Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የመጨረሻው አማራጭ

0 365

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የመጨረሻው አማራጭ

                                              ቶሎሳ ኡርጌሳ

በቅርቡ በአዲስ አበባ በተካሄደው የደቡብ ሱዳን የሰላም ስምምነት ሁለቱ የሀገሪቱ ተፋላሚ ኃይሎች የተኩስ አቁም ስምምነት መፈራረማቸው ሀገራችንና ኢጋድ በተደጋጋሚ እያደረጉት የሰላም ጥረት የበኩላቸውን ድርሻ ተወጥተዋል። በተለይም በጉባኤው ላይ የተገኙት የኢጋድ የወቅቱ ሊቀመንበርና የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር፤ የደቡብ ሱዳን ተፋላሚ ሃይሎች ልዩነታቸውን ወደ ጎን በመተው ለዜጎቻቸው ሰላም እና መረጋጋት መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰላም ስምምነቱ ተግባራዊነት የመጨረሻው አማራጭ መሆኑንም ገልፀዋል።

ይህ የጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ የመክፈቻ ንግግር የሚያሳየው ነገር ቢኖር ኢትዮጵያ ለቀጣናው ህዝቦች ሰላምና መረጋጋት ምን ያህል አሳስቧትና ትኩረት ሰጥታ እየሰራች መሆኑን የሚያሳይ ነው። የደቡብ ሱዳን ተፋላሚ ወገኖች የሀገራቸውን ህዝብ መሰረት አድርገው ለሰላም እጃቸውን እንዲዘረጉ ሀገራችን የጠየቀችው መንግስት ለሀገሩ ህዝብ ብቻ ሳይሆን ለጎረቤቶቹም ሀዝቦች ምን ያህል የሚጨነቅ መሆኑን የሚያሳይ ነው።

የኢፌዴሪ መንግስት ደቡብ ሱዳን የራሷን ነፃ ሀገር ከመሰረተች ጀምሮም ኢትዮጵያ ከአዲሲቷ ሀገር ጋር ያላት ግንኙነት በጋራ ተጠቃሚነት ዙሪያ ያተኮረ መሆኑ ይታወቃል። ይህም በንግድ፣ በመሰረተ ልማት፣ በኢንቨስትመንትና በፀጥታ ጉዳዩች ላይ ያተኩራል።

በአሁኑ ወቅትም ከአዲሲቷ ሀገር ጋር ሀገራችን ያላት መልካም ግንኙነት ቀጣናውን በልማት ለማስተሳሰር የምታደርገውን ጥረት እንደሚያጎለብት ተስፋ ተጥሎበታል። ይህም ኢትዮጵያ ከደቡብ ሱዳን ሰላም መሆን የምታተርፈው ቀጣናዊ የጋራ ተጠቃሚነትን መሆኑን የሚያስገነዝብ ይመስለኛል።

አዲሲቷ ሀገር ደቡብ ሱዳን ነፃ ከወጣች ጊዜ ጀምሮም በውስጧ የተፈጠረውን የእርስ በርስ ግጭት የኢፌዴሪ መንግስት ከኢጋድ ጋር በመሆን ችግሩን ለመፍታት ጥረት እያደረገ ነው። በዚህም ውጤቶች ተገኝተዋል። ኢትዮጵያ በሰላም ስምምነቱ ላይ ስምምነቱን የመጨረሻው አማራጭ በማለት በጠቅላይ ሚኒስትሯ አማካኝነት የገለፀችው ከዚህ ቀደም የተሰሩት ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች መቋጫ እንዲያገኙና ወንድም የሆነው የደቡብ ሱዳን ህዝብ ከሰላም ማግኘት የሚገባውን ትሩፋት እንዲያጣጥም ካላት ተነሳሽነት የመነጨ ነው።

ርግጥ የደቡብ ሱዳን ተፋላሚ ወገኖች ለዘመናት በአንድ ድርጅት ጥላ ስር ሆነው ለህዝባቸው ነጻነትና እኩል ተጠቃሚነት ሲታገሉ ቆይተው፣ የናፈቁትን ሰላምና ልማት ማጣጣም እንደጀመሩ ወዲያውኑ ወደለየለት የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ መግባታቸው የየትኛውንም ሰላም ወዳድ ህዝብ ልብ የሚሰብር ነው። በድርጅታቸው የውስጥ ውዝግብ ሳቢያ የዚያች ሀገር ህዝቦች ወደ እርስ በርሰ ጦርነት ውስጥ መግባታቸው ለከፍተኛ ሰብአዊና ቁሳዊ ጥፋት ተዳርገዋል።

ርግጥ በደቡብ ሱዳን የተከሰተው ወቅታዊ ችግር የዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ትኩረት በከፍተኛ ሁኔታ መሳብ ቢችልም፤ እልባት ከመስጠት አንፃር ግን የኢፌዴሪ መንግስትና ኢጋድን ያህል የተንቀሳቀሰ የለም ማለት ይቻላል። ምክንያቱም የሀገራችን መንግስትና ኢጋድ የቀጣናው ሰላም መታጣት ይበልጥ ስለሚያሳስባቸው ነው።

ሁላችንም እንደምንገነዘበው የዓለማችን አዲስ ሀገር በሆነችው ደቡብ ሱዳን የተከሰተው ቀውስ የአደጋው ተጋላጭ የሚያደርገው በዋነኝነት የሀገሪቱን ዜጎች መሆኑን እስካሁን ከደረሰው ሰብአዊና ቁሳዊ ኪሳራ መገንዘቡ ከበቂ በላይ ማሳያ ነው። ያም ሆኖ ግን ዳፋው ለአካባቢው ሀገራት መትረፉ አይቀሬ ነው።

የኢፌዴሪ መንግስት የደህንነት መጀመሪያም ሆነ መጨረሻ ሀገራዊ ህልውናን ማረጋገጥ ብቻ እንደሆነ በማመን፣ በደቡብ ሱዳን የተከሰተው ቀውስ እልባት ለመስጠት ቁርጠኝነታቸውን በተግባር የማስመስከር እንቅስቃሴያቸውን በመጀመር ግንባር ቀደም ሚናቸውን እየተጫወቱ ነው። የደቡብ ሱዳን ህዝቦች ሞት፣ እንግልትና ስደት አንድ ቦታ ማብቃት ስላለበትም ነው—ኢትዮጵያ የተኩስ አቁም ስምምነቱ “የመጨረሻው አማራጭ” መሆን ይኖርበታል በማለት ለህዝቦች ሰላም ያላትን ተቆርቋሪነት ያረጋገጠችው።

እንደ እውነቱ ከሆነ የኢትዮጵያ መንግስት መንግስት ለሀገራችን ሰላምና ልማት  እውን መሆን ከፍተኛ ጥረት እንደሚያደርግ ሁሉ፤ የጎረቤት ሃገሮች ሰላምና ልማትም እንዲፋጠን ካለው ፅኑ እምነት በመነጨ በጋራ ማደግ ቀዳሚ ምርጫው ነው። ‘ለምን?’ ቢሉ፤ የሀገራችን ሰላምና ልማት ለአካባቢያችን ዕድገት ድርሻ እንዳለው ሁሉ፤ የአካባቢያችን ሰላምና ልማትም ለሀገራችን ዕድገት መፋጠን የሚያበረክተው አዎንታዊ አስተዋጽኦ የላቀ እንደሚሆን በፅናት ስለሚያምን ነው።

ታዲያ በሀገራችን በመካሄድ ላይ ያለው የተፋጠነ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ልማት እንዲሁም የተጀመረው የመልካም አስተዳደር ሥርዓት ሀገራዊ ህልውናን የማረጋገጥ ዓላማን የሰነቀና ውጤቱም ለሀገራችንም ሆነ ለአካባቢያችን ሰላም ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል። የኢትዮጵያ መንግስት ለጎረቤቶቹ ሰላም የሚጨነቀው ከዚህ የጋራ ተጠቃሚነት መርሁ በመነሳት ነው። አቶ ኃይለማርያምም የሰላም ስምምነቱ “የመጨረሻው አማራጭ” መሆን እንዳለበት ያስገነዘቡት ከዚህ እውነታ በመነሳት ነው።  

እርግጥ የሰላም ስምመነት በየትኛውም ሀገር ውስጥ “የመጨረሻው አማራጭ” መሆን ይገባዋል። አንድ ሀገር ሰላምን ለማስፈን ያስችለው ዘንድ ሀዝቡን ማዕከል ማድረግ ይኖርበታል። የህዝብን ሰላም ለማስጠበቅ ሲባልም መንግስትም ይሀን ተቀናቃኝ ወገኖች ሁሉንም ዓይነት መስዋዕትነት መክፈል ይኖርባቸዋል። ባይስማሙም እንኳ ባለመስማማት ውስጥ መስማማትን ማንገስ ይኖርባቸዋል።

መንግስትም ይሁን ተፋላሚ ወገኖች ዓላማቸውን የሚያሳኩት “እንታገልለታለን” የሚሉት ህዝብ ሲኖራቸው ነው። ይህ ህዝብ ከሞተ፣ ከሀገሩ ከተፈናቀለና የስደት ኑሮን የሚገፋ ከሆነ ተፋላሚዎቹ የሚታገሉት ለራሳቸው ጥቅም እንጂ ለህዝብ አለመሆኑን ለመገንዘብ አይከብድም።

እዚህ ላይ በአንድ ወቅት ታላቁ መሪ አቶ መለስ ዜናዊ አስረስ በትጥቅ ትግሉ ወቅት የሚታገሉለት ህዝብ በደርግ መንግስት የተሳሰተ ፖሊሲ ምክንያት በድርቅ አደጋ መሞቱንና መሰደዱን ተመልክተው ለቢቢሲ የዜና አውታር “የምታገልለት ህዝብ እየሞተና እየተሰደደ ከሆነ የእኔ መታገል ትርጉም አልባ ነው” በማለት የገለፁትን እውነታ አስታውሳለሁ። ርግጥም አንድ ተፋላሚ ሃይል የሚታገልለት ህዝብ ከሌለና ወደ ጎረቤት ሀገሮች ከተሰደደ “ለማን ነው የምታገለው?” ብሎ ራሱን መጠየቅ ያለበት ይመስለኛል።

በመሆኑም ለህዝብ የተረጋጋ ሰላምና ደህንነት ሲባል ተፋላሚ ወገኖች ራሳቸውን ሳይሆን መመልከት ያለባቸው እታገልለታለሁ የሚሉትን ህዝብ ነው። እናም የደቡብ ሱዳን ተፋላሚዎች ቅድሚያ ለህዝባቸው ሁለንተናዊ ሰላም መትጋት ይኖርባቸዋል እላለሁ። የተኩስ አቁም ስምምነቱ “የመጨረሻው አማራጭ” መሆን ይኖርበታል።

ሁለቱ የሀገሪቱ ተፋላሚ ወገኖች ችግሮቻቸውን በጠረጴዛ ዙሪያ ለመፍታት በመዲናችን አዲስ አበባ ሲቀመጡ የእርስ በርስ ጦርነቱን በማስቆም የህዝባቸውን ሰላም ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል። ሀገራቸውም ከቀጣናው የኢኮኖሚ ትስስር ማትረፍ እንድትችል ህዝቡም የልማት ተጠቃሚ እንዲሆን ማስቻል አለባቸው።

የኢፌዴሪ መንግስት ሁለቱም ወገኖች የራሳቸውን ጥቅም ከማስቀደም ይልቅ፤ ለሀገራቸውና ለህዝባቸው ህልውና ቅድሚያ መስጠት እንዳለባቸው በተደጋጋሚ ከማስገንዘብ ባሻገር፤ ተቀናቃኞቹ ሃይሎች በቅርቡ አዲስ አበባ ላይ የፈረሙት የተኩስ አቁም ስምምነት “የመጨረሻው አማራጭ” መሆን እንዳለበት የሚገልፀውም ከላይ በጠቀስኳቸው ሰላም ወዳድነት፣ ህዝባዊነትና የጋራ ተጠቃሚነት እውነታዎች መነሻነት ነው።

 

 

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy