Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ያልተዘጋው በር

0 527

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ያልተዘጋው በር

                                                            ዘአማን በላይ

ህገ ወጥ ስደት አሁንም የዓለማችንና የሀገራችን ስጋት ከሆነ ሰነባብቷል። ህገ ወጥ ስደት በዓለም አቀፍ ደረጃ በእነማን አማካኝነት እንደሚካሄድ፣ የሰንሰለቱን ትስስርና የመዳረሻ አደጋውን እንዲሁም በአሁኑ ወቅት እስከ ደረሰበት የባሪያ ፍንገላ ንግድ ድረስ የተለያዩ ቅርፆችን ይዞ ተጉዟል። በሀገራችንም ችግሩን ለመከላካል መንግስት በርካታ ጥረቶችን ቢያደርግም፤ አሁንም ቢሆን ችግሩ ሊቀረፍ አልቻለም። ይህ የዜጎችን ህይወት ቀጣፊ በር አሁንም አልተዘጋም። በዚህ በር የሚመላለሱ ዜጎች በርካታ ናቸው።

ለሁኔታው መፈጠር በርካታ ምክንያቶችን መግለፅ ቢቻልም፤ ከቤተሰብ ጀምሮ እስከ ማህበረሰብ ድረስ ተያያዙ ጉዳዩች መኖራቸው ግልፅ ነው። ታዲያ ችግሩን ለመቅረፍ መንግስት የመሪነት ሚናውን እየተወጣ ነው። ይህ ብቻውን ግን በቂ አይደለም። ቤተሰብ፣ የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎችም የመፍትሔው አካል በመሆን ከመንግስት ጋር ተቀራርበው መስራት ይኖርባቸዋል። ይህ የተቀናጀ ጥረትም የተከፈተውን የስደር በር ገርበብ በማድረግ በሂደትም ሊዘጋው የሚችል ይመስለኛል።

ምንም እንኳን መንግስት ሊያሰሩ የሚችሉ ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን ቢያወጣም፤ በአፈፃፀሙ ላይ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ተሳታፊ ሆነው በቁርጠኝነት መንቀሳቀስ ካልቻሉ የሚፈለገውን ውጤት ማምጣት አይቻልም። በተለይ በህገ ወጥ ስደት ላይ የጋራ ቋሚ ዕቅድ አውጥቶ በዘመቻ መልክ እየተናበቡ መስራት ያስፈልጋል። ህዝቡ ስደትን ለማቆም በሚደረገው ጥረት ላይ የህገ ወጥ ስደትን አስከፊነት አምኖበት በእኔነት መንፈስ በቁርጠኝነት መሰለፍ ካልቻለ ለውጥ ሊመጣ አይችልም።   

ይህ የህገ ወጥ ስደት ጉዳይ የእያንዳንዳችንን በር እስኪያንኳኳ ድረስ መጠበቅ የለብንም። እናም ለችግሩ መንስዔ የሆኑ ጉዳዩችን ማወቅ ይገባል። እነዚህ የችግሩ ተዋናዮች ግብ አንድና አንድ ነው። ሆኖም ገንዘብን አገኛለሁ ብሎ በወጡበት መቅረት መኖሩን ማስታወስ ይገባል። የህገ ወጥ ስደቱን መንገድ ለመቀነስ ብሎም ለመዝጋት መንግስት ፈርጀ ብዙ ጥረት እያደረገ ነው።

በአሁኑ ወትት መንግስት ለስራ አጥ ዜጎች የስራ ዕድልን በመፍጠር መንግስትነት ኃላፊነቱን ለመወጣት የሚቻለውን ሁሉ አድርጓል፤ የህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር አደጋን ለመከላከልም ከግንዛቤ ማስጨበጥ እስከ ተጨባጭ ርምጃዎችን መውሰድ ደረጃም ደርሷል።

እንደሚታወቀው ሁሉ በመላ ሀገሪቱ በተዋረድ ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ተከላካይ ምክር ቤት ተቀቁሟል። በዚህም ህበረተሰቡ በጉዳዩ ላይ በቂ ግንዛቤ እንዲያገኝ ሰፋፊ መድረኮች ተፈጥረው እንዲወያይበትና የመፍትሔው አካል እንዲሆን በየክልሉ በርካታ ተግባራት ዕውን ሆነዋል።

ይሁንና እነዚህ ጥረቶች ሀሁሉ ተደርገው ህገ ወጥ ስደትን ማስቆም አልተቻለም። ዋነኛ መንስኤዎቹ ወጣቱን ባልሆነ ተስፋ የሚደልሉት ህገ ወጥ ደላላዎች ናቸው። ይሁንና በዚህ አነስተኛ ፅሑፍ ላይ ከህገ-ወጥ ደላሎቹ ማንነት፣ አሰራራቸውና በዝውውሩ ሂደት ከሚኖራቸው ሚና አኳያ አዘዋዋሪዎቹን የአካባቢ፣ ድንበር አሻጋሪ፣ ጉዞ አቀላጣፊ፣ ከስደት ተመላሾችና ቤተሰቦቻቸው እንዲሁም በመዳረሻ ሀገራት የሚገኙ ደላሎች በማለት ልንከፍላቸው እንችላለን።

የአካባቢ ደላሎች በመገኙባቸው ቦታዎች የተሳሳተ መረጃ በማሰራጨትና በሌሎች ዘዴዎች ለህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር አመቺ ሁኔታ የመፍጠር እንዲሁም ተጋላጭ ግለሰቦችን የመለየት ስራን ከሌሎች ጋር በመሆን ያከናውናሉ። ድንበር አሻጋሪዎቹም መደበኛ ባልሆነ መንገድ ሰዎችን የሚያዘዋውሩ በኮንትሮባንድ ነጋዴነት የሚፈረጁ ናቸው። እነዚህኛዎቹ አዘዋዋሪዎች ሰዎችን በቡድን ከአካባቢ ደላሎች ተቀብለው ለሌሎች ተመሳሳይ አዘዋዋሪዎች የማስተላለፍ ስራዎችን ይተገብራሉ።

ጉዞ አቀላጣፊዎቹም ቢሆኑ መቀመጫቸውን ትላልቅ ከተማዎች ላይ በማድረግ ወደ መዳረሻ ቦታዎቹ የሚደረገውን ጉዞና የቅጥር ሁኔታዎችን የሚያመቻቹ ሲሆን፣ ከስደት ተመላሾችና ቤተሰቦቻቸው ደግሞ ዘመድና ጎረቤቶች እናግዛለን በማለት እነርሱ ወደ ነበሩበት ሀገር ሄደው እንዲቀጠሩ በግለሰብ ደረጃ ሁኔታዎችን በማመቻቸት በመደበኛነት የሚንቀሳቀሱ ናቸው።

የእነዚህ ከስደት ተመላሽ ዜጎች እንቅስቃሴ በቤተሰባቸውም ይደገፋል። ቤተሰቦቻቸው ልጆቻቸው ውጪ ሀገር ሄደው የሚያመጡት ገንዘብ በምን ሁኔታ የተገኘ መሆኑን ስለማይገነዘቡ ከስደት የተመለሱት ልጆቻቸው ያስገኙላቸውን “ጠቀሜታዎች” በመዘርዘር የህገ-ወጥ ስደቱ ሂደት ተካፋይ ይሆናሉ።

በማወቅም ይሁን ባለማወቅ በደላልነት ተሰልፈው የዜጎቻቸውን ህይወት ለአደጋ አሳልፈው ይሰጣሉ። በመጨረሻም በእነዚህ መንገዶች ከሀገራቸው በህገ-ወጥ ሁኔታ በመውጣት ራሳቸውን ያገለጡት ዜጎች በመዳረሻ ሀገሮች ውስጥ የሚገኙ ደላሎች እጅ ላይ ይወድቃሉ።

እነዚህ ህገ-ወጥ ደላሎችም ቀደም ሲል በጠቀስኳቸው የተለያዩ ደላሎች አማካኝነት የቀረቡላቸውን ግለሰቦች፤ በማታለል፣ በማስገደድ አሊያም በማስፈራራት በቀጥታ ለብዝበዛ እንዲጋለጡ ያደርጓቸዋል።

በዚህ መንገድ ወደ ሌሎች ሀገራት ውስጥ የሚገቡ ዜጎች በመንገድ ላይ ህይወታቸው ካላለለፈና ወደ መዳረሻ ሀገሮች በሰላም ከገቡ ዕጣ ፈንታቸው ብዝበዛ ወይም ለህልፈተ-ህይወት ከሚዳርግ አደገኛ ሁኔታ ጋር መላተም ነው።

በዚህ የትስስር ህገ-ወጥ ዝውውር ውስጥ አንድ ግለሰብ ምን ያህል ገንዘብ ሊያወጣ እንደሚችል ግልፅ ነው። የገንዘቡ ምንጭ ቤተሰብ ወይም ሀብትና ንብረት በመሸጥ አሊያም ከጎረቤት ብድር የሚገኝ ሊሆን ይችላል። ይህም ሌላ ኪሳራ ነው። ህብረተሰቡ ይህን እውነታ ማወቅ አለበት። በተለይ ቤተሰብ ሁኔታውን በውል ተገንዝቦ የችግሩን አስከፊነት ለልጆቹ መግለፅ ይኖርበታል።

ቤተሰብ ልጆቹ ወደ ውጭ እንዳማትሩ እዚህ ሀገር ውስጥ ያለውን እውነታ መግለፅ ይኖርበታል። “ከመሞት መሰንበት” እንዲሉ ችግሩ የወገንን ህይወት የሚቀጥፍ በመሆኑ ቤተሰብ ቁርጠኛ አቋም መያዝ አለበት። የሚብለጨለጩ ነገሮችን አድርገው አሊያም ተጫምተው የወጣቱን ቀልብ ሊስቡ የሚችሉ ከስደት ተመላሾች ገንዘቡን በስንት ዓመት ውስጥና እንዴት ሊያገኙት እንደቻሉ፣ ገንዘብ አገኛለሁ ብሎ በባሪያ ፍንገላ ንግድ ሰለባ መሆንም ሊከሰት እንደሚችል ማስረዳት ይኖርባቸዋል።

የስደት ዓለም ኑሮ እንከን አልባና ምንም ውጣ ውረድ የሌለበት አለመሆኑንም ማስገንዘብ ያስፈልጋል። የስደት ዓለም እጅግ አሰቃቂና ህይወትን ቀጣፊ ብሎም የሰው ልጅ እንደ ሰው ሳይሆን እንደ ፍየልና በግ የባሪያ ንግድ የሚካሄድበት መድረክ መሆኑንም መግለፅ ተገቢ ነው። ከስደት ህይወት ውርደት እንጂ ክብር እንደማይገኝ፣ በህይወት የመቆየት ጉዳይ በነጠላ ክር ላይ እንደተንጠለጠለ ዳቦ ያህል እንኳ ተስፋ የሌለው እንደሆነ ማውሳት ያስፈልጋል። በሌላ በኩልም እዚህ ሀገር ውስጥ ሁሉም ነገር ተሟልቷል ሊባል የሚችል ባይሆንም፤ በመንግስት በኩል የተፈጠሩ ወጣቶችን የመደገፍ ሂደቶችን ማስረዳት ከቤተሰብም ጭምር የሚጠበቅ ነው።

ዛሬ ሀገራችን ድህነትንና ስራ አጥነትን በየደረጃው ለመቅረፍ ደፋ ቀና በማለት ላይ ትገኛለች። ይህ ጥረቷም ውጤት በማፍራት ላይ ይገኛል። በተለይም ወጣቶችና ሴቶች በአነስተኛና ጥቃቅን ኢንተርፕራይዞች እየታቀፉ ህይወታቸውን በመለወጥ ላይ ይገኛሉ።

ሌላው ቢቀር ገንዘብ ባይኖር እንኳን ተደራጅቶ በመበደር የድህነት ሁኔታን መቅረፍ እየተቻለ ወደ ውጭ ማመተር ተገቢ አለመሆኑን ቤተሰብ ለልጆቹ ማስረዳት አለበት። ጉዳይ የተሻለ ኑሮ የሚኖረው ሰውም ሳይቀር ልቡን ለስደት እያዘጋጀ በስተመጨረሻው ህይወቱን ጭምር እያጣ መሆኑንና ልጆቹም ከዚህ አሰቃቂ ጉዞ ታቅበው በሀገራቸው ውስጥ ሰርተው ማግኘት እንደሚችሉ ማስተማር ይገባል።

ገና ለገና ልጄ ወደ ውጭ ሄዶ ይደጉመኛል በሚል እሳቤ ልጆቹን ወደ እቶን እሳት ውስጥ መወርወር የለበትም። የጎረቤት ልጅ ሄዶ ገንዘብ ለቤተሰቦቹ በመላኩ ምክንያት ‘የእኔም ቢሄድ…’ ብሎ መመኘት የገዛ ልጅን ባሪያ ሆኖ እንዲኖር መፍረድና ካልሆነም ህይወቱን እንዲያጣ መጋበዝ እንደሆነ ማስተማር የማህበረሰቡ መሰረት የሆነው ቤተሰብም ተግባር ሊሆን ይገባል ባይ ነኝ።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy