Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ምርታማነትና የዋጋ ንረት

0 233

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ምርታማነትና የዋጋ ንረት

                                                        ታዬ ከበደ

በአገራችን እያደገ የመጣው ምርትና ምርታማነት በሂደት የዋጋ ንረትን ሊያረጋጋ የሚችል ነው። አንዳንድ ወገኖች መንግስት በአንድ በኩል በአገሪቱ ምርትና ምርታማነት ጨምሯል እያለ፣ በሌላ በኩል ደግሞ የዋጋ መናር መኖሩን ይገልፃል እያሉ የሚያቀርቡት ሃሳብ በጊዜው የተሰጠ አይመስለኝም። ምክንያቱም ምርትና ምርታማነቱ ቢጨምርም በአሁኑ ወቅት እየተጠቀምን ያለነው ያለፈውን ዓመት ምርት እንጂ የያዝነውን ዓመት ስላልሆነ ነው። በመሆኑም ምርቱ በአግባቡ ተሰብስቦ አርሶ አደሩ ወደ ገበያ ሲያወጣው የዋጋ ንረቱ ቁጥጥር ስር ሊውል የሚችል ይመስለኛል።

እንደሚታወቀው ሁሉ መንግስት የማስፋት ስትራቴጂን በመጠቀም በአነስተኛ የአርሶ አደር ማሳ ላይ ለውጥ ማምጣት ተችሏል። ይህም በአነስተኛ ማሳ ላይ ብዙ ምርት ማግኘት ያስቻለ፣ ተጠቃሚነትን በማረጋገጥ የላቀ ሚና ተጫውቷል። የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የተመሰረተው በግብርና ላይ እንደመሆኑ መጠን፤ የአርሶ አደሩ የአመራረት ዘይቤ መለወጡ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ተችሏል።

በዚህም ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚሆኑ ምርቶችን በበቂ ሁኔታ ማምረት ተችሏል። ይህም አጠቃላይ የሀገሪቱን ምጣኔ ሃብት ዕድገት ከፍ አድርጓል። በተለይ ባለፉት ዓመታት የተገኘው ምጣኔ ሃብታዊ ዕድገት የምርታማነት ማደግ ውጤት ነው።

ባለፉት ዓመታት መንግሥት ግብርናውን ወደ ላቀ ደረጃ ማሸጋገር አማራጭ የሌለው መፍትሔ መሆኑን ተገንዝቦ ሲሰራ ቆይቷል። በያዝነው ሁለተኛው የልማት ዕቅድ ላይም በመጀመሪያው የዕቅድ ዓመት ላይ የተገኘውን አመርቂ ውጤት ይበልጥ አጎልብቶ ለመቀጠል እየተሰራ መሆኑን መረጃዎች ያስረዳሉ።

የግብርና ልማት መዋቅራዊ ለውጥ ማምጣት ይችል ዘንድ በበሁለተኛው አምስት ዓመቱ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ትኩረት ተሰጥቶታል። እንደሚታወቀው አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ለእርሻ ሊውል የሚችል ሰፊና ለም መሬት እንዲሁም የአርሶ አደሩ ጉልበት አለ። በሀገሪቱ ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት ታዲያ ይህ ግብርናው ውጭ ከፍተኛ እምቅ ሃብት ነው። ይህ ሃብት ለዜጎች ሰፊ የሥራ ዕድል እየፈጠረ ሲሆን፤ ገና ምንም ያልተነካ እምቅ በመሆኑም ውጤት ሊያመጣ የሚችል ነው። ሀገሪቱን ለመለወጥ ወሳኙ ሃብት ተደርጎ መወሰዱም እንዲሁ።

ቀደም ሲል እንደገለፅኩት ምርትና ምርታማነት በማደጉ ሳቢያ የአርሶ አደሩ ህይወት በአያሌው ተለውጧል። እንዲያውም በአንዳንድ አካባቢ የሚገኙት አርሶ አደሮች ትርፍ አምራች እንዲሆኑ አስችሏቸዋል።

ይህ ትርፍ አምራችነታቸውም ከተጠቃሚነታቸውባሻገር ሌሎች አካባቢዎች በተፈጥሮአዊው የድርቅ አደጋ በሚጠቁበት ወቅት የሚፈጠረውን ክፍተት እየሞሉ ነው። ምርትና ምርታማነት በማደጉ ሳቢያ ከፍተኛ ምርት እንደሚገኝ ይታሰባል። መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፤ ከ345 ሚሊዩን ኩንታል በላይ የመኸር ምርት ይሰበሰባል ተብሎ ይጠበቃል።

በአብዛኛዎቹ የመኸር አብቃይ አከባቢዎች የተስተካከለ የዝናብ ስርጭት በመኖሩ በአሁኑ ወቅት ጥሩ የምርት ሁኔታ በእርሻ ማሳ ላይ መኖሩም ተገልጿል። አርሶ አደሩም በእሸትና በቡቃያ ደርጃ ያሉ ምርቶችን በአግባቡ የመጠበቅ፣ በየጊዜው ማሳውን የመፈተሽ ሰብሉ በአረም እንዳይጠቃ ክትትል ማድረጉም ተመልክቷል።

ተባዮችን በባህላዊ መንገድ መከላከል ከአቅም በላይ በሚሆንበት ወቅትም ፀረ- ተባይ ኬሚካሎችን በመርጨትና በመከላከል በአሁኑ ወቅት በጥሩ ሁኔታ ማሳ ላይ የሚገኘውን ምርት ወደ ጎተራው እስኪገባ ድረስ የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ ርብርብ እያደረጉ ነው። ምርቱ በታሳቢነት ከሚታወቀው የምርት ብክነት ባሻገር ሙሉ ለሙሉ ከተሰበሰበ የዋጋ ንረትን የሚከላከል ነው።

እርግጥ በአርሶ አደሩ እጅ እንዳለ የሚታሰበው መሬት አነስተኛ ነው። ከዚህም በተጨማሪ ካለችው መሬት የሚያገኘው ምርት ዝቅተኛ ነው። ይህን መንግሥት በሚገባ በመገንዘቡ ዘርፈ ብዙ የማሻሻል ጥረቶች አድርጓል። በውጤቱም አነስተኛ ይዞታ ያላቸው አርሶ አደሮችን ይዞ ለውጥ  ማምጣት አይቻልም የሚለውን አስተሳሰብ መስበር ችሏል። አነስተኛ ይዞታ ያላቸው አርሶ አደሮች ትኩረት ከመስጠት ይልቅ ለሰፋፊ እርሻዎች ትኩረት መስጠትና ለውጥ ማምጣትን የሚሰብኩ ወገኖች እንዳሉ ግልጽ ነው። እነዚህ ወገኖች የሚሰብኩት በግብርናው ዘርፍ ለሚሰማሩ ባለሃብቶች ትኩረት የመስጠትን አስፈላጊነት የሚሰብክ ነበር። ይህ ደግሞ ሀገራዊና ህዝባዊ ጥቅም የሚመጣበትን ምስጢር ካለመረዳት ወይም ለመረዳት ካለመፈለግ የመጣ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል።

መንግሥት አነስተኛ ይዞታ ላላቸው አርሶ አደሮች ምን ያህል ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ በተደጋጋሚ ገልጿል። ይህን የመንግሥትን ፖሊሲ ትክክለኛነት ለማረጋገጥም ተችሏል። የሚታይና አሳማኝ ውጤት ማምጣትም እንደተቻለም ከአርሶ አደሩ በላይ ምስክር የሚያሻው አይመስለኝም። ምንም እንኳን ለውጡን የማይፈልጉ ኃይሎች ስህተት ፈላጊ ሆነው ቢቀጥሉም፤ በግብርናው ዘርፍ ባመጣነው ለውጥ ብዙዎች በመስማማት ላይ ይገኛሉ። ኢትዮጵያ የአርሶ አደሩን ምርታማነት በማሳደግ፣ ለምርቱ ገበያ በማመቻቸትና ከግሉ ዘርፍ ጋር ትስስር በመፍጠር ምርትና ምርታማነትን አሳድጋ ተጠቃሚ በመሆን ላይ ትገኛለች።

አርሶ አደሩ የለውጥ መስመሩን ተረድቶ በእምነት ወደ ሥራው በመግባቱ በዓመት ሁለቴና ከዚያም በላይ ለማምረት ችሏል። እንዲሁም በከርሰ ምድርና በገጸ -ምድር ያለውን የውኃ ሃብት የመጠቀም ሰፊ ተግባር አከናውኗል።

በውኃ ማሰባሰብና ማቆር፣ የጉድጓድ ውኃን በመጠቀም የወንዝ ውኃን ጠልፎ ጥቅም ላይ በማዋል ብዙ ርቀት ተጉዟል። በመሆኑም አርሶ አደሩ ከራሱ ፍጆታ አልፎ ለከተማው ነዋሪዎች ከፍተኛ ፍላጎት የሆኑትን ምርቶች ማቅረብ ችሏል። ከነዚህ ውስጥ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች በግንባር ቀደምነት ተጠቃሽ ናቸው።

ከዝናብ ጥገኝነት በተላቀቁ አመራረት የተገኙትን ምርቶች መጠቀምም እየተቻለ ነው። የመስኖ ልማት ሥራው በበጋ የበቆሎ እሸት ተመጋቢዎች እንዲሆን አስችሎናል። ባለፉት ሁለት ዓመታት ደግሞ ሥራው ከሁለት እጥፍ በላይ አድጓል።

ለአርሶ አደሩ በዚያው ልክ ገበያው ተመቻችቷል። አርሶ አደሩ በራሱ ባቋቋማቸው የአርሶ አደሮች የህብረት ሥራ አማካይነት ምርቱን ለገበያ በተመጣጣኝ ዋጋ እያቀረበ ተጠቃሚ መሆን ጀምሯል።

በመኸር ምርት ይገኛል ተብሎ ከሚታሰበው 345 ሚሊዩን ኩንታል ውስጥም አርሶ አደሩ ወደ ገበያው ሲያወጣው የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠር ዓይነተኛ ሚና ይኖረዋል። ይህ ከፍተኛ ምርት በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፎችን የሚመታ ነው። በአንድ በኩል የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ያጎላል። በሌላ በኩል ደግሞ የዋጋ ንረትን በመቆጣጠር ረገድ የራሱን ድርሻ ያበረክታል። ታዲያ ይህን እውነታ ለመመልከት ጊዜን መጠበቅ ያስፈልጋል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy