Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የአንበሣውን ድርሻ ለህዝብ

0 284

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የአንበሣውን ድርሻ ለህዝብ

ወንድይራድ ኃብተየስ

ኢትዮጵያ ውስጥ ዛሬ አብዮት ተቀጣጥሏል። የጥልቅ ተሃድሶ መንገድ። መንግሥት ራሱን ከሕዝብ ፍላጎት ጋር ለማስተካከል ያስችሉኛል የሚላቸውን ርምጃዎች በቅደም ተከተል መውሰድ ተያይዟል። የተሻሉ አስፈጻሚዎች ናቸው የሚላቸውን ወደ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊነት አምጥቷል። መልካም ተሞክሮ ያላቸውንም ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ የሥራ ኃላፊነት አሸጋሽጓል። ዜጋው ህዝቡ በሚፈልገው ልክ ለውጥ ለማስመዝገብ ቁርጠኝነቱን አሳይቷል። መንግሥት አዳዲስ  አስፈጻሚዎችን  ወደ  ከፍተኛ የመንግሥት ሥልጣን ማምጣቱ የቀድሞዎቹ አስፈጻሚዎች ህዝብ በሚፈልገው መጠንና ፍጥነት ለውጥ አላመጡም በሚል ምክንያት እንጂ እነዚህ ግለሰቦች ምንም ዓይነት ተጨባጭ ለውጦችን ማስመዝገብ አልቻሉም በሚል ሁኔታ እንዳልሆነ ሁሉም ይገነዘባል የሚል እምነት አለኝ።  

ኢትዮጵያ ባለፉት 26 ተኩል ዓመታት በልማት ብቻ ሳይሆን በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ተጨባጭ ሊባሉ የሚችሉ ለውጦችን አምጥታለች። ይህም ውጤት የመጣው በጥልቅ ተሃድሶው ከኃላፊነታቸው በተነሱ አስፈጻሚዎች ጥረት ጭምር መሆኑን ማሰብ ተገቢ ይሆናል። እነዚህ አካሎች የአገራችን ባለውለተኞች ናቸው። ይህንንም መዘንጋት የለብንም። በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ግን አንዳንድ ጽንፈኛ ግለሰቦችና ፖለቲከኞች የቀድሞዎቹን አስፈጻሚዎች በተመለከተ የሚሰነዝሯቸው አስተያየቶች እጅጉን የወረዱና ሚዛን የማይደፉ ሆነው አግኝቼያቸዋለሁ። ለማንኛውም በዛሬው መጣጥፌ አትኩረት የምሰጠው በነዚህ የወረዱ አስተያየቶች ዙሪያ ላይ ባለመሆኑ በዚሁ ብንተላለፍ ምርጫዬ ነው።

ዛሬ በግልጽ እንደሚታየው የአገሪቱ ህዝቦች ፍላጎት በእጅጉ ጨምሯል። የጠያቂነት መንፈሱም እንዲሁ ጎልብቷል። በጥቅሉ መብቱን ጠያቂ ኅብረተሰብ መፈጠሩ በራሱ  ስኬት ነው። በአንድ አገር ጠያቂ ኅብረተሰብ መፈጠሩ በዚያች አገር የዴሞክራሲ ሥርዓት ስለመኖሩ አንዱ ማሣያ ነው።  በእርግጥ ኢትዮጵያ ውስጥ በአሁኑ ወቅት የመልካም አስተዳደር ችግሮች መኖራቸው እውነታ ነው። እነዚህ ችግሮች ይቃለሉለት ዘንድ ጠያቂ ዜጋና ምላሽ ሰጪ መንግሥት መኖሩም በአንድ ፊናው በዚህች አገር ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መኖሩን አመላካች ጭምር የሚያሳይ ነው። በአሁኑ ወቅት የኢፌዴሪ መንግሥትን የሚመራው ኢሕአዴግም በኅብረተሰቡ የተነሱ ጥያቄዎችን አምኖ እየተቀበለና በግልጽ ቋንቋ ለጥፋቱ ይቅርታ በመጠየቅ ራሱን የማስተካከል ርምጃዎችን ለመውሰድ ቃል ገብቷል። ተግባራዊ ለውጦችን በተጨባጭ ለማሳየትም አቅጣጫዎችን አስቀምጧል። በግልጽ ቋንቋም ለተግባራዊነታቸው ያላሰለሰ እንቅስቃሴ እንደሚያደርግ ለሕዝብ አሳውቋል።   

ቀደም ብዬ ለማነሳሳት እንደሞከርኩት አዲሶቹ የሥራ ኃላፊዎች የባለፈውን አስፈጻሚዎች መልካም ተሞክሮዎች በመውሰድ የታዩ ደካማ ጎኖችን በማረም አገራችንን ወደተሻለ ከፍታ ማውጣት ይጠበቅባቸዋል። የቀድሞዎቹን አስፈጻሚዎች በማጣጣል አዳዲሶቹን አስፈጻሚዎች ደግሞ ተዓምራዊ ለውጥ እንደሚያመጡ አድርጎ ተስፋ መጣል ሥነ ልቦናዊ ጫናን ያስከትላልና በተገቢው…በተገቢው እንነጋገር።

በእርግጥ መንግሥት የተሻለ አፈጻጸም ያስመዝግባሉ ያላቸውን ሾሟል። ከቦታ ቦታም አሸጋሽጓል። ተጠያቂ የሚሆኑ ካሉም በህግ አግባብ ተጠያቂ እንደሚያደርግ አሳውቋል።  ይህ ሁኔታ በኢሕአዴግ ዘንድ አዲስ አሠራር አይደለም።  የቆየ ተሞክሮው ነው። ያጠፉ ከፍተኛ ባለሥልጣናቱን ሳይቀር ተጠያቂ ያደርጋል። በዚህ አቋሙ ከጥቂት የዓለማችን ፓርቲዎች ተርታ እንደሚያሰልፈው በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል። ከሰሞኑ የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ያሳለፋቸውን ውሣኔዎችና ያስቀመጣቸውን አቅጣጫዎች መታዘብ ይቻላል። ያጠፉ ከፍተኛ አመራሮቹን እሥር ቤት ወርውሯል። የግንባሩን መሥራች  አንጋፋ ታጋዮችን ሳይቀር በጥፋታቸው ተጠያቂ አድርጓል። ዛሬም ይህ የቆየው ነባሩ ልምዱ እንደቀጠለ ነው። ይህ አሠራሩ የጎለበተና የነገሰበት ነው።

አንዳንዶች መንግሥት በላይኛው አስፈጻሚ ላይ እየወሰደ ያለውን ርምጃ  ከህዝብ ጋር ቀን ከቀን የሚያገናኙ የታችኛው አስፈጻሚ ድረስ ሊያወርደው ይገባዋል ሲሉ ይደመጣሉ። በእርግጥም ተገቢነት ያለው አስተያየት ነው። መንግሥት  ከአገር አጠቃላይ ብሔራዊ ጥቅም ይልቅ የራሳቸውንና የቢጤዎቻቸውን ጥቅም ብቻ ለሚያስቀድሙ አንዳንድ የወረዳና የቀበሌ ፈጻሚዎች ሳይቀር ምህረት አያደርግም። በራሳቸው የማይተማመኑና በፅናት የሚቆሙለት ሕዝባዊ ዓላማ የሌላቸው ራስ ወዳዶች፣ ሕዝብን በመከፋፈል፣ የህዝብን ጥቅም ችላ በማለት በየቦታው ችግር ሲፈጥሩ የነበሩትን በየደረጃው ያሉ  አስፈጻሚዎች በጥልቅ ተሃድሶው ተነቅሰው ይወጣሉ።    

በጥልቀት መታደስ ዋነኛው ዓላማ መነሻና መድረሻ የመንግሥት ሥልጣን ለህዝብ አገልግሎት ብቻ እንዲውል ማድረግ ነው። በጥልቀት መታደስ ስም  የሚካሄዱ  የግለሰቦች ለውጥ ለጥፋተኞችና ለኪራይ ሰብሳቢዎች መደበቂያ ጉድጓድ መቆፈሪያ እንዲሁም መልካሞችን ማጥቂያ መሣሪያ እንዳይሆንም መንግሥት መጠንቀቅ ይኖርበታል። በየመድረኩ ለህዝብ ጥቅም ዋስ ጠበቃ እንደሆኑ ራሳቸውን ለማቅረብ የሚሞክሩ የመድረክ አንበሦችን አካሄድ መንግሥትና ህዝብ ሊነቃባቸው ይገባል። ኅብረተሰቡ በተለይ በቅርበት የሚያውቃቸውን አስመሳይ ፈጻሚዎችንና አስፈጻሚዎችን አሁን በቅርቡ እስከታች በሚዘልቀው ጥልቅ ተሃድሶ ሂደት መለየት ይኖርበታል።

የመንግሥትን የጥልቀት መታደስ መርህ ኅብረተሰቡም በአግባብ ተረድቶ በባለቤትነት መንፈስ ቀጥታ ሊሳተፍበት ይገባል። ይህ ካልሆነ የመንግሥት ጥረት ብቻ በጥልቀት የመታደስ ሂደት ውጤት ይመጣል ብሎ ማሰብ ይከብዳል። ኢሕአዴግ በሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ደረጃ ራሱን በቁርጠኝነት ውስጡን ለማፅዳት እንደተናሳ ሁሉ ኅብረተሰቡም ከመንግሥት ጎን መሰለፍ ይኖርበታል።  ህዝብና መንግሥት  በቅርበት በመሥራት በቅርቡ የታዩ ችግሮችን መቅረፍ ካልቻሉ አገራችን  ዳግም ልትመለስ ወደማትችልበት ችግር  ውስጥ መግባቷ ጥርጥር የለውም።

በጥልቅ ተሃድሶው  የሕዝብ ቅሬታና ብሶትን መነሻ ማድረጉ መልካም ጅምር ነው። በጥልቅ ተሃድሶው ሂደት የግለሰቦችን በቡድንና በኔት ወርክ የመተሳሰር የጥቅም ግንኙነቶችን በመበጣጠስ የመንግሥት አሠራርን ለሕዝብ ግልጽና ተጠያቂነት እንዲኖረው በማድረግ ተጠያቂነት ያለው አሠራርን ማንገስ ተገቢነት ይኖረዋል። የመንግሥት አሠራርን ግልጽና ተጠያቂነት እንዲኖረው ከሚያደርጉት ነገሮች መካከል አንዱና ዋነኛው ደግሞ ሚዲያው ነው። የአገራችን ሚዲያዎችም በጥልቀት መታደስ ይኖርባቸዋል። ፐብሊክ ሰርቫንቱም ሆነ ሚዲያው የህዝብንና የአገርን ጥቅም ታሳቢ በማድረግ መሥራት ይኖርባቸዋል። ከሚያራምዱት ጽንፍ ከወጣ አዘጋገብ  ታርመው ወደቀልባቸው ቢመለሱ እላለሁ።

ዛሬ ላይ በአዲሲቷ ኢትዮጵያ የሚያስፈልጉን ሚዲያዎች የመንግሥት ጠንካራ ጎኖች የበለጡ እንዲጎለብቱ በማድረግ እንዲሁም ድክመቶቹንም በአግባብ በመተቸት ማስተካከያ እንዲደረግባቸው በማድረግ የአገራችንን የለውጥ ጉዞ ለማፋጠን የበኩላቸውን ሚና ቢጫወቱ መልካም ይሆናል። ታዲያ ይህ ሲሆን ነው በጥልቀት መታደስ እውን የሚሆነው፣ የህዝብ ተጠቃሚነትም የሚረጋገጠው። አገርም ወደፊት የሚራመደው።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy