ኢንቨስትመንትን የሚስብ ዲፕሎማሲ
ደስታ ኃይሉ
የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ በቅርቡ በኩባ ጉብኝት አድርገው ነበር። የፕሬዚዳንቱ ጉብኝት አገራችን እያከናወነች ያለችውን ስኬታማ ዲፕሎማሲ ማሳያ ነው። የአገራችን ዲፕሎማሲ ትብብርንና የጋራ ተጠቃሚነትን የሚከተል፣ የሚፈጠሩ ጊዜያዊ ችግሮችን በመነጋገርና በውይይት መፍታት የሚችልና ከየትኛውም አካል ጋር ተቧድኖ ጎራ የማይዝ በመሆኑ ስኬታማ ሆኗል።
ይህ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ኢትዮጵያ ቀጥተኛ የውጭ ኢንቨስትመንትን እንድትስብ ያደረጋትና ወደፊትም የአፍሪካ የኢንቨስትመንት ማዕከል እንድትሆን በማስቻል ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሊያበረክት የሚችል ነው።
እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት መርህ የአገሪቱን ገፅታ ከመለወጡ ባሻገር፤ በአፍሪካ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ መድረኮችም ተሰሚነቷንና ተፅዕኖ ፈጣሪነቷን ከፍ እንዲል አድርጓል። ሀገራችን እያካሄደች ያለው ዲፕሎማሲ ስኬት አንዱ ማሳያ እየተመዘገበ ያለው ፈጣንና ተከታታይ የኢኮኖሚ ዕድገት ነው። ይህ ፈጣንና ተከታታይ ልማትን በመደገፍ ረገድ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ ነው።
ማንኛውም የውጭ ግንኙነት ስራ ምን ያህል ለአንድ ሀገር ልማት ለማምጣት የውጭ ቀጥተኛና ቀጥተኛ ያልሆነ ኢንቨስትመንትን በመሳብ ረገድ አስተዋፅኦ አድርጓል ከሚል አኳያ የሚታይ ነው። በዚህረገድ ይህን ስራ የሚያከናውነው የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እጅግ በርካታ ተግባራትን ፈፅሟል፤ እየፈፀመም ነው። ይህ በሚኒስቴር መሪያ ቤቱና በሌሎች ጉዳዩ በሚመለከታቸው አካላት እየተከናወነ ያለው ጥረት እጅግ የሚያኮራ ነው ማለት ይቻላል።
በአሁኑ ወቅት በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች በተለይም በግብርና፣ በማኑፋክቸሪንግና ኢንዱስትሪ ዘርፎች የተሰማሩ የውጭ ባለሀብቶች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻቀበ መጥቷል ሀገሪቱ ለኢንቨስትመንት ምቹ መሆኗን የተገነዘቡ በርካታ የውጭ ኩባንያዎችና ባለሃብቶች መዋዕለ ንዋያቸውን ለማፍሰስ ከፍተኛ ፍላጎት የማሳየታቸው ምስጢርም ይኸው ይመስለኛል።
አገራችን በምትከተለው ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ትክክለኛ የኢንቨስትመንት ፖሊሲ በግሉ ባለሃብት መሰራት የሚገባቸውና በመንግስት ሊከናወኑ የሚገቡ ተግባራት ተለይተው በመካሄዳቸው በሁለቱም በኩል ውጤቶች እየተመዘገቡ ነው። የሀገር ውስጥም ይሁን የውጭ ባለሃብቶችን የሚሰማሩባቸውን ዘርፎች በመለየት አንፃራዊ በመሆነ መንገድ ለሀገሪቱ ዕድገት የበኩላቸውን ሚና እንዲጫወቱ እየተደረገ ነው።
የግሉ ዘርፍ የኢኮኖሚ ዕድገቱ አንቀሳቃሽ ሞተር መሆኑ በመንግሥት ታምኖበት በፍትሃዊ ውድድር ላይ እንዲመሰረት በመደረጉ ባለፉት 26 ዓመታት በርካታ አገራዊ ባለሃብቶች ተፈጥረዋል። እነአዚህ ባለሃብቶች በዓለም የገበያ ውድድር ውስጥ ጠንካራ አቅም እንዲኖራቸው ቀጣይነት ያላቸው ድጋፎች እየተደረገላቸው ነው።
በእነዚህ ዓመታት ውስጥ ባለሃብቶቹ የሃብት ባለቤት እንዲሆኑና ለዜጎች የስራ ዕድል እንዲፈጥሩ ሁኔታዎች ተመቻችተውላቸው በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ አሻራቸውን ማሳረፍ ችለዋል። አሁንም በማሳየት ላይ ይገኛሉ። በተለይም በኢንዱስትሪ ፓርኮች ዘርፍ የተገኘው ውጤት አበረታች ነው።
የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲው ጥረት ቀጥተኛ የውጭ ምንዛሬን ከማምጣት ባሻገር በአገር ውስጥ የሚከናወኑ የልማት ፕሮጀክቶችንም እየደገፈ ነው። ኢትዮጵያ የምታከናውነው የልማት ፕሮጀክቶች ተገቢ የማይመስላቸው አንዳድ ወገኖችንም ጭምር ከነበራቸው የተሳሳተ ግንዛቤ በሂደት ፈቀቅ እንዲሉ ያደረገ ነው። ከዚህ አኳያ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ማንሳት ይቻላል።
እንደሚታወቀው የህዳሴውን ግድብ በመገንባት ላይ የምትገኘው ሀገራችን፤ የጋራ ሃብትን በፍትሐዊነት ከመጠቀም መርህዋ ዝንፍ የምትል አለመሆኗን አሳይታለች። ግድቡም ወንድም የሆኑትን የሱዳንንና የግብፅን ህዝብ እንደማይጎዳ፣ ይልቁንም ከግድቡ ግንባታ ተጠቃሚ እንደሚሆን አሳምናለች።
ታዲያ ይህ እምነቷ ከምንም ተነስቶ የሚባል አይደለም—መሬት ላይ ያለውን የግድቡን ግንባታ መሰረት ያደረገ እንጂ። ከዚህ በመነሳትም እምነቷንና የትኛውንም ወገን ያለመጉዳት መርህዋን በተለያዩ ወቅቶች ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብና ለታችኛው የተፋሰሱ ሀገራት መንግስታትና ህዝቦች አስረድታለች። በሰፊ የዲፕሎማሲ ጥረቷም ግንዛቤም ማስያዝ ችላለች።
በመሆኑም የኢፌዴሪ መንግስት ይህን የዲፕሎማሲ ጥረት አጠናክሮ በመቀጠሉ ቀደም ሲል ጎረቤት ሱዳን፣ አሁን ደግሞ ወንድሞቻችን ግብፆች እውነታውን እየተረዱ መምጣት የቻሉ ይመስላል።
የሱዳንና የግብፅ መንግስት አሁን የያዙትን አቋም መፍጠር የተቻለውም በዚህ ምክንያት ነው። ይህ በጎ መንገድ እንዲበረታታም የግብፅን መንግስት ኦፊሴላዊ መግለጫን ከዚያች ሀገር ሚዲያዎች ለይቶ መመልከት ተገቢ ይመስለኛል።
በመሆኑም እስካሁን እየተደረገ እንዳለውና ፍሬ እያፈራ እንደሚገኘው ዓይነት የዲፕሎማሲ ጥረቶች መጠናከር አለባቸው። ይህ ማለት ግን በእኔ አምነት የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት በተለይም ግብፅ ከዚህ ቀደም “ታሪካዊ የውሃ ድርሻችን” የሚለውን አቋሟን ትታዋለች ማለት አይደለም። ያለፉት የግብፅ ገዥዎች ያራምዱት የነበሩትን አቋም በአንዴ ሊቀር አይችልም።
ታዲያ የኢትዮጵያን በጎ ጎን ማስተዋወቅና የምናከናውናቸውን ሀገራዊ የልማት ፕሮጀክቶችን ትክክለኛ ገፅታ የማሳየት ስራ የጥቂት ሙያተኞች ወይም የፖለቲካ ሹመኞች ተግባር ብቻ ተደርጎ መወሰድ የለበትም። የተሳካ አፈጻጸም ሊኖር የሚችለው መላው ህዝብ እንደ ሁኔታው የአገሩ አምባሳደር ሆኖ መሳተፍ ሲችል ነው።
በመሆኑም ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ በኩባ ያደረጉት ጉብኝት የሁለቱን ወዳጅ አገራት የቆየ ግንኙነትን የሚያጎለብት ቢሆንም፤ በዚያች አገር ውስጥ የተማሩ ኢትዮጵያዊያን በርካታ ናቸው። በተለይ በህክምናው ዘርፍ ኩባ የተማሩ ዜጎቻችን በርካታ በመሆናቸው በሁለቱ አገራት መካከል ድልድይ ሆነው በመስራት የዲፕሎማሲውን ጥረት መደገፍ ይኖርባቸዋል።
ከኩባ ወደ ኢትዮጵያ ሊመጣ የሚችል ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት መኖሩ አያጠያይቅም። እንዲሁም ኩባ በትምህርትና በሳይንስ እንዲሁም በእርሻ ለአገራችን ምጣኔ ሃብት የበኩሏን ደርሻ ልትወጣ ትችላለች። እናም የፕሬዚዳንቱ ጉብኝት ኩባ ለተማሩ ዜጎቻችን በር ከፋች በመሆኑ፤ ይህን ዕድል በሚገባ በመጠቀም አገርን ማገዝ እንደሚገባ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ዜጎቻችን ሊያስቡበት ይገባል እላለሁ።