Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የተስፋው ጉዞ በእናንተ ነው

0 286

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የተስፋው ጉዞ በእናንተ ነው

                                                      ደስታ ኃይሉ

የዛሬዎቹ ወጣቶች ከትላንቶቹ ይልቅ ይበልጥ ዕድለኞች ናቸሁ። ዛሬ በውድ የህዝብ ልጆች በተገኘ አስተማማኝ ሰላም ወጣቶች ትምህርታችሁን እየተከታተላችሁ ነው። የሚያውካችሁ ነገር የለም። ታላቁ መሪ አቶ መለስ ዜናዊ አዘውትረው ይነገሩ እንደነበረው “የልማት ዘበኛው ተወግዷል።” አሁን ጊዜው ሰርቶ ድህነትን ድል ማድረግ የሚያስፈልግበት ነው። መንግስት በምትፈጥሩት ስራ ተጠቃሚና የአገራችን የነገ ተስፋዎች እንድትሆኑ ፈንድ መድቧል። በዚህ ፈንድ ስራ ፈጣሪ መሆን ይገባችኋል።

እርግጥ ዛሬ የእናንተ ቀን ነው። ሌላ የማንም አይደለም። አገራችን ውስጥ እየተስፋፋ በሚገኘው ትምህርት ተጠቃሚ በመሆንም የኢትዮጵያ የነገ ተስፋዎች መሆናችሁን ማረጋገጥ አለባችሁ። ከሁሉም ነገር በላይ ደግሞ ይህን የማይገኝ መልካም አጋጣሚያችሁን በሁከትና በመናቆር ሊያጨልሙባቸሁ ከሚሹ ሴረኞች መታደግ ይኖርባችኋል።

ወጣቶች ሰላምን አጥብቀው መሻት አለባችሁ። ፀረ ሰላም ኃይሎቹ የሚፈልጉት የአገራችን ሀዝብ በአሁን ወቅት ያገኘውን ተጠቃሚነት እንዳያጣጥም መሆኑን በመገንዘብ ሴራቸውን በመመከት ወደ ልማት ስራቸው ላይ ማተኮር አለባቸው። እንደሚታወቀው ሁሉ ወጣቶች የዛሬ አፍላ የልማትና የዴሞክራሲ ኃይሎችና የነገ ሀገር ተረካቢ ዜጎች ናችሁ። ይህን የሚገነዘበው መንግስት በትምህርት የታነፀና የተገነባ አቅም እንዲኖራቸው ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ በመስራት ላይ ይገኛል።

የወጣቶችን ሁለንተናዊ ብቃት በማሳደግ በአገሪቱ የዴሞክራሲያዊ ስርዓትና መልካም ልማታዊ አስተዳደር ግንባታ እንዲሁም በኢኮኖሚ፣ ማህበራዊና ባህላዊ ልማት እንቅስቃሴዎች ውስጥ በተደራጀና በተቀናጀ አኳኋን የነቃና ግንባር ቀደም ተሳትፎ እንድታደርጉና ከውጤቱም በተገቢው መንገድ ተጠቃሚ እንደትሆኑ መንግስት ያላሰለሰ ጥረት እያደረገ ነው።

ይህን በማድረግም በአገሪቱ ወጣቶች አካበባቢ ከሥራ ስምሪት ጋር ተያይዞ የሚታየውን የተሳታፊነትና ፍትሐዊ ተጠቀቃሚነት ጥያቄ ለመመለስ እየጣረ ነው። እንዲሁም የሴቶችና የወጣቶች ፓኬጆች ትስስርና ተመጋጋቢነት ባለው ሁኔታ ተፈጻሚ እንዲሆን በንቃት በመስራት ላይ ይገኛል። በመሆኑም የተለያዩ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ልማት ዘርፎች የወጣቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ከግምት ውስጥ ያስገቡ እንዲሆኑ፣ ወጣቶች በህብረት ሥራ ማህበራት በመደራጀት የብድርና ቁጣባ አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየሰራ ነው።

በተለይም ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና ከቴክኒክ ሥልጠና ማዕከላት ተመርቀው የሚወጡ ወጣቶች ያገኙትን ዕውቀትና ክህሎት የወደፊት የአገራችን ተስፋ በሆኑ አምራች ዘርፎች ማለትም ግብርና፣ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎችና ዲጂታል ቴክኖሎጂ ላይ ተሰማርተው የወደፊት የአገራችን ልማታዊ ባለሃብቶች መፍለቂያ እንዲሆኑ ሁሉን አቀፍ ድጋፍ እየተደረገ ይገኛል። በዚህም በየክልላችሁ የስራ ዕድሎች እንዲፈጠርላችሁና ራሳችሁን ጠቅማችሁ አገራችሁንም እንድትጠቅሙ ካለጉት ጊዜያት በበለጠ ሁኔታ ዕቅድ ተይዟል።

በመንግስት በኩል ይህ ሁሉ ጥረት እየተደረገ የኢትዮጵያን ሰላም የማይሹ ወገኖች ግን ጥቃቅን ጉድለቶችን እየተከታተሉ በማራገብ እናንተን ለአመፅ ለማነሳሳት ያልጣሩበት ጊዜ የለም። ይህን እናንተን ከስራቸሁና ከትምህርታችሁ ለማሰናከል የሚደረግ ሴራን መገንዘብ ይኖርባችኋል።

እርግጥ አንድ መንግሥት ወይም የፖለቲካ ድርጅት በባህሪው ህዝባዊ ከሆነ፤ የሚያከናውናቸው ማናቸውም ተግባራት የህዝቡን ተጠቃሚነት ያማከሉ መሆናቸው ግልፅ ነው። የኢትዮጵያ መንግሥትም በባህሪው ህዝባዊና ልማታዊ በመሆኑ፤ ላለፉት 26 ዓመታት በአብዛኛዎቹ መስኮች ህዝቡን በየደረጃው ተጠቃሚ ማድረጉ የዚህ አገር ተስፋዎች ከሆኑት ወጣቶች የተሰወረ አይደለም።

ከ26 ዓመት በፊት በማንነታቸውም ይሁን በኑሯቸው አንገታቸውን ደፍተው ይሄዱ የነበሩት ወጣቶች፤ ዛሬ ቀና ብለው በአገሪቱ በመመዝገብ ላይ ከሚገኘው ፈጣንና ተከታታይ ዕድገት በኢኮኖሚው ላይ ባበረከተው አስተዋጽኦ መጠን በየደረጃው ተጠቃሚ በመሆን ወደ አዲስ ምዕራፍ እየገሰገሱ ናቸው። ለምሳሌ በእነዚህ ዓመታት ውስጥ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወጣቶች በተለያዩ የስራ መስኮች ተደራጅተው ተጠቃሚ መሆናቸውን መጥቀስ ይቻላል። በመሆኑም ወጣቶች በአሁኑ ወቅት የላቀ ተጠቃሚ ለመሆን ቁርጠኛ አቋም ይዘው ከመንግስት ጋር ተባብረው መስራት ያለባቸው ይመስለኛል።

እኔ እስከሚገባኝ ድረስ ከድህነት ጋር ፍልሚያ ገጥመው ተጠቃሚ እየሆኑ ያሉት ወጣቶች፤ በምንም ዓይነት ምክንያት ሁለንተናዊ የጥቅም ተጋሪነነታቸው የኋሊት ተጎትቶ እንዲሸረሸር አይፈልጉም። በፍፁም። ነገ ትልቅ የዕድገት ባለቤት ለመሆን ያለሙት የአገራችን ወጣቶች፤ ትኩረቱን ማድረግ ያለባቸው የትናንት ማንነታቸውን በስራ ለመቀየር ደፋ ቀና በማለት እንጂ፤ ለሁከትና ለብጥብጥ ዲስኩሮች ጆሮ በመስጠት አይደለም።

በመሆኑም እነርሱ ባህር ማዶ ሆነው ልጆቻቸውን በሰላም እያስተማሩ እዚህ ሀገር ውስጥ ያሉትንና ህይወታቸውን ለመቀየር በመትጋት ላይ የሚገኙትን ወጣቶች በእሳት ለመማገድ የሚሹ የሁከት ኃይሎችን በመመከት በስራቸው ላይ ብቻ ማተኮር ያለባቸው ይመስለኛል።

የአገራችን ወጣቶች በትንሹ ባለፉት ሁለት ዓመታት በተከሰቱት ሁከቶች ስለ እነዚህ ኃይሎች ባዶና የአሉባልታ አጀንዳ አራማጅነት እንዲሁም ስለ መንግሥት ትክክለኛነት የልማት አቅጣጫዎች የተገነዘቡ ይመስለኛል። እንደሚታወቀው ሁሉ መንግስት የወጣቶችን ተጠቃሚነት በጥልቅ ተሃድሶው ይበልጥ ለማረጋገጥ እንደሚሰራ ቃል ገብቷል።

እርግጥ የኢትዮጵያ መንግስት አደርገዋለሁ ብሎ ገቢራዊ ያላደረገው ምንም ዓይነት ነገር የለም—በየጊዜው እያደገ ከመጣው የህዝብ ቁጥር ጋር ዕድገቱ ሁሉንም ዜጎች ተጠቃሚ ካለማድረጉ በስተቀር። ያም ሆኖ አብዛኛውን ህዝብ ተጠቃሚ እያደረገ ነው።

ቀደም ባሉት ጊዜያት በአገሪቱ ውስጥ ድህነትን አቅም በፈቀደ መጠን በመቀነስ ህዝቡን በየደረጃው ተጠቃሚ እንደሚደርግ፤ ትምህርትን፣ ጤናን፣ የመሠረተ-ልማት አውታሮችን እንደሚያስፋፋ እንዲሁም ዴሞክራሲያዊ ስርዓቱ ስር እንዲሰድ አደርጋለሁ በማለት የገባቸውን የተስፋ ቃሎች ፈፅሟቸዋል። አስተማማኝ ሰላም በማረጋገጥ ረገድም የገባውን ቃል አላጠፈም። የህግ የበላይነትንም እያረጋገጠ ይገኛል። ታዲያ እነዚህን ዕውነታዎች ወጣቶቻችን አሳምረው እንደሚያውቋቸው ተስፋ አደርጋለሁ።

ከእነዚህ ተጨባጭና የማይታጠፉ ቃሎቹ በመነሳትም ወጣቶች በቅርቡ አገራችን ውስጥ  የተፈጠረውን ጊዜያዊ ችግር መንግሥት መስመር እንደሚያሲዘው ያመነ ይመስለኛል። ምክንያቱም በአሁኑ ወቅት በአንዳንድ የአገራችን ክፍል ተፈጥሮ የነበረውን ግጭት መንግሥት በቁጥጥር ስር እንዲውል በማድረጉ ነው። እርግጥ ባለፉት ጊዜያት ገዥው ፓርቲና መንግሥት የለውጥ አደራጅና ቀያሽ መሆናቸውን ወጣቶቻችን በሚገባ ስለሚያውቁ፤ ማናቸውም ጊዜያዊ ችግሮች የመፍቻቸው ቁልፍ ያለው በመንግሥትና በህዝብ እጅ እንጂ በወፍ ዘራሽ ሁከት አራማጆች አለመሆኑን የተገነዘቡት ይመስለኛል።

ያም ሆኖ ወጣቶች የዚህች አገር መመከያና ተስፋ እንዲሁም አገራችን የጀመረችው ተስፋ ሰጪ ጉዞ የሚመረኮዘው በእናንተ ላይ በመሆኑ ዓላማችሁን በተሰማራችሁባቸው የልማት መስኮች ላይ ማድረግ ይኖርባችኋል። ስራ ፈጣሪው በተመቻቸለት ሁኔታ እየተመራ በስራው ላይ፣ ተማሪውም የአገራችን የነገ ተረካቢና ገንቢ በመሆኑ ሰላምን ተመርኩዞ የልማት ተስፋነቱን ማረጋገጥ ያለበት ይመስለኛል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy