Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

መጥኔ ለእውነተኛ ታጋዮች!

0 481

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

መጥኔ ለእውነተኛ ታጋዮች!

ኢዛና ዘ መንፈስ

እያንዳንዱ ትውልድ የየራሱን ዘመን ማህበራዊ፤ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ገጽታዎች የሚገልፅ አሻራውን አኑሮባቸው ከሚያልፍ ሁነኛ መንገዶች መካከል፤ ኪነጥበብ ቀዳሚውን ስፍራ ትይዛለች፡፡ ለዚህም ደግሞ በርካታ ተጨባጭ ምሳሌዎችን እንደማሳያ እያነሳን በማቅረብ መተማመን የማንችልበት ምክንያት እንደማይኖር ደፍሮ መናገር ይቻላል፡፡ ይሁን እንጂ በዚህ አጭር ሐተታዬ ያን ማድረግ ስለሚያዳግት፤ ጉዳዩን እንዳነሳው ምክንያት ስለሆነኝ አንድ ኪነጥበባዊ የሀገራችንን የፖለቲካ ታሪክ የሚያወሳ ስራ አስታውሼ ከዚያም ወደ ዋነኛው የጽሑፌ ማጠንጠኛ ነጥብ አልፋለሁ፡፡

እንግዲያውስ ለዛሬዋ ፌደራላዊት፤ ዴሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ ኢትዮጵያ መመስረት ቁልፍ ሊባል የሚችለውን የፋና ወጊነት ሚና ስለመጫወቱ የሚታመንበት ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ፤ የደርግ ኢ.ሠ.ፓ ወታደራዊ አምባገነን አገዛዝ ይገለገልበት የነበረውን ፈርጀ ብዙ የአፈና መዋቅር፤ ባፈራረሰ የትጥቅ ትግል አማካኝነት ወደ ስልጣን መምጣቱን ተከትሎ ስለተፃፈ የመድረክ ተውኔት ነው ላነሳ የፈለግኩት፡፡ ስለሆነም አዲሱን የታሪክ ምዕራፍ መሰረት ባደረገ መልኩ፤ ስመ ጥሩው የሀገራችን ገጣሚና ፀሐፊ ተውኔት ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን “ሀሁ፤ ወይም ፐፑ?” በሚል ርዕስ ጽፎት ለመድረክ ስለበቃው የሙሉ ጊዜ ቲያትር በዛሬው ሐተታዬ ላይ ጥቂት ነጥቦችን ለማውሳት እሞክራለሁ፡፡ ምክንያቱም ደግሞ፤ ያን በሽግግሩ መንግስት ዘመን የመጀመሪያ ዓመታት ውስጥ በአዲስ አበባ ቲያትር ቤቶች የታየ የመድረክ ተውኔት የመመልከት ዕድል የገጠመን ሰዎች ሁሉ፤ እንደምናስታውሰው፤ አጠቃላይ ጭብጡ የተመሰረተበት አፅመ ታሪክ፤ በተለይም አሁን ላይ ሀገራችን ኢትዮጵያን እየገጠማት ካለው ችግር ጋር አያይዘን እንድናነሳው ግድ የሚል ሆኖ ይሰማኛልና ነው፡፡ ስለዚህም ፀጋዬ ገ/መድህን በድህረ ደርግ ኢትዮጵያ ውስጥ የተከፈተውን አዲስ ምዕራፍ “የዚች አገር ፖለቲካዊ ታሪክ አሁን ላይ ሀ ብሎ መጀመሩ ነው? ወይስ ደግሞ ፐፑ … ብሎ ሊፈፀም ይሆን?” ከሚል ስጋት በመነጨ መነፅር የተመለከተበት ተወዳጅ የመድረክ ተውኔት ስለመሆኑ በሂሳዊ ዳሰሳ ፀሐፊያን የተመሰከረለት “ሀሁ፤ ወይም ፐፑ” ቲያትር፤ በእርግጥም ያኔ ተገቢ ትኩረት አልተሰጠውም እንጂ፤ ወቅታዊውን የዘመን መንፈስ በመቅረፅ ረገድ ብዙ ትምህርት ሊወሰድበት የሚችል የታዋቂው ባለቅኔያችን ድንቅ ኪናዊ ገፀ በረከት ነው የሚል እምነት አለኝ እኔም በግሌ፡፡

ይህን የምልበት ዋነኛ ምክንያትም፤ በ1984 ዓ.ም ተፅፎ በቀጣዩ 1985 ዓ.ም መጀመሪያ ላይ ለመዲናችን የቲያትር ጥበብ አፍቃሪያን በአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት መድረክ ላይ መቅረብ እንደጀመረ የሚነገርለትን “ሀሁ፤ ወይም ፐፑ?” የተሰኘው የሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን ተውኔት፤ አጠቃላይ ታሪኩ ስለተመሰረተበት ጭብጥና የሴራ አወቃቀር፤ በያኔዋ ኢትዮጵያ ውስጥ የተከፈተው የስር ነቀል ለውጥ አዲስ ምዕራፍ የታለመለትን ግብ እንዲመታ ከመሻት ብርቱ ፍላጎት የመነጨ ጥረት ሲያደርጉ ይስተዋሉ በነበሩት የኢህአዴግ ታጋዮችና እዚህ መሀል አገር የተቀላቀሏቸው አንዳንድ ብልጣ ብልጥ ከተሜዎች እነርሱን ተተግነው የህዝቡን ሀብት ንብረት መመዝበርን የወቅቱ አዋጭ የገቢ ምንጭ አድርገው ይቆጥሩት በነበሩ ብልጣ ብልጥ ከተሜዎች መካከል የሚታይ ፖለቲካዊ የድብብቆሽ ጨዋታን መነሻ አድርጎ እንደሆነ አውቃለሁና ነው፡፡ ለዚህ አስተያየቴ ጥሩ አብነት ይሆናል የምለውም ደግሞ ቲያትሩ ላይ በመሪ ተዋናይነት ሲጫወቱ ከምናውቃቸው ገፀ ባህሪያት መካከል፤ በተለይም “ታጋይ ነጋ” የሚል ስም የተሰጠውና ደርግን በተራዘመ የትጥቅ ትግል አስወግደው ከመጡት የድል አድራጊው ሰራዊት አባላት አንዱ የሆነው በረኸኛ ወጣት ዋነኛውን ስፍራ ይይዛል፡፡ ይሁን እንጂ ኢህአዴግን የሚወክል ግንባር ቀደም ሚና እንዲጫወት የመደረጉን ያህል፤ ግን እርሱ ለመላው ኢትዮጵያውያን የብሔር ብሔረሰብ ህዝቦች የሚበጅ አዲስ ዓይነት የፖለቲካዊ ኢኮኖሚ ስርዓተ ማህበርን ለመመስረት የሚያስችል ምዕራፍ የተከፈተበት እንደሆነ አድርጎ ከልቡ ስለሚያምንበት የስርነቀል ለውጡ ሂደት ቀጣይ ዕጣፈንታ ያለውን ሃሳብ ህብረተሰቡ እንዲረዳለት ከመፈለግ በመነጨ ቅን ስሜት ሲንቀሰቀስ፤ ሌላኛው አዲስ አበቤ የቲያትሩ ገፀ ባህሪ በታጋይ ነጋ ስም እያስፈራራ ህዝቡን ያለ አግባብ ሲመዘብር እንመለከታለን፡፡

“ሀሁ፤ ወይም ፐፑ” ቲያትር ላይ ብልጣብልጡን ከተሜ ወክሎ የሚተውነው ገፀ ባህሪ፤ የታጋይ ነጋን ስልጣን ተተግኖ አዲስ አበቤውን የህብረተሰብ ክፍል እያስፈራራ ሲዘርፍና ሲያጭበረብር የሚስተዋልበት የማምታታት ዘዴ በተለይም የመንግስት ቤቶችን ከተራው ዜጋ ላይ ቀምቶ እያከራየ ያልተገባ የግል ጥቅም የሚያጋብስበት እንደሆነም ማስታወስ ይቻላል፡፡ እንዲያውም ሰውየው በወደቀው የደርግ ወታደራዊ  መንግስት ዘመን ስላካበተው መሰል የምዝበራ ተግባር ልምድ፤ እየገለፀ በመኩራራት “አሁንም ቢሆን ገና መላዋን አዲስ አበባ ከተማ አከራይቼ ስንትና ስንት ገንዘብ እሰበስባለሁ” ሲል የሚደመጥበት ትዕይንት እንዳለ ነው ትዝ የሚለኝ፡፡ ይህን ሁሉ የቅጥፈትና የማወናበድ ተግባር እየፈፀመ ህዝቡን ሲያሰቃየውና በዚያው ልክም ያለአግባብ ሲከብር የምንመለከተው ብልጣብልጡ ከተሜ፤ በታጋይ ነጋ ፊት ሲሆን ግን ስር ነቀል የስርዓት ለውጡን የምር የሚደግፍ ተራማጅ ምሁር ዜጋ መስሎ ይታይል፡፡  ከበስተጀርባ ብቻ ነው ትክክለኛ ማንነቱን የሚገልፅ ፀረ ኢህአዴግ ፖለቲካዊ አቋም ሲያራምድና ተጋይ ነጋ በፅናት የቆመለትን ዓላማ የመገዝገዝ ተግባር ሲፈፀም የሚታየው፡፡

ይሁን እንጂ ብልጣብልጡ ከተሜ የ“ሀሁ ወይም ፐፑ” ቲያትር ገፀ ባህሪ አልፎ አልፎ ወደ ትክክለኛው ፀረ ህዝብ አቋሙ የማምራት አዝማሚያ በታጋይ ነጋ ፊትም ሳይቀር እንደሚያሳይና ግን ደግሞ ታጋዩ ኮስተር ብሎ አንዳች እርምጃ ሊወስድበት ሲቃጣ፤ ወዲያውኑ የአስመሳይነት እስስታዊ ገጽታውን በማሳየት ቅን አሳቢውን በረኸኛ ወጣት ያሳምነዋል፡፡

ለምሳሌ ያህልም፤ ዳንኬረኛ ሌንሳ፤ ዳንኬረኛ ግደይና ዳንኬረኛ (እሙ?) በሚል የገፀ ባህሪ ስም ቲያትሩ ላይ የሀገራችንን ብሔር ብሔረሰቦች ወክለው የሚተውኑትን ሶስት ወጣት ሴቶች ብልጣብልጡ ከተሜ ሊተናኮላቸው ሲሞክርና ታጋይ ነጋ እየገሰፀ አደብ እንዲገዛ ሲያደርገው የሚታይበት ትዕይንት ስለመኖሩ ማስታወስ አያዳግትም፡፡ በአጠቃላይ የሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን “ሀሁ፤ ወይም ፐፑ” ወጥ የመድረክ ቲያትር ላይ ብልጣብልጡን ኢትዮጵያዊ የከተማ ነዋሪ ወንድ ወክሎ የሚተውነው ገፀባህሪ፤ ለታጋይ ነጋ ጥረት መሳካት ድጋፍ የሚሰጥ መስሎ፤ አዲሱን የታሪክ ምዕራፍ ለእርሱና ለግበረ አበሮቹ ቡድናዊ ምዝበራ እንዲያመች አድርጎ ሲጠቀምበት የሚስተዋል እጅግ መሰሪ ሰው ነው፡፡ በየትዕይንቱ ጣልቃ ለተባባሪዎቹ ስልክ እየተደወለ “ያን የቀበሌ ሊቀመንበር ታጋይ ነጋ ይሄን ያህል ቤት ከነዋሪዎች ላይ ቀምተህ እንድታስረክበኝ ብሎሀል በለው፡፡ ይህን ትዕዛዝ በፍጥነት ሳይፈጽም ቢቀር ምን ዓይነት እርምጃ ለመውሰድ እንደምንገደድም በደንብ አስረዳው እሺ!?” ሲል የሚደመጥበትን ኢ-ሞራላዊ ቅጥፈት ደግሞ፤ ዛሬ ላይ የፌደራል ስርዓቱ አሳሳቢ አደጋ ተደርጎ እስከመቆጠር የደረሰውን የኪራይ ሰብሳቢነት ፖለቲካዊ ኢኮኖሚ ችግር ፀሐፊ ተውኔቱ አስቀድሞ የተነበየበት ነበር ብለን እንድናምን የሚያስገድድ ይመስለኛል፡፡

ምንም እንኳን ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከተው ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ ወይም ደግሞ እርሱ የሚመራው መንግስት በወቅቱ የቲያትሩን ጠቃሚ ጎን ልብ ያለው ባይመስልም ቅሉ፤ የፀጋዬ ገ/መድህን ያውም ገና በግንቦት 20ው የድል ዜና ማግስት “ሀሁ፤ ወይም ፐፑ” በሚል ርዕስ የፃፈውን የሙሉ ጊዜ ተውኔት ያህል፤ ስር ነቀል የስርዓት ለውጥ ሂደቱን ሊገጥሙት ስለሚችሉ መሰረታዊ ችግሮች አበክሮ ያስገነዘበ ሌላ የኪነ ጥበብ ስራ የለም ባይ ነኝ እኔ፡፡ ይህን ስልም ደግሞ ተውኔቱን በቲያትር ቤት መድረክ ላይ ሲቀርብ ከመመልከቴም ባሻገር፤ በመፅሐፍ መልክ ታትሞ ከወጣ በኋላ ቃለ ተውኔቱን የማንበብ ዕድል ስለገጠመኝና ታሪኩ ከኢህአዴግ መራሹ የኢትዮጵያ ህዝቦች የትግል ጉዞ ጋር ጥብቅ ተዛምዶ እንዳለው ስለተረዳሁ እንጂ እንዲያው ብቻ የፀጋዬ ገ/መድህን አድናቂ ከመሆን በሚመነጭ ውዳሴ ከንቱ አይደለም፡፡ ደግሞስ “ምስጢረኛው ባለ ቅኔ” በሚል ርዕስ ከአራት መቶ በላይ ገፆች ያለው አንድ ሙሉ መፅሐፍ ሂሳዊ ዳሰሳ የተፃፈለት ብቸኛው የሀገራችን ተውኔት “ሀሁ፤ ወይም ፐፑ” አይደለም እንዴ? ይሄን የማያውቅ አንባቢ ካለም የአርክቴክት ሚካኤል ሽፈራውን “ምስጠረኛው ባለቅኔ” የተሰኘ በተጠቃሹ የፀጋዬ ገ/መድህን ቲያትር ላይ የሚያጠነጥን መጽሐፍ አፈላልጎ ያነብ ዘንድ እመክረዋለሁ፡፡

ለማንኛውም ግን፤ የዚህ መጣጥፍ ዋነኛ ዓላማ በተጠቃሹ ቲያትር ላይ ግንባር ቀደም መሪ ተዋናይ ሆኖ ሲጫወት የምናውቀው ታጋይ ነጋ፤ ለመላው የኢትዮጵያ ህዝቦች ዘለቄታዊ የጋራ ዕጣፈንታ መቃናት ይበጃል ብሎ ከልቡ የሚያምንበትን ኢህአዴጋዊ ዓላማውን፤ ለአዲስ አበባ ከተማ ስልጡን ህብረተሰብ የማስረፅ ስራ እንዲሰራ ተመድቦ፤ የማንቃትና የማደራጀት ኃላፊነቱን በመወጣት ረገድ ያሳይ የነበረውን ዓይነት ያላሰለሰ ጥረት የሚያሳዩ እውነተኛ ታጋዮች ዛሬም ድረስ ይኖሩ ይሆንን? ብየ ራሴን እጠይቅ ዘንድ የወቅቱ ፖለቲካዊ ድባብ ስለገፋፋኝ ነው፡፡ ስለዚህም ታዋቂው ኢትዮጵያዊ ባለቅኔ ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን “ሀሁ፤ወይም ፐፑ” በተሰኘ የፖለቲካ ዘውግ የጎላበት አነጋጋሪ ተውኔቱ ላይ “ታጋይ ነጋ” ሲል የሰየመው ካድሬ ገፀ ባህሪ፤ ፈጽሞ እንዳንረሳውና ሁሌም ከፌደራላዊው ስርዓት በጎ ወይም በጎ ያልሆኑ ገፅታዎች ጋር አያይዘን እንድናስታውሰው ግድ የሚሉ ውብ ሀገራዊ ህልሞች እንደነበሩት ልብ በሉልኝ፡፡ እናም፤ ግንቦት 20 ቀን 1983 ዓ.ም መዲናችንን አዲስ አበባን በሶስት አቅጣጫ መጥተው ከተቆጣጠሯት፤ ውጣ ውረድ ክፉኛ ያጎሳቆላቸው ሰሜነኛ ወጣቶች መካከል አንዱ እንደሆነ ተደርጎ በቲያትሩ ታሪክ ውስጥ ሲተውን የምናውቀውን ታጋይ ነጋን ስናስታውስ ብዙ ጥያቄ እናነሳ ዘንድ የሚገፋፉ ተያያዥ ነገሮች አብረው ይመጡብናል፡፡

ይሄን ስልም ደግሞ፤ ለመሆኑ እንደታጋይ ነጋ ከማይቀለበስ ህዝባዊ ወገንተኝነት በሚመነጭ የዓላማ ጽናት ላይ ተደላድሎ መርገጡን በሚያመለክት ልበ ሙሉነት፤ ውብና ብሩህ ህልሞቹን ለመላው ኢትዮጵያውያን የብሔር ብሔረሰብ ህዝቦች ሊያጋራ ሲጥር የሚስተዋል እውነተኛ የኢህአዴግ ካድሬ ኖሮ ያውቃል ወይ? በተለይም ደግሞ አሁን አሁን እንደ ሀገር የሚያሳስብ መሰረታዊ ችግር እያስከተለብን እንደሆነ የሚታመንበትን የአድርባይነት ወረርሽኝ እንደ “መቻቻል” ሊቆጥሩት ሲቃጣቸው የሚስተዋሉ የግንባሩ አባላት፤ እንዲሁም ከከፍተኛ እስከ መካከለኛ የሥራ ኃላፊነት ላይ ያሉ የአመራር አካላትም ጭምር በቁጥር ከመበራከታቸው አኳያ ሲታይ፤ እንደታጋይ ነጋ፤ ኢህአዴግ መራሹን የኢትዮጵያ ህዝቦች የትግል መስመር መርጦ እንዲሰለፍ ስላደረገው አሳማኝ ምክንያት፤ በማያሻማ ልበ ሙሉነት የማስረዳት ድፍረት ያለው እውነተኛ ካድሬ መኖሩን ብንጠራጠር ሊያስገርም አይገባም ማለት ይቻላል፡፡ ምናልባት ዛሬም ድረስ በማይዛነፍ ህዝባዊ ፍቅር የሚገለፅ እምነትና እውነታቸውን እንደጠበቁ የሚገኙ ትክከለኛዎቹ “ታጋይ ነጋዎች” ካሉም ደግሞ መጥኔ ለእነርሱ! የሚያሰኝ ሆኖ ይሰማኛል የሀገራችን ፖለቲካ ወቅታዊ እውነታ ጎልቶ የሚንፀባረቅበት ተጨባጭ ድባብ፡፡ መቸስ በዚህ ለፖለቲካዊ የአስተሳሰብ ወገንተኝነት ታምኖ መገኘት “ጊዜው ያለፈበት የወያኔ (ኢህአዴግ) ግራ ዘመም አክራሪ አቋም” አድርገው ሲወስዱት የሚታዩ ብልጣብልጦች እንደ አሸን በፈሉበት ዘመን፤ እንደ ታጋይ ነጋ የዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነትን አስፈላጊነት አበክሮ ሲዘምር የሚደመጥ እውነተኛ ታጋይ እንዲኖር መጠበቅ ይከብዳልና ነው እኔ ይህን ማለቴ፡፡

ኢህአዴግ መራሹ የኢትዮጵያ ህዝቦች ትግል ጉዞ ከትናንት እስከ ዛሬ ለሚታወቅበት ህብረብሔራዊ ቁመና ጥንካሬ የማይተካ ሊባል የሚችል በጎ ተፅእኖ ይፈጥራሉ ተብሎ የሚታመንባቸውን የግንባሩ ፖለቲካዊ ባህል መገለጫ ጠቃሚ ዕሴቶች፤ ከማዳበር ይልቅ ማዳከምን ይሆነኝ ብለው እንደፈሊጥ የያዙት አድርባዮች በተበራከቱ ቁጥር፤ መርህ የለሽነት መንገሱም ሳይታለም የተፈታ ጉዳይ ነው፡፡ መርህ የለሽነት የተጠናወተው ቡድናዊ ጉድኝትን እንደጠቃሚ ፖለቲካዊ ባህል ከመቁጠር የሚመነጭ የዕርስ በርስ መስተጋብርን የሙጥኝ የማለት አባዜ የሚስተዋልባቸው ፖለቲከኞች ሲበራከቱም ለአስተሳሰብ ወገንተኝነት ታምኖ መገኘት የሚያስጨንቀው የፓርቲ አባል እንዲኖር መጠበቅ ያዳግታል፡፡ በአጭሩ መርህ የለሽነት ላይ የተመሰረተ ፖለቲካዊ መስተጋብር፤ እንኳንስ እንደ ኢትዮጵያ ባለው ብዝሃነትን በአግባቡ ማስተናገድ የሚጠይቅ ነባራዊ ጥሬ ሀቅ በሚስተዋልበት ሀገር ውስጥ፤ የትም ቢሆን አሳሳቢ አደጋ ማስከተሉ አይቀርም፡፡ ለማንኛውም ግን እኔ የዛሬውን ሐተታዬን እዚህ ላይ አብቅቻለሁ፡፡

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy