Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

መግለጫ ሲፈተሽ

0 272

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

መግለጫ ሲፈተሽ

                                                      ይልቃል ፍርዱ

የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ሳምንታትን በፈጀው ጥልቅ ግምገማና የውስጥ ፍተሻ አመራሩ ራሱን በጥልቀት በማየት፣ ወደ ውስጥ በመመለከት፣ በግልጽ ችግሮችን ነቅሶ አውጥቶ ለተፈጠሩት ሀገራዊ ችግሮች በዋነኛነት አመራሩ ኃላፊነቱን እንደሚወስድ ድምዳሜ ላይ ደርሷል፤ ይህንኑ በተመለከተም ዝርዝር መግለጫ አውጥቶአል፡፡

አንድ የፖለቲካ ድርጅት በሌላውም አለም ተሞክሮ ሲታይ ይወለዳል፤ ያድጋል፤ ያረጃል። ብርታትና ጥንካሬን ካገኘ፣ ተቸክሎ ካልቀረ፣ ወደፊት በቁርጠኝት መመልከት ከቻለ የውስጡን አላሰራ ያለውን በሽታ ካስወገደና ከፈወሰ እንደ ንስር ዳግም ጉልበትና አቅም አግኝቶ በከፍታው አየር ላይ ሊበር፤ ሊምዘገዘግ ይችላል፡፡

ሆኖም ግን በትላንት ትዝታ ብቻ ተውጦ የሚቀር ከሆነ ስለትላንት ጀግንነትና ገድለ ሀዋርያት በማውሳት ከተጠመደ ሕልፈቱ የታሪክ ግዴታ ነው የሚሆነው፡፡ ምክንያቱም ማሕበራዊም ሆነ ተፈጥሮአዊ ሕግ የመለወጥና የመታደስን ከግዜ ጋር ራስን ማብቃትን የተሻለ ሁኖ መገኘትን ግድ ስለሚሉ ነው፡፡ በአሮጌ አስተሳሰብ አዲስ ወቅትን አዲስ የሆነ ትውልድን በእውቀት ጎልብቶ የተተካ የሕብረተሰብ አስተሳሰብን መምራት አይቻልም፡፡

ኢሕአዴግ የገጠመው ትልቁ ፈተና በውስጡ የተሰገሰገው ጥቅመኛ ዘራፊና ሙሰኛ ኪራይ ሰብሳቢ ኃይል መብዛትና መንሰራፋት ነው፡፡ ቀድሞ በግምገማ የደረሰበትን በጥልቀት የፈተሸውን ችግር እንዳይፈታ ወደተግባር እንዳይገባ የወሰነውን ውሳኔ ተግባራዊ እንዳያደርግ እጅና እግሩን አስሮ አላላውስ ያለው ጥገኛና ኪራይ ሰብሳቢ የሆነው በሙስና መረብ ውስጥ ተዘፍቆ እቅዶችን ሲያኮላሽ የነበረው ራሱን ድርጅቱን እየቦረቦረ ከሕዝብ ጋር እያጋጨ የነበረው ኃይል ነው፡፡

በከፋ ሁኔታ ኢሕአዴግን ከሕዝብ ጋር ያላተመውና ያጋጨው፤ ቀድሞ የገመገመውን ብሔራዊ ችግር እንዳይፈታ እጅና እግሩን ጠፍሮ የቆየው በውስጡ የነበረው የመልካም አስተዳደር ችግር እየፈጠረ፣ በሕገ መንግስቱ ስም እየማለ ሲያጭበረብር የነበረው፤ በሙስናና በዘረፋ አሳፋሪ ድርጊት ውስጥ ተዘፍቆ የነበረው ኃይል ነው፡፡

እንግዲያውማ በሀገሪቱ ታሪክ እንደ ኢህአዴግ ስርነቀል የመሰረተ ልማትና የግንባታ ስራ የሰራ ሀገሪቱን ታላቅ ወደሆነ አዲስ ምእራፍ ያሸጋገረ ድርጅት አልነበረም፤ የለምም፡፡ ኢሕአዴግ በአፍሪካ ብቻ ሳይሆን በአለምም ደረጃ ከነቻይና ቀጥሎ እጅግ ግዙፍ የሆነ ከስምንት ሚሊዮን አባላት በላይ ያሰባሰበ ድርጅት ነው፡፡ እንዲህ አይነት የገዘፈ ቁጥር ያለው የፖለቲካ ድርጅት እስካሁን በአፍሪካ የለም፡፡

ቁም ነገሩ የአባላቱ ቁጥር መብዛት አይደለም፡፡ ዋናው ጉዳይ አባላቱ የቆሙለትን የፖለቲካ መስመር ምን ያህል ያውቁታል? ለቆሙለትስ መስመር ምን ያሕል ቁርጠኛ ናቸው? ምን ያሕልስ ለሕዝብና ለሀገር በታማኝነት ይሰራሉ? የሚለው ነው፡፡

በኢሕአዴግ አባልነታቸው የሚነግዱ፣ ሕዝብን ከማገልግል ይልቅ ሕዝብን  የሚያስፈራሩ የመንግስትና የሕዝብን ሀብት የሚዘርፉ፣ ፍትሕን የሚያዛቡ፣ በሀሰት የትምህርት ማስረጃና በለብለብ እውቀት የተለያዩ መንግስታዊና ፖለቲካዊ አመራርን የጨበጡ፣ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ የማይወጡ፣ የፓርቲ አባልነታቸውን እንደሽፋን በመጠቀም ማንም አይነካንም፤ ጠያቂ የለንም በሚል በተቀመጡበት ወንበር ላይ ሁነው ከሕግና ከስርአት ውጪ ያሻቸውን ሲሰሩ፤ በመንግስትና በሕዝብ ሀብት ዘረፋ ከፍተኛ ሀብት ሲመዘብሩ የነበሩት ናቸው የሕዝብ ብሶትና ቁጣን የቀሰቀሱት፡፡ ይህ ደግሞ በሚገባ ይታወቃል፤ የኢሕአዴግ ችግሩ ፈጥኖ እርምጃ መውሰድ አለመቻሉ ነው፡፡ የስራ አስፈሚው ውሳኔ ይሄንንም የጓዳ ችግር አበጥሮ የሚፈትሽ ሆናል፡፡ አበረታች እና ሊደገፍ የሚገባው ለውጥ ሊያመጣ የሚችልም ነው፡፡  

የአሁኑ የኢሕአዴግ ስራ አስፈጻሚ መግለጫና ውሳኔ በእነዚህ አካላት ላይ የማያዳግም እርምጃ እንደሚወስድ ይጠበቃል፡፡ ድርጀቱ ራሱን በተለያየ ደረጃ በጥልቀት በሁሉም መስክ ከላይ እስከታች ባለው አመራር ውስጥ ፈትሾ በየመስሪያ ቤቱ የተዘረጉትን ሕገወጥ መረቦችና ስውር የጥቅም ቡድናዊ ቁርኝቶች  ሠራተኛውን አላሰራ ያሉ የቡድን አሰላለፎችን በመበጣጠስ የሰፈነውን የጎጠኝነትና የዘረኝነት ሰልፍን በመበጣጠስ መንግስታዊ ተቋማትና ሰራተኛው እውነተኛ የሲቪል አገልጋይ እንዲሆኑ ማድረግ ቅድሚ ስራው መሆን አለበት፡፡

ሰራተኛው በአግባቡ ነጻነቱ ተጠብቆ የሚሰራበት፤ ሀገሬ ብሎ በቅንንት የሚያገለግልበት ሁኔታ እንደሚፈጠር ይታመናል፡፡ አንዱም በየቀበሌውና በየክፍለ-ከተማው ሕዝቡን ካማረሩት የመልካም አስተዳደር ችግሮች ሌላ በየመንግስት መስሪያ ቤቱ ሰራተኛው በአግባቡ ስራውን እንዳይሰራ የመንግሰት ስራ እንዲቀዛቀዝ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረጉት ውጤቱም ደካማ እንዲሆን ያበቁት በቡድን በጎጥ በመረብ የተፈጠረው አሰራር ስለሆነ የኢሕአዴግ ስራ አስፈጻሚ በሳለፈው ውሳኔ ውስጥ ይህንን ችግር በቁርጠኝነት ከስሩ ነቅሎ ያስወግዳል የሚል እምነት አለ፡፡

በአሁኑ ሰአት መንግስታዊ ስራዎች ከሚጠበቀው በላይ ተቀዛቅዘዋል፤ ምርታማነትና ውጤታማነት ቀንሶአል፡፡ ለስራ ብቁና ውጤታማ የሆኑ ዜጎች ሳይሆን ታማኝ ሎሌነት ዋናው መስፈርት እየሆነ በዚህ መልኩ ሀገራዊ ስራዎች በበርካታ ተቋማት ውስጥ በግድየለሽነት የሚሰሩ ሆነዋል፡፡ ለዚህ ስራ መቀዛቀዝ ዋነኛ ምክንያቱ የሰራተኛው ተስፋ መቁረጥና በሙሉ ልቡ ስራዎችን መስራት አለመቻል ነው፡፡ ይህንን ሁኔታ ፈጥኖ በመለወጥ አገልግሎት አሰጣጥን ማሻሻል፣ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ይገባል፡፡ ይህ ካልሆነ ተጎጂው ሀገርና ሕዝብ ነው፡፡

የኢሕአዴግ ስራ አስፈጻሚ ውሳኔ እጅግ ጥልቅና መሰረታዊ ጉዳዮችን በዋነኛነት የያዘ በመሆኑ ስር ነቀል ለውጥ በእርግጠኝነት ያመጣል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ዋናው ነገር ፈጥኖ ወደስራ መግባት  ነው የሚጠበቅበት፡፡ ድርጅቱ ለተፈጠረው ስሕተት ችግሩ የአመራሩ መሆኑን ገልጾ ይቅርታ መጠየቁ፤ መጸጸቱን መግለጹ አንድ እርምጃ ወደፊት ተደርጎ ሊወሰድ ይገባዋል፡፡

ጽንፈኛ የሆነው የተቀዋሚ ኃይል ይህንን ጥልቅ የተሀድሶ እርምጃ እያጣጣለው ይገኛል፡፡ ኢትዮጵያ ፈርሳለች የሚለው ሙት ፕሮፓጋንዳቸው በሀሰት የተሞላ ሲሆን ኢትዮጵያ አልፈረሰችም፤ አትፈርስም፤ ልትፈርስም አትችልም፡፡ የማንነት መሰረትዋ በጥልቅና በማይነቃነቅ አለት ላይ የተገነባ በመሆኑ መፍረስ ይቅርና አይነቃነቅም፡፡

ኢትዮጵያ በግብጽ፣ በኤርትራና በግንቦት ሰባት ሴራና ደባ የምትፈርስ ሀገር አይደለችም፡፡ ውድቀትና ጥፋትዋን ለማየት የሚናፍቁ ሁሉ ቀድመው ይወድቃሉ፤ ሴራቸውም ይመክናል፡፡ የስራ አስፈጻሚው መግለጫ ጥልቅ ሀገራዊ ችግሮችን የፈተሸና የዳሰሰ የመፍትሔ አቅጣጫዎችንም የያዘ በመሆኑ የተፈጠሩትን ችግሮች በመፍታት የተጀመረው የሕዳሴ ጉዞ እንደገና በታላቅ መሰረት ላይ ጸንቶ እንዲቀጥል ያደርገዋል የሚል የብዙዎች ግምት አለ፡፡

የተለዩት ችግሮችን በመፍታት የጠንካራ ሀገር ግንባታው ይቀጥላል፡፡ ሁከቶችና ግጭቶችን ከሕዝቡ ጋር በመሆን ዳግም በማይከሰቱበት መንገድ ይፈታል፡፡ አሁንም በዋነኛነት ችግሮቹን እየፈታ ያለውና የሚፈታውም ሕዝቡ ነው፡፡ ኢሕአዴግ እንደድርጅት ግጭቶችን ለማስወገድ ከስምምነት ላይ መድረሱ የሚያመለክተው የተደረሰበትን ሀገራዊ መግባባት ነው፡፡ በዚህ መልኩ ኢህአዴግ እየወሰደ ያለው የማስተካከያ እርምጃ የሚበረታታ ነው ማለት ይቻላል፡፡

ይህ የገዥው ፓርቲ ውሳኔ የተሻለ ሀገራዊ ለውጥ ለማምጣት ያለውን ቁርጠኝነትና ተነሰሽነት በግልጽ ያሳያል፡፡ በተለያዩ የወንጀል ድርጊት ተከሰው የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲ አባላትን ለመፍታት ድርጅቱ የደረሰበት ውሳኔ ሰፊ ሀገራዊ መግባባት ከመፍጠር አንጻር የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ ነው፡፡ የዴሞክራሲ ምሕዳሩን ለማስፋት ሲባል የምሕረት ሕጉ በሚፈቅደው መልኩ ተጣርቶ እንዲፈቱ ይደረጋል የተባለው ብሔራዊ መግባባት በመፍጠር የውስጥ ችግሮችን በመፍታት የተሻለች ሀገር የመገንባት ሕልምን ተግባራዊ ለማድረግ ያስችላል፡፡

ባጠቃላይ፣ የስራ አስፈጻሚው መግለጫ ሀገራዊ አንድነትን በመጠበቅና ሰላምን ከማስጠበቅ አንጻር ከፍተኛ ቦታ የሚሰጠው ሲሆን ለውሳኔው ተግባራዊነት ሕዝብን በሰፊው ማሳተፍ ይጠበቅበታል፡፡ መርሕ ላይ ያልተመሰረቱ ግንኙነቶች፤ አለመግባባቶችና መጠራጠር የግንባሩን መሰረታዊ መስመር ለችግርና አደጋ አጋልጠውት የቆዩ ቢሆንም እነዚህን ሙሉ በሙሉ ነቅሶ በማውጣት የማያዳግም መፍትሔ ይሰጣል ተብሎ ተስፋ ተደርጓል፡፡ አሁን የሚጠበቀው ፈጥኖ ወደ ተግባር መግባት ሲሆን እንደ መንግሥትም ጠንክሮ ለመውጣት ያበቃዋል፡፡ ይህ ከላይ የዘረዘርነው የፓርቲው ውሳኔ የኃሳብና የፍላጎት ልዩነቶችን አክብሮ ለመንቀሳቀስ፣ የዲሞክረሲ ምህዳሩን ለማስፋት ወዘተ የደረሰበት ውሳኔ ነውና የሚደነቅ፣ የሚበረታታና ለሌሎችም ምሳሌ ሊሆን የሚችል ተግባር ነው የሚል እምነት አለ።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy