Artcles

ለአረንጓዴ ልማት ስኬታማነት

By Admin

January 31, 2018

ለአረንጓዴ ልማት ስኬታማነት

ወንድይራድ ኃብተየስ

 

ሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ተጀምሮ ተግባራዊ እንቅስቃሴው ቀጥሏል።  መንግሥትና ህዝቡ የአገራችንን የህዳሴ ራዕይ ለማረጋገጥ በከፍተኛ የፖለቲካ ቁርጠኝነት ተነሳስተዋል። ዕቅዱ በእውቀት እንዲመራ በውጤት የታጀቡ ስትራቴጂዎችና ስልቶች ተነድፈው እየተተገበሩ ነው። የኢፌዴሪ መንግሥት ቀደም ሲል የመጀመሪያውን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ በውጤታማ አኳኋን ማጠናቀቁ እንዲሁ የሚታወስ ነው።  

በሁለተኛው የልማት ዕቅድ ውጤታማነትን በመተግበርና ካለፉት ሂደት በመማር  አፈፃፀማቸውን በየጊዜው እያጎለበቱ ነው። በዚህም አበረታች ሊባል የሚችሉ በጎ  ርምጃዎችን ተከትሎ በመጓዝ ላይ ነው። በዚህም የልማታዊ ዕድገት እመርታ ውጤት እየታፈሰ ነው። ባለፉት ተከታታይ ዓመታት የታየውም ይኸው ነው።

በተለይም በቀዳሚው የልማት ዕቅድ ወቅት መንግስትና ህዝቡ ባደረጉት ከፍተኛ ርብርብ ውጤታማ ተግባራትን ከውነዋል። በዚህም ለሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ መደላድሎችን ፈጥረዋል። የተማሯቸውን ተሞክሮዎች እየቀመሩ ለሁለተኛው የልማት ዕድገት ዕቅድ ክንዳቸውን አበርትተዋል፤ ያጋጠሟቸውን ተግዳሮቶችን እንደ ሁኔታቸውና አመጣጣቸው እየፈቱ ወደፊት ለመገስገስ በቁርጠኝነት ተነሳስተዋል።

እንደሚታወቀው በተለይ በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን የተመዘገበው ፈጣን ዕድገት ከ1996 እስከ 2007 ባሉት 12 ዓመታት የአገራችን ዕድገት በየዓመቱ በአማካይ በ10 ነጥብ 9 በመቶ እንዲያድግ አስችሏል። በዕቅድ ዘመኑ የተመዘገበው ፈጣን የምጣኔ ሀብት ዕድገት በአገር ውስጥም ከአገር ውጭም ሰፊ እውቅናና ተቀባይነት አግኝቷል።  

ይህ የተመዘገበው ፈጣን ዕድገት በአገራችን ሕዝቦች ዘንድ ከፍተኛ መነሳሳት ፈጥሯል፡፡ የተረጋገጠው ዕድገት አርሶ አደሮች፣ የግሉ ዘርፍ እና ሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎች በፍጥነት ማደግ እንደሚቻል አስገንዝቧል። ህዝቦችንም ለተጨማሪ ዕድገት እንዲተጉ እያነቃቃቸው ይገኛል፡፡

በዕቅዱ የመጀመሪያዎቹ አምስት ዓመታት የተመዘገበው ዕድገት በውጪው ዓለምም ሰፊ እውቅናና ተቀባይነት ያገኘ እና የኢትዮጵያንም ገፅታ በመሠረቱ እየተቀየረ እንዲመጣ ያስቻለ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ በተከታታይ ፈጣን ዕድገት እያስመዘገቡ ካሉት ጥቂት የዓለም አገራት ተጠቃሽ እንድትሆን አስችሏታል፡፡ ይህ ፈጣንና ተከታታይ ዕድገቷ በዋናነት የምትከተለው የልማት ስትራቴጂ ውጤት ነው። ይህም ለዕድገቷ ዘላቂነት ትልቅ ትርጉም እንዳለው በስፋት ይታመንበታል።  

በተለይ ከጥቂት ዓመታት በፊት የአገራችን ብድር የመሸከም አቅም ደረጃ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ በዓለም አቀፍ ደረጃ በታወቁ ሦስት ድርጅቶች ተገምግሟል።  በውጤቱም ኢትዮጵያ ባለፋት ዓመታት ያስመዘገበችውን ሁለንተናዊ ዕድገትና ልማት ለማረጋገጥ ተችሏል፡፡

የአገሪቱ ፈጣን ዕድገት በቀጣዩ የመካከለኛ ዘመንም የሚቀጥል እንደሚሆን የግምገማ ውጤቱ አረጋግጧል፡፡ ይህ ዓለም አቀፍ እውቅና አገሪቱ በአለም ዓቀፍ ኢንቨስተሮች እይታ ውስጥ እንድትገባ አድርጓል። ይህም ሁኔታ ኢንቨስትመንትንና የንግድ መዳረሻነቷን የሚያጠናክር እንደሚሆን ይታመናል፡፡

ይህ እየተመዘገበ ያለው ፈጣን ዕድገት የአገሪቱን ምጣኔ ሀብት በመጠኑ ግዙፍ ከሚባሉ ጥቂት የአፍሪካ አገራት መካከል እንዲጠቀስ ያስቻለ ነው፡፡ ይኸም በተራው ለቀጣይ ዕድገት ተጨማሪ አቅም ፈጥሯል፡፡ ዓመታዊ አማካይ የነፍስ ወከፍ ገቢው ከተቀመጠው ግብ በላይ አፈፃፀም የተመዘገበበት ነው። ባለፉት ጥቂት ዓመታት የነፍስ ወከፍ ገቢ 632 ዶላር ደርሶ ነበር። በአሁኑ ወቅት ደግሞ ይህ አኃዝ ወደ 900 ዶላር ተጠግቷል።

እንደሚታወሰው በመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን መጨረሻ ላይ የተደረሰበት የነፍስ ወከፍ ገቢ የአገሪቱን የመጀመሪያ ደረጃ መካከለኛ ገቢ ያላት አገር የመሆን ራዕይን ለማሳካት የሚያስችል መሆኑን ያረጋግጣል።

በዚህ መሠረትም እስቲ በአረንጓዴ ልማት ዘርፍ ባለፉት ጥቂት ዓመታት የተከናወኑትን ተግባራት አንመልከት። በሁለተኛው የልማት ዕቅድ ምን ዓይነት ተግባራት ለማከናወን ታቅደዋል። በቅድሚያ ግን ጥቂት ስለ አረንጓዴ ልማት ምንነትና ኢትዮጵያ  የተከተለቻቸውን አቅጣጫዎች በጥቂቱ እንፈትሽ።

እንደሚታወቀው የአየር ንብረት ለውጥ የዓለማችን ፈታኝ ሁኔታ ከሆነ ሰነባብቷል። ለችግሩ በዋና ምክንያትነት የሚጠቀሱት ወደ ከባቢ አየር የሚለቀቁ የበካይ ጋዞች ልቀት መጨመርና የደን ሐብት እየተመናመነ መምጣት መሆኑን የዘርፉ ተመራማሪዎች ያስረዳሉ።

ታዲያ ችግሮቹን ለመፍታት የበካይ ጋዝ ልቀትን መቀነስና የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂን መከተል እንዲሁም የተፈጥሮ ሐብት እንክብካቤን ማጎልበትና በደን ልማት ላይ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ተመራጭ መፍትሄዎች ናቸው። እነዚህም ዓለም የተስማማባቸው ሃቆች ናቸው፡፡ በተለይም በግብርና ምርታማነት ላይ መሠረቱን ለጣለ ምጣኔ ሐብት የአየር ንብረት ለውጥ ምን ያህል ተፅዕኖ እንዳለው መገንዘብ ይቻላል።  

ኢትዮጵያም ይህን ሃቅ ቀድማ በመረዳት የአየር ንብረት ለውጥ በግብርና ምርታማነት ላይ የሚያሳድረውን አሉታዊ ተፅዕኖ ለመቋቋም የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂ ነድፋ እየሰራች  ትገኛለች፡፡

ይህ ልማት ህዝቡን ተጠቃሚ ከማድረግ ባሻገር፤ ለአካባቢ ተስማሚ መሆኑን በተጨባጭ የተገኙ ውጤቶች ህያው ምስክር ናቸው፡፡ በመሆኑም ኢትዮጵያ የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂን በመጠቀም በአካባቢ ጥበቃ ላይ በማከናወን ላይ ያለችው ተግባራትና የተገኘው እመርታ ይበል የሚያሰኝ ነው።