ማጥለቅ እና ማስረጽ
ስሜነህ
ባለፉት ሃያ ስድስት ዓመታት ኢትዮጵያ ብዙኅነትን በዴሞክራሲያዊ መንገድ ለማስተዳደር መቻሏ እሙን ነው። ይህም በብዙሃኑ ህዝቦቿ ላይ በፈጠረው የእርስ በርስ መተማመን ተረጋግጧል። መብታቸው የተከበረ ማህበረሰቦች በአንድነት ከመኖር የተሻለ አማራጭ ሊወስዱ እንደማይችሉ በተግባር መታየቱን ተከትሎ የብሔር ብሔረሰቦች መብት እስከ መገንጠል ድረስ መከበሩ የመበታተን ቁልፍ እንዳልሆነ ታይቷል፡፡ በዚህ ላይ ያልተማከለው ፌዴራላዊ አስተዳደር ሁሉም ህዝቦች ያላቸውን ፀጋ በማልማት ተጠቃሚ እንዲሆኑና በፌዴራላዊ ስርዓቱ ላይ በጎ አመለካከት እንዲያዳብሩ አስችሏል።
መንግስት ሁሉም ክልሎች በየራሳቸው ፍጥነት እያደጉ፣ ነገር ግን በአቅም ልዩነት ምክንያት የሚፈጠረውን ያልተመጣጠነ እድገት ለማካካስ በማሰብ የሚሰጧቸው እገዛዎች፣ በተለይ በዳር አካባቢ የሚገኙ ታዳጊ ማህበረሰቦችን ከመቼውም ጊዜ በላቀ ኢትዮጵያዊ ገመድ እርስ በርስ እንዲተሳሰሩ አድርጓል።
አገሪቱን ከጫፍ ጫፍ የሚያስተሳስር የማህበራዊና የኢኮኖሚያዊ መሰረተ ልማት በማስፋፋት፤ ይህንንም በተናጠል ሳይሆን በጋራ ለመጠቀም የሚቻልበት እድል ተፈጥሯል። በጥቅሉ ባሳለፍናቸው ሃያ ስድስት ዓመታት በተሰሩ ተግባራዊና የአስተምህሮ ስራዎች በአገራችን ህዝቦች ዘንድ በልዩ ልዩ መሰረታዊ ጉዳዮች ላይ ከመቼውም ጊዜ የተሻለ ብሔራዊ መግባባት ተፈጥሯል።
ህገ መንግስቱ የዴሞክራሲና የሰላም፣ የፍትህና የእኩልነት ዋስትና እንደሆነ መግባባት ተፈጥሯል። ይህም በፌስቡክ አብዮት የማይገረሰስ መግባባት ነው። በምክንያት ለሚቃወምና ለሚደግፍ ህብረተሰብ ህገ-መንግስታችን የላቀውን ዋስትና ሰጥቷል። ከፈጣኑ እድገት ጋር ተያይዘው የተከሰቱ ነባርም ሆኑ አዳዲስ የስርዓቱ ችግሮችም እንደዚሁ ከሞላ ጎደል የጋራ ስምምነት ተይዞባቸዋል።
በእነዚህ መሰረታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከመቼውም ጊዜ የተሻለ ብሔራዊ መግባባት የተፈጠረ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ ይህ ግን በፅኑ የፖለቲካ ኢኮኖሚ መሰረት ላይ የተገነባ ለመሆን የሚቀረው በመሆኑ አሁንም የመዋለልና ወደፊትና ወደኋላ የመመለስ አዝማሚያዎች እየታዩ ነው። ስለሆነም ዛሬ በሃገራችን ኢትዮጵያ በህገ መንግስቱና የህግ የበላይነት ማስከበር ላይ፣ በልማትና በህዝብ ተጠቃሚነት አጀንዳዎች ላይ እንዲሁም በነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ስርዓት ግንባታ መሰረታዊ ጥያቄዎች ዙሪያ በተነፃፃሪ የተሻለ ብሔራዊ መግባባት መፈጠሩን ከግምት ያስገባ እንቅስቃሴ ብቻ ነው የሚያስፈልገን።
በሕገ-መንግስቱ መግቢያ እንደተገለፀው የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች በሀገራቸው ዘላቂ ሰላም፣ ዋስትና ያለው ዴሞክራሲ እንዲሰፍን፣ ማህበራዊ ዕድገታቸው እንዲፋጠን፣ የራሳቸውን ዕድል በራሳቸው የመወሰን መብታቸውን ተጠቅመው በነፃ ፍላጎታቸው በሕግ የበላይነት እና በራሳቸው ፈቃድ ላይ የተመሰረተ አንድ የፖለቲካ ማህበረሰብ ለመገንባት ቁርጠኝነታቸውንና መተማመናቸውን የገለፁበት የቃል ኪዳናቸው ሰነድ መሆኑን ለአፍታም እንኳ ቢሆን መዘንጋት አይገባም።
ህገ መንግስቱን የማፅደቁ ሂደት በምልዓተ-ሕዝቡ ሰፊ ውይይትና ተሳትፎ ያለፈ በየደረጃው ከፍ ያለ ትግል የተካሄደበትና ዴሞክራሲያዊ የነበረ መሆኑን ለግጭት መነሻ ተደርገው ከሚቀርቡ ፕሮፖጋንዳዎች ጎን ለጎን ማስታወስ ያስፈልጋል። መሰረታዊ አቋሞቻቸው ተቀባይነት ያላገኘው ወገኖች የመጨረሻ ምሬታቸውን በሂደቱ ዴሞክራሲያዊነት ላይ ለማሳበብ ዛሬም እየሞከሩ መሆኑ በሚገባ ተስተውሏልና።
የህዝብ ሉአላዊ የስልጣን ባለቤትነት በሕገመንግስቱ ከተደነገገ ጀምሮ ከፌዴራል እስከ ወረዳና ቀበሌ ድረስ የህዝብ ምክር ቤቶች ተደራጅተው በህግ የተሰጣቸውን ሃላፊነት በመወጣት ላይ ይገኛሉ። በተለይም በፌዴራል ደረጃ የተቋቋሙት ሁለቱ የህዝብ ተወካች ምክር ቤት እና የፌዴሬሽን ምክርቤቶች በየአምስት አመቱ በሚደረገው አገር አቀፍ ምርጫ በዜጎች ቀጥተኛና ነጻ ምርጫ አብላጫ ድምጽ ያገኙ ፓርቲዎችና ግለሰቦች የሚሳተፉበት ነው። የተወካዮች ምክር ቤት ፖሊሲና ህግ የማውጣት፣ አስፈጻሚ አካሉን የስራ መርሃ ግብርና በጀት የማጽደቅ፣ ስራ አፈጻጸም የመከታተልና የመቆጣጠር፣ ከፍተኛ የፖለቲካ አመራሩን ሹመት የማጽደቅ፣ በክልሎች ሰብአዊ መብቶች ሲጣሱ በክልሉ ጋባዥነት ወይም በራሱ ተነሳሽነት ጣልቃ በመግባት የማረጋጋትና መፍትሄ የመስጠት፣ ወዘተ ሃላፊነት የተሰጠው ሕገመንግስታዊ ተቋም መሆኑንም ከጣልቃ ገብነት ጋር ተያይዘው ለግጭት በምክንያትነት ለሚቀርቡ መርዞች በማጠየቂያነት ማጤን ያስፈልጋል። ኅዳር 29 ቀን 1987 ዓ.ም. የፀደቀው ሕገ መንግሥት አንድ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማኅበረሰብ ለመገንባት የሚረዱ ወሳኝ ሃሳቦችን የያዘ ሲሆን፣ በፊት የነበሩ የተዛቡ ግንኙነቶችን በማረም አዲሷን ፌዴራላዊት አገር ዕውን የማድረግ ዓላማን የሰነቀ ነው፡፡ በህገ መንግሥቱ መግቢያ በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና ዋስትና ያለው ዴሞክራሲ እንዲሰፍን፣ የሕዝቡ አኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ዕድገት እንዲፋጠን፣ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብትን በመጠቀም በነፃ ፍላጎትና በሕግ የበላይነት ላይ የተመሠረተ አንድ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማኅበረሰብ የመገንባት ቁርጠኝነት ተገልጿል፡፡
የአገሪቱ ጠቅላላ ሕዝብ የየራሱ አኩሪ ባህል፣ የመልከዓ ምድር አሠፋፈር፣ በተለያዩ መስኮች ግንኙነቱ የተሳሰረ መሆኑንና አብሮ የሚኖር ስለሆነ የጋራ ጥቅምና አመለካከት እንዳለውም ተገልጿል፡፡ በዚህም መሠረት ለመጪው የጋራ ዕድል፣ ጥቅም፣ መብትና ነፃነት በጋራና በተደጋጋፊነት አንድ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማኅበረሰብ የመገንባት አስፈላጊነት ታምኖበት የፌዴራል ሥርዓቱ እውን ሆኗል፡፡ እዚህም ጋር ግን የሚቀረን ቁልፍ ጉዳይ አለ፤ በመንግስትም ሆነ በድርጅት ከፍተኛ አመራሮች ጭምር በሚገለጽ መልኩ ዴሞክራሲው አልጠለቀም፤ የፌደራላዊ ስርአቱም አልሰረጸም። ስለሆነም የችግሮች ሁሉ ምንጭ አድርገው የሚወስዱትም ቁጥራቸው ቀላል እንዳልሆነ ተገንዝቦ ማጥለቅና ማስረጽ ተገቢ ይሆናል።
ግን ደግሞ ሃሳብን በነጻ የመግለጽ ህገ መንግስታዊ መብት ሽፋን በማኅበራዊ ሚዲያዎች ውስጥ የሚስተጋቡ ጽንፍ የረገጡ አቋሞች ወጣቶችን ከመቼውም ጊዜ በላይ ነውጠኛ እያደረጓቸው ነው። አገራዊ ራዕይ የሌላቸውና የአስተዋዩን ሕዝብ የጋራ እሴቶች የሚጋፉ ግድየለሾች የሚለቋቸው ሐሰተኛ መረጃዎችና የጥላቻ ንግግሮች፣ ስሜት ኮርኳሪ በመሆናቸው በአገር ላይ ትልቅ ጉዳት እየደረሰ ነው፡፡ በእልህ፣ በቂም፣ በጥላቻና በግትርነት የተሞሉ መልዕክቶች ከግንባታ ይልቅ አፍራሽነታቸው የጎላ በመሆኑ፣ አገራችንን የውድቀት ቋፍ ላይ እያደረሳት ነው፡፡ ኃላፊነት የማይሰማቸውና ለትልቁ ኢትዮጵያዊነት ምሥል ግድ የማይሰጣቸው ደግሞ ብሔርተኝነትን ከመጠን በላይ እየለጠጡ ችግር እየጠፈሩ ነው፡፡
ሃገራችን በምትከተለው የመድብለ ፓርቲ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በማንኛውም ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን በሚከተሉ ሃገራት እንደሚደረገው ሁሉ ሃሣብን በነፃ የመግለፅ፣ የመደራጀት፣ የመሠብሠብ እንዲሁም ሠላማዊ ሠልፎችን የማድረግ መብት የተፈቀደና ህገመንግስታዊ ዋስትናም የተሰጠው መሆኑ ግልጽ ነው፡፡
ግን ደግሞ ሃሣብን በነፃነት በመግለጽ መብት ሽፋን፣ በመሠብሠብና በመደራጀት መብት ስም፣ በሠላማዊ ሰልፍ ጥላ በመከለል የሚደረግ ማንኛውንም ዓይነት ህገወጥ እንቅስቃሴ የመመከትና በህግ አግባብ እርምጃ የመውሰድ ግዴታ እንዲሁ በስልጣን ላይ ለሚገኘው መንግስት የተሠጠ ሃላፊነትና ይኸውም ሃላፊነት በህገመንግስቱ የተረጋገጠ ነው።
ዴሞክራሲያችን ለጋ ከመሆኑ በመነሳት ዴሞክራሲያዊ ስርአቱን ለመገንባት ከሚደረገው እልህ አስጨራሽ ትግል ሾልከው የሚፈፀሙ የስነ-ምግባር ጥሰቶችን አጋኖና አባዝቶ በማቅረብ ህዝቡ በስርአቱ ላይ አመኔታ እንዲያጣ ለማድረግ አሁንም ሴራው አልበረደም። ስለሆነም ያለምክንያታዊነት የሚቀሰቀሱ ግጭቶች በዚህና በማስታመም አግባብ የሚያዙ ከሆነ ህገ መንግስታዊ ስርአቱ አደጋ ላይ መውደቁ አይቀሬ ይሆናል። የብሄራዊ ደህንነት የጋራ ምክር ቤት ሰሞኑን ያወጣው መግለጫ የሚያጠይቀውም ይህንኑ ነው። በተለይ በአንዳንድ ቦታዎች ላይ አመራሩ እራሱ ዳተኛ ሆኖ መገኘቱ አስጊ ነው። ስለሆነም የከፍተኛ አመራሩን ቁርጠኝነት የሚጠይቅ ስራ ከፊታችን ተደቅኗል። የመጨረሻውም መፍትሄ የፊታችን የካቲት ከሚከናወነውን የኢህአዴግ ጠቅላላ ጉባዔ ይጠበቃል።