Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ምሁሩና የሰላም አንደበቱ

0 257

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ምሁሩና የሰላም አንደበቱ

                                                        ታዬ ከበደ

የአገራችን ምሁር ሰላምን ከማረጋገጥ አኳያ ማከናወን ያለበት መሰረታዊ ጉዳዩች አሉ። የአገራችን ምሁር በተመደበበት የሙያ መስክ ከሚያበረክተው አገራዊ ስራዎች ባሻገር፣ ነገሮችን በቸልታ ባለመመልከት የሰላም አንደበት መሆን ይችላል። ይገባልም። ምሁሩ አልፎ አልፎ ብቅ እያለ ከሚሰጣቸው ትንታኔዎች በተጨማሪ ሰላምን በአገሪቱ በአስተማማኝ መንገድ እውን ከማድረግ አኳያ የበኩሉን አገራዊ ሚና ሊወጣ ይገባል።

ምሁራን ለሕዝቦች እኩልነትና አንድነት መስራት አለባቸው። ይህን ሲያደርጉ ለሰላም እጦት የሆኑ ጉዳዩች ይዘጋሉ። እርግጥ የእኩልነት ጥያቄን መቀበል ተገቢ ነው፡፡ የኪራይ ሰብሳቢ ባህሪ ያለበት አካል የመጀመሪያ ስራው የእኩልነት ጥያቄን ማዳፈን ነው፡፡ ይፈራል፡፡ ስለ እኩልነት መስማት አይፈልግም።

ምሁራን እዚህ ሀገር ውስጥ ስለተፈጠረው የእኩልነት መብት ማውሳትና እኩልነት ካለ ሰላም ሊመጣ እንደሚችል ማስረዳት ይኖርባቸዋል። ለዚህም አገሪቱ የምትከተለውን ፌዴራላዊ ስርዓት ከእኩልነት አኳያ መቃኘት ይኖርባቸዋል።

በፌዴራላዊ ሥርዓቱ ሁሉም ኢትጵያዊ በህግ ካልተደነገገ በስተቀር በፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ መስኮች እኩል መብት እንዲኖራቸው ተደርጓል። የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ሰላም በአስተማማኝ ሁኔታ ተረጋግጧል፡፡

ዜጎች በህግ ፊት እኩል ሆነዋል። የሚከተሉት የኃይማኖትና እምነትም በእኩልነትን የሚታዩበት ህገ መንገስታዊ ስርዓት ተረጋግጧል፡፡ ፍትሕን እንዲቋደሱና በፍትሕ ስርዓቱ ውስጥ ሁነኛ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ተደርጓል፡፡ በዚህ አዲስ የእኩልነት ግንኙነትም ሁሉም በየደረጃው ተጠቃሚ እንዲሆን ተደርጓል፡፡

ትናንት ዜጎች በልማት አጀንዳ ተሳታፊ ስላልነበሩ ህይወታቸውን የሚለውጥ ሀብት የማፍራትና ከአገሪቱ ሀብት በፍትሃዊነት የመጠቀም መብት አልነበራቸውም፡፡ የሕብረ ብሄራዊ ፌዴራል ሥርዓቱ አንዱ መሠረታዊ እምነት ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የልማት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማስቻል በመሆኑ ይህ እንዲረጋገጥና ህገ መንግስታዊ ዋስትና እንዲያገኝ ተደርጓል፡፡

ባለፉት መንግሥታት በአገሪቱ ተንሰራፍቶ የኖረውን የተዛባ ግንኙነት በመፋቅ አዲስ ኢትዮጵያዊ ማንነት ለመገንባት የሚያስችሉ የማንነቶች እኩልነት ማረጋገጥ፣ ሁሉም ዜጎች ኢትዮጵያን በመገንባት የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ ማድረግ፣ በአካባቢ ጉዳዮቻቸው ላይ ወሳኝ የሚሆኑበትን የራስ አስተዳደር ማረጋገጥ በአጠቃላይ ከአገሪቱ ልማት ተመጣጣኝ ጥቅም እንዲያገኙ ማድረግ ተችሏል፡፡

የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ማንነቶች አዲስ የእኩልነት መንገድ መክፈቱንና እንደ ማረጋገጫ መሣሪያ ስለተወሰደም በዚህ አወቃቀር አዲስ የእኩልነት ግንኙነትና የጋር ህልውና እንዲመሠረት ተደርጓል፡፡

በዚህም የአዲሲቷን ኢትዮጵያ የወደፊት ዕድል የመወሰን ሥልጣን ባለቤት መሆን እንዳለባቸው በወኪሎቻቸው አማካይነት ይፋ አድርገዋል፡፡ በፌዴሬሽኑ ምሥረታ ወቅት የገቡትን ቃል በአፈፃፀም ሂደት እንዳይዛነፍ የመጠበቅ ኃላፊነት የሚሰጣቸውን ህገ መንግሥት የመተርጎም ሥልጣን ህዝቦች እውን አድርገዋል፡፡

ይህም በመከባበር፤ በመተማመንና በመተባበር በእኩልነት አብሮ ለመኖር የሰላም ዋስትና ሆኗል፡፡ ታዲያ ይህን የሰላም ዋስትና ሁኔታ በተገቢው መንገድ ማውሳትና ለህብረተሰቡ ግንዛቤ መፍጠር የምሁራን ተቀዳሚ ተግባር መሆን ያለበት ይመስለኛል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ምሁራን የመንግሥትን ሥራ መጠንከር ያለባቸውን እንዲጠናከሩ በማድረግ መተቸት ያለባቸውም እንዲተቹት፣ የግንዛቤ ለውጥ እንዲመጣ ፊት ለፊት ቀድሞ ማሳየትና ግንዛቤ መፍጠር፣ ለዕድገትና ለብልፅግና ምቹ ሁኔታ መፍጠር፣ ለሰላምና ለዴሞክራሲ መዳበር የመሥራት አገራዊ ግዴታ ተጥሎባቸዋል። በእኔ እምነት ይህን ግዴታቸውን መወጣት አገር ችግሮችን ለመቅረፍ በሚደረገው ትልግ የበኩሉን ሚና ያበረክታል።

ምሁራን በህዝቦች መካከል መኖር ስለሚገባው የአንድነት መንፈስ በማስተማር መለያየት ምንም ዓይነት መፍትሔ ሊያመጣ እንደማይችል በማስረዳት ቀዳሚዎች አስተማሪዎች መሆን አለባቸው። ስለ አንድነት ሲያወሱም አገራችን ወድዳና ፈቅዳ የተቀበለችውን ፌዴራላዊ ስርዓት ማሰብ አለባቸው—ዴሞክራሲያዊ አንድነት የችግሮቻችን መፍቻ መሆኑን ስለማስተማር።

በእኩልነትና በአንድነት መንፈስ በጋራ የሚኖሩት የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች አሁን ለደረሱበት የእኩልነት፣ የዴሞክራሲና የልማት ዘመን እጅግ በርካታ ውጣ ውረዶችን አሳልፈዋል።

ወደር የለሽ መስዋዕትነት የጠየቀ የትጥቅ ትግል አድርገውም አስከፊውን ስርዓት ከጫንቃቸው በመራራና እልህ አስጨራሽ ትግላቸው በመጣልና ታላቁን ሀገራዊ ድል በማብሰር ዛሬ ለተገኘው የፖለቲካና ማህበረ-ኢኮኖሚያዊ ስኬቶች አብቅተውናል። ይህን እውነታ ማንም ሊክደው የሚችለው አይደለም።

ባለፉት ስርዓቶች የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በገሃድ የሚጨፈለቁባቸው ጊዜያት ነበሩ። የመብት ጥያቄን ማንሳት “ውግዝ ከመአርዩስ” እንዲሉት ዓይነት ነበር። ዛሬ ላይ መላው የሀገራችን ህዝቦች በመስዕዋትትነታቸው እውን ባደረጉት የኢፌዴሪ ህገ መንግሥት ለዘመናት ጥያቄዎቻቸው ምላሽ ለማግኘት የበቁበትን ድል ተጎናፅፈዋል። ርግጥ የትናንቷ ኢትዮጵያ ለብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦቿ የሰቆቃ ምድር እንደነበረች ማንም አይክድም።

የዚያ ዘመን ሰቆቃ ተዘርዝሮ አያልቅም። እነዚያ ወቅቶች ዜጎች ኑሯቸውን በቅጡ እንዳይገፉ የተቸገሩበት፣ ተስፋቸው ተሟጥጦ ግራ የተጋቡበት፣ መቋጫ በሌለው ጦርነት፣ ረሃብና ስደት የሚንገላቱበት ነበሩ። ግና ያ ሰቅጣጭ ወቅት ዳግም ላይመለስ ሀገሪቱን ተሰናብቷት ሄዷል—ዞር ብሎ እንደማያየን ለራሱ ቃል በመግባት። እናም አሁን የምንገኝበት የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ዘመን አዲስ ምዕራፍ ነው፤ ሁሉም የኢትዮጵያ ህዝቦች የታገሉላቸው የዘመናት ጥያቄዎች መልስ ያገኙበት።

ይህ በመሆኑም ዛሬ ዜጎች ለአዲስ ህይወት ማበብ ተስፋ ሰንቀው፣ በፀና ህብረት ላይ ቆመው፣ እጅ ለእጅ ተቆላልፈው ኑሮን እያጣጣሙ ነው። ንፁህ አየር መማግ፣ በሰላም ወጥቶ መግባት፣ በነፃነት መንቀሳቀስና ሌሎች ሰላማዊ አየር በሀገራቸው ላይ እየናኙ ናቸው። ለዚህ መብቃት የተቻለው ደግሞ ውድ የህዝብ ልጆች በከፈሉት የህይወትና የአካል  መስዕዋትነት ነው። ሀገሪቱም አስተማማኝ የሰላም ማማ ላይ ወጥታለች፤ ዓለም የመሰከረለት የልማት መስመር ላይም ናት፤ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ በፅኑ መሰረት ላይ እንዲቆም ለማድረግ የተጓዘችው መንገድም ረጅም ነው። ይህ የሆነውም ሀገራችን ውስጥ ዴሞክራሲያዊ አንድነት በመኖሩ ነው። ታዲያ ይህን ሃቅ ለማስረዳት ምሁሮቻችን ቀዳሚ መሆን አለባቸው። በዚህ ተግባራቸውም ዴሞክራሲያዊ አንድነትን በህብረተሰቡ ውስጥ ይበልጥ በመፍጠር የሰላም አንደበት ሊሆኑ ይችላሉ።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy