Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

መፈታተሹ በሁሉም ዘንድ ይዝለቅ

0 248

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

መፈታተሹ በሁሉም ዘንድ ይዝለቅ

 

ዮናስ

 

ለፖለቲካ መብቶች፣ ለፍትሕና ለእኩልነት እታገላለሁ የሚል ፓርቲ ሁሉ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ አይሆንም፡፡ ዴሞክራሲንና ነፃነትን መውደድና መናፈቅም ብቻውን ዴሞክራት አያደርግም፡፡ ዴሞክራት ከተግባር ጋር በሚገናዘብ የዴሞክራሲና የእኩልነት አመለካከታዊ ለውጥ ውስጥ ራሱን አስገብቶ ፀረ ዴሞክራሲን ይዋጋል እንጂ መወጣጫውንና የግል ዝናውን በማመቻቸት ሥራ አይዋጥም፡፡ ተከራክሮ ማሳመንና ማመንን፤ በድምፅ የተበለጠበትን የፓርቲን ውሳኔ ማክበርን ዘላቂ ጥቅሜ ብሎ አርቆ የሚያይ፤ ለድርጅት የውስጥ ዴሞክራሲ ሁልጊዜ የሚቆም፤ ለአምልኩኝ ባይነት፣ ለሴረኝነትና ለሻጥረኝነት ፀር የሆነ ነው ዴሞክራት፡፡ ኢህአዴግ ይህ እንደሚጎድለው ተገንዝቦ ተሃድሶ በማድረጉ ብቻ ይህ ችግር አይፈታም፡፡ ይልቁንም ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ የእኩልነትና የዴሞክራሲ አስተሳሰብና አሠራር ያለበትና የሚኖርበት፣ ሥልጣን በአንድ ግለሰብ ወይም አካል እንዳይዋጥ ቅንብር የሚበጅበት፣ ለዓላማ፣ ለአሠራርና ለውሳኔ መታመን የሚለመድበት መሆኑን የዘነጉት ተቃዋሚዎችም የላቀና የጠለቀ ተሃድሶ ያስፈልጋቸዋል፡፡ ለራሳችን ከራሳችን ውጭ መጠበቅ የትም ስለማያደርሰን፡፡ ስለዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ ገዥው ፓርቲ በዚህ ረገድ የድርሻውን መወጣት ጀምሯል፡፡

 

ዶክተር መረራ ጉዲና እና ዶክተር ሩፋኤል ዲሳሳን ጨምሮ በፌደራል ደረጃ ክስ ተመስርቶባቸው የነበሩ ሰዎች ክስ መቋረጡን የተመለከተው ጉዳይ የቅርብ አስረጅ ነው። በቅርቡ የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ያካሄደውን ግምገማ ተከትሎ አራቱ የግንባሩ አባል ድርጅቶች ሊቃነ መናብርት በሰጡት መግለጫ ላይ “በፈፀሙት ወንጀል ምክንያት በፍርድ ቤት የተፈረደባቸው ወይም ደግሞ ወንጀል በመፈፀም ድርጊት ተጠርጥረው በአቃቤ ህግ ጉዳያቸው ተይዞ በእስር የሚገኙ አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲ አባላትን ጨምሮ ሌሎች ግለሰቦች የተሻለ ሃገራዊ መግባባት ለመፍጠርና የዴሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋት በማሰብ ክሳቸው ተቋርጦ ወይም በምህረት ህግና ህገመንግሥቱ በሚፈቅደው መልኩ ተገቢው ማጣራት ተደርጎ እንዲፈቱ ይደረጋል።” መባሉ ይታወሳል። ይህን ተከትሎም የፌደራል ጠቅላይ አቃቢ ህግ በሰጠው መግለጫ የፍርድ ሂደታቸው በመታየት ላይ የሚገኙ 528 ተጠርጣሪዎች ክስ በመጀመሪያ ዙር መቋረጡን አስታውቋል። መንግስት ተጠርጣሪዎችንና ፍርደኞችን በክስ ማቋረጥና በይቅርታ ይፈታሉ ብሎ መግለፁ የህግ የበላይነት ማስከበር ስራ ይቆማል ማለት አለመሆኑንም የፌደራሉ ዋና አቃቤ ህግ ገልጿል።

 

በጥቅሉ እርምጃው ስለሃገራችን የዴሞክራሲያዊ ሥርአት ግንባታ የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት ያለመ ነው። ግን ደግሞ ሌላና ወሳኝ የሚሆን ጥያቄ እዚህ ጋር ይመጣል፤ ይኸውም ለዴሞክራሲያዊ ሥርአት ግንባታው አለመጎልበትም ሆነ ለምህዳሩ መጥበብ ተጠያቂው ገዥው ፓርቲ ብቻ ነወይ? የሚል፡፡ መቼም መልሱ አዎ እንደማይሆን ሳይታለም የተፈታ ነው። ተጠያቂዎቹ ብዙ ናቸው፤ ልዩነቱ ድርሻቸው መለያየቱ ነው። ገዥው ፓርቲ የመንግስትም ስልጣን እጁ ላይ ነውና የመጀመሪያው ተጠያቂ መሆኑ ላይ ልዩነት አይኖርም። ስለሆነም ከላይ የተመለከተውን ጨምሮ በርካታ እርምጃዎችን መውሰዱ ተገቢ ነው። ሁለተኛ ተጠያቂ ከሆነው ጋር ድርድር መጀመሩም ከእርምጃዎቹ የሚጠቀስ ነው። ይህ ከሆነ ደግሞ ሁለተኛ ከሆነው ተጠያቂም ተመሳሳይ እርምጃና ተሃድሶ ያስፈልጋል ማለት ነው።

 

የዴሞክራሲ ሥርዓተ መንግሥት ህልውና የየትኛውም ፓርቲ ይዞታ ያልሆነ ዓምደ መንግሥት ከማደራጀት ተነጥሎ አይታይም፡፡ ገዥው ፓርቲ እነዚህን እርምጃዎች እየወሰደ የሚገኘው በሀገራችን ዴሞክራሲ እንዲዘረጋና ለዚህም ዋነኛ ተዋናይ የሚሆኑ ፓርቲዎች እንዲኖሩ ነው። ኖረውም በሕግና በተግባር እኩል እንዲሆኑ፣ በምርጫም እኩል ወጪና ወራጅ መሆን እንዲችሉ ነው። ለዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ መንግሥታዊ ዓምዶች ከፓርቲ ወገናዊነት፣ ተቀጥላነትና ይዞታነት ውጪ ነፃ ሆነው መደራጀት አለባቸው፡፡ በመንግሥት በኩል በዚህ ረገድ ያለው ቀርነት ይሥተካከል ዘንዳ መሪ ድርጅቱ ወሥኖ ወደስራ ገብቷል።

 

ይህ እርምጃ ብቻውን ግን የትም አያደርስም። ሁለተኛ ተዋናይ የሆነው ተቃዋሚ ፓርቲም ተሃድሶ ያሻዋል። በኢኮኖሚያዊና በፖለቲካዊ ዕቅዶች (በፓርቲ ምሥረታም ጭምር) የብዙ ሰዎችን ጥቅም አቀራርቦ መያዝና ብዙዎችን በመሳብ ረገድ ራሱን ሊያበቃ ይገባል። የፖለቲካ ትግል ልምምድ ትንሽም የሌላቸው፣ ይህ ይቅርና የፖለቲካ ንድፈ ሐሳባዊ አስተሳሰብ ያላበጁ ሰዎች ፕሮግራም ልትባል የማትችል ወረቀት አዘጋጅተው ብሔርተኛ ብሶትን እያንጎራጎሩ መጓዝ የማይቻልበት ጊዜ ላይ መደረሱን ታሳቢ ያደረገ ተሃድሶም ያስፈልጋቸዋል፡፡ ምክንያቱም መራጩ ሕዝብ ፓርቲዎችን ባላቸው ፕሮግራም የሚመዝንበት አቅም ፈጥሯልና ነው፤ በደልና ጥቃትን የማነፍነፍና ከዚያ አኳያ አዛብቶና አጡዞ በመተርጎም ተፎካካሪ መሆን የማይቻልበት አቅም ተገንብቷልና ነው፡፡ የሃገሪቱ እድገትም ይህንን ከማይመጥንበት ደረጃ ላይም ደርሷልና ነው።

 

የብሔር ብሔረሰብ ካባ መጎናፀፍ የብሔር ወገንተኝነትን ያጠበቀ ስሜታዊ ድጋፍ የሚገኝበት ጥሩ መደበቂያ መሆን ስለሚችልና ስለቻለ፤ ሥልጣን ፈላጊዎችና ሙሰኞች ሽፋን አድርገው ይነግዱበታል፤ ነግደውበታልም፡፡ እነሱ የፈጠሩት ድርጅት የያዘውን አቋም የብሔር ብሔረሰቡ አቋም ያደርጉታል፤ አድርገውትም ታይተዋል፡፡ ድክመታቸው ሲተች በእነሱ ላይ የተወረወረውን ትችት ብሔር ብሔረሰባቸው ላይ እንደተወረወረ አድርገው ለማምታታት ሲሞክሩ በተደጋጋሚ ተስተውለዋል። ኢህአዴግ ይህን ተገንዝቦ ከዚህ ለመውጣት እየተጋ ነው። ስለሆነም በብሄር ጥላ ስር ተከልሎ ምርጫን ማሸነፍ ይቅርና ለፉክክር መቅረብም አዳጋች መሆኑን ታሳቢ ያደረገ ተሃድሶ ተቃዋሚዎቹም ያሻቸዋል።

 

የተቃውሞው መድረክም ተመሳሳይ ተሃድሶ ያስፈልጋል የሚባለው ዛሬም መድረኩ አጋጣሚን የሚጠብቁ ጥቅመኞች የሚራኮቱበት አንድ መስክ ሆኖ እያገለገለ ስለሆነ ነው፡፡ ዴሞክራሲን፣ ነፃነትንና የብሔር መብትን ለዚህ ዓይነት ዓላማ መንገድ አድርገው የሚጠቀሙ ከዴሞክራሲነት ጋር ግን ምንም አይነት ግንኙነት የሌላቸው ጥቅመኞች በገዥው ፓርቲ ውስጥ ብቻ ሣይሆን በተቃዋሚውም ያሉ መሆኑ በተግባር በተረጋገጠበት አግባብ ላይ በአንድ ወገን ተሃድሶ ብቻ ዴሞክራሲያችንን ማንፏቀቅም አይቻልም። ለፍቼ ያደራጀሁትና ያጠናቀርኩት ፓርቲዬ እያሉ ድርጅትን እንደገዛ ንብረት ማሰብ፣ የፓርቲንም ሆነ ሌላ ታሳቢ ሥልጣንን የልፋት ድርሻ፣ የውርስ ሀብት አድርጎ መቁጠር በኢሕአዴግ ብቻ ሳይሆን በተቃዋሚዎችም ውስጥ ያለ የአገር ጠንቅ ነው፡፡ ቀውጢና ፈታኝ ሰዓት ሲመጣ መካካድ፣ አንድ ላይ ያቦኩትን በሌላው ላይ ማላከክ፣ ወደ ሌላ መገልበጥ፣ ወደ ላይ መሳብ ወዘተ ሰሞኑን እንኳን በተቃዋሚው ቤት ተስተውሏልና ነው ተመሳሳይ ተሃድሶ ያስፈልጋቸዋል ማለታችን፡፡

 

የአመራር ብቃትን የሚፈትኑና ከፍተኛ የሐሳብ ልዩነት ሊፈጥሩ የሚችሉ ከባድ ሁኔታዎችና ጉዳዮች የፖለቲካ ድርጅቶችን ቢያጋጥማቸው አዲስ ነገር አይደለም፡፡ ዛሬም ወደፊትም ያጋጥማል፡፡ የፓርቲ አመራር አጥፊ ውሳኔና አካሄድ ሊይዝ የሚችልበት ጊዜ ይኖራል፡፡ እንዲህ ያለ ሁኔታም ያጋጥማል፡፡ በዴሞክራሲያዊ መንግሥት ላይ ፀረ ዴሞክራት ሾልኮ ቢወጣ ወይም የተመረጠ የመስተዳድር ቡድን ዴሞክራሲን የሚቃረን አካሄድ ቢያሳይ፣ ሌላ መንግሥታዊ ሥርዓት ወደ መፍጠር መሄድ ሳያስፈልግ በዚያው ሥርዓት ውስጥ ማስተካከል እንደሚኖር ሁሉ ፓርቲም ዴሞክራሲያዊ ሕይወት እስካለው ድረስ አምባገነን ልሁን ባይነትና የሐሳብ ልዩነት በመጣ ቁጥር የግልበጣ ሴራ ማዘጋጀት፣ ወይም አንጃ ሠርቶ መነጠል በተቃዋሚው ቤት የግድ ሆኖ ተስተውሏልና ነው ተሃድሶው በእነርሱም ቤት መቀጣጠል ይገባዋል ማለታችን፡፡ በዚህም በዴሞክራሲያዊ አሠራር አመራር ይስተካከላል፤ አለመግባባት ይወገዳል፤ የሐሳብ ልዩነት እየተፋተገና እየተረታታ ይቀራረባል፡፡ ዴሞክራሲያዊ የውስጥ ሕይወትና የሐሳብ ነፃነት የሌለበት ፓርቲ የቱንም ያህል ትክክል አቋም ቢይዝ ሄዶ ሄዶ ማርጀቱና መምከኑ አይቀርም፡፡

 

በአንድ ሰው ብስለት ወይም ሌላ ነገር ላይ ተንጠልጥሎ ቢቆይ እንኳን ግለሰቡ አቅሙን ሲጨርስ አብሮ ያበቃለታል፡፡ የፓርቲው መሪዎች የፓርቲው የሥልጣን አካላትና ተቋማት በሙሉ በምርጫ የሚቋቋሙ ተጠያቂነታቸውም ለመራጫቸው የሆነ፣ የሚወርዱ የሚወጡትም በምርጫ ስለመሆኑ ከሚደነግግ ሕገ ደንብ ውጪ መሆን መጀመርያ የዴሞክራት ወግ አይደለም፡፡ በዚህ ላይ የሚጣሉ ፓርቲዎች በተደጋጋሚ ተስተውለዋልና ነው ተሃድሶው የአንድ ወገን ብቻ መሆን የለበትም ማለታችን።

 

ሐሳቦችና ጉዳዮች እየወጡ መነጋገሪያ እንዲሆኑ ማድረግንም ፓርቲዎች በዚህ የኢትዮጵያ ውስን ሁኔታም ውስጥ መጣርና መጋር አለባቸው፡፡ ለእውነትና ለሕዝብ ቅርብ መሆን፣ ወቅታዊ ጉዳዮች ከፓርቲ አባላት ውጪ መወያያ እንዲሆኑና ጥናቶች እንዲካሄዱባቸው ማነሳሳትም ሌላ ኃላፊነት ነው፡፡ የተቃራኒ ፓርቲዎችን አቋም መመርመርና አባላቱ በክፍት አዕምሮ እንዲገመግሙ ማድረግ የራስን አቋም ጥንካሬ ለመፈተሽና ለማጥራትም አላስፈላጊ ነው፡፡ የተቀናቃኙን ድርጅት አቋም ከአባላቱ ሊደብቅ የሚሻ የራሱ አቋም እንዳይተችና ጥፋቱ እንዳይጋለጥ የሚጥር ፓርቲ በበዛበት ሃገር ዴሞክራሲውን ወደፊት ማራመድ ሥለማይቻል ነው ተሃድሶ ያሻቸዋል ማለታችን።

 

የድርጅት ውስጣዊ ዴሞክራሲ የጥቅም ጉዳይ አይደለም፤ የህልውና ጉዳይ ነው፡፡ የጋራ አመራርን ያሰፍናል፡፡ የጋራ አመራር ባልፈዘዘበት ድርጅት ውስጥ የግለሰብ አድራጊ ፈጣሪነት መንገድ ይጠበዋል፡፡ የድርጅት አመራር ከላይ በተቀመጡ ጥቂት ሰዎች እንዳይጠለፍ ወይም በእነሱ አስተዋይነት ላይ ብቻ እንዳይወሰን የውስጥ ዴሞክራሲያዊ መድረኮች ወሳኝ ናቸው፡፡  የማያቋርጥ ሐሳብ የመስጠትና የመቀበል ሒደት ይኖራል፡፡ ሁሉንም ያሳተፈ ተከራክሮ ማሳመን የቻለ ሐሳብ፣ ግንዛቤና ሥልት ይመራል፡፡ ይህ አሠራር ድርጅትን ለመምራት ብቃት አለኝ የሚል ሁሉ ወንበር በመያዝ ላይ እንዳይተናነቅ ይረዳል፡፡ እንዲህ ያለው ልምድ  የሌለው ደግሞ በተቃዋሚው ቤት ነውና ተሃድሶው እዚያም መዝለቅ ይገባዋል፡፡

 

የድርጅት ውስጠ ዴሞክራሲ አለመግባባት የሚፈታበት የዳኝነት መድረክም ነው፡፡ ወደ ምርጫ ቦርድ ወይም ሌላ አካል የሚሄደው የፓርቲው የውስጥ አወቃቀር ይህንን ማድረግ ሲሳነው ነው፡፡ የኛዎቹ ደግሞ ይህን ሳያደርጉ ሁሌም ጣታቸውን በምርጫ ቦርዱ ላይ ይቀስራሉና ነው ተሃድሶው በእነርሱም ቤት መከናወን ይገባዋል ማለታችን፡፡   

 

ዛሬ ኢትዮጵያ የምትገኝበትን አደገኛና አሥጊ ሁኔታ ለመረዳት የዚህ ወይም የዚያ ፓርቲ አባል መሆን አያሻም፡፡ ኢትዮጵያ ግን ችግሩን ከመረዳት በላይ መፍትሔ የሚያመጣላትና መፍትሔ የሚሆናት አሁኑኑ በአስቸኳይ ትፈልጋለች፡፡ የችግሩ ምንጮች እኛው ከሆንን ደግሞ መፍትሄዎቹም እኛው እና እኛው ብቻ ነን፡፡

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy