅቱ ከትናንት ችግሮቹ እየተማረና ፈተናውንም በአጥጋቢ ውጤት እያለፈ የመጣ ህዝባዊ ኃይል ነው።

የጥልቅ ተሃድሶ መንገድ ረጅም በመሆኑ እንደ ትናንቱ ዛሬም ከህዝብ ጋር ሆኖ ራሱን በጥልቀት ይፈትሻል። በዚህም በአንዳንድ አካባቢዎች የተፈጠሩትን ሁከቶች በማርገብ ሰላምና መረጋጋትን መፍጠሩ አይቀሬ ነው። ድርጅቱ ምንም እንኳን በተለያዩ ማህበራዊ መስተጋብሮች ሊፈተን የሚችል ቢሆንም፤ ዋናው ነገር ችግሮቹን በተገቢው ሁኔታ ከህዝብ ጋር ሆኖ ለማለፍ ያደረገው ጥረትና ያስገኘው ውጤት አጥጋቢ ከመሆኑ ላይ ነው።

ኢህአዴግ በየጊዜው የሚያጋጥሙትን ጊዜያዊ ተግዳሮቶች እየፈታ የመጣ ድርጅት ነው። ኢህአዴግ ከአገራችን ህዝቦች ጋር በመሆን አምባገነኑን የደርግ ስርዓት ለመጣል ርብርብ ለማድረግ ከወሰነበት ጊዜ አንስቶ በመንግስትነት ሀገሪቱም መምራት እስከጀመረበት ጊዜ ድረስ በርካታ ተግዳሮቶች አጋጥመውታል። እነዚህ ተግዳሮቶች ድርጅቱን የተፈታተኑት ቢሆኑም፤ ከህዝብና ከመላው አባላቱ ጋር በመሆን አያሌ ችግሮችን በብቃት መሻገር ችሏል።

ለ17 ቀናት የቀየው የኢህአዴግ ግምገማ የጥልቅ ተሃድሶው ውጤት ነው። በዚህ ውጤት  የህግ የበላይነትን የማረጋገጥ ጉዳይ ላፍታም ቢሆን ጥያቄ ውስጥ ሊገባ እንደማይገባውና በዚህ ረገድ የሚታዩ የህግ ጥሰቶችን በመቆጣጠር ህግና ሰላምን በአስተማማኝ ደረጃ ማስፈን እንዳለበት ገልጿል።

እንዲሁም በየአካባቢው በህገ ወጥ መንገድ የሚደረጉ መንገድ የመዝጋት፣ የዜጎችን በነፃ የመንቀሳቀስ መብት የማወክ እንዲሁም የሕዝቡን የእለት ተለት እንቅስቃሴ የሚያስተጓጉሉ የቡድንም የተናጠልም እንቅስቃሴዎች እንዲቆሙ ለማድረግም ወስኗል። በወሰንም ሆነ በሌሎች ምክንያቶች የሚያጋጥመውን ሞትና መፈናቀል ሙሉ በሙሉ እንዲቆሙ ለማድረግም ቃል ገብቷል። በቅርቡ በኦሮሚያና በሶማሌ ክልል መካከል ባሉ አዋሳኝ አካባቢዎች ባጋጠሙ ግጭቶች ሳቢያ የተፈጠረው የዜጎች ሞትና እንግልት እንዲሁም የመቶ ሺዎች መፈናቀል በአስቸኳይ ተገቶ ተፈናቃዮች መደበኛ ህይወታቸውን በተረጋጋ መንገድ የሚመሩበት ሁኔታ ባስቸኳይ ለማመቻቸትም ወስኗል።

እነዚህ ውሳኔዎች ገዥው ፓርቲ ምን ያህል ለህግ የበላይነትና ለዜጎች ሰላማዊ ህይወት የሚጨነቅ መሆኑን የሚያረጋግጡ ናቸው። እርግጥ ኢህአዴግ ከ16 ዓመት ባካሄደው የተሃድሶ ግምገማ አድርገዋለሁ ያለውን የፈፀመ ድርጅት ነው። በዛሬው ግምገማውም ቅድሚያ ለአገር በመስጠት የገባውን ቃል አያጥፍም።

በወቅቱ በአገሪቱ ውስጥ አንዣቦ የነበረው የሙስና እና የኪራይ ሰብሳቢነት ተግባርን ለመግታት በተደረገው ትግል፣ በድርጅቱ ውስጥ ለሁለት የተከፈለውን ጎራ በመለየት ለህዝቡ የተፈጠረውን ችግር እንደሚፈታና በአገሪቱ ውስጥ ፈጣን ልማትን እንደሚያረጋግጥ ቃል ገብቶ መፈፀም የቻለ ድርጅት ነው።

በቃሉ መሰረትም ለሀገሪቱ ዕድገት መሰናክል የሆኑ አስተሳሰቦችን ለመቅረፍ የፀረ-ሙስና ኮሚሽንን በማቋቋም እንዲሁም ከኪራይ ሰብሳቢነት ጋር ግንኙነት የነበራቸውን ወገኖች ለህግ የማቅረብ የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ሰርቷል።

የአገሪቱን ኢኮኖሚም ለማሳደግ ጥሯል። በወቅቱ የሀገሪቱ ምጣኔ ሃብት የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ያደቀቀው በመሆኑ፤ይህን በማሻሻልና ህዝቡ በየደረጃው ይብዛም ይነስ ተጠቃሚ እንዲሆን አድርጓል። ዛሬ ለምንገኝበት የህዳሴ መስመርም መሰረት የጣለ ድርጅት ነው። የህዝቡን ተጠቃሚነትና በአገር ላይ ያንዣበበውን አደጋ በማስወገድ ሁሉንም ፈፅሟል።

የአሁኑ ግምገማውም ትክክል ነው። በተለይም “በአገራችን የተመዘገቡት ስኬቶች ዋነኛ ምስጢር የሕዝብን ተሣትፎ ማረጋገጥ መቻሉ ነው። በዚህም መሰረት ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው የህዝብን አመኔታ መልሶ ለማግኘትና ለህዝብ ጥያቄዎች ፈጣን ምላሽ ለመስጠት የሚያስችሉ ተከታታይ ርምጃዎችን መውሰድ እንደሚገባ ወስኗል። ህዝብ የሚደመጥበትና ወሳኝነቱ በሚገባ የሚረጋገጥበት እድል እንዲሰፋ አፅንኦት ሰጥቶታል።…” በማለት የአገርን አደጋ ለመቅረፍ የገባውን ቃል ይፈፅማል።  

እርግጥ በግምገማው ላይ ኢህአዴግ ከህዝቡ ጋር በመሆን ያሉትን ችግሮች መስመር ለማስያዝ እንደሚሰራ ገልጿል። ይህ የድርጅቱ ቁርጠኛ ቃል በህዝብ ሊደገፍ ይገባል። ህዝቡም አገርን የሚያክል ነገር ለማዳን በሚደረገው ርብርብ ውስጥ የተለመደ ግንባር ቀደም ተሳታፊነቱን ማረጋገጥ ያለበት ይመስለኛል። በህዝብ ያልተደገፈ ማንኛውም ነገር ውጤት ሊያመጣ ስለማይችል ኢህአዴግ እንዳለው የጎደለውን በመሙላትና በማረም ለአገሩ ትንሳኤ እጅ ለእጅ መያያዝ ይኖርበታል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy