Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ወደተግባር የተሻገረው ውሳኔ

0 267

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ወደተግባር የተሻገረው ውሳኔ

                                                               ይልቃል ፍርዱ

የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ውሳኔ ፈጥኖ ወደተግባር ተሸጋግሯል፡፡ መሰረታዊ ለውጦችን በሀገር ደረጃ የማምጣት ተስፋው የላቀ ነው፡፡ የችግሩ ውስብስብነትና መቆላለፍ ለአመታት ስር ሰዶ የቆየ ከመሆኑ አንጻር በአንድ ጀምበር መአልትና ለሊት አይፈታም፡፡ በሒደት ደረጃ በደረጃ ሕዝቡን ከጎኑ አሰልፎ በሚደረገው ትግል የሕዝቡን ጥያቄ በመመለስ ረገድ ትርጉም ያለው ለውጥ ይመጣል የመል ተስፋ በብዙዎች ዘንድ አለ፡፡

ኢሕአዴግ እንደ አንድ የፖለቲካ ድርጅት በሀገር ደረጃ ስርነቀል ለውጥን የመራ የኢኮኖሚ አብዮትን ስኬታማ በሆነ ደረጃ ለማራመድ የቻለ ፓርቲ ነው፡፡ ሰፊ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች እንዲካሄዱ የከተማና የገጠር ልማት፣ የግብርና፣ የቀላልና ከባድ ኢንዱስትሪ ፖሊሲ ነድፎ ወደተግባር በመግባት በሀገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በአሕጉራዊና በአለም አቀፍ ደረጃ አድናቆትን ያተረፈ ስራ በመስራት ውጤታማ መሆን የቻለ ድርጅት ነው፡፡

ኢሕአዴግ በጤናው፣ በትምህርቱ፣ የውጭ ኢንቨስትመንትን ወደሀገር ውስጥ በማስገባት በተለያዩ ዘርፎች ሀብታቸውንና እውቀታቸውን በሀገራችን ስራ ላይ እንዲያውሉ ያደረገ፤ ሀገራችን ያለባትን የኃይል አቅርቦት ችግር ለመፍታት ብሎም ለአጎራባች ሀገራት ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል በመሸጥ ሀገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ገቢ በከፍተኛ ደረጃ እንድታገኝ ግቤ አንድንና ሁለትን 6000 ሜጋዋት ሊያመነጭ የሚችለውንና ስራው 60 በመቶ የተጠናቀቀውን የታላቁን ሕዳሴ ግድብ ያለምንም የውጭ እርዳታ ብድርና ድጋፍ በኢትዮጵያ ሕዝብ መዋጮ ለመስራት ያቻለ መሪ ድርጅት ነው፡፡

ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲው መስክ የላቀ ስኬታማነት አስመዝግባለች፡፡ አዲስ አበባ ከአፍሪካ ሕብረት ዋና መቀመጫነቷ ሌላ፤ ከኒውዮርክና ከቤልጂየም ቀጥሎ ሶስተኛዋ አለምአቀፍ የዲፕሎማቲክ መቀመጫ እንደትሆን፤ እንዲሁም በምስራቅ አፍሪካ ተደማጭና ተጽእኖ ፈጣሪ ሁና የወጣችባቸው አንጸባራቂ ድሎች ሁሉ የተገኙት በዚሁ በኢሕአዴግ የአመራር ዘመን ነው፡፡ በዚህ ዙሪያ ብዙ ማለት ብዙ መጥቀስ ይቻላል፡፡ ይሁን እንጂ የስኬቶቹን ያህል እጅግ የከፋ ሀገራዊ አደጋን የሚጋብዙ ስሕተቶችም ተፈጽመዋል፡፡ አሁን ርብርብ እየተደረገ ያለው እነዚህን አደገኛ ስሕተቶች ለማረምና ቀድሞ ወደነበረው የብቃት ደረጃ ለመመለስ ነው፡፡  

ሕገመንግስቱን ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ በማድረግ ረገድ በከፍተኛው አመራር ደረጃ የታዩት መሰረታዊ ችግሮች የችግር አድማሳቸውን እያሰፉ እስከታች ዘልቀው ቆይተዋል፡፡ ይህን ሁሉ ተጨባጭ ሀገራዊ ስኬቶችንና እድገቶችን ለማስመዝገብ የበቃው ኢሕአዴግ በራሱ ውስጥ የተፈጠሩት መሰረታዊ ችግሮች በግንባር ድርጅቶቹ ውስጥ አለመተማመን እስከ መፍጠር በመድረሱ በሀገራዊ ሁኔታው ላይ ከፍተኛ ችግር ደቅኖ ቆይቶአል፡፡

የሙስናና ሕገወጥ የኮንትሮባንድ ንግድ መስፋፋት በሀገራዊ ኢኮኖሚው ላይ ታላቅ አደጋ ጋርጦአል፡፡ የመልካም አስተዳደርና የፍትሕ ችግር ስር መስደድ፣ የመሬት ቅርምትና ሽያጭ፣ የሕገወጥ ደላላዎች መንሰራፋትና ከቢሮክራሲው ጋር ባላቸው ቁርኝት በመንግስት አመራር በተለያየ ደረጃ ከተቀመጡ ኃላፊዎች ጋር የፈጠሩት የጥቅም ስንሰለት (መረብ) ሕዝብ  በከፍተኛ ደረጃ እንዲማረር፣ እንዲንገሸገሽ፣ ተስፋ እንዲቆርጥ፣ በኢሕአዴግ ላይም ቀድሞ የነበረው እምነት እንዲሸረሸር አይነተኛ ምክንያት ሆነዋል፡፡ ለዚህ ሁሉ ያበቁት ደግሞ የራሱ ታማኝ የሚባሉ አባላቶች ናቸው፡፡

በዚህም ምክንያት በሀገራችን የተለያዩ አካባቢዎች የሰላም መደፍረስና ግጭቶች፣ የሀብትና ንብረት መውደም፣ የዜጎች ሕይወት መጥፋትና የብዙ መቶ ሺሕ ዜጎች ከመኖሪያ ቀኤያቸው መፈናቀል ተከስቶአል፡፡ ግለሰቦች በየራሳቸው ምክንያት የሚፈጥሯቸውን አለመግባባቶች ወደጎሳና ዘር ግጭት ለመውሰድ የተደረጉ ተደጋጋሚ ግጭቶች የሕይወት ዋጋ አስከፍለዋል፡፡

አጠቃላይ ሁኔታው በሀገሪቱ ሰላማዊና የተረጋጋ ሁኔታ ላይ ችግር ፈጥሮ ቆይቶአል፡፡ የኢኮኖሚው መቀዛቀዝ በንግድ ልውውጡና ግብይቱ በመማር ማስተማሩ ሂደት ላይ ሁሉ ከፍተኛ ተጽእኖ አሳድሮአል፡፡ ይህን ሀገራዊ ሁኔታ በጥልቀት ለመፈተሸ ሶስት ሳምንት ያህል ግዜ የወሰደው የኢሕአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በተፈጠሩትና ተጨባጭ ሁነው በታዩት ሀገራዊ ጥልቅ ችግሮች ላይ በግልጽ ተወያይቶ የደረሰበትን ድምዳሜና ውሳኔ በገሀድ ለሕዝብ ይፋ አድርጎአል፡፡

የፓርቲው ማእከላዊ የትኩረት ነጥብ ሕዝብና ሀገር ብቻ ነው፡፡ ችግሮቹን በግልጽ በተጠያቂነትና ኃላፊነት መንፈስ መፍታት፤ በየአካባቢው የተፈጠረውን የሰላም መደፍረስና አለመረጋጋት ማስወገድ፤ በኢኮኖሚው ላይ እያደረሰ ያለውን ጫና መክላት፤ ሰላማዊ የሕዝብ ዝውውርና እንቅስቃሴ ወደ ቀድሞው ቦታው እንዲመለስ ማድረግ፤ ሕግን የመጠበቅና የማስከበር ስራን ማካሄድ በዋነኛነት በፍጥነት ወደተግባር የሚለወጡ ሁኔታዎች መሆን እንዳለባቸው በመሰነው መሰረት ወደ ተግባር ገብቶአል፡፡

በጥቂት ሳምንታት ውስጥም የሚታዩ ለውጦች እየተመዘገቡ ነው፡፡ ፓርቲው ለሀገራዊ መግባባት መፈጠር እስረኞችን እፈታለሁ ባለው መሰረት እስረኞች ተፈተዋል፡፡ የተፈጠረውን ሁኔታ በመጠቀም መሰረታዊ የሸቀጥ አቅርቦቶችን ዋጋ በማናርና በመደበቅ ሕዝቡን በማስመረር የበለጠ እንዲከፋ ሲያደርጉ የነበሩ ነጋዴዎችን ሴራ በመበጣጠስ መሰረታዊ ሸቀጦች በተለይ በኢኮኖሚ አቅሙ ዝቅተኛ ለሆነው የሕብረተሰብ ክፍል እጥረት እንዳይፈጠርበት ፈጥኖ በማቅረብ ረገድ (ስኳር፤ ዘይት ወዘተ ) መንግስት ለሕዝቡ ያለውን ወገንተኝነት  በተግባር እያሳየ ነው፡፡

የሕዝባዊ አገልግሎት አሰጣጡ በየቦታው በአዲስ የመነቃቃት ስሜት የሚታዩ ጅምር ለውጦችን መሻሻሎችን እየሳየ ነው፡፡ በአንድ ግዜ ለረዥም ግዜ የተጠራቀመ ችግርን ለማስወገድ ባይቻልም በሂደት ከፍተኛ ለውጦች እንደሚገኙ ያሉት ሁኔታዎች አመላካች ናቸው፡፡

የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ውሳኔ በፈርጀ ብዙ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ እንደመሆኑ መጠን ሰፊ ስርነቀል ለውጦች እንደሚደረጉ ይጠበቃል፡፡ ዋናው ስሕተቶችንና የተፈጠሩ ችግሮችን አንጥሮ በመለየቱ ረገድ የተደረሰበት ስምምነት ሲሆን ይህንን ወደተግባር በመለወጡ ረገድ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ባደረገው ጥሪ መሰረት ሁሉም ዜጋ፣ ምሁራን፣ ሲቪክ ማሕበራትና የተለያዩ አደረጃጀቶች የየበኩላቸውን ሀገራዊ ድርሻ ሊወጡ ይገባል፡፡

የችግሩ ግዝፈት ሲታይ ጉዳዩ ለመንግስት ብቻ የሚተው አይደለም፡፡ መንግስት ብቻውን ሊወጣውም አይችልም፡፡ ወሳኙ ኃይል ሕዝብ ነው፡፡ የሀገሩ ባለቤት የሀገሩ ጠባቂ ሀገርን ወደላቀ የሰላምና የእድገት የሚያሸጋግረው ሕዝብ ነው፡፡ አብሮነት መቻቻል መከባባር መደማመጥ በሀገርና በሰላም በልማት ጉዳይ ጸንቶ መቆም አዲስ ምእራፍ መክፈት ወቅቱ የሚጠይቀው ግዴታ ነው፡፡

ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው የደረሰበት ውሳኔ ሕይወት አግኝቶ ወደተግባር ሊለወጥ የሚችለው በሰፊ ሕዝባዊ ተሳትፎ ብቻ ነው፡፡ ሀገራዊ የምክክር መድረኮችን በስፋት ማዘጋጀትና ጉዳዩን በየክፍለ ከተማውና በየወረዳው ማውረድ፤ ሕዝቡ በነጻነት አስተያየቱን እንዲሰጥ መድረኮችን ማመቻቸት ለችግሮች ሁሉ መፍትሔ ለማስገኘትና ሰፊ መግባባትን ለመፍጠር ይረዳል፡፡

ሁከት፤ ብጥብጥ፤ ትርምስ፤ እርስ በእርስ መናቆር ለሀገራችን አይበጃትም፤ ከእነዚህም የሚገኝ የአንድ ሳንቲም ትርፍ የለም፡፡ የኢኮኖሚውን እድገቱን፣ የኢንቨስትመንት ፍሰቱን፣ የቱሪስት ገበያውን፣ የገቢና ወጪ ንግዱን ሰላማዊ የሆነ የሕዝብ መስተጋብሩን የመማር ማስተማሩን ሂደት ሁሉ ይጎዳል፤ ያፋልሳልም፡፡ አርሶ አደሩ ለፍቶ ደክሞ ያገኘውን አዝመራ ለገበያ አውጥቶ ካልሸጠ፤ የነገ ሀገር ተረካቢ የሆነው ወጣት በስርአቱ ትምህርቱን መከታተል ካልቻለ፤ ዜጎች በሰላም ከቤታቸው ወጥተው በሰላም ወደ ቤታቸው መመለስ ከተሳናቸው፤ የእለት ስራ የሚሰሩ ዜጎች የትም ሮጠውና ሰርተው ማደር ካቃታቸው ይሄ ሀገር መታመሟን፤ መታወኳን ያሳያል፡፡ ይህ ደግሞ ሊፈታና መፍትሔ ሊያገኝ የሚችለው ሕዝብና መንግስት በአንድነት በመቆም በጋራ መስራት ሲችሉ ነው፡፡

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy