Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የተቋሙ ትንበያና መገለጫዎቹ

0 327

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የተቋሙ ትንበያና መገለጫዎቹ

ዳዊት ምትኩ

ሰሞኑን ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (IMF) አገራችን በ2010 ዓ.ም 8.5 በመቶ የኢኮኖሚ እድገት እንደምታስመዘግብ ተንብዩዋል። ታዲያ ለዚህ እድገቱ መገኘት ወሳኝ የሚባሉ ጉዳዩችንም አብሮ አንስቷል። በዚህም መሰረት ኢንዱስትሪ ፓርኮችን መስፋፋት፣ የውጪ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንቱ መጨመርና አገሪቱ በቅርቡ ያደረገችው የገንዘብ ምንዛሬ ለውጥ በዓመቱ ለሚመዘገበው የኢኮኖሚ እድገት ትልቅ ፋይዳ ጉዳዩች መሆናቸውን አውስቷል።

ይህ የተቋሙ ትንበያ መገለጫ፤ መንግስት ዛሬም እንደ ትናንቱ የሚከተላቸው ትክክለኛ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ውጤታማ መሆናቸውን፣ እድገቱን ለማፋጠን የሚሰጠው ቀጥተኛ አመራር ጠንካራ መሆኑን እንዲሁም የመንግስትን አመራር ተከትሎ ለዕድገቱ በመስራት ላይ የሚገኘው ታታሪው ህዝባችን በስራ ላይ እንደሆነ የሚያሳይ መሆኑን አመላካች ነው።

እንደሚታወቀው ሁሉ መንግስት በሁሉም የአገራችን አካባቢዎች የኢንዱስትሪ ፓርኮችን እየገነባ ነው። ግንባታቸው ተጠናቆ ወደ ስራ የገቡ ፓርኮችም አሉ። ይህ የመንግስት ተግባር በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዘመን ተግባራዊ እየተደረገ ያለ ተግባር ነው።

ፓርኮቹ የውጭ ቀጥተኛ በአዳዲስ ኢንቨስትመንቶችም ሆነ በነባር ኢንዱስትሪዎች ውስጥ የምርታማነት የጥራትና የተወዳዳሪነት ደረጃ እመርታና መዋቅራዊ ለውጥ እንዲያመጣ በከፍተኛ ደረጃ መንቀሳቀስ እንዲቻል የሚያደርጉ ናቸው። በልማት ዕቅዱ ዘመን በኢኮኖሚው ላይ የሚታይ መዋቅራዊ ለውጥን ለማስጀመር የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ በየዓመቱ ቢያንስ የ24 በመቶ ዓመታዊ አማካይ ዕድገት ማስመዝገብ ይኖርበታል። ይህ ማለት በ2012 ዓ.ም የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ በአጠቃላይ ኢኮኖሚው ያለውን ድርሻ ወደ ስምንት በመቶ ከፍ እንዲል ለማድረግ እየተሰራ ነው።

ስራው ሲጠናቀቅ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪው ድርሻ በአሁኑ ወቅት ከሚገኝበት በአራት እጥፍ እንዲያድግ በማድረግ ወደ መጀመሪያው የመካከለኛ ጉዞ መንገድ ለመድረስ ለታለመው ዕቅድ እስከ 18 በመቶ የማድረስ ግብን ያሳካል ተብሎ ይታመናል። አገራችን ለያዘችው የመካከለኛ ገቢ ራዕይን ለማሳካትም መደላድል ይፈጥራል።

እርግጥ መዋቅራዊ ለውጡን ገቢራዊ በማድረግ ረገድ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪው የኤክስፖርት ሚናው ሁነኛ ማሳያ ነው። ዛሬን ከነገ ጋር ብናስተያየው የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ አሁን ካለው ሁኔታ አኳያ ሲታይ ከጠቅላላው የኤክስፖርት ገቢ ከአስር በመቶ አይበልጥም። ይህን ለማሳደግ እየተሰራ ያለው ስራ የገንዘብ ተቋሙ እንዳለው በአገራችን ኢኮኖሚያዊ እድገት ላይ ለውጥ ያመጣል።

በገንዘብ ተቋሙ የተነሳውና ለተያዘው ዓመት ኢኮኖሚያዊ እድገት የሚያስገኘው የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ነው። የኢፌዴሪ መንግስት በሀገሪቱ መዋዕለ ንዋያቸውን በማፍሰስ፣ በኢንቨስትመንት ለመሰማራት ፍላጎት ያላቸው የውጭ ባለሃብቶችን ለመሳብ የተለያዩ ማበረታቻዎችን በማመቻቸት በሩን ከፍት በማድረግና በተለያዩ አለም አቀፋዊ መድረኮች ተጨባጭ ሁኔታውን በማስረዳት በርካታ የውጭ ባለሃብቶችን በመሳብ ላይ ነው። በዚህም የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን በመሳብ የውጭ ምንዛሬ እያገኘ ነው።

መንግስት በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች በተለይም በግብርና፣ በማኑፋክቸሪንግና ኢንዱስትሪ ዘርፎች የተሰማሩ የውጭ ባለሀብቶች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻቀበ መምጣት ችሏል።

አገራችን እየተከተለችው ባለው ምቹ የኢንቨስትመንት ምህዳር ነፃ የመሬት አቅርቦት መዘጋጀቱ፣ የአበባ ማምረቻ ስፍራዎች በመንገድ እና በኤሌክትሪክ እንዲተሳሰሩ መደረጋቸው፣ የታክስ እፎይታ ጊዜ መኖሩ በርካታ የውጭ ባለሃብቶች ወደ ሀገራችን እንዲሳቡ ዋነኛው ምክንያት ሆኗል ማለት ይቻላል። ይህም የአገሪቱን ኢኮኖሚ ከማጠናከር አኳያ የራሱን ሚና እየተጫወተ ነው።

መንግስት አገሪቱንና ህዝቦቿን ከድህነት ከኋላቀርነት ለማላቀቅ የነደፈው ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መስመር ተግባራዊ በማድረግ ተስፋ ሰጪ ዕድገት በማስመዝገብ ላይ እንደሚገኝ የውጪው ዓለምና ባለሃብቶቻቸው ሳይቀሩ እየመሰከሩለት ይገኛሉ። ከመመስከር ባለፈም፤ የሀገራችንን መፃዒ ዕድል ከወዲሁ በአንክሮ አጢነው በኢንቨስትመንት ዘርፍ ለመሳተፍ በልማት እግሮቻቸው ወደ ሀገራቸን እየተመሙ ነው።

በአገራችን ውስጥ እየደገ የመጣ፣ ተጠቃሚ እንዲሁም መካከለኛ ገቢ ያለው የህዝብ ቁጥር መጨመሩ፣ ፈጣን የከተሞች ዕድገት መታየቱና ሳቢ የኢንቨስትመንት አሰራር መኖሩ የውጭ ባለሃብቶችን እየሳበ ነው። እንዲሁም ሀገራችን በምስራቅ አፍሪካ ፈጣን ዕድገት እያስመዘገቡ ካሉ ሀገራት ውስጥ አንዷ ስለሆነችና እያደገ የመጣውን ፍላጎት ለማሟላት አቅም ያላት መሆኗ ባለሃብቶቹ ለሚሳተፉበት የኢንቨስትመንት ዘርፍ ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል። ይህም በተያዘው ዓመት ዘርፉ ለኢኮኖሚያችን ማደግ አንዱ ምክንያት እንዲሆን አስችሎታል።

የገንዘብ ተቋሙ ለያዝነው ዓመት ኢኮኖሚ ማደግ ሌላኛው ምክንያት አድርጎ ያቀረበው አገራችን በቅርቡ ያደረገችው የውጭ ምንዛሬ ለውጥ ነው። ይህ በተጠና ሁኔታ የተደረገው የምንዛሬ ለውጥ የአገርን ኢኮኖሚ የሚያሳድግ መሆኑ ግልፅ ነው። መንግስት የብር ምንዛሬው ከዶላር ጋር ያለው ለውጥ በ15 በመቶ እንዲቀንስ ያደረገው አስቦበትና የሚያመጣውን ኢኮኖሚያዊ ጥንካሬ ከግምት ውስጥ አስገብቶ ነው።

መንግስት ይህንን እርምጃ ሲወስድ በዋነኝነት እየተዳከመ ያለውን የኤክስፖርት ገበያ ለማጠናከር መሆኑ ይታወቃል። በአንድ አገር ውስጥ ኤክስፖርት ምርት ሊጠናከር ካልቻለ በውጭ ምንዛሬ ረገድ ችግር መግጠሙ አይቀርም። ይህም አገሪቱ ለልማት ጠቃሚ የሆኑ ነገሮችን ከውጭ እንዳታስገባ ያደርጋል። በተለይ አገራችን በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ የያዘችውን ትልም ለማሳካት እንዲህ ዓይነቶቹን እርምጃ መውሰድ ይኖርባታል።

እንደሚታወቀው ሁሉ ፈጣን ዕድገታችን፣ የመሠረተ ልማት ኘሮግራሞቻችንና የግል ኢንቨስትመንትና ንግድ ሥራዎች የሚፈልጉትን የውጪ ምንዛሪ በአስተማማኝ ሁኔታ ለማቅረብ እና በውጪ ዕርዳታና ብድር ያለን ጥገኝነት ለመቀነስ እንዲቻል በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን እቅድ ተይዟል፡፡

ኤክስፖርት ላይ ለመረባረብ የታቀደው ኢኮኖሚያችን በአገር ውስጥ ገበያ ብቻ ሳይታጠር በሰፊው የዓለም ገበያ ላይ ተመስርቶ በፍጥነት እንዲያድግ ለማድረግም ጭምር ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በዓለም ገበያ ገብተን ምርቶቻችንን በስፋት ለመሸጥ ያቀድነው ተወዳዳሪነታችንን ማጐልበት ያስፈልጋል። ይህን ለማድረግ ደግሞ የገንዘብ ምንዛሬን ማስተካከል ይገባል። ምንዛሬው በመስተካከሉም እነሆ በያዝነው ዓመት በኢኮኖሚው ላይ ለውጥ ያመጣ አንዱ ተግባር ሆኖ በዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም ላይ ተተንብዩዋል። እነዚህ የኢኮኖሚው እድገት መገለጫዎች መንግስት የሚከተላቸው የልማት ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ምን ያህል ትክክል እንደሆኑ፣ ፖሊሲዎቹን ለማስፈፀም የሚሰጠው ቀጥተኛ አመራር ምን ያህል አግባብነት ያለውና አገራችንንም ለመለወጥ የተስፋ ብርሃን መሆኑን የሚያረጋግጡ ናቸው።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy