የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ ከመጭው ሰኞ ጀምሮ በግብጽ ይፋዊ የስራ ጉብኝት ሊያደርጉ ነው።
ለሶስት ቀናት በሚያደርጉት ጉብኝት ከግብጹ ፕሬዚዳንት አብዱል ፈታ አል ሲ ሲ ጋር ይወያያሉ ተብሏል።
በጉብኝቱ ሁለተኛ ቀንም በግብጽ ፓርላማ በመገኘት ንግግር እንደሚያደርጉ ከግብጹ አል ማስሪ አል ዩም የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
ከፕሬዚዳንት አል ሲ ሲ ጋርም በታላቁ የህዳሴ ግድብ ወቅታዊ ጉዳይ ዙሪያ ይወያያሉም ነው የተባለው።
ከዚህ ባለፈም በግብጽ የአለም ባንክ ያደራድረን ጥያቄ ላይ የኢትዮጵያን ምላሽና አቋም በተመለከተም ማብራሪያ እንደሚሰጡ ነው የተነገረው።
የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት በግብጹ ጉብኝት ላይ የሚሳተፈው ልዑክ አባላት ናቸው።
የአሁኑ ጉብኝት ባለፈው ታህሳስ ወር ሊካሄድ ታስቦ ወደ ጥር ወር የተላለፈው መሆኑንም ዘገባው አያይዞ ጠቅሷል።
ባለፈው ታህሳስ 17 የግብጹ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሜህ ሽኩሪ በአዲስ አበባ ጉብኝት ማድረጋቸው ይታወሳል።
በጉብኝታቸውም ከጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝና ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ጋር በታላቁ የህዳሴ ግድብና በሃገራቱ የሁለትዮሽ ግንኙነት ዙሪያ መክረው ነበር።
በጉብኝታቸው ወቅትም በግድቡ ዙሪያ በሚካሄደው የሶስትዮሽ ውይይት ላይ የአለም ባንክ ገለልተኛ አደራዳሪ ሆኖ ይቅረብ የሚል ሀሳብ የያዘ ረቂቅ ሀሳብ ማቅረባቸው የሚታወስ ነው።
ከታላቁ የህዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያ፣ የሱዳንና የግብፅ የውሃ ሚኒስትሮች 7ኛውን የጋራ ስብሰባ ከህዳር 2 እስከ ህዳር 3 ቀን 2010 ዓ.ም በግብፅ ዋና ከተማ ካይሮ ማካሄዳቸውም የሚታወስ ነው።
በካይሮ የተካሄደው ስብሰባም ቀደም ሲል ጥቅምት 8 ቀን 2010 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተካሄደው የቀጠለ ሲሆን፥ ባልተቋጩ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት በማድረግ እና ጉዳዮቹን ለመቋጨት ያለመ ነበር።