Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የጉብኝቱ አንድምታ

0 229

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የጉብኝቱ አንድምታ

ዳዊት ምትኩ

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ፣ በአፍሪካና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተደማጭነት ያለት አገር ናት። አገራችን ዛሬ ሁሉም የዓላማችን ክፍሎች የሚያደምጧት ሆናለች። በተለይም በምትከተለው ለማንም የማይወግን የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ተሰሚነቷ ጨምሯል። በመካከለኛው ምስራቅ ላይ ያላት ሚናም እየጨመረ ነው።

ሰሞኑን የኳታር ኤታማዦር ሹም ጉብኝት ኢትዮጵያ ከወታደራዊ ጉዳዩች ውጭ በኢንቨስትመንትና በንግድ ረገድ አገራችን ከመካከለኛው ምስራቅ አገራት ጋር ያላት ጠንካራ ግንኙነት አንዱ ማሳያ ይመስለኛል። የኳታርና የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንትና ንግድ በአሁኑ ወቅት ያለበት ደረጃ አርኪ የሚባል ነው። ከሌሎች የመካከለኛው ምስራቅ አገራት ጋር ያላትም ግንኙነት በተመሳሳይ ደረጃ ላይ ይገኛል።

የኤታማዦሩ ጉብኝት በዋነኛነት ያጠነጠነው ከወታደራዊ ትብብር በመለስ ባሉት የኢንቨስትመንትና የንግድ ግንኙነትን ከማጠናከር አኳያ ነው። ይህ የንግድና የአንቨስትመንት ቁርኝት ደግሞ አገራችን ከማንኛው አገር ጋር የምታደርገውና ድህነትን ለመቅረፍ የምታደርገው ጥረት ማሳያ መሆኑ ግልፅ ነው።

እንደሚታወቀው የአገራችን የውጭ ግንኙነት በመርህ ላይ የተመሰረተ ነው። መርሁ አገራችን በሁለትዮሽ መንገድ ከየትኛውም ሀገር ጋር የምታደርገው ግንኙነት ተባብሮ በማደግ፣ ያላትን የተፈጥሮ ሐብት እጅ ለእጅ ታይዞ በመጠቀም በጋራ ለማደግ ያለመም ነው። ማንኛውም የዚህ ፅሑፍ አንባቢ እንደሚያውቀው ሀገራችን የእርስ በርስ ግጭትና ስር የሰደደ ድህነት ተምሳሌት ተደርጋ ትታወቅ ነበር።

ታዲያ በዚህ አሳፋሪና መጥፎ ምሳሌነት የተሳለችው ኢትዮጵያ፤ ካለፉት 26 ዓመታት ወዲህ ገፅታዋን በመለወጥ ላይ ትገኛለች። የኢፌዴሪ መንግስትና መላው ህዝቦቿ አንድነት ፈጥረው በእነዚህ ዓመታት ባከናወኗቸው ዘርፈ ብዙ ተግባራት በዓለም አቀፉ መድረክ በአዲስ ገፅታ መታየት ጀምራለች።

በተለይ ላለፉት 10 ዓመታት በኢትዮጵያ መንግስትና ህዝብ ያላሰለሰ ጥረት ሀገራችን ውስጥ ጠንካራ፣ ፈጣንና ተከታታይ የኢኮኖሚ ዕድገት እየተመዘገበ ከመሆኑም በላይ፤ ሀገራችን በዓለም አቀፍ የፖለቲካና ዲፕሎማሲ መድረኮች ተሰሚነቷ እየጎለበተ መጥቷል። ታዲያ ሀገሪቱ እነዚህን ስኬታማ ድሎች ለመቀዳጀት የቻለችው በተለያዩ ዘርፎች ተቀርፀው ተግባራዊ በተደረጉ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች አማካኝነት መሆኑ ከማንም የተሰወረ አይደለም።

በሀገሪቱ ውጤታማ ከሆኑት ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ውስጥ የውጭ ጉዳይና የሀገራዊ የደህንነት ፖሊሲና ስትራቴጂ አንዱ ሲሆን፤ በእኔ እምነት በዚህ ፖሊሲና ስትራቴጂ ውስጥ የተመለከተውና ከሀገራት ጋር የሚደረገው የሁለትዮሽ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ዘርፍ በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀስ ነው። ይህ ዘርፍ የሀገራችንን ተፈላጊነት ያጠናከረና ልማታዊ ዲፕሎማሲውን ከፍ በማድረግ ላይ ይገኛል።

ይህን አባባሌን ለማረጋገጥም ያለፉትን ድሎች ሳንጠቅስ፤ በቅርቡ አገራችን ከግብፅ፣ ከደቡብ ሱዳን፣ ከሶማሊያና ከሱዳን ሪፐብሊክ እንዲሁም ከሳዑዲ አረቢያ፣ ከኳታር፣ ከተባበሩት አረብ ኢምሬትስና ከሌሎች አገራት ጋር እያደረገች ያለችው በጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተ ግንኙነት መጥቀስ የሚቻል ይመስለኛል። የኳታሩ ኤታማዦር ሹም ጉብኝትም ከዚህ የተለየ አይደለም።

በመርህና በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተው የኢትዮጵያና የኳታር ግንኙነት ከዛሬ ሶስት ዓመት በፊት ግንኙነቱ ሊታደስ መቻሉን እናስታውሳለን። እናም ከሶስት ዓመታት በፊት የኳታሩ አሚር ሼክ ሐማድ ቢን ካሊፋ አልታኒ በኢትዮጵያ ያደረጉት ይፋዊ ጉብኝት ሁለቱ ሀገራት ግንኙነታቸውን ዳግም እንዲያድሱ በር ሊከፍት ችሏል።

በጉብኝቱ ወቅትም ሀገራቱ ተደጋጋሚ ቀረጥን በማስቀረት፣ በአየር ትራንስፖርት፣ በኢንቨስትመንት ከለላ፣ በባህልና ንግድ ላይ ተባብረው ለመስራት የሚያስችሏቸውን ጨምሮ ሌሎች 11 የመግባቢያ ስምምነቶችን ተፈራርመዋል። ስምምነቶቹን ወደ ተግባር ለመለወጥም ብዙ ጥረት ተደርጓል።

የኳታሩ አሚር ከዚም ወዲህ ወደ አዲስ አበባ መጥተው ባደረጉት ጉብኝት ከኢትዮጵያ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ጋር ተወያይተዋል። በውይይቱም የሁለቱን ሀገራት የኢኮኖሚና የኢንቨስትመንት ግንኙነት ይበልጥ ማሳደግ እንዲሁም ፖለቲካዊ ትስስርን ማጠናከር በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ መክረዋል። ኢትዮጵያም በባለስልጣናቶቿ አማካኝነት የአገራቱ የሁለትዮሽ ግንኙነት ይበልጥ እንዲጠናከር፤ የኳታር ባለ ሃብቶች በኢትዮጵያ በግብርና፣ በማዕድንና በአገልግሎት ዘርፎች እንዲሰማሩ መጠየቋ አይዘነጋም። በእኔ እምነት የኤታማዦሩ ሰሞነኛ ጉብኝት እነዚህን ጉዳዩች ለማጠናከር ያለመ ነው።

አገራችን እንደምትፈልገውና ከማንኛውም አገር ጋር ለማድረግ የምትሻውን በሰጥቶ መቀበልና በጋራ ተጠቃሚነት ዙሪያ ያተኮረ ነው። ኤታማዦር ሹሙን ጨምሮ ሌሎች የኳታር ባለስልጣናት በየጊዜው ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት በኢንቨስትመንትና በንግድ ለመሳተፍ ፍላጎት ማሳየታቸው ኢትዮጵያ ላለፉት ዓመታት ስትከተለው የነበረው ፖሊሲ ውጤት ያስገኘው ድል ነው ማለት ይቻላል።

እርግጥ በመርህ የሚመራው የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ አገራችን ከየትኛውም አገር ጋር ለጋራ ተጠቃሚነት የምትሰራና ይህን ወሳኝ መርህ ተፃርሮ እስካለቆመ ድረስ ከማንኛውም አገር ጋር በአጋርነት መንፈስ እንደምትተባበር የሚያረጋግጥ ነው።

እርግጥ እንደ ኳታር ዓይነት ያሉ የመካከለኛው ምስራቅ አገራት ኢትዮጵያ ውስጥ በግብርናው ኢንቨስትመንት ዘርፍ ቢሳተፉ ራሳቸውን ጠቅመው ኢትዮጵያንም ሊጠቅሙ ይችላሉ። እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ ውስጥ በተለይም በቆላማው የሀገራችን አካባቢዎች ለግብርና ስራ ምቹ የሆነ እጅግ ሰፊ ያልለማ መሬት አለ። ይህ መሬት ደግሞ ጥቅም መስጠት አለበት። እናም መሬቱን በአግባቡ በመጠቀም የግብርና ኢንቨስትመንትን ማስፋት ይገባል።

ያም ሆኖ ግን ይህን መሬት አርሶ ለመጠቀም ካፒታል ያስፈልጋል። የኳታርና የሌሎች የመካከለኛው ምስራቅ አገር ባለሃብቶች መዋዕለ ንዋያቸውን በዚህ ዘርፍ ላይ ማዋል ከቻሉ፤ ከግብርና ሊገኝ የሚችለውን የጋራ ተጠቃሚነት ማጎልበት ይቻላል።

ይህም ኢትዮጵያን ከመሬቷ ተጠቃሚ እንድትሆን ያደርጋታል። በርካታ ዜጎቿም የስራ ዕድል ያገኛሉ። ሁለቱም ወገኖች ተጠቃሚነታቸው ይጎለብታል። የኳታር ባለሃብቶች ወደ አገራችን ገብተው ይህን ዕድል እንዲጠቀሙ ባለስልጣኖቻቸው እንደ ሌሎቹ የመካከለኛው ምስራቅ አገራት ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸው ተቢና ትክክል ነው። የሰሞኑ የኳታር ባለስልጣን ጉብኝትም አንድምታው ከዚህ አኳያ መታየት ያለበት ይመስለኛል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy