Artcles

ለጉባኤው ስኬት

By Admin

January 11, 2018

ለጉባኤው ስኬት

                                                     ደስታ ኃይሉ

በቅርቡ በመዲናችን የሚካሄደው የአፍሪካ ህብረት ጉባኤ ኢትዮጵያ ለአፍሪካዊያን ወንድሞቻችን ያደረገችውን አንኳር ጉዳዩች እንድንመለከት የሚያደርገን ነው። አገራችን ባለፉት ጊዜያት ያካሄደቻቸውን ጉባኤዎች በአፍሪካ አንድነት ድርጅት (ህብረት) መስራችነቷና የህብረቱ መቀመጫ ጭምር በመሆኗ ሳቢያ በአፍሪካዊያን ዘንድ ያላትን ተሰሚነት ማትረፍ ችላለች። የአፍሪካዊያን የችግር ጊዜ አጋርና መመኪያ በመሆኗ በአፍሪካዊያን ወንድሞቻችን ዘንድ የአህጉሪቱ ቃል አቀባይና ድምፅ እስከመሆን የደረሰች አገር ናት።

ኢትዮጵያ ለቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት (አ.አ.ድ) መመስረትና ለአሁኑም ለአፍሪካ ህብረት መጠናከር ያበረከተችውን ድርሻ እንዲሁም ለአፍሪካ አገራት ሰላም መሆን ጥረት እያደረገች ትገኛለች። ለአፍሪካ ህዝቦች ነፃነት፣ ሰላምና መረጋጋት እንዲሁም የልማት ቁርኝት ከማድረግ በዘለለ የአፍሪካ ድምፅ ሆና የአህጉሪቱ ጥቅሞች እንዲከበሩ ያደረገች ባለውለታ አገር ነች።

አገራችን እንደ ህብረተየ መስራችና እንደ ዋና መቀመጫነቷም የትኛውም የፖለቲካ ሥርዓት ይሁን የቱም በአፍሪካዊ ወንድማማችነትና መንፈስ ተቀብሎ በማስተናገድ፣ ጭቆናና በደልን፣ ግፍና ብዝበዛን በመቃወም አቅሟ የፈቀደውን ሁሉ አድርጋለች። አለመግባባትና ግጭቶች ሲከሰቱም በማብረድ ረገድ ተሳትፎዋ ቀላል አልነበረም። በአህጉሪቱ የሚፈጠር አለመረጋጋትን በመረጋጋት በመተካት፣ የተጎዱትን በማቋቋምና የተቸገሩትን በመርዳት የማይናወጥ አቋሟን ስታንጸባርቅ ኖራለች።

ኢትዮጵያ አህጉሪቱን ከቅኝ አገዛዝ ሙሉ በሙሉ በማውጣትና አፍሪካውያን ነጻነታቸውንና ክብራቸውን ለመመለስ እንዲሁም አፍሪካን ወደ ኢኮኖሚ ዕድገት ለመምራት በተደረገው ትግል የማይነጥፍ አስተዋጽኦ ስታደርግም ቆይታለች።

ከድርጅቱ ምስረታ በፊት አፍሪካን ለሁለት ከፍሏት በነበረው በክዋሜ ንኩርማና በብዘሁኑ ቡድኖች መካከል የነበረው የአካሄድና የአስተሳሰብ ልዩነት እንዲፈታ በማድረግ ታላቅ አስተዋጽኦ አበርክታለች። ሀገራችን ወራሪውን የጣሊያን ኃይል ታግላ ነጻነቷን በማስመለስ ያስመዘገበችው ድል በአህጉሪቱ ለነጻነት ሲደረግ የነበረውን ትግል በማቀጣጠል በርካታ ሀገሮች ነጻነታቸውን እንዲጎናጸፉ አድርጓል።

እ.ኤ.አ በ1960ዎቹ አፍሪካውያን በቅኝ አገዛዝ ሲሰቃዩ በዓለም-አቀፍ ፍርድ ቤት እየቀረበች በሕግ ትሟገትላቸውና ትከራከርላቸው የነበረችውም አገራችን ናት። በቅኝ አገዛዝና በአፓርታይድ ሥርዓት ሲሰቃዩ የነበሩ አፍሪካውያን የሞራል፣ የዲፕሎማሲና የቁሳቁስ ድጋፍ በማድረግ ሚናዋንም በሚገባ ተወጥታለች።

በንጉሱ ዘመን ሀገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን ጥሪ በመቀበል የሰላም አስከባሪ ሃይሏን ለሁለት ዓመታት በኮሪያ ልሳነ ምድር አዝምታለች። በአሁኗ ኮንጎ ዴሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ የነበረውን ችግር ለመፍታትም የኢትዮጵያ ሠላም አስከባሪ ኃይል እ.ኤ.አ. ከ1960 እስከ 1964 በነበረው ጊዜ ውስጥ ግዳጁን ሥነ-ምግባር በተሞላበትና ሁኔታ የተሳካ ሥራ አከናውኗል። ለደቡብ አፍሪካ፣ ለናሚቢያና ለዚምባቡዌ የነጻነት ትግል ወታደራዊ ስልጠና በመስጠት ያደረገችው አስተዋጽኦም በታሪክ ሲወሳ የሚኖር ነው።

ከደርግ ግብዓተ-መሬት በኋላ ሰላም መርሁ የሆነው መንግስታችን አፍሪካዊ አስተዋጽኦውንና ሃላፊነቱን ከምንጊዜውም በላቀ ሁኔታ ተወጥቷል፤ እየተወጣም ነው። በዚህ መሰረትም በሩዋንዳ እ.ኤ.አ በ1990ዎቹ በተከሰተውና የዓለምን ሕዝብ ባስደነገጠው የዘር ማጥፋት እንቅስቃሴ ሰላም እንዲያስከብሩ ከተደረጉት ሀገሮች አንዷ ኢትዮጵያ እንድትሆን አስችሏል።

አዲሱ የፈረንጆች ሚሌኒየም ሲጀመር በቡሩንዲ ሁቱና ቱትሲ የተባሉ ጎሳዎቿ ግጭት ውስጥ ነበሩ። ዘር ለይቶ የተፈጠረውን ዘግናኝ ድርጊት ለማስቆም በአፋጣኝ ሠላም አስከባሪ ኃይላቸውን እንዲልኩ ከተደረጉት አገሮች መካከል ኢትዮጵያ ቀዳሚዋ ናት። በዚህም ታሪካዊ አስተዋጽኦዋን አበርክታለች። በላይቤሪያም እንዲሁ አፍሪካዊ ሃላፊነቷን ተወጥታለች።

በሱዳን ዳርፉር ግዛት ከሌሎች ሀገሮች ጋር በመሆን ባሰማራችው ሠላም አስከባሪ ሃይልም የእርስ በርስ ግጭት እንዳይከሰት በማድረግ ላይ መሆኗም ይታወቃል። ሱዳንና ደቡብ ሱዳን በይገባኛል በሚከራከሩበት የአብዬ ግዛት ከዓለም ብቻውን የተሰማራ ሠላም አስከባሪ ኃይል በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጥላ ሥር በማሰማራት በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነቷን ያሳደገ ተግባር እያከናወነች ነው።

አገራችን በሁለቱም ሀገሮች መንግሥታትና ህዝቦች ያላት አክብሮትም ከፍተኛ ነው። ሀገራችን በምሥራቅ አፍሪካ ሀገሮች ሰላም፣ ጸጥታና መረጋጋት ከፍተኛ ሚና እየተጫወተች ባለችው ሚና በሶማሊያ የነበረውን መንግሥት- አልባነትና አክራሪነት በመታገልም ውጤታማ መሆን ችላለች። በአሁኑ ወቅትም በአሚሶም ጥላ ስር ሆና አሸባሪነትን ከምስራቅ አፍሪካ ለማስወገድ በሚደረገው ጥረት ግንባር ቀደም ተሳታፊ ሆና ተግባሯን በአፍሪካዊ ወንድምነት እየተወጣች ትገኛለች።

እርግጥ ሰላማቸው የተረጋገጠ፣ በኢኮኖሚያቸው የበለጸገና ዴሞክራሲ ያበበባቸው ጎረቤቶች የጋራ ጥቅም መሠረት መሆናቸው የማይታበይ ቢሆንም፤ ሀገራችን ከዚህ ባለፈ ለጎረቤቶቿ ህዝቦች ሰላም ያለማሰለስ በመሥራት ላይ ትገኛለች። በሞሮኮና በአልጄሪያ፣ ናይጄሪያ ውስጥ የቢያፍራ የመገንጠል እንቅስቃሴን እንዲሁም በሱዳን የቤኛኛ እንቅስቃሴ ከማዕከላዊ መንግሥታት ጋር የነበራቸውን ግጭት በመፍታት ታሪካዊ አስተዋጽኦ ማበርከቷም የሚዘነጋ ሃቅ አይደለም።

የኢትዮጵያ ሚና ሰላምን በማስከበር ብቻ የታጠረ አይደለም። ከዚህም አልፋ እያስመዘገበችው ያለው ልማታዊ እመርታ በአፍሪካዊያን ወንድሞቿ ዘንድ ተመራጭ እንድትሆን አድርጓታል። ኢትዮጵያ በኢኮኖሚው መስክ ያላት አህጉራዊ ትብብር ኮሜሳ በሚሰኘው በምሥራቅና የማዕከላዊ አፍሪካ የጋራ ገበያ ትስሰር የተጠናከረ ውህደት ለመፍጠር ያላት ሚናም ከፍተኛ ነው።

በመሠረተ-ልማት ግንባታ መስክ ንግድና ኢንቨስትመንትን ለመሳብም ጥረት ታደርጋለች። የኢኮኖሚ ዕድገት ለማምጣት ተሳታፊና ተጠቃሚ ለማድረግም በመሥራት ላይ ነች። ከጅቡቲ፣ ሱዳንና ደቡብ ሱዳን ጋር የመንገድ ግንኙነት በመፍጠር ለጋራ ጥቅም በመትጋት ላይ ትገኛለች።

ከጅቡቲ ጋር የሚያገናኝ የባቡር መሥመር ግንባታው እየተገባደደ ሲሆን፤ ከኬንያ ጋር የሚያገናኘው መሥመርም ዝርጋታው ተጠናቆ ስራ ለመጀመር ታሪፍ ወጥቶለታል። ለጅቡቲ የኤሌክትሪክ ኃይል በማቅረብ ተጠቃሚ እንድትሆን ከማድረጓም በላይ፤ ኬንያንም በተመሳሳይ ሁኔታ እንድትጠቀም በመጣር ላይ መሆኗን መረጃዎች ያስረዳሉ።  

አገራችን በምትከተለው ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ መርህም ተቀባይነት ያላት ናት። በዚህ አስተሳሰቧም የአባይ ውኃ አጠቃቀም ፍትሃዊ በሆነ መልኩ መጠቀም አስፈላጊነቱን አምናም እየሰራች ነው። ይህ ፍትሐዊ አስተሳሰቧም በአፍሪካዊያን ዘንድ ተቀባይነት ያለው ነው።

በአህጉሪቱ መልካም አስተዳደርና ዴሞክራሲን ለማስፈን የተያዘውን ጥረትም በአፍሪካ እርስ በርስ መገማገሚያ ስልት (ኔፓድ) በንቃት ተሳታፊ ናት። በታላቁ መሪያችን በአቶ መለስ ዜናዊ ወቅትም ይሁን በአቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ወቅት ኔፓድ ውስጥ ወሳኝ ተሳታፊ ሆና ቀጥላለች። እነዚህ ተግባራቷ አፍሪካዊያን በልዩ ዓይን እንዲያዩዋት አድርገዋል። በዚህም ሳቢያ ጉባኤያቸውን እዚህ አዲስ አበባ ውስጥ ለማድረግ የማይፈልጉ የአፍሪካ መሪዎች የሉም። በቅርቡ ለሚያካሂዱት ጉባኤ ስኬት ሁሉም የድርሻውን በመወጣት የአገራችንን ገፅታ ይበልጥ ማጉላት ይኖርበታል።