Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የፓርቲዎቹ ውሎ ሲዳሰስ

0 305

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የፓርቲዎቹ ውሎ ሲዳሰስ

                                                      ዘአማን በላይ

አገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራ መድረካቸው በማከናወን ላይ የሚገኙት ድርድርና ውይይት ለሀገራችን ያለው ፋይዳ ከፍተኛ ነው። ፓርቲዎቹ ቀደም ባሉት ጊዜያት የምርጫ ህጉን ለማሻሻል ስምምነት ላይ መድረሳቸው ይታወቃል። በአሁኑ ወቅት ደግሞ በፀረ ሽብር ህጉ ዙሪያ እየተወያዩ ይገኛሉ። ታዲያ ይህን የውይይት መንፈስ መዳሰስ ተገቢ ነው።

የእስካሁኑ የፓርቲዎቹ ዴሞክራሲያዊ ውይይቶችና ድርድሮች ችግሮችን በዴሞክራሲያዊ መንገድ ለመፍታት የሚያስችል ርምጃ መሆኑ በተጨባጭ እየታየ ነው። ይህ ለሀገር ጠቃሚ የሆነ ውይይትና ድርድር ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል። ምክንያቱም በውይይቶቹ ላይ ሁሉም ተደራዳሪ አካል የመሰለውን ሃሳብ በማቅረብ፣ ያልመሰሉትን ደግሞ በመቃወም እንዲሁም ሃሳብ ከቀረበ በኋላ በሚዛናዊ እሳቤ ጉዳዩን በማጤን ለሀገራዊ ጥቅም ሲባል ድርድር እየተካሄደ መሆኑን ማንም ስለሚታዘብ ነው።

እዚህ ላይ ሰሞኑን ድርድር እየተካሄደበት ያለውን የፀረ ሽብር ህግን የድርድር ሂደት ከማንሳቴ በፊት፤ ለግንዛቤ ይረዳ ዘንድ ስለ አዋጁ ጥቂት የእውነታ ሰበዞችን መምዘዝ ያስፈልጋል ብዬ አምናለሁ። እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ የጀመረችው የዕድገትና የዴሞክራሲ ስርዓት ባህል ግንባታ ሂደት ስኬታማ ሆኖ እንዲቀጥል፤ አስተማማኝ ሰላም የሰፈነበት ምህዳርን መፍጠር አሌ አይባልም። ምክንያቱም ፈጣን ልማትን ማምጣትና ከተመፅዋችነት መላቀቅ ለሀገራችን የሞትና የሽረት ያህል የህልውና ጉዳይ ስለሆነ ነው። ታዲያ ሰላምን በማረጋገጥ ሂደት ውስጥ ለብሔራዊ ደህንነቷ ስጋት የሆኑ እንቅስቃሴዎችን መከላከልና መቆጣጠር የግድ ይላታል።

ከዚህ አኳያ ባለፉት ዓመታት የሀገራችን የብሔራዊ ደህንነት ስጋቶች ናቸው ተብለው ከሚጠቀሱት ተግባሮች ውስጥ አንዱና ግንባር ቀደም ተጠቃሹ የሽብርተኝነት እንቅስቃሴ ነው። ሽብርተኝነት የራሱ መንስኤዎችና ዓላማዎች ቢኖሩትም ቅሉ፤ በውጤትነት የሚያስከትለው አደጋ ግን ምን ያህል ዘግናኝና ጭካኔ የተሞላበት ተግባር መሆኑን የማይገነዘብ ሰው የሚኖር አይመስለኝም። ዛሬ የዓለም መንግስታት ይህን እጅግ በጭካኔ የተሞላ አደጋ ለመግታት በጋራ ለመስራት እየተስማሙ ይገኛሉ።

ሀገራችን የሽብር ድርጊት ቀዳሚ ገፈት ቀማሽ መሆኗ ግልፅ ነው። የቀጣናው ሀገርም ይሁን በሽብርተኝነት ተግባር ከመመታታቸው በፊት ኢትዮጵያ የመጀመሪያውን በትር የቀመሰች ሀገር ናት። በምሳሌነት ለመጥቀስ ያህል፤ በቀድሞው የግብፅ ፕሬዚዳንት በነበሩት ሆስኒ ሙባረክ ላይ አዲስ አበባ ውስጥ የተቃጣው የግድያ ሙከራ፣ የትራንስፖርትና መገናኛ ሚኒስትር በነበሩት በአብዱልመጂድ ሁሴን ላይ የተካሄደው የግድያ ሙከራና በግዮንና ዋቢ ሸበሌ ሆቴሎች እንዲሁም በመዲናችንና በክልል ከተሞች ህዝባዊ መገልገያዎች ላይ የተፈፀሙት የቦምብ ጥቃቶች ይህን እውነታ አስረጅ ናቸው።

በሌላ በኩልም የኤርትራ መንግስት በግንባር ላይ ተዋግቶ ያጣውን ድል በሽብር ተላላኪዎቹ አማካኝነት የሚያገኝ መስሎት እያቀነባበረ በተለያዩ ጊዜያት ተላላኪዎቹን መልዕክት አድራሽነት እንዲፈፅሙት አቅዷቸው፣ ነገር ግን በህዝቡና በፀጥታ ሃይሎች ትብብር የከሸፉ የሽብር ሙከራዎች ተደማሪ ማሳያዎች ናቸው። በሌላ በኩልም በጎረቤት ሶማሊያ የመሸገው አልሸባብ የሀገራችን ልማት አደጋ ሆኖ ዛሬም ድረስ ዘልቋል—ምንም እንኳን ቡድኑ በአሁኑ ወቅት እየተዳከመ ቢሆንም።

ታዲያ ይህ ሁኔታም ድህነትን ለመቅረፍ ትግል ለምታደርገው ሀገራችን አሜኬላ እሾህ መሆኑ ግልፅ ነው። ይህን የሽብርተኝነት አደጋ ተከላክሎ ሰለማችንን አስተማማኝ ለማድረግ ይቻል ዘንድም የኢትዮጵያ መንግሰት ቁርጠኛ አቋም መውሰዱ ይታወቃል። የሽብርተኝነትን አደጋ ለመከላከል የህግ ማዕቀፍ ተበጅቶለት አደጋውን ለማስቀረት ጥረት እየተደረገ ነው።

ርግጥ ሽብርተኝነት የዜጎችን ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ የሚገታ፣ የመንግስትን የማስፈጸም አቅም የሚያዳክም ብሎም በሀገር ደረጃ የተጀመረውን የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታን የሚያደናቅፍ አሊያም የሚያጓትት አሉታዊ ውጤት ያለው አፍራሽ ተግባር መሆኑን በመገንዘብ መንግስት የፀረ-ሽብርተኝነት ህግን አውጥቷል። ህጉ በየጊዜው በሀገራችን ብሔራዊ ደህንነት ላይ የተቃጡ የሽብር ጉዳዮችንና ወደፊት ሊኖሩ በሚችሉ ስጋቶች ላይ ተንተርሶ የተዘጋጀ ነው። እናም በአሁኑ ወቅት በዚህ አዋጅ ዙሪያ ገዥው ፓርቲና ተቃዋሚዎች በሰጥቶ መቀበል ላይ የተመሰረተ ዴሞክራሲያዊ ድርድርና ውይይት እያካሄዱ ነው።

የፀረ ሽብር አዋጁ ሀገራዊ ጠቀሜታ ዙሪያ ለግንዛቤ ይረዳ ዘንድ ይህን ያህል ካልኩ ዘንዳ፤ አሁን ደግሞ ሰሞኑን በህጉ ዙሪያ እየተካሄዱ ስላሉት ዴሞክራሲያዊ ድርድር ላምራ። በድርድሩና በውይይቱ ላይ የሚነሱት ጉዳዩች ሁሉም ፓርቲዎች የእኔ የሚሉትን ሃሳብ እያራመዱ ናቸው። ገዥው ፓርቲም በሃሳቦቹ ዙሪያ የሚስማማባቸውንና የማይስማማባቸውን ጉዳዩች በዝርዝር ከነ ምክንያታቸው አቅርቧል።

ፓርቲዎቹ በፀረ-ሽብር ህጉ ዙሪያ መሻሻል፣ መሰረዝና መጨመር ባሏቸው አንቀፆች ላይ ለአራት ጊዜያት ድርድር አካሂደዋል። በዚህ መሰረትም ‘ህጉ ከሀገሪቱ ህገ መንግስትና ከወንጀል ህግ እንዲሁም ከዓለም ዓቀፍ የሰብዓዊ መብት ስምምነቶችና ህጎች ጋር ይጣረሳል’ በሚል በተደራዳሪ ፓርቲዎች ባለፈው ወር ለቀረቡ ሃሳቦች ገዥው ፓርቲ ምላሽ ሰጥቷል። በዚህም የፀረ ሽብር ህጉ አንቀፆች ከህገ መንግስቱ አንቀፆችና ከወንጀል ህጉ ጋር ያላቸው ተያያዥነት እንዲሁም ከዓለም አቀፍ ህጎች፣ ስምምነቶችና ከተለያዩ አገሮች ተሞክሮዎች አንጻር ያለውን ተዛምዶ በዝርዝር አስረድቷል።

ህጉ ከሀገሪቱ ህገ መንግስትና የወንጀል ህግ እንዲሁም ከዓለም ዓቀፍ የሰብዓዊ መብት ስምምነቶችና ህጎች ጋር ይጣረሳል’ የሚለውን የተደራዳሪ ፓርቲዎችን ትችት ለመቀበል “አሳማኝ ምክንያት አላገኘሁበትም” ብሏል። ተጣምረው የሚደራደሩት 11 የፖለቲካ ፓርቲዎች የአዋጁ ስድስት አንቀጾች መሰረዝ፣ አምስት አንቀጾች ደግሞ መሻሻል አለባቸው በሚል ያቀረቡትን የድርድር ሃሳብም ተቀባይነት እንደሌለው አስታውቋል።

ለዚህም በምክንያትነት ያቀረበው በተደራዳሪ ፓርቲዎች እንዲካተቱ የቀረቡ አዳዲስ አንቀፆች በወንጀል መቅጫ ህጉ ውስጥ የተካተቱ ናቸው የሚል ነው። መሰረዝና መሻሻል አለባቸው የተባሉ የአዋጁ አንቀፆች ከሀገሪቱ ብሔራዊ ደህንነት፣ የህዝቡን ሰላምና መረጋጋት ከመጠበቅና የህግ የበላይነት ከማስከበር አኳያ ጠቃሚ በመሆናቸው ቅቡል ሊሆኑ እንደማይችሉ አስረድቷል። በተለይ በፀረ ሽብር ህጉ ከአንቀፅ 3 እስከ 12 የተዘረዘሩት የቅጣት ደረጃዎች ከሌሎች ሀገሮች የፀረ ሽብር አዋጆች ጋር ሲነፃፀር ዝቅተኛ መሆኑን የኢህአዴግ ተደራዳሪዎች አስረድተዋል።

በአዋጁ ላይ የተገለፀው “ሽብርተኛ” እና “ሽብርተኝነት” የሚለውን ትርጓሜ ግልፅ ከማድረግ አኳያም የተሻለ ስያሜና ትርጉም ከቀረበ እንደሚቀበል ገዥው ፓርቲ አስታውቋል። በፀረ ሽብርም ይሁን በወንጀል ህጉ ላይ ፖሊስ ተመጣጣኝ የኃይል እርምጃ እንዲወስድ የሚፈቅዱ አንቀፆች ተፈፃሚነት እስከ ምን ድረስ ነው የሚለውን ለመወሰን ደረጃውን የጠበቀ የህግ ማዕቀፍ መውጣት እንዳለበትም ፓርቲዎቹ ተስማምተዋል።

ከዚህ ጋር ተያይዞም ፓርቲዎቹ ባደረጉት ድርድር በአሸባሪነት ተጠርጥረው በህግ ጥላ ስር የዋሉ ግለሰቦች ጉዳያቸው ተጣርቶ በነፃ ከተለቀቁ በኋላ ማግኘት ስለሚገባቸው የሞራል ካሳ  ፈንድ ለማቋቋም ገዥውን ፓርቲ ጨምሮ ሁሉም ተደራዳሪዎቹ ተስማምተዋል።

ተደራዳሪ ፓርቲዎቹ የፀረ ሽብር ህጉን በተመለከተ እያደረጉ ያሉት ሰሞነኛ ውሎ ድርድር የማጠቃለያ ውጤትና የፓርቲዎቹን የአቋም መግለጫ በቀጣይ ለመስጠትም ተስማምተው በቀጠሮ ተለያይተዋል።

ርግጥ ፓርቲዎቹ እስካሁን ካደረጓቸው ድርድሮች በመነሳት ቅድሚያ ለአገራዊ ጥቅም በመስጠት በአዋጁ ዙሪያ የጋራ ድምዳሜ ላይ እንደሚደርሱ እንደ ዜጋ እምነቴን ለመግለፅ እፈልጋለሁ። ምክንያቱም ዋናው ጉዳይ ማንኛውም ህግ ለሀገር ምን ያህል ይጠቅማል ብሎ በሰከነና ጥሞና በተሞላበት ሁኔታ ማሰብ ስለሆነ ነው።

ያም ሆኖ እንዲህ ዓይነቱ መናበብ ያለበት ድርድርና ውይይት ለሀገር ያለው ጠቀሜታ ከፍተኛ በመሆኑ በሌሎች ሀገራዊ ጉዳዮችም ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል። ድርድሩና ውይይቱ ዴሞክራሲን ይበልጥ ለማጎልበትና የህዝብ ወኪል የሆኑ ፓርቲዎች ድምፃቸውን እንዲያሰሙ ለማድረግ ታስቦ የሚከናወኑ በመሆናቸው ጥልቀታቸው ጨምሮ የዴሞክራሲያዊ ባህላችን መገለጫ መሆን ያለባቸው ይመስለኛል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy