Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

መሰናክሎችን ተቋቁሞ ስኬታማ የሆነው ኢኮኖሚያችን

0 289

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

መሰናክሎችን ተቋቁሞ ስኬታማ የሆነው ኢኮኖሚያችን

                                                             ይልቃል በፍርዱ   

በምእራቡና በታዳጊ ሀገራት መካከል ያለውን ኢኮኖሚያዊ እድገት አስመልክቶ የሚሰጡ የምሁራን አስተያየቶችን የመቀበሉ ሁኔታ እንደየሀገራቱ የፖለቲካ መሪዎች ወይንም የፖለቲካ ፓርቲዎች የአመለካከት አድማስ የሚመዘን ነው የሚሆነው፡፡

“ታዳጊ” ተብለው የሚጠሩት ሀገራት እምቅ የተፈጥሮ ሀብት እንዳላቸው ምእራባውያን ጠንቅቀው ያውቃሉ፡፡ የእነዚህ ሀገራት መሰረታዊ ችግሮች በእውቀትና በቴክኖሎጂ የታነጸ፤ የተማረ ኃይል አለመኖር ወይንም አንሶ መገኘት፤ እንዲሁም ብቁ የዘመኑ ቴክኖሎጂ ባለቤት አለመሆናቸው ሲሆን ይህም ባላቸው ሰፊ የተፈጥሮ ሀብት ለመጠቀም እንዳይችሉ አድርጓቸዋል፡፡

በዋነኛነት ታዳጊ ሀገራት ራሳቸውን ከተረጂነትና ደሀነት ለማውጣት የሚቀርጹዋቸው ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች በተጨባጭ ሀገራዊ ሁኔታቸውን መሰረት ያደረገ ሳይሆኑ በውጭ መንግስታት ወይንም ግዙፍ አለማቀፍ ተቋማት ተፅእኖ ስር የወደቁ ናቸው፤ ይህም፣ እስከዛሬ እንደታየው ፖሊሲዎቻቸው ውጤታማ ሊሆኑ አልቻሉም፡፡

ታዳጊ ሀገራት ለልማትና ለእድገት የሚቀርጹት ፖሊሲና ስትራቴጂ በራሰቸው ሀገራዊ እውነት ላይ ብቻ መሰረት ያደረገ፤ ችግሮቻቸውን በአግባቡ የሚፈታና የሚመልስ፤ ሕዝባቸውን ከደሀነትና ኋላ ቀርነት ሊያወጣ የሚችል፤ ስራ አጥነትን የሚቀርፍ ሀገራቸውን በሚታይ የልማት ጎዳና ሊያራምድ የሚችል መሆኑን ደግመው ደጋግመው ማረጋገጥ ይጠበቅባቸዋል፡፡ በዚህ መልኩ የተቀረጸ ፖሊሲም ሆነ ስትራቴጂ የተጠበቀወን ውጤት ሊያስገኝ ይችላል፡፡ የሌላ ሀገር የኢኮኖሚ እድገት ሞዴልን በተወሰነ ደረጃ መውሰዱ ምንም ችግር ላይኖረው ይችላልዐ ሙሉ በሙሉ መገልበጥ ግን ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል፡፡

ኋላቀር የሆነና በባሕላዊ ግብርና ላይ ተመስርቶ የኖረን ኢኮኖሚ ወደፈጣን ልማትና እድገት ፈጥኖ ለማስገባት ብዙ የቤት ውስጥ ስራዎችን መስራትንም ይጠይቃል፡፡ በሕዝቡ ውስጥ ሰፊ የለውጥ አምጪነት ስነልቡና እንዲዳብር ማድረግ፤ አዲስ የለውጥና የስራ ተነሳሽነትን መንፈስ እንዲሰፍን ጠንክሮ መስራት የመጀመሪያው ደረጃ ነው የሚሆነው፡፡ ምክንያቱም የሚመጣው ስርነቀል ለውጥ እንግዳ ስለሚሆንበት ሊቃወመው የሚችልበት አጋጣሚ ሰፊ ነው፡፡ ሕዝብ አምኖ ሲቀበለው ደግሞ ስርነቀል ለውጥ ያስመዘግባል፡፡ ኢትዮጵያ የተከተለችው መንገድ ይሄንኑ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ለዘመናት ያልነበሩ የማይታሰበና ሊሆን ይችላል ተብሎ ያልተገመተ ኢኮኖሚያዊ እድገትን ማስመዝገብ ችላለች፡፡ ኢሕአዴግ ተጨባጭ ሀገራዊ ሁኔታን መሰረት ያደረገ ከደሀነትና ኃላቀርነት ለመውጣት ወደተሻለ የእድገት ምእራፍ እንድትሸጋገር በቀየሳቸው ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች፤ በተለይም በመጀመሪያው አካባቢ ከአይኤምኤፍና ከወርልድ ባንክ ጠንካራ ተቃውሞና እኛ ባልናችሁ መንገድ ብቻ ሂዱ የሚል ግፊት የነበረበት ቢሆንም በተግባር በታየ ለውጥ ማሸነፍ ችሎአል፡፡

ኢሕአዴግ እናንተ ማገዝ ያለባችሁን አግዙን ለሀገራችን ልማትና የኢኮኖሚ እድገት የሚያዋጣውን መንገድ የምናውቀው እኛ ነን በሚል የቀየሰውን የኢኮኖሚ እድገት ፖሊሲና ስትራቴጂ በከተማ ልማት፤ በመሰረተ ልማት መስፋፋት፤ በኮንስትራክሽን ዘርፍ፤ በግድብና፣ የኃይል ማመንጫ ግንባታ፤ በገጠር ልማት ወዘተ በአጭርና በረዥም ግዜ ግብ ውስጥ በማካተትና ተግባራዊ በማድረግ በተጨባጭ የሚታዩ ለውጦችን አስመዝግቧል፡፡

በጤናው አገልግሎት ዘርፍ ከጤና ጣቢያ እስከ መካከለኛና ከፍተኛ ጤና ጣቢያዎች አልፎም ሆስፒታሎችን በመገንባትና በማስፋፋት፤ በትምህርቱ መስክ ከአንደኛ ደረጃ እስከ ኮሌጆችና ዩኒቨርሲቲዎች ድረስ በማስፋፋት ቀድሞ ከነበሩበት እጅግ አነስተኛ ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ በማሳደግ፤ በገጠር ልማት ፖሊሲው እርሶ አደሩንና አርብቶ አደሩን በዘመናዊ መልክ ተጠቃሚ ያደረጉ ስኬቶች ተመዝግበዋል፡፡

በተለይም አንድን ሀገር በከፍተኛ ደረጃ ሊያሳድግ የሚችለው ለንግድ ልውውጡ አመቺና ቀልጣፋ የሆኑ ደረጃቸውን የጠበቁ ዘመናዊ መንገዶችን በመስራትና በማስፋፋት፤ ከተሞችን ከከተሞች የሚያገናኙ አስፋልቶችን በመዘርጋት ቀድሞ መንገድ ባልነበረባቸው አካባቢዎች ደግሞ መንገዶችን በመስራትና በማስፋፋት የንግድ ልውውጡ በሕብረተሰቡም ዘንድ ሩቅ የነበሩ አካባቢዎችን  በቀላሉ በመድረስ እንዲቀራረብ ማድረግ ችሎአል፡፡ ይህ ደግሞ ለእድገት አገር ሁለንተናዊ እድገት መሰረት የሆነ ትልቅ ስራ ነው፡፡

ቀላል የከተማ ባቡር መስመር ግንባታ በአዲስ አበባ፤ የውጭና የገቢ ንግዱን የሚያቀላጥፈው በቅርቡ የተመረቀው የኢትዮ-ጅቡቲ የርቀት የባቡር መስመር ግንባታው ተጠናቆ ስራ መጀመሩ፤ የተለያዩ ኃይል ማመንጫ ግድቦች ግንባታ 6000 ሜጋ ዋት ሊያመነጭ የሚችለውን የታላቁን ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ጨምሮ ለሀገራዊ የኢኮኖሚ እድገታችን መስፈንጠር ያላቸው ፋይዳ እጅግ የገዘፈ ነው፡፡

በመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን የተወጠኑት እቅዶች የተለጠጡና የተጋነኑ ናቸው ተብሎ የተነገረ ቢሆንም በእቅዱ መሰረት ለመስራት የቻሉት ከፍተኛ ሀገራዊ የኢኮኖሚ እድገት ለውጥ እንዲመጣ በማድረግ ረገድ ከነጉድለታቸው ውጤታማ የነበሩ ሲሆን፤ ሳይሰሩ የቀሩትና ወደ ሁለተኛው የትራንስፎርሜሽንና እቅድ ዘመን ተሸጋግሩትም በመሰራት ላይ ይገኛሉ፡፡

ከመጀመሪያው የእቅድ ዘመን ትግበራ ብዙ ልምዶችን የቀሰምን፤ ከድክመቶቻችንም ለጥንካሬ የሚበጁ ተሞክሮዎችን የወሰድን በመሆኑ የአሁኑ እቅድ ትግበራ ከበፊቱ በተሻለ ሁኔታ በመከናወን ላይ ይገኛል።

ሀገራችን በብዙ መስኮች ያስመዘገበቻቸው የልማትና የኢኮኖሚ እድገት ስኬቶች ከእኛም አልፎ በሌሎች ሀገራት በምሳሌነት የሚጠቀሱ ሆነዋል፡፡ በመጀመሪያው አካባቢ ይቃወሙ የነበሩት ምእራባውያን በተጨባጫ ባዩት የኢኮኖሚ እድገት ስኬትና ሞዴልነት የተሳካ እድገት ለመመዝገብ በመቻሉ ኢትዮጵያን በተጠቃሽ ምሳሌነት እያወደሷት ይገኛሉ፡፡ ሌሎች ሀገራትም ከሀገራችን ልምድና ተሞክሮ በመውሰድ ላይ ይገኛሉ፡፡

የዘመናዊና አለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎች መስፋፋት፤ ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት በአለም ቅርስነት የተመዘገቡ ከአስራ አንድ በላይ ታሪካዊ ቦታዎችና መንፈሳዊ እሴቶች፤ ከአስራ ሁለት በላይ የስነፅሁፍ ስራዎች ያሏት ሀገር መሆንዋ ተመጣጭ የቱሪዝም መዳረሻ እያደረጋት ይገኛል፡፡

ኢሕአዴግ በቀረጸውና ስኬታማ በሆነው የኢኮኖሚ ፖሊሲና ስትራቴጂ መሰረት በሀገር ውስጥ የተመዘገበው ስርነቀል እድገት እንዳለ ሆኖ የውጭ ኢንቨስትመንትን በመሳብ ረገድ በአለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂ የሆኑ የተለያዩ ሀገራት ኩባንያዎች በተለያየ ዘርፍ እውቀቱ፣ ልምዱና እውቅናው ያላቸው ሁሉ በሀገራችን ገብተው በመስራት ላይ ይገኛሉ፤ ለዜጎቻችን የልምድና የእውቀት ሽግግርም በማድረግ ላይ ናቸው፡፡

በኢትዮጵያ ገብተው ለመስራት ጥያቄ የሚያቀርቡ አለም አቀፍ ኢንቨስተሮች ቁጥር ከግዜ ወደግዜ እየጨመረ በመሄድ ላይ ይገኛል፡፡ በአፍሪካና በአለም እውቅናን ያተረፈ፣ በተደጋጋሚም ተሸላሚ የሆነ እጅግ ዘመናዊ የሆኑ፣ የወቅቱን ምርጥ ቦይንግ አውሮፕላኖች በባለቤትነት የያዘ የአለም አቀፉ አቪየሽንና የስታር አሊያንስ አባል የሆነ ትርፋማ አየር መንገድም ባለቤት ነች ኢትዮጵያ፡፡ አየር መንገዱ በስፋት ያደገው በኢሕአዴግ ዘመን ነው፡፡ ለኢኮኖሚያችን እድገት የሚያበረክተው የላቀ አስተዋጽኦ ነው፡፡

ባለፈው አመት ስራ የጀመሩትና በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች መስፋፋት የጀመሩት የኢንዱስትሪ ፓርኮቻችን በአፍሪካ ደረጃ ኢትዮጵያን የኢንዱስትሪ ማእክል እንደሚያደርጋት የተለያዩ አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሀን ዘግበዋል፤ ትክልል ናቸው፡፡ እነዚህ ዘርፈ ብዙ የኢኮኖሚ ስኬቶች የተመዘገቡት ኢሕአዴግ በቀረጻቸው የኢኮኖሚ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ነው፡፡ ሲያጣጥሉት የነበሩት ያፈሩበት ኢትዮጵያን በፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ምሳሌነት ለመጥቀስ የተገደዱበት ሁኔታ ነው የተፈጠረው፡፡ ይህ ስኬት  ቀደም ሲል ሲቃወሙ የነበሩትን ምእራባውያን ምስክርነታቸውን በተደጋጋሚ እንዲሰጡ ያስገደደ ሆኖአል፡፡

ጠንካራ የኢኮኖሚ እድገት መገንባት በመቻሉ ነው አምና ተከስቶ የነበረውን ድርቅ እንደጥንቱ የውጭ እርዳታ ሳይጠበቅ በራሳችን አቅም ለመመከትና ለመከላከል የተቻለው፡፡ ወደፊትም በዘላቂነት ድርቅን ለመመከትና ለማስወገድ የሚያስችል አቅም ለመገንባት በሰፊው እየተሰራ ይገኛል፡፡ ሀገራችን ኢትዮጵያ ጠንካራ የኢኮኖሚ አቅም ለመገንባት በመብቃቷ በዲፕሎማሲውም መስክ የበለጠ ስኬታማና ተደማጭ ሆናለች፡፡  የተከበረችና ተጽእኖ ፈጣሪ የሆነች፣ በአለም አቀፍ ደረጃም ሶስተኛዋ የዲፕሎማቲክ ከተማና ሀገር እንድትሆን አስችሎአታል፡፡

ባጠቃላይ በአንድ ዘመን ኋላቀር የነበረ ጥንታዊ ግብርናን የኢኮኖሚ መሰረትዋ አድርጋ ለረዥም ዘመን የኖረች ሀገር ዛሬ ወደ ኢንዱስትሪ እብዮት ዘመን እየተሸጋገረች ትገኛለች፡፡ ይሄ ራሱን ችሎ ታላቅ ሀገራዊ ድል ነው፡፡ ልማቱና እድገቱ በሰፊው ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡ ኢትዮጵያ በታላቅ የኢኮኖሚ እድገት ተስፋ ላይ የምትገኝ ሀገር ናት፡፡ የተከሰቱ የውስጥ ችግሮችን ለመፍታት መንግስት ለሕዝቡ የገባውን ቃል በተግባር የመተርጎም እርምጃዎች እያሳየ በመሆኑ ይሄንን ሀገርን ከደሀነት የማውጣትና የማሳደግ ጥረት ማገዝና ውጤታማ እንዲሆን በማድረጉ ረገድ ባለቤት የሆነው ሕዝብ  ሚና ወሳኝ ነው፡፡

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy