Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ለመልካም አስተዳደር ስኬት …

0 450

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ለመልካም አስተዳደር ስኬት …

ኃብተየስ ወንድራድ

በቅርቡ በአንዳንድ የአገሪቱ አካባቢዎች የተለያዩ ተቃውሞዎች ሲሰሙ ነበር። በእርግጥ ተቃውሞው አግባብነት ሊኖረው ይችል ይሆናል። ተቃውሞው የተገለፀበት አካሄድ ግን ህይወትና ንብረት ያወደመ በመሆኑ ሠላም ወዳዱን ህዝብ ያሳዘነ ሆኗል። ኃላፊነት የጎደለውም ነው። የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በተደራጀና በእቅድ እንጂ በሁከት መፍታት አይቻልም። በሁከት የሚመጣ ለውጥ አገርን ይበታትናል። ህይወት ይቀጥፋል። ንብረት ያወድማል። አንዳንዱ ነውጥማ በኅብረተሰቡና በመንግሥት ጥረት በቁጥጥር ሥር ባይውል ኖሮ የሚያስከትለው ጉዳት በቀላሉ የሚታይ አልነበረም።

ኢትዮጵያ ውስጥ ዛሬ ላይ ልዩነቶችን በውይይትና በሰከነ መንገድ መፍታት የሚያስችል ባህል ሙሉ በሙሉ ዳብሯል ባይባልም መልካም ጅምሮች እንዳሉ በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል። ይህ ባለበት ሁኔታ ችግሮችን በስሜት በመነዳት በሁከትና በረብሻ ለመፍታት መሯሯጥ ሌላ ተልዕኮ እንዳለ ያስመስላል። እንዲህ ካለው ሰይጣናዊ ተግባራት ጀርባ የጠባቦችና የትምክህተኞች ሴራ ስለመኖሩ ምንም አያጠራጥርም። የአደባባይ ሚስጥር ነው። እነዚህ የጥፋት ኃይሎች የናፈቋትን ሥልጣን ለማኘት ሲሉ የማይወጡት ተራራ የማይወርዱት ቁልቁለት የለም። ይህንንም ከሁለት አሥርት ዓመታት በላይ አይተናል።  አሁን ላይ እነዚህ ሁለት እጅግ ጽንፍ አቋምን የሚያራምዱ የጥፋት ኃይሎች ድንገት ግንባር ገጥመው የጥፋት መርዛቸውን እየረጩ ናቸው። እነዚህ የጥፋት ኃይሎች የመርዛማ ተልዕኳቸው ማስፈፀሚያ ለማድረግ እየተሯሯጡ ያሉት በተለይ ወጣቱን በመጠቀም  ነው።

መንግሥት የህዝብን ድምጽ ማክበር መቻሉ አንዱ የመልካም አስተዳደር መገለጫ ነው። የህዝብ ትክክለኛ ተቃውሞን ሽፋን በማድረግ ፀረ ሠላም ኃይሎች ሠላማዊ ተቃውሞውን ወዳልተፈለገ ግጭት እንዲያመራ በማድረግ የሰዎች ህይወት እንዲጠፋ፣ አካል እንዲጎድል እንዲሁም የመንግሥትና የግለሰቦች ንብረት እንዲወድም አድርገዋል። እነዚህ ፀረ ሠላም ኃይሎች የተወሰኑ ወጣቶችን በተለይ ተማሪዎችን በማሳሳት ለድብቅ አጀንዳቸው መጠቀሚያ አድርገዋቸዋል።

ስለእውነት እንነጋገር ከተባለ ሁሉም ኢትዮጵያዊ እንደ አገር እየተመዘገበ ካለው ልማትና ሠላም ባልተለያየ ሁኔታ እኩል ተጠቃሚ መሆን ስለመጀመሩ የማይካድ ሀቅ ነው። አገሪቱ የዕድገት ጎዳናን ተያያዘችው እንጂ ችግሮቿ በሙሉ እልባት አገኙ ማለት አይቻልም። በርካታ ሊስተካከሉ የሚገቡ ውስብስብ ችግሮች አሉባት። ያን ታሳቢ ማድረግ ይገባል።  የፌዴራሉ ሆነ የክልል መንግሥታት በየአካባቢያቸው የሚስተዋሉ ችግሮችን ተጋግዘው ለመቅረፍ የሚያስችሉ ተግባራትን እየከወኑ ይገኛሉ። እስካሁን የተመዘገቡ ድሎችን በመጠበቅ ለተጨማሪ ድል መሥራት ይገባል እንጂ ያሉትን እያወደሙ ዕድገትን ማሰብ ተላላነት ነው።  

የክልል መንግሥታት በየደረጃው ካሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር በመወያት የመልካም አስተዳደር  ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችሉ ርምጃዎችን መውሰድ ጀምረዋል። ይህ በጎ ተግባር  እሰየው ያስብላል። መንግሥት ከፌዴራል እስከ ቀበሌ የዘረጋውን መዋቅር በየወቅቱ እየፈተሸ መጓዝ ይገባዋል። በአምቻ ጋብቻ፣ በወንዝ በአገር ልጅ፣ በዘመድ አዝማድ ኔት ወርክ በተሳሰረ ግንኙነት በተመደበ የሥራ ኃላፊና ተሿሚ የመልካም አስተዳደር ሊሰፍን ይችላል ብሎ ማሰብ አስቸጋሪ ይሆናል።  

ኢሕአዴግ ለዚህ የበቃው በጠንካራ የግምገማ ሥርዓቱ ነው። ይህ የኢሕአዴግ ድንቅ የግምገማ ባህል ሰሞኑን ይበልጥ ተጠናክሮ ወሣኝ የሚባሉ ውሣኔዎችን ለማሳለፍ ሲበቃ ተመልክተናል። ያበረታታል። ሁሉንም ችግሮች ግን ወደ መንግሥት ባይወረወርም መንግሥት በየወቅቱ ሊያስተካክላቸው የሚገቡ በርካታ ግድፈቶች መኖራቸውን መጥቀስ  ይቻላል። መረጃ እንጂ ማስረጃ አልተገኘም በሚል አንዳንድ የሥራ ኃላፊዎች በሥነ ምግባርም ይሁን በአቅም ማነስ ሥራን በድለውና ኅብረተሰብን አማረው ሲያበቁ ግምገማ ተካሄደ ተብሎ አንዳንዶቹ ካሉበት ቦታ ይነሱና ወደተሻለ ቦታ ሲዛወሩ ቀሪዎቹ  ደግሞ በተመሳሳይ የሥራ ኃላፊነት ሌላ ቦታ ላይ ተዛውረው እንዲሰሩ ሲደረጉ ታዝበናል።  ይህን በጽናት የሚታገል አሠራርን መዘርጋት አሁንም ጊዜ የሚሰጠው ተግባር አይደለም።

ሥነ ምግባርና በአቅም ማነስ ምክንያት እስከዶቃ ማሰሪያቸው የተገመገሙ በኅብረተሰቡ የተጠሉ የመንግሥት ተሿሚዎች  ከአንዱ የሥራ ኃላፊነት ቦታ ወደሌላው እየተዘዋወሩ እንዲሰሩ የሚደረጉት እውነት እነሱን የሚተኩ ሌሎች ግለሰቦች ስለማይገኙ ወይስ የእከክልኝ ልከክልህ አሠራር ውጤት በመኖሩ? የኢሕአዴግ የግምገማ ባህል እንኳንስ ለድል አጥቢያ ታጋዮች ይቅርና መሥራች ለነበሩ አንጋፋ የድርጅት መሥራቾችም ቆርጦ ለመጣል አልተመለሰም። ኢሕአዴግ የልከክልህ እከክልኝ አካሄድን ዛሬም እንደ ከዚህ ቀደሙ ቆራርጦና ጠራርጎ ማጥፋት ካልቻለ ድርጅቱንም ሆነ አገራችንን የሚጠቅም አይደለም።  በ2008 ዓ.ም ምርጫ ኅብረተሰቡ ለኢሕአዴግ በነቂስ ወጥቶ ድምጹን የሰጠው እንዲህ ያሉ ህዝብን የሚያማርሩ ኃላፊዎችን በአግባብ እንዲጠየቁ እንደሚያደርግ ስለሚያውቅ ነው። እምነትም ስላለው ነው።

ባለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት ኢትዮጵያ ፈጣንና ቀጣይነት ያለው የማህበራዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊና ፖለቲካዊ ለውጦችን ማስመዝገብ የቻለችው መንግሥትና ህዝብ  ተቀራርበው መሥራት በመቻላቸው ነው። ይህ በህዝቦች ሁለንተናዊ ተሳትፎና በመንግሥት ጠንካራ ፖሊሲና ስትራቴጂ መንደፍ እንዲሁም አመራር ሰጪነት የተገኘው አመርቂ ውጤት ማስቀጠል የሚቻለው ኢሕአዴግ የመጣበትን የትግል መስመር ሲያስጠብቅ ብቻ ነው። ኢሕአዴግ ለአስመሳዮች፣ ለአድርባዮች፣ ለሌቦችና ህዝብን ለሚያማርሩ የሥራ ማነቆዎች  ጥላ ሊሆናቸው አይገባም።

መልካም አስተዳደርን በማስፈን የመንግሥት ተሿሚዎች ብቻ ሳይሆኑ ሲቪል ሰርቫንቱም ትልቅ ኃቀላፊነት አለበት። ሲቪል ሰርቫንት ማለት ማንኛውም በመንግሥት መሥሪያ ቤት በቅጥርም ሆነ በፖለቲካ ሹመኝነት የመንግሥትን ፖሊሲና ስትራቴጂ የሚያስፈፅም የህዝብ አገልጋይ ማለት ነው፡፡ የሲቪል ሰርቪሱ ለአንድ አገር ሁለንታናዊ ዕድገት ስኬትም ይሁን ውድቀት ትልቅ አስተዋጽኦ አለው፡፡  በመሆኑም መንግሥት በሹመኞቹ ላይ ብቻ ሳይሆን በኤክስፐርት ደረጃ እያደረገ ያለውን የማጥራት ሥራ አጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል።

መልካም አስተዳደር ከዴሞክራሲ ባህል መጎልበት ጋር ትልቅ ቁርኝት አለው። የኢትዮጵያ  ዴሞክራሲ ባህል ገና ጅምር ላይ ነው። ዴሞክራሲ  ከጊዜ ጋር የሚዳብርና የሚጎለብት  ነው። መልካም አስተዳደርን ማስፈን የሚቻለው ሁሉም በተሰማራበት መስክ በተጠያቂነት መንፈስ ማገልገል ሲችል ነው። በመሆኑም ማንኛውም ሲቪል ሰርቫንት የመልካም አስተዳደር መስፈንን ከህልውናው ጋር ሊያቆራኘው ይገባል። ከዚህም ባሻገር ሲቪል ሰርቫንቱ የህዝብ አገልጋይ ለመሆን በህዝብ ገንዘብ የተማረና ልምድ የቀሰመ በመሆኑ አገርንና ህዝብን በቅንነት የማገልገል ኃላፊነትና ግዴታ ጭምር  አለበት።

መንግሥት የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመቅረፍ የተለያዩ ጥረቶችን በማድረግ ላይ ይገኛል። ይህ እውን ሊሆን የሚችለው እያንዳንዱ ሲቪል ሰርቫንት የተጣለበትን ኃላፊነት በብቃት መወጣት ሲችል ነው። በመሆኑም መንግሥት መልካም አስተዳደርን ማስፈን የሚችለው ሲቪል ሰርቫንቱን ላይ ተመስርቶ  በመሆኑ ሁሉም ሲቪል ሰርቫንት በጥብቅ ዲሲፕሊን በተደራጀ ሁኔታ  መልካም አስተዳደርን ለማስፈን በሚደረገው ርብርብ የራሱን ሚና ሊጫወት ይገባዋል።

ሲቪል ሰርቫንቱም ልማታዊ አስተሳሰብን በማዳበር አንደ ህዝብ አገልጋይነት የተሰጠውን አደራ በታማኝነትና በተጠያቂነት መንፈስ መንግሥት የቀረጻቸውን ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች አምኖ በመቀበል ሌሎችም አምነው ተቀብለው ተግባራዊ እንዲያደርጉ መታገል ይጠበቅበታል፡፡ ህዝብ ማገልገል ኩራት ነው። በቅንነትና በታማኝነት ኅብረተሰብን የሚያገለግሉ ሲቪል ሰርቫንት እንዳለ ሁሉ ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ የተጣለባቸውን ኃላፊነታቸውን ተጠቅመው የግል ጥቅማቸውን የሚያሳድዱ በርካቶች ናቸው። በሥነ ምግባራቸው የተመሰከረላቸው መንግሥትና ህዝብ የጣለባቸውን አደራ በአግባብ የሚወጡ ሲቪል ሰርቫንት እንዳሉ ሁሉ  በየሴክተሩ ተሸሽገው ህዝብ መንግሥትን እንዲያማርር ሆን ብለው የሚሰሩ ሲቪል ሰርቫንቶች እንዳሉ ጠንቅቆ በማወቅ መንግሥት የማጥራት ሥራውን አጠናክሮ ሊቀጥልበት ይገባዋል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy