Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ዘላቂ ሠላም ላይ እናተኩር

0 221

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ዘላቂ ሠላም ላይ እናተኩር

ብ. ነጋሽ

በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሱማሌ አዋሳኝ አካባቢዎች የተፈጠረውን ግጭት በሁለቱ ክልሎች ህዝቦች መሃከል የተካሄደ አለመሆኑን ህዝቡ ምስክርነቱን ሲሰጥ መቆየቱ ይታወቃል። ይሁን እንጂ በሁለቱም ወገን በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ዜጎች ከኑሯቸው ተፈናቅለዋል። የሞቱትም ቁጥራቸው ቀላል እንዳልሆነ ይነገራል። የሃገሪቱ ከፍተኛ የስልጣን አካል የሆነው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጉዳዩን የሚመረምር የሱፐር ቪዥን ቡድን አቋቁሟል። የሱፐርቪዥን ቡድኑ ግጭቱ ከተባባሰበት ነሃሴ ወር ማገባደጃ እስከ ህዳር 30፣ 2010 ዓ/ም ግጭት የተቀሰቀሰባቸውን የሁለቱ ክልሎች አካባቢዎችና በግጭቱ የተፈናቀሉ ዜጎች ያረፉባቸውን የገጠር ቀበሌዎችና የከተማ መጠለያ ጣቢያዎች ጎብኝቶ ለምክር ቤቱ ሪፖርት አቅርቧል።

ቡድኑ ታህሳስ 26፣ 2010 ዓ/ም ለምክር ቤቱ ያቀረበው ሪፖርት፣ በተፈናቃዮች ላይ የደረሰው ኢሕገመንግሥታዊ ተግባር በሁለቱ ክልሎች ሕዝቦች ሳይሆን በልዩ የፀጥታ ኃይሎች፣ የየአካባቢው ፖሊሶችና ሚሊሻዎች፣ የአስተዳደር አካላት የተፈጸመ መሆኑን በመስክ ምልከታው ወቅት ተረድተናል ይላል። ኢሰብአዊ በሆነ መልኩ ህጻናት ወላጆቻቸውን ማጣታቸውን፣ በሴቶች ላይ ፆታዊ ጥቃት መፈጸሙን፣ ሕፃናትና እናቶች ላይ ዘግናኝ በደል መፈጸሙን ሪፖርቱ አመልክቷል።

የሱፐርቪዥን ቡድኑ ያነጋገራቸው የግጭቱ ተጠቂዎች በሰጡት አስተያየት በሁለቱ ክልሎች መሃከል የተፈጠረው አለመግባባት ለግጭት ምክንያት እንዳይሆን እንዲሁም በዜጎች ላይ ጉዳት እንዳያደርስ በማድረግ ረገድ መንግስት ላይ ያደረባቸውን ቅሬታ ገልጸዋል። በሪፖርቱ ላይ እንደተመለከተው የግጭቱ ተጎጂዎች ያቀረቡት ቅሬታ፣ በሠላም አብረን ለዘመናት በምንኖር ሕዝቦች መካከል ታይቶ የማይታወቅ ግፍ ሲፈጸም መንግሥት ፈጥኖ እርምጃ መውሰድ ሲገባው ዝም ብሎ ተመልክቶናል፤ ዘግይቶም ቢሆን ያለንበትን ሁኔታ የተመለከቱ አመራሮችም መፍትሔ አልሰጡንም የሚል ነው።

የብሄራዊ የደህነነት ምክር ቤት ሰብሳቢና የመከላከያ ሚኒስትሩ አቶ ሲራጅ ፈጌሳ የምክር ቤቱን የአንድ ወር አፈጻጻም ግምገማ መነሻ በማድረግ ጥር 2፣ 2009 ዓ/ም በአጠቃላይ የሃገሪቱን ሰላምና መረጋጋት አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ ግጭት ተቀስቅሶባቸው የነበሩ የኦሮሚያና የኢትዮጵያ ሱማሌ ክልሎች አካባቢዎች አሁን ያሉበትን ሁኔታ የተመለከተ መረጃ ሰጥተዋል። በዚህ መሰረት፣ በኦሮሚያና የኢትዮጵያ ሱማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢ ግጭት በተቀሰቀሰባቸው ስፍራዎች ክልሎቹ በጠየቁት መሰረት የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት ገብቶ ሁኔታውን ማስተካካሉ ተገልጿል።

ግጭት ተቀስቅሶ ከነበረባቸው አካባቢዎች የክልሎቹ የፖሊስና ልዩ ሃይል እንዲሁም ሚሊሻ እንዲወጣ መደረጉን፣ አሁን አንጻራዊ ሰላም መስፈኑን አቶ ሲራጅ ፈጌሳ አስታውቀዋል። በሁለቱ ክልሎች ህዝቦች መሃከል ቀደም ሲል የነበረው ሰላማዊ ግንኙነት መቀጠሉን አስመልክቶም፣ በጋራ ሲጠቀሙባቸው የኖሩትን፣ ከግጭቱ በኋላ አንዱ ሌላውን እንዳይጠቀም ክልከላ ጥለውባቸው የነበሩ የውሃ ጉድጓዶችን በጋራ መጠቀም መጀመራቸውን፣ የጠፉ ከብቶችን አዋጥተው የከፈሉበትና አንዱ ሌላውን በምግብ ሰብል የሚረዳበት ሁኔታ መፈጠሩን ገልጸዋል። ይህም ግጭቱ የሁለቱ ህዝቦች አለመሆኑን እንደሚያረጋግጥ አቶ ሲራጅ አመልክተዋል።

እንደተባለው ከአንድ ዓመት በላይ ጊዜ ያስቆጠረውና በሃገሪቱ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ለበርካቶች ሞትና መፈናቀል ምክንያት የሆነው የኦሮሚያና የኢትዮጵያ ሱማሌ አዋሳኝ አካባቢዎች ግጭት በህዝብ መሃከል የተካሄደ ባለመሆኑ፣ የግጭቱ ዋና ተዋናዮች አደብ እንዲይዙ ሲደረግ ሁኔታዎች ወደነበሩበት መመለሳቸው አይቀርም። እናም አጥፊዎችን በቁጥጥር ስር በማዋል የህግ የበላይነትን የማረጋገጥ ጉዳይ ጊዜ ሊሰጠው አይገባም።

አሁን አሳሳቢውና ከፍተኛ ስራ የሚጠይቀው ጉዳይ በግጭቱ ምክንያት የተፈናቀሉ በመቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ዜጎች ጉዳይ ነው። በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ዜጎችን በመጠለያ ካምፕ አስቀምጦ የአስሸቸኳይ ጊዜ እርዳታ እያቀረቡ ማቆየት ተፈናቃዮቹን ለእንግልት የሚያጋልጥ መሆኑ እውነት ነው። በመሆኑም በተቻለ መጠን በሁለቱ ክልሎች መሃከል አስተማማኝ ሰላም በማስፈንና የህግ የበላይነትን በማረጋገጥ ተፈናቃዮቹ ወደቀድሞ ኑሯቸው እንዲመለሱ ማድረግ ይገባል። በዚህ ረገድ የተጀመሩ ስራዎች መኖራቸው ቢነገርም በተጨባጭ ግን ለውጥ ያመጣ ስራ መከናወኑን የሚያመለክት ማስረጃ የለም።

ተፈናቃዮቹን ወደነበሩበት መመለስን አስመልክቶ ግጭት ተቀስቅሶ የነበረባቸውን አካባቢዎችና ተፈናቃዮች የሰፈሩበትን አካባቢዎች የጎበኘው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሱፐርቪዥን ቡድን ያቀረበውን ሪፖርት ተከትሎ የተፈናቃዮችን ሁኔታ አስመልክቶ ከምክር ቤቱ አባላት ጥያቄዎች ተነስተው ነበር። ተነስተው በነበሩ ጥያቄዎች ላይ የፌዴራልና አርብቶ አደር ጉዳዮች ሚኒስትሩ አቶ ከበደ ጫኔ ምላሽ ሰጥተዋል። ሚኒስትሩ በሰጡት ምላሽ፣ ተፈናቃዮችን ወደ አካባቢያቸው ለመመለስ ቅድሚያ ሕዝባዊ የሰላም ኮንፍራንስ ለማካሄድ ቢታቀድም በነበሩ ችግሮች ዘግይቷል፤ ሁለቱ ክልሎችም በዚህ ጉዳይ ተቀናጅተው በጋራ መሥራት ላይም ክፍተቶች ነበሩባቸው ብለዋል። በአሁኑ ወቅት ግን ተፈናቃዮችን ወደነበሩበት የመመለስ ሥራ መጀመሩን አመልክተዋል።

ተፈናቃዮቹን ወደነበሩበት የመመለስ ስራ አስተማማኝ ሰላም መስፈኑን ማረጋጋጥ ስለሚፈልግ የአርብቶ አደርና የፌደራል ጉዳዮች ሚኒስትሩ አቶ ከበደ ጫኔ እንደገለጹት በሁለቱ ክልሎች ህዝቦች መሃከል የሰላም ኮንፈረንስ ማካሄድ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው። አሁን በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች የተፈጠረው አንጻራዊ ሰላምና በህዝቦች መሃከል ቀድሞ የነበረው የአብሮነት ኑሮ ማንሰራራት መጀመር የሰላም ኮንፈረንስ ለማካሄድ አመቺ በመሆኑ ጊዜ ሳይወሰድ እድሉን መጠቀም ይገባል። ከዚሁ ጎን ለጎን ግጭቱ ከተቀሰቀሰበት ጊዜ ጀምሮ በደረሰው ጉዳት እጃቸው ያለበት የሁለቱም ክልሎች የወንጀል ተጠርሪዎች በሙሉ በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው ፍርድ ቤት መቅረብ ይኖርበታል። ይህ የህግ የበላይነትን ስለሚያረጋግጥ ተፈናቃዮቹ ወደነበሩበት እንዲመለሱ የሚያበረታታ መተማመን እንደሚያሳድርባቸው መታወስ አለበት።

እስካሁን ያሉ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በርካታ ተፈናቃዮች ወደነበሩበት የመመለስ ፍላጎት አላሳዩም። ተፈናቃዮቹ የመመለስ ፍላጎት እንዲኖራቸው ከላይ የተገለጹት አስተማማኝ ሰላም የማስፈንና የህግ የበላይነትን የማረጋገጥ ጉዳይ ወሳኝ መሆኑን የሁለቱም ክልሎች መንግስታትና የፌደራል መንግስት ሊያስታውሱ ይገባል። ይህ ሁኔታ ወደቀድሞ ኑሯቸው መመለስ የሚፈልጉትን ተፈናቃዮች ቁጥር በእጅጉ እንደሚጨምረው መታወቅ አለበት።

ከዚህ በተረፈ ቀድሞ ወደነበሩበት መመለስ ያልፈቀዱ ተፈናቃዮችን በግዳጅ መመለስ አይቻልም። በመሆኑም ባሉበት ክልል እንዲቋቋሙና የተረጋጋ ኑሮ እንዲኖሩ ማስቻል አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው። በዚህ ረገድ በኦሮሚያ ክልል ተጨባጭ እንቅስቃሴ ተጀመሯል። ለምሳሌ በምስራቅ ሸዋ ሞጆ ከተማ፣ በደቡብበ ምዕራብ አርሲ ዞን ጥቁር ውሃና ሻሸመኔ ከተሞች፣ በፊንፊኔ ዙሪያ ዱከምና ለገጣፎ ከተሞች በህዝብ ትብብር ተፈናቃዮቹን ለማሰፈር የመኖሪያ ቤቶች ግንባታዎች እየተካሄዱ ነው። ተፈናቃዮቹን በዘላቂነት ለማቋቋም የሚያግዙ ገንዘብ የማሰባሰብ እንቅስቃሴዎችም እየተከናወኑ ይገኛሉ። በኢትዮጵያ ሱማሌ ክልል በኩልም ተመሳሳይ እንቅስቀሴዎች እየተከናወኑ መሆኑን የሚያመለክቱ መረጃዎች አሉ።

እንግዲህ፣ በፍቃዳቸው ወደነበሩበት ኑሮ ለመመለስ ፍቃደኛ ያልሆኑትን አስገድዶ መላክ ስለማይቻል ለማቋቋም የሚደረገው ጥረት በጎ ነው። ይሁን እንጂ ተፈናቃዮቹን እንደ አዲስ ማቋቋም እጅግ ውድ አማራጭ መሆኑ፣ እንዲሁም አዲስ ኑሮ ጀማሪዎች የሚያስፈልጋቸው የመኖሪያ ቤት ብቻ ሳይሆን መተዳደሪያ ስራም መሆኑን ማሰብ ያስፈልጋል። እናም በተቻለ መጠን ተፈናቃዮቹን ወደነበሩበት መመለስ የሚያስችል ተግባር ላይ ማተኮር ተገቢ ነው። ለሁለቱ ህዝቦች ዘላቂ ግንኙነት የሚበጀው አማራጭም ተፈናቃዮቹን ወደየነበሩበት በመመለስ የቀድሞ የአብሮነት ህይወታቸውን እንዲቀጥሉ ማደረግ ነው። የዘላቂ ሰላም ዋስትና የሚሆነውም ይህ አማራጭ ነው። እናም ወደነበሩበት የመመለሱ ጉዳይ ልዩ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy