Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ከጋራ መግባባቶቹ ባሻገር

0 274

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ከጋራ መግባባቶቹ ባሻገር

ዳዊት ምትኩ

አራቱ የኢህአዴግ አመራሮች በድርጅታቸው ግምገማ ዙሪያ አስተያየት መስጠታቸው ይታወቃል። እንደሚታወቀው ሁሉ የህብረተሰቡ ፍላጎት በአሁኑ ወቅት ድርጅቱ ወደ ተግባር እንዲገባ ነው። ይህ ፍላጎት በተጨባጭ ወደ መሬት ወርዶ ህዝቡ ያነሳቸው ትክክለኛ ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ ማድረግ ያስፈልጋል። ለዚህም በመግለጫው ላይ የተነሱትንና አመራሩ የጋራ መግባባት ላይ የደረሰባቸውን ጉዳዩች ህዝቡ በትክክለኛ መንገድ እንዲገነዘባቸው ማድረግ ያስፈልጋል።

ለአብነት ያህል “በልማትና በአገራዊ አንድነት ዙሪያ መትጋት ሲኖርባቸው ህዝብን ከህዝብ ጋር በሚያራርቅ አፍራሽ ተግባር ውስጥ የተሰማሩ የግልና የመንግሥት የሚዲያ ተቋማት አካሄዳቸውን የሚያስተካክሉበት ሁኔታ ለመፍጠር ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ይንቀሳቀሳል” በማለት የተቀናጁ እርምጃዎችን እንደሚወስድ በገባው ቃል መሰረት በእንድም ይሁን በሌላ መንገድ ማስቆም ይኖርበታል።

እንደሚታወቀው ሁሉ የሚዲያ ስራ በሀገራችን ውስጥ እንደ ማንኛውም ለዴሞክራሲያዊ ስርዓታችን ግንባታ ጠቃሚ የሆነ ልማት ሁሉ የሚያበረክተው አስተዋፅኦ የላቀ ነው። ይህም እንደ እኛ ላለው ታዳጊ አገር የሚኖረው ፋይዳ ከፍተኛ ነው። የህብረተሰቡን ሞራል ከፍ በማድረግና ለልማት እንዲነሳሳ በመቀስቀስ ረገድ መገናኛ ብዙሃን ጉልህ ሚና አላቸው።

ምንም እንኳን የግድ ችግር ይከሰት ባይባልም ገና ወፌ ቆመች ዳዴ እያለች ባለች አገር የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታው ውስጥ እንከን አይጠፋም ብሎ መከራከር የዋህነት ነው፡፡

በፈርጀ ብዙ የስም ማጥፋት ዘመቻ እየተነሳሱ የአገራችንን ገፅታና የሕዝባችንን አብሮነት የሚሸረሽሩ ተራ አሉባልታዎችን መንዛት አግባብ አለመሆኑ ያግባባናል ተብሎ ይታሰባል፡፡ ለምን ቢባል ጋዜጠኝነት ሙያም ቢሆን የአገርን ብሔራዊ ጥቅምን የሚያስቀድም የሥራ ዘርፍ ነውና፡፡ እናም ጋዜጠኞቻችን አሊያም ብሎገሮቻችን ሕዝቦቻቸውን ለኒዮ ሊብራሊስቶች በሚመች መልኩ ብዕራቸውን አሹለውና ምላሳቸውን ስለው ለእኩይ ምግባር ሲራኮቱ ማስተዋል ያሳዝናል፤ ያስተዛዝባል፡፡

እርግጥ በተጨባጭ እንደተረጋገጠው ጥቂት የማይባሉ የኘሬስ ሰዎች ለምዕራባዊያን አገልጋይ ሆነው ተሰልፈው እስከመሸለም ደርሰው ነበር፤ ዛሬም ቢሆን የሚታጩ የጠፉ አይመስለኝም፡፡ በጥቅማ ጥቅም እየተደለሉ ሕዝብን ከመሸጥና አገርን ከመለወጥ ወደኋላ እንደማይሉም ቀደምት ተግባራቸው ምስክር ነው፡፡

ምን ይህ ብቻ፡፡ የሌላውን ሃሣብና አመለካከት በብዕር ከመሞገት ይልቅ የተከራካሪውን ስብዕና ማለትም ብሔሩን፣ ኃይማኖቱን፣ ቋንቋውን እየጠቃቀሱ በማንቋሸሽና ስም በማጥፋት፣ የዜጐችን ማንነት በማዋረድና በማጥላላት ላይ ጊዜያቸውን የሚያጠፉ አንዳንድ የግል ኘሬሶች አቆጥቁጠው እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡

ቁጥራቸው እንደ ያኔው አይብዛ እንጂ ዛሬም ብቅ ብቅ ማለት ጀምረዋል። ከፊሎቹ ሕዝቡ ራሱ አንቅሮ ስለተፋቸው፤ ከፊሎቹ ደግሞ መንግሥት አጥፊ አካሄዳቸውን ተገንዝቦ በወቅቱ ሥርዓት ስላስያዛቸው አሊያም ኪሳራ መሸከም ተስኗቸው ከጨዋታው ውጪ ሆነዋል፡፡

እዚህ ላይ አንድ ቁምነገር ማስተዋል ተገቢ ይሆናል፡፡ ጋዜጣን የፅንፈኞችና የአሸባሪዎች አስተሳሰብ ማራመጃ በማድረግ ህገ መንግሥቱንና ህገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በአመፅ ለመናድ መቀስቀሻ ማድረግ ከቶ እንደማይቻል የጋራ መግባቢያ ልንይዝ ይገባል፡፡

ፀሐፊዎቹ እንደሚያትቱት መንግሥት በነፃው ፕሬስ ስም የተሸፈኑ ወንጀለኛ ጋዜጠኞችን ለምን መረን አልለቀቃቸውም? የሚሉ ከሆነ ይህ የሚያነጋግር ጉዳይ ነው፡፡ አመጽንና ሁከትን የሚሰብኩ እንዲሁም እርስ በርሳቸው እንደ እፉኝት ተበላሉ እያሉ የሚያነሳስ የጥፋት ተስፈኞችን አይቶ እንዳላዩ ማለፍ ከአንድ ኃላፊነትና ሰብዓዊነት ከሚሰማው መንግሥት አይጠበቅም። መንግሥት ሽብርን የሚነዙ የአሸባሪ ተባባሪዎችን በህግ ተጠያቂ ማድረጉ ሥራውም፣ መብቱም፣ ግዴታውም፣ ኃላፊነቱም ጭምር መሆኑ መዘንጋት የለበትም። ይህን በማድረጉም የኘሬስ አፈና ተደርጐ መወሰድ አይገባም፡፡

ነባራዊው ዓለም ሆነ የጋዜጠኝነት ሙያ የሚያስረዳን ነጥብ ነፃ ኘሬስ ነፃ ውንብድና ወይም ነፃ ሽፍትነት አለመሆኑን ነው፡፡ ነፃ ኘሬስ የግል ፍላጐታችን የበላይነት እንድንቀዳጅ ስንል ብቻ የሌለን ነገር በመፍጠርና ውሸትን በመፈብረክ፣ ከፍ ሲልም የሌሎችን መብትና ሉዓላዊነት ኢ-ስነ ምግባራዊ በሆነ መንገድ የምንገፋበትና የምንነግድበት ሸቀጥም አይደለም፡፡

እናም ስነ ምግባሩን በጠበቀ ሁኔታ ዘገባዎች መቅረብ ይኖርባቸዋል፡፡ በዚህ ረገድ መንግስት አንዱን ከሌላው የሚያጋጩና ብሔሮችን ባልዋሉበት ቦታ እየፈረጁ የሚንቀሳቀሱ መገናኛ ብዙሃን ላይ ቁጥጥር ማድረግ ያለበት ይመስለኛል፡፡ ይህ ሲደረግም ሁለት ጉዳዩችን ማቻቻል የሚገባ ይመስለኛለ፡፡ አንደኛው ሚዲያ በማህበረሰቡ ውስጥ ሊሰጠው የሚችለውን ጥቅም በማይጎዳ መልኩ ማየት ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ ህግና ስርዓትን አክብረው የሚንቀሳቀሱ መገናኛ ብዙሃንን በማበረታታት ነው፡፡

እንደሚታወቀው ሁሉ ልማታዊ ጋዜጠኝነት በዴሞክራሲ ባልዳበሩ ሕዝቦችና መንግሥታት ዘንድ ቁልፍ የብልጽግና መሣሪያ እንደሆነ ነው፡፡ አመለካከቱ ህዝቦችን ለልማት ለማነሳሳትና የብልጽግና ከፍተኛው ማማ ላይ እንዲወጡ ማስቻል ነው። በየትኛውም ዓለም የሚሰራበት የንቅናቄ መሣሪያም ይኸው ነው፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የሕዝቦች አብሮነት የሚጠብቅበትን፣ የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ የሚዳብርበትን እንዲሁም የመተሳሰብና የጋራ ልዕልና የሚሰፍንበትን ቀመር ይሰብካል፤ በዚህ ዓላማና ዙሪያ ተንቀሳቅሶ ይሰራል፡፡ ይህ እሳቤ ዛሬ በለፀጉ በምንላቸው አገራት ሣይቀር የታለፈበት ጎዳና ነው፡፡

በአንድ ጀንበር የተነገባ የዴሞክራሲ ሥርዓትም ይሁን የኘሬስ ነፃነት አስተሳሰብ መቼም ኖሮ አያውቅም፡፡ በመሆኑም ችግሮች መኖራቸው የግድ ነው ባይባልም፤ በሥራ ሂደት እንከኖች ባጋጠሙ ቁጥር የተሰማሩበትን የፖለቲካ ነውጠኝነት እውን ለማድረግ በአሥር ሺህዎች አባዝቶ ነገሮችን ለማወሳሰብና ህዝብና መንግሥትን ለማምታታት የሚደረግ ሴራ ግን አግባብነት እንደሌለው ነግሮ ማለፍ ተገቢነት እንዳለው መጠቆሙ ተገቢነት ይኖረዋል፡፡

የነፃ ኘሬስና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ህግና ሥርዓት ከሚፈቅደው ውጭ አፈንግጦ መረን በመውጣት ያልተገባ ጥቅም ለማግበስበስ በማሰብ ብቻ ከንቱ መሯሯጥ ተገቢ አይደለም። በልማትና በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ መካከል ፍፁም የማይፈታ ዝምድና በመኖሩ ልማትና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን የሚያስታርቅና ሁሉን እውነታዎች አግባብቶና አጣጥሞ የሚያራምድ የኘሬስ ፍልስፍና ማቋቋምና ምቹ አውድን መፍጠር ከማንኛውም ሕዝባዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ልማታዊ መንግስት የሚጠበቅ ቁልፍ ተግባር መሆኑም መዘንጋት የለበትም፡፡

ይህ ሲባል ግን ልማትንና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለማስፈን ኘሬስ መታፈን አለበት ማለት አይደለም፡፡ በአገራችንም ወንጀለኛ እንጂ ነፃ ኘሬስ የታፈነ ባለመሆኑ ጉዳዩ ብዙ የሚያሟግት አይደለም፡፡ እናም አንዳንድ የህዝብና የግል ሚዲያዎች በአገራችን ውስጥ ተፈጥሮ የነበረውን ሁከት በማራገብ የተጫወቱት ሚዲያ ቀላል ባለመሆኑ ችግሩን ለመቅረፍ ገዥው ፓርቲ እወስደዋለሁ ያለውን ቃል አጠናክሮ መቀጠል ያለበት ይመስለኛል፡፡

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy