Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ጠንካራው አቋም

0 276

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ጠንካራው አቋም

                                                   ደስታ ኃይሉ

የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ የሰጠው መግለጫ በርካታ ጉዳዩች ላይ የሚያተኩር ነው። የአገርንም ችግር የሚታደግ ነው። መግለጫው ስራ አስፈፃሚው ራሱን በሚገባ የተመለከተበት፣ የተከሰቱትን ጊዜያዊ ችግሮች ለመፍታት ቃል የገባበትና ለተግባር አንድነት መሰረት የሆነው የአመለካከት አንድነት መፈጠሩን ያበሰረበት ነው።

ይህን የአመለካከት አንድነት ወደ ተግባር መለወጥና ከህዝቡ ጋር በመሆን ለተፈጠሩት ጊዜያዊ ችግሮች ዘላቂ መፍትሔ በመስጠት በአገራችን ላይ አንዣቦ የነበረውን አደጋ እንደሚቀርፍ የሚያስረዳም ጭምር ነው። ይህ አደጋን የሚያስቀር ጠንካራ አቋምም ወደ ተግባር በመቀየር ላይ ይገኛል።

ኢህአዴግ ያጋጠሙትን ችግሮች በመፍታት ረገድ ተሞክሮ ያለው ድርጅት ነው። የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ግንባር (ኢህአዴግ) ከሀገራችን ህዝቦች ጋር በመሆን አምባገነኑን የደርግ ስርዓት ለመጣል ርብርብ ለማድረግ ከወሰነበት ጊዜ አንስቶ በመንግስትነት ሀገሪቱም መምራት እስከጀመረበት ጊዜ ድረስ በርካታ ተግዳሮቶች አጋጥመውታል። እነዚህ ተግዳሮቶች ድርጅቱን የተፈታተኑት ቢሆኑም፤ ከህዝብና ከመላው አባላቱ ጋር በመሆን አያሌ ችግሮችን በብቃት መሻገር ችሏል። እናም በዚህ ፅሑፍ ከደርግ መውደቅ ማግስት፣ በተሃድሶው ወቅት፣ በምርጫ 97 እና በአሁን ወቅት ከመልካም አስተዳደርና ተያያዥ ጉዳዩች አንፃር ያጋጠሙትን ችግሮች በዋነኛነት በማንሳት ድርጅቱ የተጓዘባቸውን አባጣና ጎርባጣ መንገዶችን ለማሳየት እሞክራለሁ። ይህ ምልከታዬም ገዥው ፓርቲ በትናንት ስህተቶቹ ዛሬን ማቃናት እንደሚችልና በዘወትር ተማሪነቱ እየተፈተነ የመጣ በመሆኑ፤ አሁን ያጋጠመውን ፈተና በሰከነና ህዝብን ማዕከል ባደረገ ሁኔታ የመፍታት ባህልና ብቃት ያለው መሆኑን የሚያሳይ ይመስለኛል።

እስቲ ለማንኛውም በደርግ ውድቀት ማግስት ድርጅቱን ካጋጠመው ተግዳሮት ልነሳ። እንደሚታወቀው የአምባገነኑን ስርዓት መውደቅ ተከትሎ በ1983 ዓ.ም ከ17 የማያንሱ የታጠቁ የብሔር ቡድኖች ነበሩ። እነዚህ ቡድኖች የተለያዩ ዘውግ ያላቸው ናቸው። የተወሰኑት ጠባቦችና ትምክህተኞች ሲሆኑ፤ ሌሎቹ ደግሞ በፅንፈኛ አክራሪነት የተሰለፉ ነበሩ። በወቅቱ ደርግን ገርስሶ ስልጣን የያዘው ኢህአዴግ እነዚህ ቡድኖች ለሀገራችን የጋራ መፍትሔ እንዲሹ ባቀረበላቸው ጥሪ መሰረት የሽግግር መንግስቱን ለመቀላለቀል ከያሉበት ቦታ ወደ ሀገራቸው መምጣታቸው ይታወሳል። ለኢህአዴግ የእነዚህን የማይጣጣም ፍላጎት ያላቸውን ቡድኖች ፍላጎት ማቻቻል አንድ ተግዳሮት ነበር፤ በሌላ በኩል ደግሞ የቡድኖቹን የተበታተነ ፍላጎት የተመለከቱ አንዳንድ ተንታኞች ‘ኢትዮጵያ ትበታተናለች’ የሚል ሟርትን ሲያቀርቡ ነበር።

ሆኖም ኢህአዴግ እነዚህን ተግዳሮቶች ለመፍታት የራሱን መንገዶች ተከትሏል። በተለይም ድርጅቱ በመጀመሪያዎቹ የስልጣን ዓመታት የተሸጋገረው በአራቱም የሀገሪቱ ማዕዘናት የሰላምና ማረጋጋት ስራዎችን ወደ ማከናወኑ ነበር።

በዚህም በውድ የህዝብ ልጆች አኩሪ መስዕዋትነት የተገኘውን ድል ለመንጠቅ የሚሯሯጡ ፀረ ሰላም፣ ፀረ- ልማትና ፀረ-ዴሞክራሲ ኃይሎችን የማፅዳት ተግባሮችን ፈፅሟል። በወቅቱ ኢህአዴግና ሌሎች ታጣቂ ኃይሎች ለሀገራዊ ሰላም ሲሯሯጡ ራሱን “ኦነግ” እያለ ይጠራ የነበረው የጠባቦች ቡድን ይህንን የተቀደሰ ዓላማ አልቀበልም በማለት የጦረኝነት አቅጣጫን በመምረጥ ማፈንገጡ የሚዘነጋ አይደለም። ሆኖም ኢህአዴግ ችግሩን እንደ አመጣጡ በመቀበልና መፍትሄ በማበጀት ብልህነት በተሞላበት ሁኔታ ተወጥቶታል።

ዛሬም ድርጅቱ ከህዝብ ጋር ሆኖ ማናቸውንም ጊዜያዊ ችግሮች የመፍታት ብቃት አለው። ለዚህም ነው በመግለጫው ላይ “የአገራችን የወደፊት እድል የሚወሰነው የጀመርነውን የህዳሴ ጉዞ ጠብቀን ድሎቻችንን በማስፋትና ድክመቶቻችንን አርመን ዳር ለማድረስ ስንችል ብቻ ነው። በመሆኑም የአጋጠሙንን ጊዜያዊ መሰናክሎች ሁሉ በፅናት ተፋልመን ዴሞክራሲያዊና ልማታዊ ድሎቻችንን ለማስፋት የተለመደ ድጋፋችሁና ወሳኝ እንቅስቃሴያችሁ እንዳይለየን፤ በአጠፋንበት እያረማችሁ፣ በአጎደልንበት እየሞላችሁ አገራችንን ተባብረን እንገንባ” በማለት ጥሪውን ለመላው የአገራችን ህዘቦች ያቀረበው።

ኢህአዴግ የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የፈጠሩት ፓርቲ ነው። ከትናንት ተግባራቶቹ ዛሬ እየተማረ የመጣ ነው። በህዝብ ይሁንታንና ፍላጎትን መሰረት በማድረግ ለስልጣን የበቃና እንደ ገዥ ፓርቲ ስራዎቹን ከህዝብ ጋር እየተመካከረ የሚፈፅም ድርጅት ነው።

ጠንካራ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች እንዲሁም በጠንካራ አመራር፣ አባላትና ደጋፊዎች የሚመራና የሚደገፍ ድርጅት ነው። በህዝብ እየታረመ ለህዝብ የሚሰራ ድርጅትም ነው። እናም ይህ ህዝብ እስካለ ድረስ ኢህአዴግም መኖሩ አይቀርም።

ገዥው ፓርቲ ባለፉት 26 ዓመታት መንግስት የሀገሪቱን ኢኮኖሚ በገበያ ተኮር ሥርዓት እንዲራመድ በማድረግ፣ ዕድገቱ ቀጣይና ተከታታይ እንዲሆን ብሎም የህብረተሰቡን የኑሮ ደረጃ ማሻሻል ችሏል። በዚህም በገጠርም ሆነ በከተማ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ሀገሪቱ እያስመዘገበችው ካለችው የምጣኔ ሃብት ዕድገት ተጠቃሚ በመሆን የነብስ ወከፍ ገቢያቸው እንዲያድግ ማድረግ የቻለ ነው።

በተለያዩ ቅቶች የህዝቡን አመኔታ የሚሸረሽሩ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ላይ እንደ አምናው ከህዝቡ ጋር በመሆን ተገቢውን የእርምት ርምጃ ወስዷል። ይህም የድርጅቱን ህዝባዊነት የሚያሳይ ነው።

የኢህአዴግን መስመር ዛሬ አፍሪካዊ ወንድሞቻችን እንደ “ሞዴል” እየወሰዱት ነው። ድርጅቱ ከትናንት ችግሮቹ እየተማረና ፈተናውንም በአጥጋቢ ውጤት እያለፈ የመጣ ህዝባዊ ኃይል ነው።

የጥልቅ ተሃድሶ መንገድ ረጅም በመሆኑ እንደ ትናንቱ ዛሬም ከህዝብ ጋር ሆኖ ራሱን በጥልቀት ይፈትሻል። በዚህም በአንዳንድ አካባቢዎች የተፈጠሩትን ሁከቶች በማርገብ ሰላምና መረጋጋትን መፍጠሩ አይቀሬ ነው። ድርጅቱ ምንም እንኳን በተለያዩ ማህበራዊ መስተጋብሮች ሊፈተን የሚችል ቢሆንም፤ ዋናው ነገር ችግሮቹን በተገቢው ሁኔታ ከህዝብ ጋር ሆኖ ለማለፍ ያደረገው ጥረት ነው።  

ገዥው ፓርቲና መንግስት ሁሌም በአሰራሮቻቸው ላይ ግልፅነትንና ተጠያቂነትን በማስፈን የህዝቦችን ህገ መንግስታዊ ፍላጎት እውን እያደረጉ መጥተዋል። ህዝብ መጠንከርና መሻሻል በሚገባቸው ጉዳዩች ላይ የሚሰጡትን አስተያየቶችንም ይቀበላሉ። ይታረማሉ።

እናም ሀገሪቱን በመምራት ላይ የሚገኘው መንግስት የህዝቦች የዘመናት ጥያቄ የሆነውን ዴሞክራሲ በጥልቀት ማስፋትና ማጎልበት ይጠበቅበታል። የአሰራሩን ተጠያቂነትና ግልፅነት በዚያኑ ልክ ለህዝቡ ማረጋገጥ አለበት። ዴሞክራሲ ሲጎለብት ይበልጥ አሳታፊ፣ ግልፅነት የተሞላበትና ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍሎች በበቂ ሁኔታ ሊያሳትፍ የሚችል ይሆናል። የሁሉንም የህብረተሰብ ክፍሎች ጥያቄዎችን በማሟላት ከህዝቡ ጋር ሆኖ ጠንካራ ስራ ማከናወን ይኖርበታል። ጠንካራ አቋሙን ዳግም ማረጋገጥ አለበት።

 

 

  

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy