NEWS

ለአገር አቀፍ ተደራዳሪ ፓርቲዎቹ በፀረ ሽብር አዋጁ ላይ ማብራሪያና ግብረ መልስ ተሰጠ

By Admin

January 09, 2018

በፀረ ሽብር አዋጁ መሻሻል፣ መሰረዝና መጨመር ባለባቸው ጉዳዮች ላይ ፓርቲዎች ድርድር አደረጉ፡፡

ተደራዳሪ ከሆኑት 14 አገር አቀፍ ፓርቲዎች ባለፈው ታህሳስ “በፀረ-ሽብር አዋጁ መሻሻል፣ መሰረዝ እና መጨመር አለባቸው” ያሏቸውን አንቀፆች በፅሑፍ ለኢህአዴግ ማቅረባቸው ይታወሳል።

በዛሬው የድርድር ሂደት ሶስቱ በተናጠልና 11 አገር አቀፍ ፓርቲዎች በጋራ ዋና ዋና ያሏቸውን የማሻሻያ ሃሳባቸውን በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ተደራዳሪ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ “የፖለቲካ ስነ-ምህዳር ያጠባሉ፣ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ላይ እንቅፋት ይፈጥራሉ” ያሏቸውን የመደራደሪያ ሃሳባቸውን አቅርበዋል።

ሁሉም ተደራዳሪ ፓርቲዎች “የአገሪቷ ፀረ-ሽብር ህግ አስፈላጊ ነው” ብለው እንደሚያምኑም ነው ያመለከቱት።

ተደራዳሪ ከሆኑት 11 አገር አቀፍ ፓርቲዎቹ በፀረ ሽብር አዋጅ ቁጥር 652/2001 ላይ “አሉን” ያሏቸውን አራት የማሻሻያ፣ ስድስት የሚሰረዙና አምስት የሚጨመሩ የአዋጁ የድርድር ሃሳቦች ላይ ማብራርያ አቅርበዋል።

በዚህም ኢህአዴግ የሽብር ድርጊት በባህሪው ካለው ውስብስብነት፣ የወንጀሉ አደገኛነት እና ጊዜ የማይሰጥ ከመሆኑ አኳያ ፀረ ሽብር ህጉ ዓለም አቀፋዊ ደረጃ ያሟላ፣ ሊሰርዝ እና ሊሻሻል የሚያስችል ህጋዊ መሰረት ያለው ምክንያት እንዳላገኘበት ምላሽ ሰጥቷል።

በዚህም ኢህአዴግ መሰረዝ አለባቸው የተባሉትን አራቱን እና መሻሻል አለባቸው ተብለው የቀረቡትን ስድስት የአዋጁን አንቀፆች በተመለከተ ያልተቀበለበትን ምክንያት አብራርቷል።

በአዋጁ ላይ መጨመር አለባቸው በተባሉት አምስት የአዋጁ አንቀጾች ላይ ግንባሩ እንደሚስማማ እና በአብዛኛው ተግባራዊ እየሆኑ ያሉ መሆናቸውንም አብራርቷል።

መኢብን ፈንድ የማቋቋሚያ እና ተከሳሾች በማወቅ እና ባለማወቅ የፈፀሙትን ጥፋት የማጣራት ሂደትን በተመለከተ ጥያቄ አቅርቧል።

ኢህአዴግ ከፈንድ ጋር በተያያዘ የሚታይ ጉዳይ ካለ እናየዋለን፤ “በማወቅ እና ባለማወቅ ፀረ ሽብር ህጉን ተላልፈው የሚገኙ ሰዎችን በተመለከተ አዋጁ የሚሻሻልበት አሳማኝ ምክንያት የለም” ሲል ምላሽ ሰጥቷል።

ፀረ ሽብር አዋጁ “ከአገሪቷ ህገ-መንግስት ጋር ይጣረሳል፣ ህገ-መንግስታዊ መሰረትም የለውም እንዲሁም ራሳቸውን ነፃ ታጋዮች ብለው የሰየሙ ለምን አሸባሪዎች ይባላሉ” የሚል ጥያቄ በኢራፓ በኩልም ቀርቧል።

“አዋጁ ህገ-መንግስታዊ ስርዓት የለውም ማለት በፍፁም የተሳሳተ እና በምክንያታዊነት ያልተደገፈ ነው” ሲል ኢህአዴግ ማብራሪያ ሰጥቶበታል።

ማንኛውም ግለሰብ ይሁን ድርጅት የውጭ እና የአገር ውስጥ ዜግነት ይኑረው በሽብርተኝነት ድርጊት ተሳትፎ ከተገኘ በፀረ ሽብር አዋጁ ጉዳዩ እንደሚታይ እና ስያሜም እንደሚያገኝ ገልጸዋል።

በመሆኑም ኦነግ፣ ግንቦት ሰባት፣ ኦጋዴን ነፃ አውጪ ይሁን ሌሎች አሸባሪ የሚለውን ስያሜ በኢፌዴሪ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አማካኝነት ስያሜው የተሰጣቸው ድርጅቶች መሆናቸውን ግንባሩ አስታውቋል።

ኢህአዴግ በገዳ ስርዓት አራማጅ በኩል የቀረበውን የማሻሻያ እና የመቀነስ የድርድር ሃሳብም እንደማይቀበል ይፋ አድርጓል።

ፓርቲዎቹ በአዋጁ ላይ ተጨማሪ ድርድር ለማድረግ ጥር 3 ቀን 2010 ዓ.ም ቀጠሮ ይዘው ተለያይተዋል።

ምንጭ፥ ኢዜአ