ሁከትና እና ብጥብጡን እንደ ወደረርሽኝ የሚያዛምትብን ማነው?
ሰለሞን ሽፈራው
እንደዚህ ፀሐፊ ጽኑ እምነት፤ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ዜጋ ወይም ደግሞ የህብረተሰብ ክፍል በነውጥ የሚመጣ ለውጥ ለሀገራችን እንደማይበጃት አሳምሮ ይረዳል፡፡ ይህ የሆነውም ደግሞ መንግስት አሊያም ሌላ ጉዳዩ የመለከተው ባለድርሻ አካል ህዝቡ በነውጥ ለሚመጣ ለውጥ ድጋፉን እንዲነፍግ የሚያደርግ ስራ ስለሰራ አይደለም፡፡ ይልቅስ እያንዳንዱ የሀገራችን ብሔሮች፤ ብሔረሰቦችና ህዝቦች አስተማማኝ ሰላምና መረጋጋት የሚያሳጣ የለውጥ ፍለጋ ጥረት ድምር ውጤቱ ምን ሊሆን እንደሚችል፤ ከትናንቱ የጋራ ታሪካችን የተማሩበት አግባብ ስላለ እንጂ፡፡ ከዚህ የተነሳም እኛ ኢትዮጵያውያን እንደህብረተሰብ የምንገለጽበት ነባራዊና ህሊናዊ እውነታ አሁን አሁን በተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎች በተደጋጋሚ ሲከሰቱ ለሚስተዋሉት የሁከትና ብጥብጥ ተግባራት መቀስቀስ የተመቻቸ ነው ተብሎ አይታመንም፡፡
ምንም እንኳን በዛሬዋ ኢትዮጵያ ውስጥ የመልካም አስተዳደር እጦትና እንዲሁም የፍትህ ርትዕ መጓደል ችግር ያላስመረረው ህዝብ እንደማይኖር፤ መንግስት ራሱም ጭምር ያመነበት ጉዳይ መሆኑ ባያከራክርም፤ ግን ደግሞ ችግሩን መፍታት የሚቻለው ደም በሚያፋስስና ሀገር በሚያወድም የነውጠኝነት እንቅስቃሴ ነው ብሎ የሚያምን የህብረተሰብ ክፍል እንደሌለ ደፍሮ መናገር ይቻላል፡፡ በየትኛውም የክልላዊ መንግስት ዞንና ወረዳ፤ ብሎም የከተማ አስተዳደር ስር የሚገኝ ኢትዮጵያዊ ህዝብ እንዳች ሕጋዊ ምላሽ የሚያስፈልገው የመብት ጥያቄ ሊኖረው እንደሚችል ቢገመትም ቅሉ፤ በትርጉም የለሽ የሁከትና ብጥብጥ ተግባር አማካኝነት ጠብ የሚል መፍትሔ እንደማይኖር ግን ሰላም ወዳዱ ህብረተሰባችን አበክሮ ይረዳል፡፡ ይልቁንም ደግሞ እኛ ኢትዮጵያውያን ብሔሮች፤ ብሔረሰቦችና ህዝቦች እንደ የአንድ ሀገር ህብረተሰብ የሐዘን ማቅ ለብሰን የታየንበትን የዘመነ ቀይ ሽብሩን የዕርስ በርስ ዕልቂት ለማስታወስ በሚያስችል ዕድሜ ላይ ለምንገኝ ዜጎች፤ ሰላም ምን ያህል የከበረ ዋጋ እንዳለው ይገባናል ባይ ነኝ እኔ በግሌ፡፡ ለነገሩ ከደርግ የቀይ ሽብር ጭፍጨፋ የመትረፍ ዕድል የገጠመን የዚያን ክፉ ዘመን ትውልድ አባላት ጎራ ለይተን ለ17 ዓመታት በዘለቀው የዕርስ በርስ ጦርነት የተገዳደልንበት አሳዛኝ የቅርብ ጊዜ ታሪካችንስ ቢሆን የሚዘነጋ ነው እንዴ? ኧረ በፍፁም ሊረሳ የሚችል አይደለም ያ የዕልቂት ዘመን!!
ታዲያ ለምንድነው በተለይም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እዚህም እዚያም ሲከሰት የሚስተዋል ደም አፋሳሽ የሁከትና ብጥብጥ ተግባር የተበራከተው? እውን በመሰል ሀገር አውዳሚ የነውጠኝነት እንቅስቃሴ አማካኝነት አሁን ሀገራችን ኢትዮጵያ ውስጥ የሚስተዋሉ ፖለቲካዊ፤ ምጣኔ ሀብታዊና ማህበራዊ ችግሮችን ለመቅረፍ የሚያስችል የተሻለ ለውጥ ይመጣልን? ወይስ ደግሞ በዓመታት ጥረት የተገነቡ የመሰረተ ልማት ተቋሞቻችንን በቀናት ዕድሜ እያወደሙ እቺን የፈረደባት ሀገር ስር ከሰደደው የድህነትና የኋላ ቀርነት አዙሪት እንዳትወጣ ማድረግ በራሱ “የሰላማዊ ትግል መገለጫ ዴሞክራሲያዊ መብት” የሚመስላቸው ተቃዋሚ ፖለቲከኞች እንደ አሸን የፈሉበት ዘመን ላይ ደርሰናል ብለን እንመን? ነው አንዳንድ ድርጊቱን እጅግ አምርረው ሲያወግዙ የሚደመጡ ሰላም ወዳድ ወገኖቻችን እንደሚሉት “ጥቁር ቆዳ ለብሰው ኢትዮጵያን እንዲያፈርሱ የተላኩ ምዕራባውያን የሀገራችን ታሪካዊ ጠላቶች በመካከላችን እኛኑ መስለው እየተንቀሳቀሱ” ይሆን? ወዘተ የሚሉ ጥያቄዎችን እናነሳ ዘንድ የሚያስገድዱ ወቅታዊ እውነታዎች መኖራቸውን መካድ እንደማይቻል ሊሰመርበት ይገባል፡፡
ለምሳሌ ያህልም ባለፈው ቅዳሜ ጥር 12 ቀን 2010 ዓ.ም ወልዲያ ውስጥ የተቀሰቀሰው የሁከትና ብጥብጥ ተግባር ከተማዋን ለፈርጀ ብዙ ኪሳራ የዳረገ ጥፋት የማስከተሉን ያህል፤ ተጨባጭ መንስኤው አለመታወቁን መስማት ጉዳዩን ዕንቆቅልሽ ያደርገዋል፡፡ ይባስ ብሎም የወልዲያውን ማርገብ ስለመቻሉ በሰማን ማግስት፤ ተመሳሳይ የሁከትና ብጥብጥ ተግባር በዚያው የሰሜን ወሎ ዞን ስር ወደሚገኘው ራያ ቆቦ ወረዳ ተዛምቶ ሚጢጢዋ ቆቦ ከተማም ሰላሟን ያጣችበት ችግር እንደተፈጠረ ከወደዚያው የመጣ መረጃ አረዳን፡፡ የነውጠኝነት እንቅስቃሴውን እንዲፈጠር ያደረገው ምክንያት ምንድነው? ብለን ስንጠይቅ አሁንም አጥጋቢ ምላሽ የሚሰጠን ሁነኛ የመረጃ ምንጭ አለማግኘታችን ግን የበለጠ ግር እንድንሰኝ ማድረጉ አልቀረም፡፡ እንዲያውስ እኔን በዚች ጽሑፌ ርዕስ የሁከትና ብጥብጡን ተግባር እንደወረርሽኝ የሚያዛምትብን ማነው? ስል ለመጠየቅ የተገደድኩት ያለምክንያ እንዳይመስላችሁ፡፡ ይልቅስ ይህ ጥያቄ የበርካታ ሰላም ወዳድ ኢትዮጵያዊያን ዜጎችም ጭምር እንጂ የኔ ብቻ እንዳልሆነ ጉዳዩ የሚመለከታቸው የመንግስት ባለድርሻ አካላት ከእስከዛሬው የተሻለ አጥጋቢ ምላሽ ይሰጡበት ዘንድ ይጠበቅባቸዋል የሚል እምነት ስላለኝ ነው፡፡ ስለሆነም ይሄን ጥያቄ በማያወላዳ መልኩ የሚመልስ ተጨባጭ መረጃ እስካልተገኘ ድረስ የሕግ የበላይነትን ለማስፈን የሚደረገው ጥት ሁሉ ትርጉም ያለው ውጤት ሊያመጣ ይችላል ብሎ ማመን ያዳግታልና ለመሰል ሀገር አቀፋዊ ችግሮቻችን ዘላቂ መፍትሔ በማፈላለግ ረገድ ኃላፊነት የተጣለባቸው አካላት ልፋታቸው የእውር ድንብር እሩጫ ሆኖ እንዳይቀር መጠንቀቅ ይኖርባቸዋል እላለሁ፡፡
በግልጽ አነጋገር፤ ከታህሳስ 2008 ዓ.ም ጀምሮ እስከሰሞነኛው የሰሜን ወሎ ዞን ሁለት ከተሞች አሳዛኝ ዜና ድረስ ተመሳሳይ ሊባል የሚችል ቅኝት ያለው ሀገር አውዳሚ የሁከትና ብጥብጥ ተግባር እየተቀሰቀሰ ክስተቱ ከመደጋገሙ የተነሳ መላውን ኢትዮጵያውያን የብሔር ብሔረሰብ ህዝቦች ለብርቱ የሀገራዊ ደህንነት ስጋት እንዲጋለጡ እስከማድረግ የመድረሱን ያህል፤ ግን ደግሞ ይሄን ሁሉ ፈርጀ ብዙ ጥፋት ሲያስከትልብን ለሚስተዋለው የነውጠኝነት ወረርሽኝ ትክክለኛ መንስኤው ምን እንደሆነ የሚታወቅበት አግባብ ያለ አለመምሰሉ በእርግጥም ጥያቄ ያጭራልና ነው እኔም ከእስከዛሬው የተሻለ ማብራሪያ ይሰጥበት ማለቴ፡፡ ደግሞስ እንደ ኢትዮጵያ በርካታ ዜጎቿ የተሻለ ኑሮ ለመኖር ሲሉ ወደየትኛውም ክፍለ ዓለም ሲሰደዱ የሚስዋሉባት ድሃ አገር ውስጥ፤ የነውጠኝነት አባዜ በተጠናወታቸው አካላት የተጠና እንቅስቃሴ ለውድመትና ለጥፋት ተግባር እየተዳረገ ያለው ውስን ሀብትና ንብረት እንዴት በዋዛ ፈዛዛ የሚታለፍ ጉዳይ ሊሆን ይችላል? ስንትና ስንት ወጣት ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን በሕገ ወጥ መንገድ እየተሰደዱ ለተለያየ አደጋ የሚጋለጡትና ኢሰብዓዊ ድርጊት ሲፈጸምባቸው የሚታየው እኮ እዚህ አገር ቤት በሚቀሰቀስ የአመፃ ተግባር ምክንያት እንደቀልድ እየወደመ ያለውን ሀብት ንብረት ፍለጋ እንጂ ሌላ የተለየ ጉዳይ ኖሯቸው አይደለም ለፈርጀ ብዙ ስቃይ የሚዳረጉት፡፡
መንስኤው እንኳን በቅጡ ከማይታወቀው የሁከትና ብጥብጥ ተግባር ጋር በተያያዘ የፀጥታ መደፍረስ ችግር ምክንያት ክቡሩ የሰው ልጅ ህይወት ያለ አግባብ ሲቀጠፍ የምናየውስ እስከመቼ ነው ወገኖቼ!? መቼስ አሁን አሁን ለሀገራችን ህዝቦች የሰርክ ክስተት እየሆነ የመጣ የሚመስለውን የግጭት አዙሪት የመልካም አስዳደር ችግር ያስከተለው አድርገን ብንወስድ ጉዳዩ ተራ የዋህነት ሊሰኝብን ይችላል አይደል? ስለዚህም እንደኔ እንደኔ አደገኛውን የሁከትና ብጥብጥ ተግባር በማያዳግም መልኩ ማስቆም የሚቻለው ድርጊቱን በተጠና ቅንብር ማዛመት ስለያዙት አካላት ትክክለኛ ማንነት የተሟላ መረጃ ሲኖረን እንደሆነ ይሰማኛል፡፡ አለበለዚያ ግን የምስራቁን የፀጥታ ቀውስ የመፍታት ጥረት ስንጀምር ከበሰተ ደቡብ-ምዕራብ ሌላ ተመሳሳይ ችግር ተፈጥሮ እንዲገኝ ምናልባትም ከኛ በተሻለ መልኩ የሚንቀሰቀሱ ኃይሎች ሰለመኖራቸው ከእስከዛሬው ተደጋጋሚ ክስተት ብቻ መረዳት አይከብድም፡፡ ይህ ዓይነቱ ሁኔታ ህዝባችን ስልጣን ላይ ባለው መንግስት አመኔታ እንዳይኖረው ከማድረግ አኳያ ሊያሳድር የሚችለው አሉታዊ ተፅእኖ ቀላል ግምት የማይሰጠው ከመሆኑም ባሻገር፤ የጋራ ህልውናችን የተመሰረተባትን ሀገር ለውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት የሚያጋልጥ ስርዓት አልበኝነትን ሊያስከትል እንደሚችል ነው አንዳንድ ቅን አሳቢ ምሁራን የሚገልፁት፡፡ ለአብነት ያህልም ባለፈው ሐሙስ ጥር 17 ቀን 2010 ዓ.ም በምሽት ዜና እወጃ አየር ላይ ከዋለው የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ዕለታዊ ዘገባ በመካከል አንዱ “ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎች እየተስተዋሉ ያሉትን የዕርስ በርስ ግጭቶችና አለመግባባቶች ትክክለኛ መንስኤ ከመረዳት የሚመነጭ አፋጣኝ መፍትሔ መስጠት እንደሚገባ ምሁራን አሳስቡ” የሚል እንደነበር ማስታወስ ይቻላል፡፡
ኢ.ብ.ኮ ለዚህ ዘገባው በምንጭነት የጠቀሰው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በዕለቱ የተካሄደውን ስለ ሀገራችን ወቅታዊ ጉዳይና ይልቁንም ደግሞ ስለሰላማችን መጓደል የሚመክር መድረክ ሲሆን፤ ለዚህም መድረኩ ላይ ጥናታዊ ጽሑፍ ያቀረቡ ናቸው ያላቸውን ሁለት ምሁራን ያናገረበትን ማጣቀሻ ለዋቢነት ያክል አስደምጦናል በብሔራዊ ሬዲዮው፡፡ እናም ሁለቱ የአዲሰ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን በአፅንኦት ያስገነዘቡት ተመሳሳይ ነጥብ ቢኖር “እኛ አንዲህ በየጥቃቅኑ ምክንያት የዕርስ በርስ ቁርቁስና ፍጥጫ ውስጥ ስንገባ የምንስተዋልበትን ችግር በዘላቂነት የሚፈታ ስር ነቀል የእርምት እርምጃ ካልተወሰደ ሀገሪቱ ዕድገቷን ለማይፈልጉ ታሪካዊ ጠላቆቿ ጥቃት የምትጋለጥበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላልና ጉዳዩ በደንብ ይታሰብበት” የሚል ነው፡፡ በምንም ዓይነት ጊዜያዊ አለመግባባቶች ተገፋፍተን ሀገራዊ እድገታችንን አደጋ ላይ ሊጥል የሚችል እርምጃ ከመውሰድ መጠንቀቅ እንደሚጠበቅብንም ጭምር ምሁራኑ አክለው መክረዋል፡፡ ስለዚህ እኔ ራሴም እቺን ሐተታዬን የምቋጨው ለኢ.ቢ.ሲ. ዜና ዘጋቢ ጋዜጠኛ ከላይ የተጠቀሰውን አስተያየት የሰጡት ሁለቱም የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን የሰነዘሩትን ሃሳብ ጠቃሚ ሆኖ እንዳገኘሁት በመጠቆም ይሆናል፡፡ የመጣጥፌ ማጠንጠኛ ርዕሰ ጉዳይ ሆኖ የተነሳውን የሀገራችን ወቅታዊ ችግር በማጠቃለል ረገድ የሚመለከታቸው ሁሉም የፌደራሉና እንዲሁም ደግሞ የክልላዊ መንግስታት ባለድርሻ አካላት በተለይም የምሁራኑን ምክር እንደጠቃሚ ግብዓት ወስደው ትርጉም ያለውን ዘላቂ መፍትሔ ሊያመጣ የሚችል የእርምት እርምጃ እንደሚወስዱም ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ በተረፈ የዛሬውን ሐተታዬን እዚህ ላይ አብቅቻለሁ፡፡ መዓሰላማት!