Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ከንግግሩና ከድጋፉ በስተጀርባ

1 380

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ከንግግሩና ከድጋፉ በስተጀርባ

                                                      ቶሎሳ ኡርጌሳ

ከመሰንበቻው የህዳሴውን ግድብ አስመልክቶ ሁለት ክስተቶች ተስተውለዋል። አንደኛው ክስተት፤ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በሱዳን ካርቱም ከሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ኦማር ሐሰን አልበሽር ጋር በቅርቡ ባደረጉት ውይይት ፕሬዚዳንቱ አልበሽር ‘የግድቡ ግንባታ በታችኛው የተፋሰሱ ሀገራት ላይ ምንም ዓይነት ጉዳት የማያመጣና ችግር የማያስከትል በመሆኑ የሱዳን ድጋፍ አይለየውም’ ብለዋል። ትንሽ ቆይተውም ፕሬዚዳንት አልበሽር ‘ኢትዮጵያዊያን ወንድሞቻችን ግድቡን አሁን ያለበት ደረጃ ላይ አድርሰውታል። ግድቡ የጋራ በመሆኑ ቀሪው ስራ የእኛ ነው። ጎበዝ! ግድቡን ለማጠናቀቅ ምላሽ የምንሰጥበት ጊዜ አሁን ነው’ ሲሉ መደመጣቸው ነው።

ሁለተኛው ክስተት ደግሞ፤ የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) ሴክሬታሪያት ለታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ግንባታ የሚውል የ150 ሺህ ዶላር ድጋፍ በዋና ፀሐፊው ኢንጂነር ማህቡብ ሙዓሊም አማካኝነት መለገሱ ነው። እንደሚታወቀው ቀደም ሲል ኢጋድ የታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ለቀጣናው ኢኮኖሚያዊ ውህደት ያለውን ፋይዳ ከግምት ውስጥ በማስገባት 250 ሺህ ዶላር በስጦታ ለማበርከት ቃል ገብቶ የነበረ ሲሆን፤ በቃሉ መሰረት ሰሞኑን የለገሰው ገንዘብ የመጀመሪያው መሆኑ ተገልጿል። ቀሪውንም በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደሚያበረክት ዋና ጸሐፊው አስታውቀዋል።

ታዲያ እዚህ ላይ ‘እነዚህ ሁለት ክስተቶች ምን ማለት ናቸው?’ ብሎ አሊያም ‘ከክስተቶቹ በስተጀርባ ያለው እውነታ ምንድነው?’ የሚል ጥያቄን ተገቢና አስፈላጊ ይመስለኛል። ርግጥ ክስተቶቹን የህዳሴው ግድብ ለታችኛው የተፋሰሱ ሀገራት ካለው ጠቀሜታና ሀገራችን ቀጣናውን በምጣኔ ሃብት ለማስተሳሰር ካላት የፀና አቋም አኳያ ስንመለከተው፤ ኢትዮጵያ ከግድቡ አኳያ እየተከተለችው ያለችው የፍትሐዊ ተጠቃሚነት  አሰራር ምን ያህል ትክክለኛ መሆኑን የሚያሳይ ነው።

እስቲ በቅድሚያ ከፕሬዚዳንት ኦማር ሐሰን አልበሽር ‘ግድቡ በታችኛው የተፋሰሱ ሀገራት ላይ ምንም ዓይነት ጉዳት የማያመጣ…የጋራ በመሆኑ ቀሪው ስራ የእኛ ነው’ ከሚለው አባባል እንነሳ። በእኔ እምነት፤ ይህ የፕሬዚዳንት ሐሰን አልበሽር አባባል ከዛሬ ስድስት ዓመት በፊት ለግድቡ ግንባታ መሰረተ ድንጋይ ሲቀመጥ የታላቁ መሪ አቶ መለስ ዜናዊ ግድቡ ለታችኛው የተፋሰሱ ሀገራት ያለውን ጠቀሜታ ለመጠቆም “…ግድቡን ለመገንባት ከሚያስፈልገው አጠቃላይ ወጪ 30 በመቶውን ሱዳን፣ 20 በመቶውን ደግሞ ግብፆች መሸፈን ይኖርባቸው ነበር።…” ያሉትን እውነታ ያስታውሰኛል።

‘ለምን?’ ከተባለ፤ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር በዚህ አባባላቸው ለማስገንዘብ የፈለጉት፤ ግድቡ በታችኛው የተፋሰሱ ሀገራት (በግብፅና በሱዳን) ላይ ጉልህ አሉታዊ ተፅዕኖ የማያስከትል ብቻ ሳይሆን፣ ሁለቱ ሀገራት ተጠቃሚ በመሆናቸው ግድቡን እንደ ራሳቸው ንብረት በመቁጠር ወጪውን መጋራት ይኖርባቸው እንደነበር ነው። ዳሩ ግን በተፋሰሱ ሀገራት መካከል እንዲህ ዓይነት ትብብር ባለመኖሩ ኢትዮጵያ ግድቡን በራሷ ገንዘብ፣ ዕውቀትና ጉልበት ብቻዋን ለመገንባት ተገዳለች። ይህ በመሆኑም በአሁኑ ወቅት ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የሰንደቅ ዓላማ ፕሮጀክት ሊሆን ችሏል።

ርግጥ ፕሬዚዳንት አልበሽር ‘ታላቁ የህዳሴ ግድብ በታችኛው የተፋሰሱ ሀገራት ላይ የሚያስከትለው ጉዳት የለም…ቀሪው ስራ የእኛ ነው።…’ ሲሉ ከምንም ተነስተው አይመስለኝም—ግድቡ ያለውን ጠቀሜታ በሚገባ በመገንዘባቸው እንጂ። አዎ! ሀገራችንና ህዝቦቿ በመገንባት ላይ የሚገኙት ታላቁ የህዳሴ ግድብ ክንዋኔ የሌሎችን ጥቅሞች ለመፃረር ሳይሆን የጋራ ጥቅሞችን ለማጣጣም ተብለው የሚሰሩ መሆናቸውን መገንዘብ ያስፈልጋል። ምክንያቱም ኢትዮጵያ የአባይ ወንዝን ከሌሎቹ የተፋሰሱ ሀገራት ጋር ፍትሃዊ በሆነ መልኩ ለጋራ ዕድገት ጥቅም ለማዋል ብቻ የምትፈልግ ሀገር በመሆኗ ነው።

ይህን ሃቅ በአስረጅ ለማስደገፍ ኢትዮጵያ በተከዜ ወንዝ ላይ የኤሌክትሪክ ሃይል የሚያመነጭ ግድብ ስትገነባ ያደረገችውን ማስታወስ ይገባል። ይኸውም በወቅቱ ኢትዮጵያ ግድቡን ስትገነባ ስለ ራሷ የኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጨት ብቻ አይደለም ያሰበችው። የሱዳን አርሶ አደሮችን ታሳቢ አድርጋ ቀጣናዊ ኃላፊነቷን በሚገባ ተወጥታለች። በዚህም በተከዜ ወንዝ ሳቢያ ቀደም ሲል በደለል ይዋጡ የነበሩት የሱዳን አርሶ አደሮች እፎይታን እንዲያገኙ አድርጋለች። ፕሬዚዳንት አልበሽር ይህን የሀገራችንን ማንነት በሚገባ ያውቃሉ። እናም ሀገራችን ታላቁን የህዳሴ ግድብ ስትገነባም፤ የጎረቤት ሀገሮችን፣ በተለይም የታችኛውን የተፋሰሱን ሀገራት ተጠቃሚነትን ከግምት ውስጥ እንዳስገባችም በሚገባ ያወቁ መሪ ናቸው።  

የህዳሴው ግድብ የምንገነባው ያለብንን የኤሌክትሪክ ኃይል እጥረት ለማቃለል ነው። እርግጥም ሌላ አጀንዳ የለንም። ለዚህም ነው መንግስት በተደጋጋሚ ‘እኛ ብሔራዊ ጥቅማችንን ብቻ የምንመለከት ግለኞች አይደለንም፣ አባይ ድንበር ተሻጋሪ ዓለም አቀፍ ወንዝ እንደመሆኑ መጠን የግብፅንና የሱዳንን ፍላጎቶችንና ጥቅሞችን ለማጣጣም የተቻለንን ሁሉ እናደርጋለን’ በማለት ሲገልፅ የምንሰማው። ርግጥም ሃቁ ይህ ከሆነ ዘንዳ አማካዩ ወርቃማ መንገድ ተመራጭ ነው። ሁሉንም የተፋሰሱን ሀገራት በፍትሐዊነትና በእኩልነት መንገድ የሚዳኘው ይህ ሁሉም አሸናፊዎች የሚሆኑበት ወርቃማ መንገድ ተመራጭነቱ አያጠያይቅም። ይህ እውነታ ደግሞ ከሱዳኑ መሪ የተሰወረ አይደለም።

እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ፣ ሱዳን፣ ግብፅና ደቡብ ሱዳን በአፍሪካ ካሉት የተወሰኑ ሀገራት ውስጥ ድሃ ህዝቦችን የያዙ ሀገሮች ናቸው። እናም ድህነትን ለመቀነስ፣ ህዝባዊ አገልግሎቶችን ለማስፋፋትና የሥነ-ምህዳር መራቆትን ለመከላከል ይበልጥ መስራት ይኖርባቸዋል። ለዚህ ደግሞ ፍቱን መድሃኒቱ ሊሆን የሚገባው ከባቢያዊ የልማት ትስስር ነው።

በተለይም ኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ሱዳንና ግብፅ በአሁኑ ወቅት የጋራ የተፈጥሮ ሃብቶቻቸውን ፍትሐዊ በሆነ መንገድ በጋራ ሊጠቀሙ እንዲችሉ ሀገራችን የበኩሏን ድርሻ እየተወጣች ነው። ኢትዮጵያ የሁለቱን ሱዳኖቹን ነዳጅ መግዛት ትችላለች። ሱዳን፣ ኬንያና ግብፅ ደግሞ ከኢትዮጵያ በውሃ አማካኝነት የሚመነጭ የኤሌክትሪክ ሃይልን ለመግዛት ይችላሉ። የየብስ ትራንስፖርት በማደራጀትም የሀገራቱን የንግድ ትስስር ይበልጥ ሊያቆራኙት የማይችሉበት ምክንያት የለም።

ይህ ኢኮኖሚያዊ ቁርኝት በአካባቢው ተባብሮ የማደግ መንፈስን የሚያጎለብት ከመሆኑም በላይ፤ የህዝባቸውን ድህነት ለመቀነስ፣ የአየር ለውጥ ተፅዕኖን ለመቋቋም፣ የህዝብ ቁጥር ማደግን ለመከላከል እንዲሁም የምግብ ዋስትናቸውን ለማረጋገጥ ወሳኝ ሚና አለው። በእኔ እምነት ፕሬዚዳንት አልበሽር እነዚህን በጋራ ተባብሮ የማደግ ክንዋኔዎችን በሚገባ የተገነዘቡ ናቸው።

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሚሰራበት ስፍራ ከሱዳን ድንበር በ20 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚሠራ በመሆኑ ሱዳን ይህን ውኃ ለመስኖ ሥራ በስፋት እንድንጠቀምበት ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር ይሆናል። በተቃራኒው ኢትዮጵያ በዚህ ውኃ ለመስኖ ሥራ የምትጠቀምበት መንገድ አይኖረውም። በሱዳን የሚገኘው ጀበል አወል ግድብን ማከማቸት በሚችለው አንድ ነጥብ አምስት ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውኃ በትነት መልክ የሚባክነው ከፍተኛ ውሃን ብክነት የሚታደግ ነው።

በግድቡ ግንባታ ሳቢያ በክረምት ወራት በእጥፍ የሚጨምረው የአባይ ውኃ ሱዳንን በደለል አያጥለቀልቅም። ኃይለኛ ጎርፍ የዚያችን ሀገር መሠረተ ልማት እያወደመ ማስቸገሩ ያከትማል። ሱዳንንም በየዓመቱ እስከ መቶ ሚለዮን ዶላር ከማውጣት የሚያድናት ይኸው ግድብ መሆኑን ፕሬዚዳንት አልበሽር የተገነዘቡት ጉዳይ ነው። እናም ‘ግድቡ በታችኛው ተፋሰሱ ሀገራት ላይ ምንም ችግር አይፈጥርም፣ ግድቡን ኢትዮጵያዊያን አሁን ያለበት ደረጃ አድርሰዋል፣ የእኛ ስለሆነም ቀሪውን መጨረስ አለብን’ ቢሉ የሚገርም አይደለም።  

በኢጋድ ሴክሬቴሪያት የተለገሰው 150 ሺህ ዶላርም ልዩ ትርጓሜ ያለው ነው። ይኸውም ኢጋድ ራሱ እንዳለው ልገሳው የተደረገው ኢትዮጵያ ቀጣናውን በልማት ለማስተሳሰር የምታደርገውን ጥረት ለማበረታታት ነው። ይህም ሁሉም የኢጋድ አባል ሀገራት በግድቡ ቀጣናዊ ጠቀሜታ ላይ ያላቸውን እምነት የሚያሳይ ነው። ልገሳው ለምስራቅ አፍሪካ ምጣኔ ሃብታዊ ችግር መፍትሔው ምስራቅ አፍሪካዊ መሆኑንም የሚያመላክት ነው።

እኔ እስከሚገባኝ ድረስ ኢጋድ ለግድቡ ግንባታ ያደረው የገንዘብ ድጋፍ ግድቡ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የቀጣናው ሀገራት ጭምር መሆኑንም የሚያረጋግጥ ነው። እናም ይህን የቀጣናው ሀገራት ጭምር የሆነን ሃብት በጋራ ማልማት እንደሚገባ ለታችኛው የተፋሰሱ ሀገራት ትልቅ ትምህርት የሰጠ ይመስለኛል። ኢትዮጵያ ቀጣናው በጋራ ተያይዞ እንዲያድግ እያደረገች ላለችው ተግባር ዕውቅና የሰጠም ጭምር ነው ማለት ይቻላል።

አዎ! ሀገራችን በዘመነ-ሉላዊነት (Globalization) ለብቻዬ አድጋለሁ የሚል እምነት የላትም። የቀጣናው ሀገራት መድከም የራሷ መድከም፣ የቀጣናው ሀገራት ብርታትና ጥንካሬ የእርሷ ብርታትና ጥንካሬ መሆኑን በሚገባ የምትገነዘብ ናት።

ርግጥ እኛ ኢትዮጵያዊያን እንደ ሌሎች “ለብቻችን እንዲህ እንሁን” ብለን አናውቅም። እናም የታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታችን ትኩረትም ማንንም ለመጉዳት ያለመ እንዳልሆነ ማንኛውም አካል ሊያውቀው ይገባል። አብሮ መብላትና ተያይዞ ማደግ የቆየ ኢትዮጵያዊ እሴት መለያ ባህሪም ነው። ይህ ባህሪያችን ትናንት የነበረ፣ ነገና ከነገ በስቲያም ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል።

እናም በእኔ እምነት ከፕሬዚዳንት ኦማር ሐሰን አልበሽር ንግግርና ከኢጋድ ሴክሬቴሪያት ድጋፍ ባሻገር ያሉት ተቀንጭበው ሲታዩ ይህን ይመስላሉ። ታዲያ ለግድቡ የራሱን አስተዋፅኦ እንደሚያደርግ አንድ ዜጋም እኔም ሁለቱ አካላት በግድቡ ላይ ስላላቸው ‘የእኔነት’ መንፈስ እንዲሁም ቀጣናዊ ጠቀሜታውን ተገንዝበው ላሳዩት አጋርነት ምስጋናዬን ልቸራቸው እወዳለሁ። አማን ያሰንብተን።  

 

  1. David Begna says

    I thank God for what is going on in Ethiopia. No more war and no more poverty. This generation of is the most lucky and blessed generation of all.This is the result of diplomatic and negotiation victory of EPRDF. Good job.

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy