Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የሠላም ዋጋ በስንት ይተመን

0 480

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የሠላም ዋጋ በስንት ይተመን

አባ መላኩ

የሰው ልጅ በህይወት ለመኖር ቅድሚያ የሠላሙ ባለቤት መሆን ይኖርበታል። የሰው ልጅ ስለ ሌላው መሠረታዊ መብቶቹ ከማሰቡ በፊት ስለ ሠላሙ መስፈን መጨነቅ ይኖርበታል። ስለ ልማትና ስለዕድገት ከማሰላሰል በፊት የሠላም መረጋገጥ ዋስትና ሊያገኝ ይገባል። እናም ሁሉም ዜጋ ስለ አገሩ ሠላም ይበልጥ ማሰብና መጠበብ ይኖርበታል።   

ሠላም ከሌለ ምንም ነገር ስለማይኖር በሠላም ጉዳይ መደራደር አያስፈልግም። ሠላም ከሌለ የትኛውም የኅብረተሰብ ክፍል የሚመኘውን ተጠቃሚነት እውን ማድረግ አይቻልም። ሠላም ከሌለ ልማትንም ይሁን ዴሞክራሲን ማስፋትና ማረጋገጥ አይቻልም። ሠላም በሌለበት ሁኔታ ከእነዚህ መሠረታዊ መብቶች ባሻገር ዋነኛውና በህይወት የመኖር ዋስትና ሊኖር አይችልም።

በእርግጥ ሠላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ የማይነጣጠሉ ጉዳዮች ናቸው። ሠላም ከሌለ ስለ ልማትና ዴሞክራሲ ማሰብ ዋጋ የለውም። እንደ ኢትዮጵያ ያለች ከድህነት ለመውጣት የምትታትር አገር ሠላምና መረጋጋቷን ማስጠበቅ ወሣኝ ተግባሯ አድርጋ መንቀሳቀስ ይኖርባታል።

ለአንድ አገር ልማትና ዕድገት ሠላም ከምንም በላይ የገዘፈ ዋጋ እንዳለው አያጠያይቅም። እንደ እውነቱ ከሆነ የሠላም ዋጋ በምንም ዓይነት ምድራዊ ዋጋ ሊለካ አይችልም።  

እንደሚታወቀው ሁሉ የኢትዮጵያ ህዝቦች አሁን የተገኘውን ሠላም ለማምጣት በአያሌው ታግለዋል። ሠላምን ጨምሮ የዘመናት ጥያቄያቸው የነበሩትን ልማትና ዴሞክራሲን እውን ለማድረግ በብርቱ ታግለዋል። በርካታ መስዋዕትነቶችንም ከፍለዋል። የኢትዮጵያ ህዝቦች በቀደምት ሥርዓቶች በርካታ ግፎች ደርሰውባቸዋል። በመስዋዕትነታቸው በደላቸውን ሽረዋል።  

 

ህዝብና መንግሥት ይህን ተግባር እያከናወኑ ያሉት ሠላምና መረጋጋት ለአንድ አገር ልማት ያላቸውን ትልቅ ፋይዳ ስለሚገነዘቡ ነው። በመሆኑም በመላ አገሪቱ ያለውን ሠላምና መረጋት አሁን ካለው በላይ ይበልጥ አስተማማኝ በማድረግ ለአገራቸው ልማት ቀጣይነት የበኩላቸውን ድርሻ መወጣት ይኖርባቸዋል።

የአገራችን ህዝቦች በሠላምና መረጋጋት እጦት ይህ ትግላቸው እንዲቀለበስባቸው አይሹም። መላው የአገራችን ህዝቦች በተለይም ያለፈው አምባገነናዊና ‘የሁሉም ችግሮች መፍትሄ ጦርነት ነው’ የሚለው ሥርዓት የፈጠረውን እልቂት በሚገባ ስለሚገነዘቡ የሠላምን ዋጋ ጠንቅቀው ያውቃሉ። የትናንት የጦርነት ሰቆቃን በሚገባ ይገነዘባሉ።  

የአዲሲቷ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዛሬ እንደ ትናንቱ ጦርነት ያንዣበበበትን የሰቆቃ ህይወት መምራትን አይፈቅዱም። የጥይት አረሮች ድምጾችን ማዳመጥ አይመርጡም። ለአቅመ -አዳም የደረሱ ልጆቻቸውን ሳይቀር በግዳጅ ብሔራዊ ውትድርና ወደ ጦር ሜዳ ለመላክ አይነሳሱም። እነዚህ ሁሉ ከዛሬ 27 ዓመታት ገደማ የነበሩ ትውስታዎቻችን በሠላም ትሩፋቶች ተተክተዋል። ይህ አስተማማኝ የሠላም ምህዳር የኋሊት እንዲቀለበስ አይሹም። የኢትዮጵያ ህዝቦች ዛሬ በልማትና በዴሞክራሲ ባህል ግንባታቸው ላይ አተኩረዋል።

በተገኘው አስማማኝና ዘላቂ የሠላም ቁመና ታጅበውም ህዳሴያቸውን እውን ለማድረግ እጅ ለእጅ ተያይዘው ቆመዋል። በሠላማቸውና በመረጋጋታቸው ከፍታቸውን ለማረጋገጥ ዝግጁ ሆነዋል። እናም እዚህም ሆነ እዚያ ይህን የሠላምና የመረጋጋት መንገድ ለመዝጋት የሚፈልጉ የውስጥም ይሁን የውጭ ኃይሎችን ጨርሶውኑ አይታገሷቸውም።  

በአገራችን አንዳንድ አካባቢዎች ተፈጥሮ የነበረው ግጭት በአሁኑ ወቅት በህዝቡ፣ በፌዴራልና በክልል መንግሥታት የጥምረት ሥራዎች አንጻራዊ በሚባል ደረጃ  በቁጥጥር ሥር ውሏል። የሚቀሩ ሥራዎች ቢኖሩም፤ የህግ የበላይነት ግን እየተከበረ ይገኛል።  

በአሁኑ ወቅት በአንዳንድ አካባቢዎች የሚስተዋሉትን የሠላምና የመረጋጋት ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ከፀጥታ ኃይሎች ጋር ተባብረው በመሥራት ላይ ይገኛሉ። እርግጥ በየትኛውም አገር ውስጥ ሠላም እንዲሰፍን ከተፈለገ ያለ ህዝብ ተሳትፎ ምንም ዓይነት ውጤት ሊመጣ አይችልም። የሠላምን ዋጋ ዋነኛ መዛኙ ኃይል ህዝብ ነው። ህዝብ የሠላሙን ዋጋ የሚተምነው ጥቅሙን ጠንቅቆ ስለሚያውቅ ነው።

ሠላም የሚተመንበት አሊያም የሚሰፈርበት ልኬት አለው ሊባል አይችልም። ከግለሰብ የነገ ማንነት ህልም አንስቶ እስከ የአገር ህዳሴ እውን መሆን ድረስ ሠላም ዋጋው እጅግ የገዘፈ ነው። የአንድ አገር ሠላም የህዝቧቿ ሠላም ነውና።

በመሆኑም ዜጎች መብትና ግዴታዎቻቸውን ሲያውቁና ሌላውን ለማስተማር ሲነሳሱ የአገር ሠላም ይረጋገጣል። ልማትና ዕድገትም ይደረጃሉ፤ ዴሞክራሲያዊ እሴቶችም በዚያው ልክ እያበቡ ይሄዳሉ።

እዚህ ላይ ሊሰመርበት የሚገባ ቁም ነገር አለ። ይኸውም የአገርን ሠላምና ደህንነት መጠበቅ የመንግሥት ኃላፊነት ብቻ አይደለም — ዋነኛው ተዋናይ የሆነው የአገራችን ህዝብ ጭምር እንጂ። ህዝቡ በያለበት ሆኖ ሠላሙን ከጠበቀ ሠላምን ለማደፍረስ የሚሯሯጥ የትኛውንም ኃይል ከቁጥጥሩ ሥር ለማድረግ ብዙ አይቸገርም።  

የሠላምን ምንነት የሚገነዘብ ህዝብ ውስጥ ፀረ ሠላምነትን ማንገስ በእጅጉ ይከብዳል።  ህዝብ የሚገለገልባቸውን ማንኛውንም ዓይነት ንብረቶችንና የግለሰቦችን ሐብት ለማውደም አይቻልም — ሕዝቡ በራሱ ይጠብቃቸዋልና። ለፀረ ሠላም ኃይሎች ከንቱ ፕሮፖጋንዳ የማይፈታ የትኛውም ዜጋ ንብረቱ በምንም ዓይነት መንገድ እንዲወድም አይሻም።

በተለይ ወጣቱ እንደ ማንኛውም የኅብረተሰብ ክፍል ከሠላም ተጠቃሚ መሆን ይሻል። ተጠቃሚነቱን ማሳካት ያለበት ግን በህጋዊና ህጋዊ መንገድ ብቻ ነው። ወጣቱ አገራችን ውስጥ ከተገኙት የልማት ውጤቶች አቅም በፈቀደ መጠን ተጠቃሚ መሆን አለበት። ይሁንና ተጠቃሚነቱ ሊረጋገጥ የሚችለው በሠላማዊና ህጋዊ መንገድ እንጂ በሁከትና በብጥብጥ አለመሆኑን ማወቅ ይኖርበታል።

እርግጥ ለዴሞክራሲ ግንባታም ሆነ ለልማት መጠናከር ወሣኝ የሆነውን ሠላምን በጋራ ለማቆም መንግሥትን ጨምሮ ሁሉም አካል ሠላማዊ የውይይት ባህልን እየገነባ መሄድም ያስፈልጋል። ሠላምና ልማት ወዳዱ የኢትዮጵያ ህዝብ የፀረ ሠላም ኃይሎች እኩይ ሴራን ጠንቅቆ ያውቃል። ሠላሙን ለማናጋትና በአገሪቱ እየተመዘገበ ካለው ፈጣንና ተከታታይ ዕድገት በየደረጃው ተጠቃሚ እንዳይሆን የሚሹ አካላትን አይፈልግም።

ሠላምን ተፃርረው ኢትዮጵያ ውስጥ ችግር ለመፍጠር የሚባጁ ኃይሎች ፍላጎታቸው የሠላም አይደለም፤ የብጥብጥና የሁከት እንጂ። እቅዳቸው የመብት ተጠቃሚነት ሳይሆን የመብት አዋኪነትና የኪራይ ሰብሳቢነት እንጂ። ዓላማቸው ሁሉም በየደረጃው የሚጠቀምበትን ሥርዓት ለመፍጠር ሳይሆን የዜሮ ድምር ፖለቲካ መጫወትን መምረጥ እንጂ። ፍላጎታቸው የመከባበርና የመቻቻል ሳይሆን የጠባብነትና የትምክህተኝነት መስመር መከተል እንጂ። ስሜታቸው የነጻነት መንገድን መያዝ ሳይሆን የባርነት ቀንበር መጫንን እንጂ። ይህ ሁሉ ግን ከኢትዮጵያ ህዝብ የሚሰወር አይደለም። በመሆኑም አሁን የተገኘው ልማት በሠላምና መረጋጋት የመጣ መሆኑን ይበልጥ በማወቅ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ለዚሁ የሠላም አውድ መትጋትና እጅ ለእጅ መያያዝ ይገባዋል።

 

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy