Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የትምህርት ማዕዶች ክራሞት

0 376

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የትምህርት ማዕዶች ክራሞት

                                                          ታዬ ከበደ

በማንኛውም አገር ውስጥ ዩኒቨርስቲዎች የዕውቀት መገብያዎች፣ የሰላም ደሴቶችና የቀለም ቀንዶች ናቸው። የእኛ አገር ሁኔታም ከዘህ የተለየ አይደለም። የአገራችን ዩኒቨርሲቲዎች የሰላም ደሴቶችና የትምህርት ማዕዶች ናቸው። ቀደም ሲል በአንዳንድ ዩኒቨርስቲዎች ውስጥ የነበሩት አለመረጋጋቶች ዛሬ ተወግደው ዩኒቨርስቲዎቹ ወደ ተረጋጋ የመማር ማስተማር ሂደት ውስጥ ገብተዋል።

አሁን ያለው የዩኒቨርስቲዎቹ ድባብና ክራሞት ሰላምና መረጋጋት የታየበትና የመማር ማስተማር ሂደቱም የተጠናከረበት ሁኔታ ነው። በየዩኒቨርስቲዎቹ ውስጥ የመማር ማስተማር ሂደቱ እንዲቀጥል መንግስት ከህብረተሰቡ ጋር አንድ ላይ ሆኖ በመስራቱ ነው። ይህ የጋራ ጥረት በአጠቃላይ የሰላምና መረጋጋት ስራዎች ውስጥም ይበልጥ ተጠናክሮ መታየት ይኖርበታል።

በየዩኒቨርስቲዎቹ ጥረቱ ስኬታማ ሊሆን የቻለው ህብረተሰቡ ለሰላም ካለው ቀናዒ አስተሳሰብ መሆኑና መንግስትም የተማሪዎቹን ጥያቄዎች ለመመለስ ባደረገው ሰፊ እንቅስቃሴ ነው። በአሁኑ ወቅት መንግስት ለተማሪዎች ጥያቄዎችን ተገቢውን ምላሽ እየተሰጠ ነው። በዚህም ሳቢያ በአሁኑ ወቅትም አዳዲስ ዩኒቨርስቲዎች ሳይቀሩ ሰላማዊ ትምህርት ጀምረዋል። ይህም የትምህርት ማዕዶቹ የሰላም ደሴት ለመሆናቸው ማረጋገጫ ይመስለኛል።

እርግጥ መንግስት በዩኒቨርስቲዎቹ ውስጥ የመማር ማስተማር ሂደቱ እንዲስተጓጎል ባደረጉ አካላት ላይ የህግ የበላይነትን ለማንገስ እንደሚሰራ ገልጿል። ተማሪዎችን ወዳልተፈለገ የሁከት መንገድ የመሩ ወገኖችና የአስተዳደር ሰራተኞች በአገሪቱ የህግ ማዕቀፍ ውስጥ እንዲቀጡ ለማድረግ ታስቧል። ይህም የትኛውም አካል ህግና ስርዓትን ተላልፎ እስከተገኘ ድረስ ተጠያቂ መሆኑን የሚያመላክት ነው።

እንደሚታወቀው ሁሉ በፌዴራልም ይሁን በክልሎች ውስጥ የትኛውም አካል ከህግ በላይ ሊሆን አይችልም። ከተጠያቂነት አኳያ የህግ የበላይነት በሁሉም አካባቢዎች የግድ ገቢራዊ መሆን ይኖርበታል። የህግ የበላይነትን ለማስጠበቅም የተጠያቂነት አሰራር ከምንግዜውም በላይ መጎልበት ይኖርበታል።

የህግ የበላይነት ልዕልና ሊጠበቅ ይገባል። የህግ የበላይነት ልዕልና ካልተጠበቀ በሀገሪቱ የሚረቀቁ ማናቸውም ህጎች በሚፈለገው መጠን ገቢራዊ ሊሆኑ አይችሉም። ህጎች በሚፈለገው መጠን ገቢራዊ ካልሆኑና በቸልታ የሚታለፉ ከሆኑ የዜጎች መብቶች ሊሸራረፉ ይችላሉ። የመብት መሸራረፎች ደግሞ አንዱ እንዳሻው እንዲፈነጭ የሚያደርገው ሲሆን፤ ሌላው ደግሞ ህግና ስርዓትን አክብሮ እንዲንቀሳቀስ ያደርገዋል።

ይህም ህግና ስርዓትን የሚያከብረው ዜጋ ሌላውን በመመልከት ወደ ተሳሳተ መንገድ ሊያመራ ይችላል። በመሆኑም ይህን ችግር ለመቅረፍም የህግ የበላይነት ልዕልና ገቢራዊ መሆን አለበት። በመሆኑም ህግና ስርዓትን የማስከበር ተግባር በህግ አስፈፃሚው አካል በሚፈፀምበት ወቅት የተለየ ትርጓሜ ሊሰጠው አይገባም። ህግን ማስከበር የየትኛውም ስርዓት የውዴታ ግዴታ ነው።

የህግ የበላይነትን መፃረር ስርዓት አልበኝነትን የሚፈጥር ከመሆኑም ባሻገር፤ ህጎች ለሁሉም ዜጎች እኩል እንዳይሰሩ ያደርጋል። እናም ‘ሁሉም ሰው በህግ ፊት እኩል ነው’ የሚለውን ህገ መንግስታዊ መርህ ገቢራዊ ለማድረግ የህግ የበላይነት በማያሻማ ሁኔታ መረጋገጥ ይኖርበታል።

የህግ የበላይነት መከበር ለሀገር ሰላምና መረጋጋት ብሎም ልማትን ለማሳለጥ ቁልፍ ሚና ይኖረዋል። ቀደም ሲል እንደጠቀስኩት የህግ የበላይነት ከሌለ ሰላም የሚባልን ነገር ማሰብ አይቻልም። ሰላም ከጠፋ ደግሞ ስለ ልማትና ዴሞክራሲ ማሰብ አይቻልም። ፀረ-ልማትዊነትና ፀረ-ዴሞክራሲያዊነት ቦታውን ይረከባሉ። ይህ ሁኔታ ደግሞ እንደ እኛ ሰላምን፣ ልማትንና ዴሞክራሲን የህልውናው ጉዳይ ላደረገ ሀገር አሜኬላ እሾህ መሆኑ አያጠያይቅም።

እርግጥ ኢትዮጵያ የጀመረችው የዕድገትና የዴሞክራሲ ሥርዓት ባህል ግንባታ ሂደት ስኬታማ ሆኖ እንዲቀጥል፤ አስተማማኝ ሰላም የሰፈነበት ምህዳርን መፍጠር የግድ ነው። ምክንያቱም አገራችን ፈጣን ልማትን ማምጣትና ከተመፅዋችነት መላቀቅ ብሎም ዴሞክራሲን መገንባት የሞት ሽረት ያህል የህልውና ጉዳይ አድርጋ ስለያዘችው ነው። ታዲያ ሰላምን በማረጋገጥ ሂደት ውስጥ ለብሔራዊ ደህንነቷ ስጋት የሆኑ እንቅስቃሴዎችን መከላከልና መቆጣጠር ያስችላት ዘንድ የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ የሚኖርባት ይመስለኛል። ይህ አሰራር በየኒቨርስቲም ይሁን በአርሶ አደር አሊያም በመንግስት ስራ አስፈፃሚ መስሪያ ቤትይም ይሁን ግለሰብ ላይ ተፈፃሚ የሚሆን ነው።

እዚህ ላይ በአገራችን ዩኒቨርስቲዎች ውስጥ የሚገኙ ተማሪዎች መገንዘብ ያለባቸው ዕውነታ አለ። ይኸውም የአገራችን ፌዴራላዊ ስርዓት የግጭቶች ምክንያት ሊሆን የማይችል መሆኑን ነው። ምክንያቱም ሥርዓቱ ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት እንዲጎለብትና እንዲያብብ በአጠቃላይ ላለፉት 26 ዓመታት በተለይም ባለፉት 10 ዓመታት በርካታ ተግባራቶችን ሲያከናውን የነበረና በዚህም አበረታች ውጤት ያመጣ በመሆኑ ነው።

ያም ሆኖ በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ውስጥ እውን በመሆን ላይ የሚገኘው ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነትን የሚፃረሩ ተግባራትን ጠንክሮ ማስወገድ ይገባል። ለዚህ ደግሞ የትምህርት ማዕዶቹ ውስጥ የሚገኙት ተማሪዎች ግንባር ቀደም ሚና ሊኖራቸው ይገባል።

እንደሚታወቀው ሁሉ ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት የሀገራችን ህዝቦች እሴት እየሆነ ነው ማለት ይቻላል። ይህ እሴት የሀገራችንን አንድነት በማጠንከር ኢትዩጵያዊነት እንዲያብብ እያደረገ መሆኑን ነው። የዩኒቨርስቲ ተማሪዎቹ ይህን ኢትዮጵያዊ ባህል በማጎልበትና ይበልጥ ስር እንዲሰድ አስፈላጊውን ርብርብ ማድረግ አለባቸው።

ዛሬ በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታም የተተገበረው ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት ፍሬ ማፍራት ችሏል። ምክንያቱም ፅንሰ ሃሳቡ ከሌሎች ብሔሮችና ብሔረሰቦች ጋር በሰላም የመኖርና ችግርንም በውይይት ለመፍታት የሚያስችል ማህበረሰባዊ ግንኙነትን በብቸኝነት መከተል ስለሆነ ነው።

ዩኒቨርስቲዎቻችን ደግሞ የዚህ እውነታ መገለጫዎች ናቸው። የብሔር ብሔረሰቦች አመላካቾች ናቸው። ዛሬ ‘የእገሌ ብሔር ዩኒቨርስቲ ይገባል፣ የእገሌ ደግሞ አይገባም’ የሚባልበት ዘመን አይደለም። ያንን ከፋፋይ ዘመን የዛሬዎቹ ተማሪዎች አያቶችና አባቶች በከፈሉት መስዕዋትነት አልፈውታል።

ይህ ትውልድ ዛሬ ያለ አንዳች ስጋትና መሳቀቅ በየትምህርት ማዕዶቹ ላይ ተገኝቶ ትምህርቱን የመከታተለ ዕድል አግኝቷል። ይህን ዕድል በአንዳንድ የራሳቸው አጀንዳ ባላቸው ሃይሎች ማስነጠቅ የለበትም። ሁከትን ለሚፈጥሩ ወገኖች መሳሪያ ሆኖ ራሱን እንደ ጧፍ መንደድ የለበትም። እናም አንገቱን ቀና አድርጎ የዚህች አገር መመከያና ኩራት መሆኑን ማሳየት የሚኖርበት ይመስለኛል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy