Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የሚዲያው ኃላፊነትና የመንግስት ሚና

0 311

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የሚዲያው ኃላፊነትና የመንግስት ሚና

                                                             ይልቃል ፍርዱ

የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ለሳምንታት በዘለቀ ስብሰባው ካሳለፋቸው ቁልፍ ውሳኔዎች ውስጥ በኮሚዩኒኬሽንና ሚዲያው ዘርፍ ያለውን ችግር መቅረፍ የሚለው አንዱ ነው፡፡ ሚዲያ በማያከራክር መልኩ ግዙፍ ተደራሽነት ያለው በሰኮንዶችና በደቂቃዎች ውስጥ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብን በያለበት ለመድረስ የሚያስችል አቅም ያለው ለሀገር ግንባታ፣ ለሁለንተናዊ ልማት፣ ለሰላም መጎልበት ወዘተ ከፍተኛውን ድርሻ ሊወጣ የሚችል፤ የዛኑም ያህል ጥፋትና ውድመት ሊያስከትል የሚችል ትልቅ ኃይል ነው፡፡

ሚዲያን በአግባቡ መያዝና መጠቀም ካልተቻለ በተለይ በዚህ ዘመን የተከሰተው ማሕበራዊ ሚዲያ ያለብዙ ድካምና ውጣ ውረድ በአንድና ሁለት መስመር መልእክት ሀገርና ሕዝብ የሚያናጋበት፣ ሰላም የሚያደፈርስበትና ደም መፋሰስ የሚያመጣበት ዘመን ላይ ደርሰናል፤ ይሀው እውነታም በበርካታ የአለማችን ክፍሎች ታይቶአል፡፡ በእኛም ሀገር ይሄው ሁኔታ እንዲከሰት ያለመታከት እየሰሩ ያሉ ማሕበራዊ ሚዲዎች አሉ፡፡

ሜን ስትሪም ሚዲያው ማለትም የቀድሞው ፕሬስ፣ ቴሌቪዥንና ሬድዮ በዘመናቸው ብቸኞቹ የዜና ምንጭና ለሕዝብ ተደራሽ የነበሩበት ዘመን ዛሬ ከሞላ ጎደል በማሕበራዊ ሚዲያው እየተነጠቁ ይገኛሉ፡፡ ማሕበራዊ ሚዲያው ለበጎ ተግባር የመዋሉን (በፍጥነት መልእክቶችን ለማስተላለፍ፣ ለእውቀትና ለምርምር ወዘተ አገልግሎት የመስጠቱን ያህል) በቂ እውቀት በሌላቸው፣ ኃላፊነት በማይሰማቸውና ለሰው ልጅ ክብር በሌላቸው ግለሰቦች እጅ ሲወድቅ ትልቅ ሀገራዊ ጥፋት ያስከትላል፡፡

የሰው ልጅ ሕይወት በነዚሁ ሰዎች እኩይ ተግባር ምክንያት አንዱን ዘር የማንቋሸሽ፣ የመሳደብ፣ የመዝለፍ፣ ስሜትን የሚጎዳ ጽሁፍ ማሰራጨትና መልቀቅ የተነሳ በተመሳሳይ ሰአት በመቶ ሺዎች ወይንም ሚሊዮኖች ተደፈርን ተሰደብን በሚል የበቀል ስሜት አምርረው እንዲነሱ ጠብና ሁከት ውስጥ እንዲገቡ ያደርጋል፡፡ ይህን ተከትሎ የሚነሳውን ረብሻ ንብረት ማቃጠል የሰው ሕይወት መጥፋት እያየነው እንገኛለን፡፡

ቀደም ሲል የጠቀስነው የስራ አስፈጻሚው ውሳኔ ለሕዝብ ከተገለጸ ገና ወር ቢሆነው ነው፡፡ ይሁን እንጂ ውሳኔውን ወደ ተግባር የማዋል ስራ ተጀምሮአል፡፡ በርግጥ ሚዲያውን በትክክል ወደሚፈለገው ደረጃ ለማምጣት የረዥም ግዜ የቤት ስራን ይጠይቃል። መግለጫው በመሰጠቱ ብቻ በአንድ ግዜ የሚመጣ ለውጥ የለም፡፡

ሚዲያው ሀገራችን ካለችበት ተጨባጭ ሁኔታ አንጻር ትኩረት ሰጥቶ መስራት ያለበት ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን ነው፡፡ ችግሮች በውይይትና በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ፤ ሕብረተሰቡ በሀገራዊ ሰላምና መረጋጋት ዙሪያ የተሻለ ግንዛቤ በመፍጠር ለሰላሙ እንዲቆም የማድረግ ስራ ነው መከወን ያለበት፡፡ በዚህ ረገድ በመንግስት ስር ያለው የፐብሊክ ሚዲያ (አሌክትሮኒክሱም ሆነ ፕሬሱ) ብዙ ርቀት ሄዶ መስራት ቢጠበቅበትም በአንጻራዊነት የተሻለ ነው ማለት ይቻላል፡፡

በተለይ አሁንም ሀገራዊ አደጋ ሁኖ ትልቅ ጥፋት እያስከተለ ለሕዝቡ ሰላምና መረጋጋት ጠንቅ የሆነው የሕዝብን አብሮነት እየናዱ ለከፋ በቀል እያነሳሱት ያሉት ገዢውን ፓርቲ እንደግፋለን በሚል ስም የሚጽፉት ብሎገሮች ናቸው፡፡ እነዚህ አካላት ሕዝብን ከሕዝብ ለማጫረስ ታጥቀውና ቆርጠው የተነሱ ይመስላል፡፡ ቅንጣት ታክል የኃላፊነት ስሜት የማይሰማቸው፣ በሕዝብ ላይ ያላቸውን ንቀት በአደባባይ በመዝለፍና በመሳደብ የሚያሳዩ፤ ለከፋ በቀል የሚያነሳሱ፣ ባልተገራ ብእራቸው የሕዝብን ስብእና የሚያዋርዱ ናቸው፡፡ እነዚህ ሀይሎች ምንም ቢከሩና ቢዘከሩም ዛሬም ከትላንቱ ስህተታቸው ለመማር ፈቃደኝነቱ የላቸውም፡፡

በአንዳንድ ሚዲያዎቻችን የምንሰማቸው ዜናዎችም ሆኑ ፕሮግራሞች የሚቀርቡት በራሱ በመንግስት/ክልሎች ሚዲያ(ዎች) ሲሆን የመልእክቱ አስተላላፊዎችም ለመንግስትና ለፓርቲው ቅርበት ያለቸው አካላት ናቸው። ከሁሉም በበለጠ ከነዚህ ወገኖች የሚጠበቀው ሕዝብን የማረጋጋት ስራ በሰፊው መሰራት ነው፡፡ ነገር ግን አንዳንዴ ይህ ሲሆን አይታይምና ሊታረም ይገባዋል።

ኢሕአዴግ ባሳለፈው ውሳኔ መሰረት ወደተግባር እየገባ ባለበት በዚህ ወቅት ትልቁ የሰላምና መረጋጋት ጠንቅ ሆኖ ሀገር ለማወክና ሰላሙን ለማደፍረስ እየሰራ ያለው ሶሻል ሚዲያው ነው፡፡ ከሕዝብ ሰላም ማጣትና መታወከ ከሀገር ሰላም መደፍረስ የሚያገኙት ጥቅም ምን እንደሆነ ባይታወቅም በእንዴት አይነት የከፋ የዘረኝነት በሽታ እንደተለከፉ ለመረዳት ስራዎቻቸው በቂ ምስክሮች ናቸው፡፡

በኢሕአዴግ ስር የተሰባሰቡት አራቱ ድርጅቶች የቅድሚያ ትኩረት ማድረግ ያለባቸው በዘረኝነት ልክፍት የተጠመዱትን፣ በስሙ የሚነግዱትን፣ ሕዝብን ከሕዝብ ለማባላት ሆን ብለው ታጥቀው የተነሱትን፣ ሠራዊቱን የደገፉ መስለው የበለጠ ከሕዝብ የሚያጋጩትንና ሌሎች መሰል ስራዎች የተጠመዱትን ሀይሎች አደብ ማስያዝ ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች እንደግፈዋለን የሚሉትንም ድርጅት ይበልጥ ከሕዝቡ ውስጥ እንዲወጣ በማድረግ ረገድ ትልቅ ስራ ሲሰሩ የቆዩና እየሰሩ ያሉ ናቸውና አደብ የማስያዙ ጉዳይ ጊዜ የሚሰጠው ሊሆን አይገባም፡፡

በማህበራዊ ሚዲያው ዘርፍ የተሰማሩና ጥቂት የማይባሉ ሀይሎች በማያከራክር ሁኔታ በከፋ የዘረኝነት ድጥ ውስጥ ወድቀው ሌላውን ይዘው ለመጥፋት፣ ጭርሱን ሀገርን ለማፈራረስና አንዱ ሕዝብ በሌላው ላይ እንዲነሳ ለማድረግ ያልጎነጎኑት ሴራ፣ ያልጫሩት እሳት የለም፡፡ ሕዝብ ሁኔታውን ለይቶ ስለተረዳው የከፋ ጥላቻ ውስጥ እንዲወድቅ አድርገውታል፤ ይህ ደግሞ እንደ ሀገርም እንደ ሕዝብም ያሳዝናል፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ እንደነዚህ፣ በማሕበራዊ ሚዲያ ተዋናይ ነን እንደሚሉት አይነት የዘረኝነትን በሽታ የሚያስፋፉ  ሰዎች በሀገራችን ታይቶም፤ ተሰምቶም አይታወቅም፡፡ (ወደው አልነበረም ለካ የቱርኩ ኤድሮጋንና የግብጹ ሲሲ ለቁጥር አታካች የነበሩትን ማሕበራዊ ሚዲያዎች የዘጉት ያስብላል)፡፡

ሚዲያው መስራት ያለበት ችግሮች ሁሉ በሰላማዊ መንገድ የሚፈቱበትን የሕዝብ ሰላምና መረጋጋት የሚመጣበትን ሁከትና ግጭት ደም መፋሰስ እንዳይኖር የማድረግ ሕዝባዊና ሀገራዊ ኃላፊነት ያለውን ስራ ነው፡፡ አንዳንድ ግዜ ከጉዳዮች ክብደትና በሕዝብ ውስጥ ከሚፈጥረው ከባድ ስሜት የተነሳ የሚፈጥረውንም አደጋ፤ ምክንያትና ውጤቱን በማጤን መረጃዎች በሚዲያ የማይተላለፉበት ሁኔታ አለ፡፡ ይህ የሚደረግበት አቢይ ምክንያት ደግሞ ድርጊቱን ለመሸፈን ሳይሆን የባሰና የከፋ ጥፋት እንዳይከሰት ለማድረግ ሲባል ነው፤ በሰላማዊ መንገድ የሚፈቱ ችግሮች ሁሉ አደጋና ጥፋትን የመቀነስ ትልቅ አቅም ያላቸው መሆኑን ከግምት ውስጥ በማስገባትም ጭምር ነው፤ ከነበረው ወይንም ከታየው በላይ የከፋ አደጋ እንዳይከሰት ለመከላከልም ሲባል ነው፡፡

አንዱን ችግር ለመወጣት ሲሞከር በሌላው ድንገተኛ ክስተት በመጠመድ በችግር አዙሪት ውስጥ መጥመልመል እንደገና ፈተና ውስጥ መግባት በዚህ ሲባል በዚያ ለሚያፈተልከው ውጥረትና የሰላም መደፍረስ በተረጋጋ ሁኔታ እልባት ለማምጣት ያልተቻለው የሕዝቡን ስሜት በጥላቻ እያደፈረሱ ባሉት ማሕበራዊ ሚዲያዎች አማካኝነት ነው፡፡

ለማጠቃለል፤ ማሕበራዊ ሚዲያው በአሁኑ ሰአት ለኢትዮጵያ ትልቅ አደጋን የደቀነ የሰላምና የመረጋጋት ጠንቅ መሆኑን ቀጥሎአል፡፡ ከስራ አስፈጻሚው መግለጫ በኋላ የተወሰነ ቀናት አንጻራዊ ሰላምና መረጋጋት በማሕበራዊ ሚዲያውም በኩል ታይቶ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ የከፋ እልቂትና ጥፋት የሚከሰትበት አሳሳቢ ሀገራዊ አደጋ አሁንም ከፊታችን እንደተደቀነ ነው። አሁን ለሀገራችን የሚያስፈልገው ግጭት፣ ሁከትና ደም መፋሰስን የሚያባብስ ሚዲያ አይደለም፤ የሕዝብ መለያየትን ሳይሆን ሰላምና መረጋጋትን፣ አብሮነትን፣ መደማመጥና ውይይትን የሚሰብክ ሚዲያ ነው የራበን። ሀላፊነት የጎደላቸው ሚዲዎች ሳይሆኑ የናፈቁን ሰላምን ሊያሰፍኑ የሚችሉ ሚዲያዎች ናቸው ብርቅ የሆኑብን።  መስፋትና መበራከት ያለባቸው እነዚህ ሆነው ሳለ እንደአሸን እየፈሉ ያሉት ግን በተቃራኒው ያሉ ናቸው፡፡ (ይህን ስንል በመንግስት በኩል ለመረጃ ነፃነት ትኩረት በመስጠት፤ የተከሰቱ ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የሚያስችሉ ሰፊና ግልጽ የውይይት መድረኮችን በማዘጋጀትና ሚዲያዎችን በመጋበዝና በማሳተፍ፣ የህዝብ አስተያየቶች በቀጥታ እንዲሰራጩ ማድረግ የመጠበቅበት መሆኑ እንዳለ ሆኖ ማለታችን ነው፡፡) ለዚህ ሁሉ ደግሞ፣ በዋናነት የሚዲያ ሪፎርም ያስፈልገናልና ሪፎርሙ የቅድሚያ ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy