Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ሕገ-መንግስቱን በማወቅና ባለማወቅ መካከል

0 666

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ሕገ-መንግስቱን በማወቅና ባለማወቅ መካከል

                                                            ይልቃል ፍርዱ

ሕገመንግስቱን በውል ጠልቆ የመረዳትና ተግባራዊ የማድረግ ችግር ገዝፎ ይታያል፡፡ አይደለም በሕዝቡ ግንዛቤ ለመፍጠር በኃላፊነት ቆመው ሕገመንግስቱን ተግባራዊ እናደርጋለን በሚሉት ወገኖች ዘንድም ሕገመንግስቱ የደነገጋቸውን፤ የያዛቸውን አንቀጾች በትክክል ያለመረዳት ችግር መኖሩ ግንዛቤን ካገኘ ሰንብቷል።

ሕገመንግስቱ የሕጎች ሁሉ የበላይ ሕግ ነው፡፡ በመሆኑም በሁሉም ዘንድ ሊከበርና ሊተገበርም ይገባዋል፡፡

የመንግሰት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽቤት በሕገመንግስቱና በሀገራዊ ገጽታ ግንባታ ረገድ ለሕዝብ ክንፍ ተወካዮችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በደብረ ዘይት ከተማ የሶስት ቀናት የውይይት መድረክ አዘጋጅቶ ነበር፡፡ መድረኩን የከፈቱት የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽቤት ኃላፊ ሚኒስትር ዶ/ ነገሪ ሌንጮ ናቸው፡፡

የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት ሚኒስትር ነገሪ ከሁሉም በላይ አኩሪ የሆኑ ባሕሎቻችንንና እሴቶቻችንን በማዳበር የገጠሙንን ችግሮች ለመፍታት ጠንክሮ መስራት እንዳለበት፤ ሀገራዊ ሰላማችንን ጠብቆ የተመዘገቡትን ፈጣን ሀገራዊ የኢኮኖሚ ልማትና እድገት ውጤቶችን ለማስቀጠል በርትቶ መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ ሀገራችን ከድሕነት ተላቃ በእድገት ጎዳና ላይ የምትገኝ በመሆንዋ ሀገራዊ ሰላማችንንና እድገታችን ጠብቀን መራመድ እንደሚገባ በዚህ ረገድም የሕዝብ ክንፉ ሕዝቡን የሚወክል በመሆኑ ከፍተኛ ሀገራዊ ድርሻና ኃላፊነቱን መወጣት እንደሚጠበቅበት፤ ከሁሉም በላይ የቆዩ ባሕላዊ እሴቶቻችንን በመጠበቅ፣ በመከባበር፣ በመደማመጥና በመቻቻል ማንኛውንም ችግር በሰላም በመፍታት አኩሪ እሴቶቻችንን እና ባሕላችንን ጠብቀን መሄድ እንደሚገባን፤ በዚህም የሀገራችንን ሰላም መጠበቅ እንዳለብን ገልጸዋል፡፡

በሕገመንግስቱ ላይ የመወያያ ጽሁፍ ያቀረቡት የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዚደንት አቶ በሪሁ ተወልደ ብርሀን ሲሆኑ የተሳታፊዎችን ቀልብና ስሜት ሙሉ በሙሉ በገዛ መልኩ የሕገመንግስቱን ምንነት ከዚህ በፊት ማንም ገልጾና አስረድቶ በማያውቀው መልኩ፤ ተሳታፊውም እስኪደመም ድረስ በጣም በግልጽነት፣ የበለጠ መረዳትና ግንዛቤ እንዲፈጠር አድርገው አስረድተዋል፡፡

ይህ የአቶ በሪሁ ጥናትና ገለጻቸው ለካንስ ሁላችንም ከዚህ ቀደም ሲል ሕገመንግስቱን አናውቀውም ነበር የሚል ስሜት በመላው ተሳታፊ ዘንድ እንዲፈጠር አድርጓል፡፡ አዎን ሕገመንግስቱን በስም ከመጥቀስ በዘለለ በውስጡ የያዘውን ግዙፍ ሀገራዊ ፋይዳ ያላቸውን አንቀጾች ምንነት ከፍተኛ ኃላፊዎች ሕብረተሰቡም በቅጡና በውል አያውቀውም፡፡

ለሰብአዊ መብት ጥበቃ የሰጠውን ግዙፍ መብት፤ ለመናገር በነጻነት ሀሳብን ለመግለጽ ለፕሬስ ነጻነት፤ ለግለስብ ዜጋ የሚሰጠውን ሕጋዊ የመብት ጥበቃ፤ የመሬትና ይዞታና ባለቤትነትን በተመለከተ፤ የፌደራል መንግስቱን ስልጣንና የክልሎችን መብት በተመለከተ፤ ሙስናን ኪራይ ሰብሳቢነትን፤ በሕዝብና በመንግስት ስልጣን ያለአግባብ መጠቀም፤ በሕዝብ ላይ የመልካም አስተዳደር ችግር መፍጠር ወዘተ ጸረ ሕገመንግስት ተግባራት መሆናቸውን በግልጽ አብራርተዋል፡፡

ሕገመንግስቱን ጠንቅቆ አለማወቅ፤ በአግባቡ ለመረዳት አለመቻል ነው የተዛባ ትርጉም ለሚሰጡት ወገኖች መነሻ የሆናቸው፡፡ ሕገመንግስቱ ምን ያህል አንቀጾችን እንኳ እንደያዘ ለምን እንደቆሙ የማሳወቅ ስራ በስፋት አልተሰራም፤ ሕዝቡ በቂና የተጣራ ግንዛቤ እንዲያገኝ አልተደረገም፡፡ይህም ዋናው ክፍተት ነው፡፡

አቶ በሪሁ ሀገራችን ኢትዮጵያ በቀድሞው ዘመን በፍትሀ ነገስት ትተዳደር እንደነበር፤ የመጀመሪያው ሕገመንግስት በቀዳማዊ ኃይለስላሴ ዘመን በ1923 አ/ም እንደተቀረጸ፤ የመጨረሻው ስልጣን ስዩመ እግዚአብሄር ነን ብለው አዋጅ ያስነገሩት ንጉሰ ነገስቱ ብቻ ሀገር የመምራትና የማስተዳደሩ ኃላፊነት እንዳላቸው፤ ስልጣኑ ሲወርድ ሲዋረድ  በመጣው ከንጉሳዊ ቤተሰቦች ተወላጆች መውጣት እንደማይችል በሕገመንግስቱ ሰፍሮ ይገኝ እንደነበረ አስረድተዋል፡፡

የ1923ቱ ህገመንግስት በ1948 አ/ም ማሻሻያዎች ተደርገውበታል፡፡ ከዚያን በኋላ ሌላ አዲስ ሕገመንግስት የተቀረጸው ደርግ ወደ ስልጣን ከመጣ በኋላ ነው፡፡

በ1987 የወጣውና አሁን በስራ ላይ ያለው የኢፌዲሪ መንግስት ሕገመንግስት 106 አንቀጸች ያሉት ሲሆን ከነዚህ ውስጥ ከ1/3ኛው በላይ ስለሰብአዊ መብቶች የሚደነግግ ነው፡፡ ቀድሞ በነበሩት ሕገመንግስቶች ጠንካራ ማእከላዊ መንግስት በመመስረቱ የክልሎች ልማት ተዳክሞአል፡ ጸረ ልማት ሆነዋል፤ አምባገነንነትን መስርተዋል፤ ብዝሀነትን ያለማስተናገድ ሰፊ ችግር ታይቶአል፡፡ የማደግ ችግር፤ ኢዲሞክራሲያዊነት በመስፈኑ የተለያዩ የሕዝብ ንቅናቄዎችና አመጾችም በተለያዩ የሀገሪቱ ክልሎች እንደነበሩ አቶ በሪሁ  አስረድተዋል፡፡

እንደ አቶ በሪሁ አገላለጽ ባለፉት ስርአቶች የተለያዩ ብሔራዊ ጭቆናዎች ነበሩ፡፡ ይህን በተመለከተ ፕሮፌሰር እንድርያስ እሸቴ በ1965 (እኤአ) አውስትራሊያ በትምህርት ላይ በነበሩበት ግዜ ስለብሔራዊ ጭቆናና ስለብሔራዊ ማንነት መጻፋቸውን አቶ በሪሁ ገልጸዋል፡፡ በአሀዳዊ ስርአት የራስ አስተዳደር የሚባል ነገር የለም፡፡ የፌደራል ሕግመንግስቱ በብዙ መመዘኛ በኢትዮጵያ ታሪክ እጅግ የተሻለው አለም አቀፍ ሕጎችንና ድንጋጌዎችን ያካተተ ለዜጎችም ለሀገሪቱም ተመራጭ  የሆነ ነው፡፡

ሆኖም ግን ኢትዮጵያ ለዘመናት ከኖረችበት አሀዳዊ ስርአት በአንድ ግዜ ወደ ፌደራል ስርአት የተደረገ ሽግግር በመሆኑ ነው ግርታን፣ መደናገርን፣ የተዛባና ያልተስተካከለ ትርጉም በሚሰጡት ኃይሎች ውዥንብር መንዣ የሆነው፡፡ አንድ ሕገመንግስት ሀገራዊ ራእይን፣ እድልንና ተስፋን ሰንቆ የያዘ ነው፡፡ ሕገመንግስቱ በሕዝቦች መካከል የነበሩ የተዛቡ ታሪካዊ ግንኙነቶችን የብሔር ብሔረሰቦች መብት፤ ባሕላቸው፣ እምነታቸው፣ እሴቶቻቻቸው ወዘተ የሁሉም በእኩልነት የተከበረባት እንዲሆን አድርጎአል፡፡

በፌደራል የተቀበለችው የፌደራለ ስርአት መንግስቱና በተወካዮች ምክር ቤት ውስጥ በሀገር አቀፍ ደረጃ በሚደረግ ምርጫ ወኪሎቻቸውንና ተሳታፊያቸውን የሚልኩበት፤ ለክልላቸው ልማትና እድገት በፌደራል መንግስቱ በሚወጣላቸው የበጀት ቀመር መሰረት ክልላቸውን የሚያስተዳድሩበት፤ በልማት እንዲራመድ የሚያደርጉበትና ክልላቸውን በነጻነት የሚመሩበት የራሳቸውን የክልል ፓርላማ መስርተው የሚያስተዳሩበት ነው፡፡

የክልሎች ሕገመንግስት መነሻው የፌደራሉ ሕገመንግስት ነው፡፡ ከፌደራል መንግስቱ ሕገመንግስት የሚቃረን ሕግ ሊያወጡ አይችሉም፡፡ ሕግመንግስቱ መንግስት የዜጎችን መብት የመጠበቅ ግዴታ እንዳለበትም በግልጽ ይደነግጋል፡፡

ይህ ብቻ አይደለም፤ ሕገመንግስቱ የሀሳብ ልዩነቶች ያለገድብ እንዲንሸራሸሩ፤ የመናገርና ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት የተከበረ መሆኑን በገልጽ ያስቀመጠ ነው፡፡ መልካም አስተዳደር ስንል የሕገ መንግስት ጉዳይ ነው፡፡ መልካም አስተዳደርን አለማስፍን፤ ሕዝብን በአግባቡና በስርአቱ አለማገልገል፤ በሕዝብ ስልጣን ያለአግባብ መጠቀም የመንግስትና የሕዝብን ሀብት በሙስና መዝረፍ ሕገመንግስታዊ ጥሰት ነው፡፡

በየትኛውም መስፈርት የራስ ያልሆነውን መሸጥም ሆነ መለወጥ ወንጀል ነው፡፡ መሬትም ሆነ ሌሎች ማእድናት በአጠቃላይ የሀገሪቱ የተፈጥሮ ሀብት በሕገመንግስቱ መሰረት የሀገሪቱ ሕዝቦች የጋራ ሀብት ነው፡፡ የታሪክ፣ የቋንቋ፣ የኃይማኖት፣ የባሕል ልዩነቶች ቢኖሩም በጋራና በአንድነት ተከባብረን፣ ተደማምጠን፣ ተቻችለን፣ የጋራ ሀገርን በጋራ እናሳድግ፣ እናልማና ከድሕነት እንውጣ፤ አንድ ጠንካራ የፖለቲካ የኢኮኖሚ ማሕበረሰብ እንፍጠር፤ አንዱ ካለአንዱ አያድግም ነውና ዋናው የሕገመንግስቱ መልእክት፡፡ ብዝሐነትን በማክበር አብሮነትን፣ መልካም ግንኙነትን፣ ስነልቦናዊ አንድነታችንን ወዘተ በማጎልበት ሰላማችንንና እድገታችንን ጠብቀን የተሻለች፣ ያደገችና የበለጸገች ሀገር እንፍጠር ነው ዋናው መሰረተ ሀሳብ፡፡

የኢፌዴሪ ሕገ-መንግስት በ106 አንቀጾች (እና በርካታ ንኡስ አንቀጾች) በግልጽና በማያሻማ ሁኔታ የሚከተሉትን አስፍሯል፤

ዜግነትን (አንቀጽ 6) የሕዝብ ሉአላዊነት (አንቀጽ 8) የሕገመንግስት የበላይነት (አንቀጽ9) ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች (አንቀጽ 10) የመንግስት አሰራርና ተጠያቂነት (አንቀጽ 12) የሕይወት፤ የአካል ደሕንነትና የነጻነት መብት (አንቀጽ14) ኢ-ሰብአዊ አያያዝ ስለመከልከሉ (አንቀጽ 18) የተያዙ ሰዎች መብት (አንቀጽ 19) የኃይማኖት የእምነትና የአመለካከት ነጻነት (አንቀጽ 27) የአመለካከት እና ሀሳብን በነጻ የመግለጽ መብት (አንቀጽ 29) የንብረት መብት (አንጽ 40) የሠራተኞች መብት (አንቀጽ 42) የፌደራል መንግስት ስልጣንና ተግባር (አንቀጽ 51) የክልል ስልጣንና ተግባር (አንቀጽ 52) ሌሎችንም በዚሁ መልክ ይዘልቃል፡፡ ሕገ መንግስቱ አለም አቀፍ ሕግጋትን ያካተተ፤ ለዜጎች ሁለንተናዊ መብትም የማይሸራረፍ ዋስትናን ያጎናፀፈ ነው፡፡

ለምሳሌም ያህል ንቀጽ 9 የሕገመንግስት የበላይነት በሚለው ስር ንኡስ አንቀጽ 1 ሕገመንግስቱ የሀገሪቱ የበላይ ሕግ ነው፡፡ እንዲሁም የመንግስት ማንኛውም አካል ወይም ባለስልጣን ውሳኔ ከዚህ ሕገመንግስት ጋር የሚቃረን ከሆነ ተፈጻሚነት የለውም ይላል፡፡  እንዲሁም አንቀጽ 12 የመንግስት አሰራርና ተጠያቂነት በሚለው አንቀጽ 1 ላይ የመንግስት አሰራር ለሕዝብ ግልጽ በሆነ መንገድ መከናወን አለበት ይላል፡፡ አንቀጽ ሁለት በበኩሉ ማንኛውም ኃላፊና የሕዝብ ተመራጭ ኃላፊነቱን ሲያጎድል ተጠያቂ ይሆናል  ይላል፡፡ አንቀጽ ሶስት ሕዝቡ በመረጠው ተወካይ ላይ እምነቱን ባጣ ግዜ ከቦታው ለማንሳት ይችላል ይላል፡፡ ይህ ደግሞ ዲሞክራሲያዊና ሰብአዊ መብትን የማክበርና የማስከበር ጉዳይ ነው፡፡

ባጠቃላይ፣ ይህ ከላይ በመጠኑ የጠቃቀስናቸው እንደመነሻ የሚወሰዱ ሲሆን፤ እራሳችንን በራሳችን ሕገ መንግስቱን ምን ያህል አውቀዋለሁ? ብለን በመጠየቅ፤ ይህን በልካችን የተሰፋውን ህገመንግስታችንን የበለጠ ለማወቅ ጥረት እናድርግ፤ እሱን አበጥሮ ማወቅ ማለት ስለሁለንተናዊ መብታችን አበጥሮ ማወቅ ማለት ነውና እናስብበት። ይህን ማለት ያስፈለገበት አቢይ ምክንያት ሕገ-መንግስቱን በማወቅና ባለማወቅ መካከል ሰፊ ክፍተት በመታየቱ ነው።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy