Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ችግሮችን በመለየት የታየው ቁርጠኝነት በመፈፀምም ይደገም

0 524

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ችግሮችን በመለየት የታየው ቁርጠኝነት በመፈፀምም ይደገም

ብ. ነጋሽ

የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ከሚቴ ከታህሳስ 3 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ ለ17 ቀናት ያካሄደውን ስብሰባ ባለፈው ዓርብ አጠናቆ መግለጫ አውጥቷል። የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ከአራቱም እህትማማች ድርጅቶች ማለትም ከህወሃት፣ ብአዴን፣ ኦህዴድና ደኢህዴን የተወከሉ እኩል ቁጥር ያላቸውን አባላት የያዘ የግንባሩ የአመራር አካል ነው። ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው አገሪቱ የምትገኝበትን ወቅታዊ ሁኔታ መነሻ በማድረግ ሰፊና ዝርዝር ግምገማ ማካሄዱን በመግለጫው አሳውቋል። ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው በዚህ ስብሰባ ቀደም ሲል የተጀመረውን የመታደስ ሂደትና የደረሰበትን ደረጃ እንዲሁም በአገሪቱ የሚታዩ የቆዩና ወቅታዊ ችግሮችን ከነዝርዘር መገለጫቸው በመለየት በመንስዔና መፍትሄዎቻቸው ላይ መክሮ የሃሳብ አንድነትና መተማመን መፍጠር መቻሉንም አስታውቋል።

መግለጫው በስብሰባው ላይ ተነስተው ስምምነት የተደረሰባቸውን እንዲሁም ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ያሳለፋቸውን ወሳኔዎች የሚመለከቱ በርካታ ጉዳዮችን ይዟል። ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ስምምነት የደረሰባቸውና ውሳኔ ያሳለፈባቸው ጉዳዮች በርካቶች በመሆናቸው በአንድ የጋዜጣ ጽሁፍ ሁሉንም ማንሳት አይቻልም። ይሁን እንጂ በዚህ ጽሁፍ ለብዙዎች ስሜት ቅርብ የሆኑ አንድ ሁለት ጉዳዮችን ለመመልከት ወድጃለሁ።

መግለጫው የስራ አስፈጣሚው ስብሰባ በመላው የአገራችን ህዝቦች ከባድ ተጋድሎ የተመዘገቡ ስኬቶችን ለመጠበቅና ለማስፋት እንዲሁም ከምንም ነገር በላይ በአመራር ድክመት የተፈጠሩትን አደጋዎችና ሥጋቶች ለመቅረፍ በሚያስችል ስምምነትና መግባባት መጠናቀቁን ያመለክታል።

ኢህአዴግ ችግሮች ሲገጥሙት የችግሮችን ምንጭ ፍለጋ ወደውጭ ከማማተር ይልቅ ወደውስጥ ተመልክቶ ራሱን የመመርመር ባህል ያዳበረ ድርጅት ነው። ራሱን ፈትሾ ድክመቶችን ለህዝብ ይፋ ሲያደርግ ይህ የአሁኑ የመጀመሪያው አይደለም። በተለይ በ1993 ዓ.ም፣ በ1997 ዓ/ም ከተካሄደው ሶስተኛ ዙር አገራዊ ምርጫ በኋላ፣ እንዲሁም በ2008 ዓ.ም ይህን ማድረጉን ብዙዎች ያውቃሉ ብዬ እገምታለሁ። በሰሞኑ የሥራ አስፈጻሚ ስብሰባ ላይ የሰፈረውም ይህነኑ የሚያመለክት ነው። ይህ ራስን የመመርመርና ችግሮችን ለይቶ ለህዝብ ይፋ የማድረግ አካሄድ የተለመደ ስለሆነ በዚህ ላይ በዙ ማለት አይቻልም። ግን እንደ ትልቅ ጥንካሬ የሚወሰድ መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል።

የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው መግለጫ፤ “. . . ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በርከት ባሉ የአገራችን አካባቢዎች ሰላምና መረጋግት እየደፈረሰ ሁከት የለት ተለት ክሰተት እየሆነ መጥቷል። በክልሎችም ሆነ በክልሎች መካከል በልዩ ልዩ ሰበቦች የሚከተሰተው የሰላም መደፍረስ ለዜጎቻችን አሳዛኝ ሞት መበራከትና መቁሰል እንዲሁም ከባድ መፈናቀል ምክንያት ሆኗል። በተጨማሪም ከፍተኛ የንብረት ውድመትና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ መገታት አስከትሏል። ይህ ለረጅም አመታት በሰላም በኖረችው አገር ውስጥ የስጋት መንፈስና ጭንቀት ፈጥሯል። ከየቦታው እየተነሱ ያሉ ግጭቶች ከሰው ሞትና ከንብረት ውድመት በዘለለ የሃገራዊ ሕልውናችን ለአደጋና ሕዝባችንን ለጥፋት ቋፍ ያደረሱበት ሁኔታ ከመኖሩ በላይ ለውጭ ጥቃት ተጋላጭነታችንን የመጨመር ውጤት አስከትለዋል። ይህም በአጭር ቃል የመበልፀግ ተስፋና የሐገራዊ ሰላም መናጋት የተፋጠጡበት ሁኔታ ላይ እንደድንገኝ አድርጎናል። ከዚህ በመነሳት ስራአስፈፃሚ ኮሚቴያችን ህገመንግስታዊ ዴሞክራሲያችንን በታማኝነት ተግባራዊ ማድረግ ብቻ ሳይሆን መድረኩ የሚጠይቀውን ሁኔታ መነሻ በማድረግም ማስፋትና የግጭት መንስኤዎችን መቅረፍና የአገራችንን ሰላም ወደተለመደው አስተማማኝ ሁኔታ በአጭር ጊዜ መመለስ እንደሚገባ ወስኗል።” ይላል።

በመግለጫው ላይ የተነሱት ጉዳዮች በተለይ ከ2008 ዓ/ም ጀምሮ የሰርክ ክስተት ሆነዋል። ኢህአዴግ በ2008 ዓ/ም ለሰዎች ህይወት መጥፋትና ንብረት ውድመት ምክንያት የሆኑ ሁከቶችና ግጭቶች መንስኤ የመልካም አስተዳደር መጓደል፣ ኪራይ ሰብሳቢነትና የወጣቶች ስራ አጥነት መሆኑን ገምግሟል። የችግሩ ምንጭ ደግሞ በመንግስት አመራር ላይ ያሉ ሰዎች የመንግስትን ስልጣን የህዝብ ማገልገያ መሳሪያ አድርገው ከመውሰድ ይልቅ ለግል ጥቅም ማደላደያ አድርገው መውሰዳቸው መሆኑንም አሳውቋል። በጥልቀት የመታደስ ንቅናቄ ያወጀውም ይህን ግምገማ መነሻ በማደረግ ነበር። በጥልቀት የመታደስ ንቅናቄውን መነሻ በማደረግ ችግሮቹን ያቃልላሉ ተብለው የታመነባቸው በርካታ እርምጃዎች ቢወሰዱም ሁከቶች የተለያየ ለኳሽ ሰበቦችን መነሻ በማደረግ መልካቸውን እየቀያየሩ የቀጠሉበት ሁኔታ ነው ያለው። ይባስ ብሎ በተለይ በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሱማሌ ክልሎች መሃከል ለበርካቶች ሞትና በመቶ ሺሆች ለሚቆጠሩ ዜጎች መፈናቀል ምክንያት የሆነ በሃገራችን ያልተለመደ አይነት ግጭት ተቀስቅሷል።

ይህ በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሱማሌ ክልሎች መሃከል የተፈጠረው አለመግባበባትና ግጭት ሃገሪቱን ለማተራመስ ለሚፈልጉ ሃይሎች መልካም አጋጣሚን ፈጥሮ አጠቃላይ የሃገሪቱን ሰላምና መረጋጋት ለስጋት አጋልጧል። አጠቃላይ አሁን ሃገሪቱ ያለችበት ሁኔታ ሲታይ በአንድ በኩል ባለፉ አንድ ተኩል አስርት ዓመታት በተመዘገቡ የህዝቡ ኑሮ ላይ ተጨባጭ ማሻሻል ያስመዘገቡ እድገትና ልማቶች የይቻላል መንፈስና ተሰፋ ፈጥረዋል። ሃገሪቱ የብልጽግና ማማ ላይ የሚያደርስ መሰላል ላይ ወጥታለች። በሌላ በኩል ከላይ የተጠቀሱት ሁከቶችና ግጭቶች በረዱ ሲባሉ መልካቸውን እየቀያያሩ ሁለት ዓመት ተሻግረው ሶስተኛውን መያዛቸው፣ እንዲሁም ኪህ በፊት በሃገሪቱ ታይቶ በማያውቅ ሁኔታ ጉዳት ያስከተለ ግጭት ማጋጠሙና ሁከትና ግጭቱን ለማቀጣጣል በማህበራዊ ሚዲያ የሚደረገው ርብርብ ሃገሪቱ የብልጽግና ማማ ላይ ከሚያደረሳት ከጨበጠችው መሰላል ላይ ትፈጠፈጥ የሆን? የሚል ስጋት አሳድሯል። ህዝቡ አሁን በዚህ ስጋትና ተሰፋ መሃከል እየዋለለ ነው።

እናም ድርጅቱ ለችግሩ ትኩረት ሰጥቶ መፍትሄ ለማበጀት መወሰኑ ሰላም ወዳድ በሆኑ ዜጎች ዘንድ ተስፋን ፈጥሯል። ይህ ውሳኔ በመግለጫ ወረቀት ላይ ተወስኖ እንዳይቀር የብዙዎች ምኞት ነው። ለሁለት ዓመታት የዘለቀው የሰላም እጦት እያደረ ህዝቡን ተስፋ እያስቆረጠው፣ ኢኮኖሚው ላይ የሚያደርሰውም ጫና እየበረታ ሃገሪቱን ሊያሽመደምድ እንደሚችል መታወቅ አለበት።

የኢህአዴግ የስራ አስፈጻሚ ያወጣው መግለጫ ላይ ትኩረት ልሰጠው የፈለኩት ሌላው ጉዳይ የሃገር አንድነትን በተመለከተ የሰፈረው ሃሳብ ነው። በዚህ ዙሪያ መግለጫው፤ “ድርጅታችን የሁሉም ህዝቦች እኩልነት በተከበረባት አገራችን አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማህበረሰብ የመገንባትን መርህ ተክትሎ ሲንቀሳቀስ ቆይቷል። በተጨባጭም አገራችንን ከመበታተን ቋፍ አውጥቶ አዲስ አይነት ዴሞክራሲያዊ አንድነትና የእኩልነት ትስስር በመገንባት ረጅም ርቀት ተጉዟል። ይህ በአገር አቋራጭ የመሰረተ ልማት አውታሮች የማይበጠስ ትስስር እንዲፈጠር አድርጓል። ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ በሃገራችን በየደረጃው እየተካሄዱ ያሉና ሊካሄዱም የሚገባቸው የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቶች የድርጅታችን ሃገራዊ ራዕይና የፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓታችንን በሚያጠናክር መልክ በማስኬድ ረገድ ቁጥራቸው የማይናቅ ጉድለቶች በአመራሩ ተፈጽመዋል። በአጭሩ በህብረተሰባችን ዘንድ ህገመንግሥታዊ ሥርዓቱን፣ ልማታዊ አስተሳሰብና፣ በብዝሃነት ላይ የተመሠረተ ኢትዮጵያዊ አንድነት በማጠናከር ረገድ የተሰራው ስራ መሆን የሚችለውን ያህል ውጤት ሳያመጣ እንደቀረ ሥራ አስፈፃሚው ባደረገው ግምገማ ማረጋገጥ ችሏል። በዚህ የተነሳ ብሄረሰባዊና አገራዊ ማንነትን አስተሳስሮ በመገንባት በኩል የታየውን ጉድለት በአፋጣኝና በአስተማማኝ መንገድ መፍታት እንደሚኖርብን ታምኖበታል።” ይላል።

ይህ ሃሳብ የሃገሪቱ አንድነት ላይ የሚያተኩር ነው። አንድ ብዙ ሰው ያልተረዳው ኢህዴግም በሚገባው ልክ ያላስረዳው ሆኖ የሚሰማኝ ነገር ኢህአዴግ ከማንም በላይ ለኢትዮጵያ አንድነት የቆመ መሆኑን ነው። ኢህአዴግ ደርግ ተወግዶ በስልጣን ላይ በቆየባቸው ጊዜዎች ሁሉ ስለኢትዮጵያ አንድነት ነው የሚያወራው። የመበታተን ስጋት ያስፈራዋል። የኢህአዴግን አንድነት ከሌሎች የሚለየው በብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች እኩልነት ላይ የተመሰረተ መሆኑ ነው። ብሄራዊ ማንነቶችን በመጨፍለቅና እውቅና በመንፈግ የሚመጣ አንድነት ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦችን ወደነጻነት ትግል እንዲገቡ ስለሚያስገድዳቸው የሃገሪቱ ሰላም የናጋል አንድነቷም ለአደጋ የጋለጣል ባይ ነው። በእኔ አረዳድ ኢትዮጵያን አንድ አድርጎ ማስቀጠል የሚያስችለው የኢህአዴግ አማራጭ ነው።

ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ለአንድ ክፍለ ዘመን ያህል ጭቆና ተጭኗቸው ስለኖሩና በርካቶቹ ለነፃነት የትጥቅ ትግል በማካሄድ ላይ ስለነበሩ ከደርግ ውድቀት በኋላ ጫና ስር የነበረውን ማንነታቸውን ማቃናት ላይ ያተኮሩበት ሁኔታ ታይቷል። ይህም ኢትዮጵያዊ አንድነት ሁለተኛ ተግባር እንዲሆን አድርጓል፤ ቢያንስ እስከአሁን ባለው ጊዜ ውስጥ። እርግጥ ህገመንግስቱ ብዝሃነት ላይ የተመሰረተ አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማህበረሰብ እንደሚመሰረት ይደነግጋል። ይህ ብቻ አይደለም። ህገመንግስቱ በአንቀጽ 88 ላይ መንግስት የብሄሮችን፣ ብሄረሰቦችንና ህዝቦችን እኩልነት፣ አንድነትና ወንድማማችነት የማጠናከር ግዴታ እንዳለበት ይደነግጋል።

እንግዲህ የኢህአዴግ መግለጫ በዚህ የራሱ ፕሮግራም ላይ የሰፈረና በህገመንግስቱም የተደነገገ ኢትዮጵያዊ አንድነትን የማጠናከር ተግባር ላይ ችግር እንዳለበት ነው ያሳወቀን። ይህ ችግር የፈጠረው ክፍተት ሃገሪቱን ማናጋት ለሚፈልጉ አካላት ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በጥርጣሬ እንዲተያዩና ወደግጭትም እንዲገቡ ማድረግ የሚያስችል ቅስቀሳ ለማካሄድ እድል የሰጣቸው ይመስለኛል። በቀጣይነት የሚገነባው ብዝሀነት ላይ የተመሰረተ አንድነት ነው። ማንነታችንን እንደጠበቅን በመሃከላችን ጠንካራ አንድነት እንዲመሰረት መንግስት ብቻ ሳይሆን ሁሉም የሃገሪቱ ሰላምና ዘላቂነት የሚያሳስበው ቅን አሳቢ ዜጋ ሁሉ ሊረባረብበት የሚገባ ጉዳይ ነው።

በአጠቃላይ ኢህአዴግ በሃገሪቱ እየተለመዱ የመጡ ግጭቶችን በማስቀረት ሰላም የበላይነት እንዲያገኝ ለማድረግ እንዲሁም ኢትዮጵያዊ አንድነትን ለማጠናከር የያዘው አቋም የሁሉም ኢትዮጵያዊ ምኞት ነው። ይህ ምኞት ግን ከመግለጫ አልፎ መሬት ላይ ወርዶ መታየት አለበት። ያም ሆነ ይህ ችግሮችን መለየት ወደግብ የሚያደርስ የመጀመሪያው እርምጃ ቢሆንም በራሱ ግብ አይደለም። እናም ኢህአዴግ ወደውስጥ በመመልከት ችግሮችን ለመለየት ያሳየውን ቁርጠኝነት፣ ውሳኔዎቹን ተግባራዊ በማደረግ ችግሮችን ማሰወገድም ላይ ሊደርመው ይገባል።   

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy