Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የማይታጠፍ ቃል በተግባር

0 352

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የማይታጠፍ ቃል በተግባር

                                                             ይልቃል ፍርዱ

የኢሕአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የተከሰቱ ሀገራዊ ጉዳዮችን በጥልቀት ከፈተሸና ከመረመረ በኋላ ለተፈጠሩት ሀገራዊ ቀውሶችና ችግሮች ከፍተኛው አመራር ኃላፊነቱን ወስዶ፤ በግልጽም ሕዝቡን ይቅርታ ጠይቆ በመስራት እንደሚክስ ገልጾአል፤ መግለፅ ብቻም ሳይሆን ወደ ስራም ገብቶአል፡፡ በዚህም መሰረት መሰረታዊ ለውጦች ይመጡባቸዋል ተብለው የሚጠበቁ ሰፊ ዘርፎች አሉ፡፡ በውሳኔው መሰረት በየደረጃው የሚታዩ ለውጦችን ለማየት የሕዝቡም ጉጉትና ፍላጎት ከፍተኛ ነው፡፡

በስራ አስፈጻሚው ኮሚቴ ውሳኔ መሰረት ትልቁ ጉዳይ የተከሰተውን ሀገራዊ ቀውስና ምስቅልቅል ከሕዝቡ ጋር በመሆን መፍታት፤ የዲሞክራሲ ምሕዳሩን ማስፋት፤ የመልካም አስተደደር ችግሮችን መቅረፍ፤ በዲሞክራሲ ግንባታ ሂደቱ ውስጥ ሕዝቡን በስፋት ማሳተፍ፤ በአመራሩ ደረጃ ግልጽነትና ተጠያቂነት እንዲሰፍን ማድረግ፤ በየቦታው የሚታየውን የሰላምና መረጋጋት ችግር ከሕዝቡ ጋር በመሆን ወደነበረበት የተረጋጋ ሰላም መመለስ፤ የተጀመሩትን ሀገራዊ የልማትና የእድገት ስራዎች በአስተማማኝ መሰረት ላይ እንዲቀጥል ማድረግ ዋነኞቹ ናቸው፡፡ በዚህም መሰረት 8 ዋና ዋና ውሳኔዎችን አሳልፎ ወደ ትግበራ ገብቶአል፡፡

ብሔራዊ መግባባት ከመፍጠርና የዲሞክራሲ ምሕዳሩን ከማስፋት አንጻር የታሰሩ እስረኞችን እንደሚፈታ መንግስት በገለጸው መሰረት በርካታ እስረኞች ተፈተዋል፡፡ በፌደራል ደረጃ ከ500 በላይ በክልሎች ደረጃም፣ በተለይ በኦሮሚያ ክልል ከ2000 በላይ እስረኞች ከሰሞኑ ተፈተዋል፡፡ ጉዳያቸው ተጠንቶና ታይቶ እስከ ሁለት ወር ባለው ግዜ ውስጥ በምሕረት የሚፈቱ እንዳሉም መንግስት ገልጾአል፡፡ ሲጀመርም መንግስት ግለሰብ ዜጎችን የወንጀልና ከወንጀል ድርጊት ጋር ተያያዥ በሆነ ሁኔታ ውስጥ በተጨባጭ ተጠርጥረው ወይንም በአመጽና በሁከት ተግባር ቀጥተኛ ተሳታፊ ሁነው እስካልተገኙ ድረስ ዝም ብሎ በመነሳት ሰዎችን የማሰር ፍላጎት የለውም፡፡

አንድ ሀገር በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ ሕግና ስርአትን ማስከበር ካልቻለች ቀጣዩ ሁኔታ ስርአተ አልበኝነት ገፍቶ በመውጣት በሕብረተሰቡ ሰላማዊ ሕይወት ላይ ከፍተኛ አደጋ  ይደቅናል፡፡ መንግስት አንዱ ሕገመንግስታዊ ግዴታው የዜጎችን ሰላማዊ ሕይወትና ደሕንነት የመጠበቅና የማስጠበቅ ተግባር ስለሆነ እንዲህ አይነት ሁኔታዎችን በዝምታ ሊያልፍ አይችልም፡፡ የግድ ሕግና ስርአትን የማስከበር ኃላፊነት አለበት፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ በሕግ ተጠያቂ የሚሆኑ ይታሰራሉ፡፡ ይህ እውነት በእኛ ሀገር ብቻ ሳይሆን በመላው አለም የሚሰራበትና ከመንግስት ኃላፊነትና ግዴታ ጋር የተያያዘ ነው፡፡

መንግስት በተለያዩ አካባቢዎች በሚነሳ ግጭት የሰው ሕይወት ሲጠፋ፣ ንብረት ሲወድም፣ ሲቃጠልና ሲዘረፍ፣ የዜጎች ሰላማዊ ሕይወት ሲስተጓጎል በዝምታ ሊመለከት አይችልም፡፡ በየትኛውም መስፈርት ሰላምና ጸጥታን የማስከበር ኃላፊነትና ግዴታ የግለሰቦች ሳይሆን የመንግስት ነው፡፡ በእርግጥ በዚህ አስቸጋሪ ሰላም በማስከበሩ ሂደት  ውስጥ የጸጥታ ኃይሉ በሕግ ከተቀመጠለት ኃላፊነትና ግዴታ ካለፈ በሕግ መጠየቁ አንዱ ሕግና የሕግ የበላይነትን የማስከበሩ ስራ አካል ነው፡፡

በዘረፋ ወንጀል የሕብረተሰቡን ሰላምና ደሕንነት በማወክ ተደራጅተውና መሳሪያ ታጥቀው በዝርፊያ ስራ የተሰማሩ፣ የሰው ሕይወት የሚያጠፉ ሁሉ ዛሬም ነገም በሕግ መጠየቃቸው ግድ ነው፡፡ ይህ እንዳለ ሁኖ ማንኛውንም የፍትሕ፣ የመልካም አስተዳደርና ሌሎችንም ከመብት ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ጥያቄዎች በሕጋዊ መንገድ በሰላም ማቅረብ ሲቻል ወደሁከት ብጥብጥና ረብሻ ያመሩ፣ የሰው ሕይወትና ንብረት መውደምን ያስከተሉ የሕብረተሰቡን ሰላምና መረጋጋት ያወኩ ተግባሮች በስፋት በተለያዩ አካባቢዎች ታይተዋል፡፡

ሁኔታውን ከማረጋጋት አልፈው ለደረሰው ጉዳት ተጠያቂ የሆኑ ሰዎችን በሕግ ተጠያቂ ማድረግና ማጣራት፣ የጥፋተኝነታቸውን ደረጃ በበቂ ማስረጃ መለየት ለድርጊቱ ተመጣጣኝ የሕግ ቅጣት መስጠት በሁሉም ሀገር የሚሰራበት ሕግን የማስከበር ዳሚ ስራ ነው፡፡ በየትኛውም መልኩ የዜጎች ሕይወት መጥፋት፤ የግለሰብም ሆነ የሕዝብ የመንግስት ሀብት መውደም የለበትም፡፡

በአብዛኛው በዚህ ተግባር ወጣቱን በተሳሳተ መንገድ በስሜታዊነት በመቀስቀስ ያሰማሩት ከጀርባ ያሉ የውስጥና የውጭ ኃይሎች እንዳሉ ቢታወቅም እነሱ በቀጥታ አይሳተፉም፡፡ የሚጠቀሙት ወጣቱን በስሜታዊነት እንዲነሳ በመቀስቀስና ጥፋት እንዲያደርስ በመገፋፋት ነው፡፡ ይህን ሁኔታ ተረድቶ ወጣቱ ከድርጊቱ እንዲታቀብ ወደስራ እንዲሰማራ ራሱንና ቤተሰቡን እንዲለውጥ በየክልሉ ሰፋፊ ፕሮጀክቶች ተቀርጸው  ተግባራዊ ሁነዋል፡፡

በቁጥጥር ስር የዋሉትን በመምከር ተመልሰው በዚህ አይነቱ ድርጊት እንዳይሳተፉ በማስታወቅ ብዙ ሺህ ወጣቶች በተለያየ ግዜ ከታሰሩበት ተለቀዋል፡፡ መንግስት በመሰረቱ ጥፋተኛ ሁነው የተገኙ ሰዎች በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ሲያደርግ ዋናው ከጥፋታቸው ተጸጽተውና ታርመው መልሰው ሕብረተሰቡን እንዲያገለግሉ እንጂ የተለየ አላማ  ኖሮት አይደለም።

መንግስት በስራ አስፈጻሚ ኮቴው ውሳኔ መሰረት እስረኞችን እፈታለሁ ያለውን ቃሉን አከብሮ በየደረጃው እስረኞች እንዲፈቱ እያደረገ ነው፡፡ እስረኞችን የመፍታቱ ውሳኔ የተላለፈው የበለጠ ሀገራዊ መግባባትን ለመፍጠር፣ ችግሮችን ሰላማዊ በሆነ መንገድ ለመፍታት የዲሞክራሲ ምሕዳሩን ለማስፋት፣ ዜጎች ከእስር ተፈተው ተመልሰው ሕብረሰተቡን እንዲያገለግሉ ከማድረግ አላማ የመነጨ እንጂ በውጭ ኃይሎች ጫናና ግፊት የተፈጸመ አይደለም፡፡

ይህን አይነቱን ሀሳብ እያሰራጨ ያለው ጽንፈኛው ተቃዋሚ በጎ ነገር ለማሰብ ያልታደለ በመሆኑ የሀሰት ፕሮፓጋንዳውን ቢነዛ የሚገርም ነገር የለውም፡፡ ትልቁ ሀገራዊ ችግሮችን በሰላምና በመግባባት መንፈስ መፍታት መቻል ነው፡፡ ለሀገር ሰላምና መረጋጋት ሳይሆን ሰላም እንዲደፈርስ ሁከትና ብጥብጥ እንዲነግስ በፌስክና በማሕበራዊ ሚዲያው ሲቀሰቅስ ውሎ የሚያድረው ጽንፈኛ ኃይል የሀገርና የሕዝብ ሰላም አያሳስበውም፡፡

በሚጠፋው ክቡር የሰው ልጅ ሕይወትም ሆነ በሚወድመው የሀገር ንብረት በሰው ቁስል እንጨት ስደድበት አይነት ምኑም ስለማይነካ እየተቀባበለ አሉባልታና የሀሰት ፕሮፓጋንዳውን ሲረጭ ሕዝብን የተሳሳተ አመለካከት እንዲዝ የማድረግ ስራ ሲሰራ ውሎ ያድራል፡፡ ይህን ያድርግ እንጂ በተጨባጭ ለውጥ የማምጣት አቅም እንደሌለው ያውቀዋል፡፡ የኢሕአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ውሳኔ ወደተግባር እየገባ በመሆኑ መሰረታዊ ለውጥ እንደሚያመጣ የተፈጠሩት ችግሮች በሙሉ ደረጃ በደረጃ በሂደት እንደሚስተካከሉ ግልጽ ነው፡፡

 

ከፍተኛ  አመራሩ  አገሪቱ  ያስመዘገበቻቸውን መልካም ነገሮችና እየተከሰቱ ያሉ ችግሮችን  በሀቀኝነትና  በተሟላ  ሁኔታ  ፈትሾ ውሳኔ ላይ ሲደርስ ይህንንም በግልጽ ለሕዝብ አሳውቆ ወደተግባር ሲገባ የሚታይና የሚጨበጥ መሰረታዊ ለውጥ እንደሚመጣ ይህንንም በቁርጠኝነት እንደሚያሳካው ይታወቃል፡፡ ከዚህ በመነሳት የራሱንና የሀገሪቱን ችግሮች ለመቅረፍና መልካም ውጤቶችን ለማስፋትና እየጨመረ ለመሄድ ወደተግባር ገብቶአል፡፡

መንግስት የሕግ የበላይነትን በመጣስ ልዩ ልዩ ጥፋቶችን የሚፈጽሙ አካላት በሕግ ተጠያቂ እንዲሆኑ የማድረግ ስራውን አጠናክሮ ይቀጥላል፡፡ ዋናው የሀገር የሕዝብ ሰላምና መረጋጋት መከበርና ተጠብቆ መቀጠል መቻሉ ነው፡፡ ሕግና ደንቡን ተከትሎ ሕጋዊ  ተጠያቂነት እንዲኖር እንዲሰፍን ያደርጋል፡፡

መንግስት የተፈጠሩትን ግዜያዊና ወቅታዊ ችግሮችን በመፍታት አገራችን  የጀመረችውን  የልማት፣ የእድገትና የለውጥ፣ እንዲሁም ሕዝብን የመጥቀም ጉዞ በተደራጀ አቅም የማፋጠን ስራዎችን ይሰራል፡፡ ባስቀመጠው  አቅጣጫ መሰረት የእስረኞች መፈታት ጉዳይ መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት ከሚሰራባቸው ጉዳዮች ውስጥ አንዱ እንጂ ዋነኛው ጉዳይ አይደለም፡፡ ከዚህ አንጻር የጽንፈኛው ኃይል ጩሀት መሰረታዊውን አጀንዳ ሊቀይረው አይችልም፡፡ እስከአሁን ባለው ግዜ መንግስት ቃሉን ጠብቆ እስረኞችን ፈቷል፡፡ ቃል በገባው መሰረት ቃሉን ጠብቆ ጉዳያቸው እየተጣራ በምህረት የሚወጡትም ይለቀቃሉ፤ ሌላ የተለየ ነገር የለውም፡፡

የመንግስትም ሆነ የሕዝቡ ትኩረትና ዋናው አጀንዳ የሀገራችንን ወቅታዊ ችግሮች መፍታት፤ ሀገራዊ መግባባትን ለመፍጠር የዲሞክራሲ ምሕዳሩን ማስፋት፤ የሕዝቡን ጥያቄ መመለስ ሲሆኑ፤ ለዚህም ልዩ ልዩ አቅጣጫዎችን አስቀምጦ ተግባራዊ ማድረግ ጀምሮአል፡፡

የእስረኞች መፈታት ጉዳይ በአንድ ርእስ ስር ከተጠቃለሉ በርካታ ነጥቦች ውስጥ  አንዱ ብቻ ነው፡፡ ጽንፈኛ ኃይሉ ሙሉ ትኩረቱን በእስረኞች መፈታት ላይ ብቻ በማድረግ ይህንንም ተመርኩዞ አሉታዊ ቅስቀሳዎችን በማሰራጨት ስራ ላይ መጠመዱ ፋይዳ የለውም፡፡ የስራ አስፈጻሚው ኮሚቴ ያሳለፋቸው ውሳኔዎች ተግባራዊነት የማይታጠፍና የማይቀለበስ ነው፡፡

ሙስናን ጸንቶ በመታገል መልካም አስተዳደር ማስፈን፤ በመንግስታዊ አሰራር ውስጥ ግልጽነትና ተጠያቂነት እንዲኖር ማድረግ፤ የዲሞክራሲ ምሕደሩን ማስፋት፤ ዲሞክራሲውን ማጎልበትና ግልጽ ወይይት እንዲኖር ማስቻል ላይ በጥልቀት የሚሰራ ሲሆን፤ ሌሎችም የተገቡት ቃሎች ተግባራዊ ይሆናሉ፡፡ በእርግጥ የሚጠበቀው ለውጥ ሁሉ በአንድ ግዜ ይመጣል ማለት ግን አይቻልም፤ በሂደት ነው እየጎለበተና እየጠራ የሚሄደው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም እንደገለጹት በፈጸሙት ወንጀል ምክንያት በፍርድቤት የተፈረደባቸው አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲ አባላትን ጨምሮ ሌሎች ግለሰቦች ሕግና ሕገመንግስቱ በሚፈቅደው መልኩ ተገቢው ማጣራት ተደርጎበት በምሕረት ይለቀቃሉ፤ ይህም የተሻለ ሀገራዊ መግባባት ለመፍጠር የሚያስችል በመሆኑ ይሄው ስራ በተቀመጠለት መስመር መሰረት እየተከናወነ ይገኛል፡፡ ክልሎችም ይሁንኑ የፌደራሉ መንግስት ታሳሪዎች ሕጉ በሚፈቅደው መጠን አስፈላጊውን ማጣራት በማካሄድና በምሕረት የሚለቀቁትን  በመለየት ስራ ላይ ይገኛሉ፡፡

ባጠቃላይ፣ መንግስት እስረኞችን እየለቀቀ ያለው በጫና ወይንም በውጭ ኃይሎች ግፊት አይደለም፡፡ ለሕዝቡ ጥያቄና አስተያየቶች በሰጠው ተጨባጭ ምላሽ መንግስት የሕዝብን ጥያቄ ሰምቶ አክብሮ መልቀቁ በእጅጉ የሚያስመሰግነው ስራ ነው፡፡ ሌሎችንም ችግሮች በዚህ መልኩ ሕዝብን እያዳመጠና እየተናበበ ደረጃ በደረጃ እንደሚፈታ ልንጠራጠር አይገባም፡፡ ሕዝብን የሚሰማና የሚያዳምጥ መንግስት ስለመሆኑም ማረጋገጫ ነው፡፡ እስረኞች ይፈታሉ ሲባል ሁሉም እስረኞች አይፈቱም፡፡ ከባድ ወንጀለኞች በርካታ ነፍስ ያጠፉ ነፍሰ-ገዳዮች፤ ሕብረተሰቡን ሲዘርፉና የማፍያ ቡድን መስርተው በብዙ መልኩ ሲንቀሳቀሱ፣ ሲገድሉና ሲዘርፉ የነበሩና በተጨባጭ ማስረጃ የተፈረደባቸውን ወንጀለኞች መልቀቅ ማለት ተመልሶ ሕብረተሰቡን እንዲያጠቁ፣ እንዲዘርፉና ሌላ ተጨማሪ ወንጀል እንዲፈጽሙ ማድረግ ማለት ነው፡፡ እነዚህ መፈታት አለባቸው ብለው ለሚጮሁት ሁሉ ይህ የሕግ የበላይነትን የሚሸረሽርና ፍጹም ተቀባይት የሌለው መሆኑን፤ ነገ ከነገ ወዲያም ወንጀልን የሚያበረታታ እንደሚሆን ሁሉም ወገን ሊረዳው ይገባል፡፡

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy