Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

እየገነነ የመጣው የኢትዮጵያ ከፍታ…

0 399

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

እየገነነ የመጣው የኢትዮጵያ ከፍታ…

ኃብተየስ ወንድይራድ

በህዝቦች መፈቃቀድ ላይ መሠረት ያደረገ ጠንካራ ዴሞክራሲያዊ መንግሥት መገንባት ችላለች – ኢትዮጵያ። ዘላቂነት ያለው ሠላም በአገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካ በተለይ በቀንዱ አካባቢ እንዲሰፍን ጉልህ ሚና በመጫወት ላይ ትገኛለች – ኢትዮጵያ። በዚህም ተጨባጭ ለውጦች በመመዝገብ ላይ ናቸው። ኢትዮጵያ ስትከተለው የነበረው አምባገነን አሃዳዊ ሥርዓተ ተደምስሶ ያልተማከለና የህዝቦች ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶችን ያከበረ ፌዴራላዊ መንግሥት ከተቋቋመ ይኸው 27 ዓመታት ሊቆጠር ወራት ቀሩት። በእነዚህ ዓመታት ኢትዮጵያ ከውድቀት ተነስታ በርካታ ድሎችን ማስመዝገብ ችላለች።

 

አንዳንዶች ኢትዮጵያ ላስመዘገበችው ድሎች “27 ዓመታት እጅግ በጣም ረጅም ጊዜ ነው። መንግሥት አልሰራም” የሚል መከራከሪያ ሲያነሱ ይደመጣሉ። ይሁንና በደርግ ውድቀት ማግሥት ኢትዮጵያ በሁሉም ዘርፎች ከዜሮ በታች ሊባል በሚችል ደረጃ ላይ የነበረች አገር መሆኗን ልብ ማለት ይገባል። በተቃራኒው አለም ዓቀፍ ተቋማትን ጨምሮ በርካቶች የእነዚህን ቡድኖች የመከራከሪያ ነጥብ ውድቅ አድርገውታል። ምክንያቱም ኢትዮጵያ ባለፉት 27 ዓመታት በየዘርፉ በርካታ ተጨባጭ ለውጦችን ማስመዝገብ የቻለች አገር እንደሆነች ገልፀውላታልና። ባለፉት 27 ዓመታት ኢትዮጵያ ያስመዘገበቻቸውን አንዳንድ ለውጦች በጥቂቱ እንዳስስ።  

 

በእነዚህ ዓመታት የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ባደረጉት ጥረት አዲሲቷን ኢትዮጵያ መሥርተዋል። በርካቶች ኢትዮጵያ መስቀለኛ መንገድ ላይ ቆማለች፤ ወደ አዘቅቱ ልትወርድ ነው፤ እንደ ምሥራቅ አውሮፓ አገራት ልትበጣጠስ ነው ወዘተ… ሲሉ አሟርተዋል። ሆኖም ያ ሁሉ መላምት ስህተት ሆኖ ታልፏል። የህዝቦቿን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ያከበረች፣ ፈጣንና ቀጣይነት ያለው ባለሁለት አኃዝ የምጣኔ ሀብት ዕድገት ማስመዝገብ የቻለች፣ ለቀጠናው መረጋጋት ዋስትና የሆነች አዲስ አገር ሆናለች – ኢትዮጵያ። ለእነዚህ ሁሉ ድሎች መገኘት በዋናነት የኢትዮጵያ ህዝቦች ትልቁን ሚና ተጫውተዋል። በዚህ አጋጣሚ ደግሞ እነዚህ ድሎች እንዲገኙ ሕዝቦችን ያስተባበረው  ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግም ሊመሰገን ይገባዋል።

 

ባለፉት 27 ዓመታት ኢትዮጵያ በአለም ዓቀፍ መድረኮች ያላት ተደማጭነት እየተሻሻለ መምጣቱን መረዳት ይቻላል። ትናንት ትታወቅበት የነበረው ድህነት፣ ረሃብና ጦርነት ዛሬ ሙሉ በሙሉ ጠፍቷል ማለት ይቻላል። ጥግ ደርሰናል ብለን ባንኩራራም አንገት የሚያስደፋ ሁኔታ በኢትዮጵያ ውስጥ እንደሌለ ግን በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል። ባለፉት ሥርዓቶች በተለይ በደርግ ወቅት ከበርካታ የአፍሪካ አገሮች አንሳ ትታይና ስሟም  ከረሃብና ጦርነት ጋር ተያይዞ ይጠቀስ የነበረውን ሁኔታ ማስታወስ ይቻላል።

 

ዛሬ ላይ ግን አፍሪካን ማስተባበር የቻለች፤ ለአፍሪካ ሠላም ዋስትና የሆነች፣ ለአካባቢው አገሮች ህዝቦች መጠጊያ ከለላ ለመሆን የበቃች የአፍሪካ ዋስ ጠበቃ አገር – ኢትዮጵያ። ባለፉት 50 ዓመታት በኢትዮጵያ ታሪክ ተከስቶ የማያውቅ መጠነ ሰፊ ድርቅ ተከስቶ በነበረበት እንኳን እዚህ ግባ የሚባል አለም ዓቀፍ ዕርዳታ ባልተገኘበት ሁኔታ አገራችን ድርቁን መቋቋም ችላለች። መንግሥት የተከሰተው ድርቅ ወደ ረሃብ እንዳይቀየር ተግቶ በመንቀሳቀሱ በድርቁ ሣቢያ የሞተ ሰው ይቅርና ከአካባቢው የተፈናቀለ የለም። ይህ ትልቁ ስኬት ነው።

 

የፌዴራል ሥርዓቱ የውስጥ ችግሮችን መፍታት እንደቻለ ሁሉ ኢኮኖሚክ ዲፕሎማሲን መሠረት ያደረገው የአገሪቱ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲም ኢትዮጵያ ከውጪው ዓለም ጋር ያላትን ግንኙነት ውጤታማ እንዲሆን አስችሎታል። የአገሪቱ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲም የኢትዮጵያን ምጣኔ ሀብታዊ ጠቀሜታ ከማረጋገጡ ባሻገር በቀጠናው አገሮች መካከል ምጣኔ ሀብታዊ ትስስር እንዲፈጠር በማድረጉ በአካባቢው አገሮች ዘላቄታዊነት ያለው  ሠላም አስፍኗል።  

 

የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ስኬት የውስጥ ግንኙነታችን ነፀብራቅ ነው የሚባለውም ያለምክንያት አይደለም። መንግሥት የሚከተለው ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ አካሄድ በአገሪቱ ዘላቂ ሠላም እንዲሰፍን ከማስቻሉም ባሻገር ይታይ የነበረውን ሥር የሰደደ ድህነት በተግባር መቀነስ አስችሏል።

ኢትዮጵያ ባለፉት 27 ዓመታት ባስመዘገበችው ስኬት ዓለምን ያስደመመ ፈጣን የምጣኔ ሀብት እድገት እንዲሁም ጠንካራ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በመገንባት ላይ ትገኛለች። የፌዴራል ሥርዓቱ ያስተማረን ትልቅ ቁም ነገር ቢኖር በህዝቦች መካከል መቻቻል፣ መከባበርና መተማመን እንዲጎለብት ማድረጉ ነው። የአገሪቱ አንድነት በጠንካራ መሠረት ላይ እንዲቆም አስችሎታል። በመሆኑም የፌዴራል ሥርዓቱ የውስጥ ችግርን መፍታት ከማስቻሉ በላይ ኢትዮጵያ በአካባቢው አገሮችም ሆነ በአፍሪካ ሠላም እንዲሰፍን ትልቅ  ኃላፊነት በመወጣት ላይ ትገኛለች።

 

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ሆነ በአለም አቀፍ መድረክ ያላት ተሰሚነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጥቷል። በአገሮች መካከል ግጭት ወይም ያለመግባባት ሲከሰት የኢትዮጵያ ከፍተኛ ባለሥልጣናት በአደራዳሪነት ወይም ሸምጋይነት ግንባር ቀደም ተመራጭ እየሆኑ መጥተዋል። በተጨባጭም ውጤት ማስመዝገብ ችለዋል። ለአብነት በሱዳንና በደቡብ ሱዳን መካከል የነበረው ያለመግባባት በኢትዮጵያ ሸምጋይነትና የሠላም አስከባሪ ኃይል ጥረት ሠላም ሰፍኗል። በተመሳሳይ በሱዳን በዳርፉር፣ በላይቤሪያ፣ በሩዋንዳ፣ ቡሩንዲ  ተከስቶ የነበረውን ግጭት ለማስወገድ አገሪቱ ያበረከተችው አስተዋጽዖ ከፍተኛና መቼም የሚረሳ አይደለም።  

 

በሶማሊያ ያለው የአልቃይዳ ክንፍ የሆነው ጽንፈኛው አልሸባብን በሶማሊያና በአካባቢው አገሮች ያደርስ የነበረውን ዘግናኝ እልቂት ለመመከት ኢትዮጵያ የአንበሣውን ድርሻ ትይዛለች። ይህን ጽንፈኛ ኃይል በመዋጋት ኢትዮጵያ የከፈለችው መስዋዕትነትና አሁን ላይ በሶማሊያ  ለተገኘው  ሠላም  አገሪቱን ግንባር ቀደም ተመስጋኝ ያደርጋታል።   የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በተሰማራባቸው የሠላም ማስከበር አገራት ሁሉ በሚያሳየው ምስጉን ሥነ ምግባሩ አድናቆት የተቸረው ነው። በየትኛውም አገር መከላከያ ሠራዊት የመንግሥቱና የህዝቡ ነፀብራቅ ነው። የኢትዮጵያ የመከላከያ ሠራዊትም ለግዳጅ በተሰማራባቸው አገሮች ሁሉ ምሥጋና የተቸረው  የህዝብንና የመንግሥትን አደራ በአግባብ መወጣት በመቻሉ ነው። በመከላከያ ሠራዊቱ ሁሉም ሊኮራ ይገባል።  

ኢትዮጵያ የአካባቢውን አገሮች በምጣኔ ሀብታዊ ጥቅም በማስተሳሰርና በቀጠናው ዘላቂ ሠላም እንዲሰፍን ለማድረግ በርካታ ተግባራትን በመከወን ላይ ትገኛለች። የአገሪቱ ምጣኔ ሀብት ከጎረቤት አገራት ጋር በንግድ፣ በባህል፣ በሠላም ማስከበር፣ ወዘተ…ትስስሩ እየጠነከረ  መምጣት ጀምሯል። ኢትዮጵያና ጅቡቲ የጠነከረ ግንኙነት መመሥረት በመቻላቸው ሁለቱ አገራት በፖለቲካ፣ ምጣኔ ሀብትና ማህበራዊ ጉዳዮች ጥብቅ ቁርኝት ፈጥረዋል። ጅቡቲ የባህር በሯን ለኢትዮጵያ በማከራየት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ታገኛለች።  በተመሳሳይ ኢትዮጵያ የታዳሽ ኃይል፣ የተለያዩ የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶች  ውጤቶችን ለጅቡቲ  በማቅረብ ተመሳሳይ ጥቅም ታገኛለች።    

 

በተመሳሳይ ኢትዮጵያ ከሌሎች ጎረቤት አገሮች ማለትም ከደቡብ ሱዳን፣ ከሱዳን፣  ከኬንያ እንዲሁም ከሶማሊያ ጋር አካባቢውን በምጣኔ ሀብት ሊያስተሳስሩና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን ሊያጠናክሩ የሚችሉ የተለያዩ መሠረተ ልማቶችን ማለትም የመንገድ፣ የኃይል አቅርቦት፣ የአካባቢ ሠላም፣ ንግድ ወዘተ…እንዲስፋፉ ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ ነች። በዚህም አገራቱ አብረው የማደግ ተስፋ እንዲያድርባቸው አድርጋለች። አገሪቱ ይህን የምታደርገው የአካባቢው አገሮች በምጣኔ ሀብት ጥቅም የሚተሳሰሩ ከሆነ የቀጠናው ሠላም ዘለቄታዊነት ከማረጋገጥ ባለፈ የምሥራቅ አፍሪካ አገሮች የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱ ይጠናከራል።

 

ሌላው ጉዳይ ኢትዮጵያ ለሁሉም ጎረቤት አገራት ዜጎች እንደሁለተኛ አገር በመሆን ከሰሐራ በታች ካሉ የአፍሪካ አገራት ከፍተኛ ቁጥር ያለውን ስደተኞችን ማስጠለል ብቻ ሳይሆን ለስደተኞች ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ኮሚሽን ጭምር ሙገሳን የተቸራት አገር ሆናለች።  በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ከሶማሊያ፣ ከደቡብ ሱዳን፣ ከኤርትራ፣ ከኬንያ፣ ከሱዳን እንዲሁም ከተለያዩ የአፍሪካ አገራት የተሰደዱ ከስድስት መቶ ሺህ በላይ ለሚሆኑ ስደተኞች መጠለያ ሆናለች። ከሁለት አሥርት ዓመታት በፊት የነበረውን የአገሪቱን ሁኔታ ስናስታውስ እንኳን ለሌሎች አገሮች ዜጎች መጠለያ ልትሆን ይቅርና የራሷ ህዝቦችም በጦርነትና በረሃብ ሣቢያ የትውልድ ቀያቸውን ጥለው የሚሰደዱባት አገር ነበረች። ስደተኞችን ማስጠለል የሚፈጥረው ማህበራዊም ሆነ ምጣኔ ሀብታዊ ጫና ከባድ ነው። ቢሆንም ኢትዮጵያ አቅም በፈቀደ ሁሉ ለስደተኞች ሁኔታዎች እንዲሟሉላቸው እያደረገች ትገኛለች። ኢትዮጵያ ይህን እያደረገች ያለችው በህዝቦች መካከል ያለው መተሳሰብ የበለጠ እንዲጠናከር በማሰብ እንጂ ይህን ያህል ቁጥር ያለው ስደተኞችን ማስተናገድ የሚያመጣው ጫና ቀላል የሚባል አይደለም።

ኢትዮጵያ በእነዚህ መልካም ተግባራቶቿ በአለም ያላት ተቀባይነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጥቷል። ዛሬ ላይ የኢትዮጵያን ወዳጅነት የማይፈልግ የአፍሪካም ሆነ የአለም ታላላቅ አገራት ፈልጎ ማግኘት ይከብዳል። ኢትዮጵያን ያልጎበኘ የዓለም መሪም የለም።    ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አገሪቱ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ያላት ተሰሚነት፣ በአፍሪካ ህብረት ያላት የመሪነት ሚና እንዲሁም በኢጋድና በሌሎች ትላልቅ መድረኮች ያላት ተሰሚነት ማደግ ከሰማይ የወረደ መና ሳይሆን መንግሥት በተገበራቸው ትክክለኛ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ሣቢያ መሆኑን ማመን ተገቢ ይሆናል። ዛሬ ላይ እየገነነ የመጣው የኢትዮጵያ ከፍታ አሁንም በጉዞ ላይ ነው።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy