የተፋሰስ ልማትና የመስኖ ስራ
ዋኘው መዝገቡ
በተፈጥሮ ሀብት የታደለና ሁሉንም የአየር ንብረት አቅፎ የያዘ መሬት በጋ ከክረምት የማይነጥፍ ወንዞች ባለቤቶች ሁነን ለዘመናት በድርቅና ረሀብ ስንጠቃ የኖርንበት ታሪክ ከእንግዲህ ዳግም ላይደገም እየተቀየረ ያለበት ዘመን ላይ ደርሰናል፡፡ ይሄንን የተጀመረ ስራ ጠንክሮ የማስቀጠሉ ኃላፊነትና ግዴታ ደግሞ የተተኪው ትውልድ ይሆናል፡፡
ሀገራችን በተለያዩ ዘመናት በቂ፣ በተለያዩ ሙያዎች የተማረና የሰለጠነ የሰው ኃይል ስላልነበራት ጭምር ሀገራዊ ልማትና የኢኮኖሚ እድገት ለማምጣት ፈተና ሁኖ ኖሯል፡፡ በድሕነት አቅሟ ያስተማረቻቸውና ታላቅ ተስፋ የጣለችባቸው ልጆችዋ ከድሮ ጀምሮ በብዛት ከሀገር ወጥተዋል፡፡ እነዚህ ወገኖች በሀገር ኖረው ያስተማራቸውን ቤተሰብና ድሀ ሀገራቸውን በማገልገል በሀገራቸው ሆነው በመስራት የኢኮኖሚ እድገትና ልማት ማምጣት ይችሉ ነበር፤ አልሆነም፡፡
የሕዝብን ኑሮ ማሻሻልና መለወጥ የሚታይና የሚጨበጥ ሀገራዊ ስኬት ማስመዝገብ ሲችሉ እውቀታቸውንና ጥበባቸውን ይዘው በመውጣት በአውሮፓ ከፍተኛ ተከፋይ በመሆን ይኖራሉ፡፡ በዚህ ረገድ እንደ ኢትዮጵያ የወላድ መሀን ተብሎ የሚጠራ ሀገር ያለ አይመስልም፡፡
በተለይ የሀገራችን የኢኮኖሚ መሰረት ተደርጎ ለዘመናት በኖርንበት የግብርናው ዘርፍ መሰረታዊ ለውጥ እየመጣ ቢሆንም ይሄንን ዘርፍ በላቀ ደረጃ ትርፋማና ውጤታማ በማድረግ ረገድ ዘመናዊ ግብርናን፤ የአፈር አያያዝን፤ የዘመናዊ መስኖ ልማት አጠቃቀምን በስፋት ማስተማር የሚችሉ የመስኩ ባለሙያዎች ዛሬም ካሉበት ሁነው ሀገራቸውን ማገዝ ይችላሉ፡፡
በቀድሞ ታሪካችን እኛ ባለብዙ ወንዞችና ኃይቆች ባለቤት ሆነን ስንራብ እልም ባለ በረሀ ውስጥ የሚኖሩ ሀገራት ደግሞ ችግር ብልሀትን ይፈጥራል እንዲሉ እዛው በረሀ ላይ ሰብል አብቅለው በምግብ ራሳቸውን ችለው ለሌሎችም ተርፈው ይኖራሉ፡፡ ዛሬ ላይ የእኛም ሁኔታ በዘመናዊ የመስኖ ልማት ስራ ስርነቀል በሆነ መንገድ እየተቀየረ ይገኛል፡፡
ሀገራችን በብዙ መልኩ ተፈጥሮ ሲበዛ የቸራት ብትሆንም ሳንጠቀምበት ኖረናል፡፡ ዛሬ ግን መጠቀም ለችግሮቹም መላና መፍትሄ ማግኘት ተችሎአል፡፡ ከተፈጥሮ ዝናብ ጥገኝነት ለመላቀቅ ዝናብ ባይዘንብም በድርቅና በረሀብ ስር ላለመውደቅ ብዙ አማራጮችን መመልከት የተቻለበት ግዜ ነው፡፡
የግብርና ባለሙያዎቻችን አርሶ አደሩንና አርብቶ አደሩ ባለበት ቦታ በመገኘት ለአመታት ስለመሬት አያያዝና አጠቃቀም፤ የመሬት መሸርሸር እንዴት እንደሚከሰትና እንዴትስ መከላከል እንደሚችሉ፤ ከባድ ዝናብ በሚዘንብበት ወቅት ውሀውን ጉድጓድ በመቆፈር ወደውስጥ እንዲሰርግ ማድረግ ያለውን ጠቀሜታ፤ ውሀን በሰፊ ቦታ ቆፍሮ በማጠራቀም ውሀ በማይኖርበት ሰአት እንዴት ለጓሮ አትክልት በመስኖ መጠቀም እንደሚችሉ ሁሉ በስፋት ተምረው ተግባራዊ አድርገውታል፤ ተጠቃሚም ሆነዋል፡፡
የውሀ ግድቦችን በስፋት በመስራት ለመስኖ ልማት በማዋል በጋ ከክረምት የማይነጥፍ ምርት እንዴት ማግኘት እንደሚችሉ በስፋት መማር በመቻላቸው ዛሬ በስፋት በተግባር ላይ እያዋሉት ይገኛሉ፡፡ ዛሬ እንደ በፊቱ በከባድ ዝናብ ታጥቦ የሚወሰድ መሬት የለም፡፡ በዘመቻ መልክ በሁሉም ክልሎች በተሰሩ እርከኖች አደጋውን መክላት ተችሎአል፡፡
እንዲያውም ቀድሞ ተራቁተው የነበሩ መሬቶች በተደረገው የአፈር መንከባከብና ጥበቃ መልሰው እጸዋት በማብቀል የአየር ንብረቱን መለወጥ ችለዋል፡፡ ያገጠጡ ተራሮችና መሬቶች በደን ተሸፍነዋል፡፡ ዛሬ ላይ በሀገር አቀፍ ደረጃ ልዩ ትኩረት አግኝቶ በመሰራት ላይ ያለው የተፋሰስና የመስኖ ስራ ከፍተኛ ለውጦችና ውጤቶችን ማስመዝገብ ችሎአል፡፡
በተለይ በበጋ ወራት ጠጣርና ደረቅ ሞቃታማ አየር በሚከሰትበት ወቅት ድርቅ በብዛት ይከተል የነበረ ቢሆንም ዛሬ ላይ መፍትሄው የተፋሰስ ልማትና የመስኖ ስራን በስፋት ማስፋፋት ሁኖ በመገኘቱ በሁሉም ክልሎች በዘመቻ መልኩ ብዙ ሺህ ሕዝብ በማሳተፍ ስራው በየአመቱ በመሰራት ላይ ነው፡፡
በበጋ ወራት የምናካሂደው የግብርና ዝግጀት በምግብ ራስን ለመቻል እየተገነባ ላለው ሀገራዊ አቅም ጠንካራ መደላድል ይፈጥራል፡፡ የመስኖ ልማት ከዝናብ ጥገኝነት በማላቀቅ ረገድ ድርቅን የመቋቋም አቅም ከማስገኘቱም በላይ የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ የዜጎችን ለረሀብ ተጋላጭነት ሙሉ በሙሉ ያስወግዳል፡፡ ከዚህ አንፃር አገራችን በመስኖ ልማት ረገድ የላቁ ውጤቶችን እያስመዘገበች ትገኛለች፡፡
ቀድሞ በአርብቶ አደርነት ይተዳደሩ የነበሩ አካባቢዎች ሰፋፊ የውሀ ግድቦችን በመስራት በመስኖ ልማት ተጠቃሚ ሁነው በተረጋጋ ሰፈራ/መንደር መኖር፣ ማምረትና መሸጥም ጀምረዋል፡፡ ለዚህም የአፋርና የሶማሌ ክልል አርብቶ አደሮች አሁን ያሉበት ሁኔታና የደረሱበት የአኗኗር ዘይቤ በማስረጃነት ተጠቃሽ ናቸው፡፡
የመስኖ ልማት ውሀን መጥኖ እንደአስፈላጊነቱ በመጠቀም ለተፈለገው የአትክልትና የሰብል ልማት በማዋል ረገድ ብክነትን በመከላከል ውጤታማ ስራ እንዲሰራ እንሰሳት በውሀ ማጣት ለችግር እንዳይጋለጡ ያደርጋል፡፡ አርሶ አደሩም ሆነ አርብቶ አደሩ በመስኖ የሚያለማው መሬት በአቅራቢያው በመገኘት ስለሆነ ሩቅ ተጉዞ ጉልበቱን አያባክንም፡፡ በመስኖ ልማት የሀገራችን አርሶአደርና አርብቶአደር ዛሬ እየተጠቀመ ቢሆንም ወደፊት በስፋት ተጠቃሚ የሚሆንበት እድል ከፊቱ መኖሩ ደግሞ መጪውን ጊዜ የበለጠ ብሩህ ያደርገዋል፡፡
ከበርካታ መረጃዎች መረዳት እንደሚቻለው በመስኖ ልማት አጠቃቀም ረገድ በሀገራችን የተመዘገበው ለውጥ ግዙፍ ነው፡፡ መንግስት በቅርቡ ይፋ ያደረገው የመስኖ ልማት ካርታ ተጠቃሚነት የመስኖ ስራ እንዲሰፋ እንዲያድግ ከማድረጉም በላይ በምግብ ዋስትና ራሳችንን ለመቻል እንዲሁም ድርቅን ለመከላከል ለሚደረገው ብሔራዊ ትግል ከፍተኛ እገዛ ያደርጋል፡፡ ለዚህም ነው ለመስኖ ልማት እጅግ ከፍተኛ የሆነ ትኩረት በመንግስት በኩል የተሰጠው፡፡
ባጠቃላይ፣ ሀገራችን የምግብ ፍጆታዋን በራስዋ ለመሸፈን በምታደርገው ጥረት ውስጥ ከፍተኛውን ሚና እየተጫወተ ያለው የመስኖ ልማት ነው፡፡ በቂ የምግብ ፍጆታ እንዲኖር፤ በየግዜው እያሻቀበ የሚሄደውን የምግብ ዋጋ ንረት ማረጋጋት እንዲቻል እየተደረገ ያለውም በመስኖ ልማት ውጤቶች/ምርቶች ነው። የወጣቶቻችን ተጠቃሚነትም በቃላሉ የሚታይ አይደለም። እስከ አሁን በመስኖ ልማት በተሰሩት ስራዎች ወጣቶቻችን በከፍተኛ ደረጃ ተሳታፊ በመሆን ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ በተለያዩ ፕሮጀክቶች በመሳተፍ አትክልቶችን የማልማትና ከገበያም ጋር የማስተሳሰር ስራ እየሰሩ ይገኛሉ፡፡ አንደኛው የመስኖ ልማት ፋይዳ ለወጣቱ ሰፊ የስራ እድል የፈጠረ መሆኑ ሲሆን በሁለተኛ ደረጃም ከዚሁ ስራ የሚያገኙት ገቢ ለራሳቸውና ለቤተሰባቸው መተዳደሪያ መሆኑ የሚበረታታ ነው፡፡ በመሆኑም፣ የመስኖ ልማት ስራ በዘመናዊ የቴክኖሎጂ መሳሪያዎች እየታገዘ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ማድረግ አማራጥ የሌለው ተግባር ይሆናል።