Artcles

ምክንያታዊነትና ሥሜታዊነት!

By Admin

January 15, 2018

ምክንያታዊነትና ሥሜታዊነት!

አባ መላኩ

አሁን ላይ አገራችን ወደ ቀድሞ መረጋጋቷ ተመልሳለች። ነገሮች መልክ ምልካቸውን እየያዙ ናቸው። በኢህአዴግ እህት ድርጅቶች መካከል ለ17 ቀናት የተካሄደው ግምገማ የድርጅቱን ቀደምት መደጋገፍና መናበብ እንደገና እንዲያብብ አድርጎታል። የሃሳብ ስምምነት ከተግባር እንደሚቀድም ሁሉ  ድርጅቱ  የሚታዩ ጥንካሬችን  ለማጎልበት በተመሳሳይ ለሁከትና ነውጥ የዳረጉንን ህጸጾች  ለማስተካከል ከስምምነት ደርሷል። እንደእኔ እንደኔ  ህብረተሰቡም ይህ ስምምነት በተግባር እንዲጸም ከድርጅቱ ጎን ሊሰለፍ ይገባል ባይ ነኝ።  ምክንያቱም የኢህአዴግ ህይወት የተመሰረተው በህዝባዊ ድጋፍ ላይ ነው። እስካሁን ያለውን የኢህአዴግ ስኬቶች ብንመለከታቸው ሁሉም በጠንካራ ህዝባዊ ድጋፍ  የታጀቡ ሆነው እናገኛቸዋለን። የአገራችንን የዴሞክራሲ ስርዓት ሊጎለብት፣ ዕድገታችን ሊፋጠንና የህዝብ ተጠቃሚነት የሚረጋገጠው ምክንያታዊ አስተሳሰብ ሲጎለብት እና ስሜታዊነት ሲወገድ ብቻ ነው።  

አሁን ላይ በሁሉም አካባቢዎች ግጭት ተወግዷል፣ መረጋጋት እየሰፈነ ነው፣ በበርካታ አካባቢዎች በተካሄዱ ህዝባዊ ኮንፍረንሶች ላይ የታየው መንፈስ ህዝቦች እንደቀድሞው በመቻቻልና በመረዳዳተ መኖር እንደሚፈልጉ፤ ተፈናቃዮችም ወደየቀያቸው እንዲመለሱ ሁኔታዎች እየተመቻቹ፣ በቀጣይም እንዲህ ህዝቦችን የሚከፋፈል ነገር  በመካከላቸው ሊፈጥር እንደማይችል  የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች  አስረግጠው ሲናገሩ ተመልክተናል፤ አድምጠናል። ሰላም ዋስትና የሚኖረው በህብረተሰቡ ተሳትፎ ሲታጀብ ብቻ ነው። ሰላም ለማስከበር መንግስት  የትኛውንም ያህል ቁጥር ያለው የጸጥታ ሃይል ቢያሰማራም ህብረተሰቡ  ሰላሙ የእኔ ነው እስካላለ  የመንግስት ጥረት ብቻ ዕርባና የለውም።

ለዘላቂ ሰላም መረጋገጥ የሁላችንም ጥረት እንደተጠበቀ ሆኖ ሚዲያው የሚያበረክተው ሚና ደግሞ የማይተካና ወሳኝ ነው። ሚዲያ በሁለት ፊት የተሳለ ቢላዋ  ነው። ይህም ማለት ሚዲያን በአግባብ መምራት ከተቻለ የልማትና የዕድገት መሰላል ነው። ይህ ካልሆነ ግን ያልታሰበንና ያልተፈለገን ውጤት ሊያስከትል እንደሚችል  ተመልክተናል። በመሆኑም ሚዲያዎቻችን ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይገባል።  የማህበራዊ  ሚዲያዎች መስፋፋት  ለዓለማችን ይዞላት ከመጣው መልካም ነገር  ባሻገር ያመጣባትም ጣጣ በቀላሉ የሚታይ አይደለም።  በማህበራዊ ሚዲያ ሳቢያ  ዓለማችን  በቀውስ እየተናጠች  እንደሆነች ሁሉ  በአገራችንም የቀውስ ምንጭ እየሆኑ  ናቸው።  በደንባራ በቅሎ ቃጭል ተጨምሮ  እንዳይሆን የእኛዎቹ ሚዲያዎች ሚዛናዊ ዘገባዎችን በማቅረብ  የአገርንና የህዝብን  ጥቅም ታሳቢ ማድረግ ይኖርባቸዋል ባይ ነኝ።

ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ማለት ብዝሃነትን ማስተናገድ መቻል  ማለት ነው። ኢትዮጵያ የበርካታ እምነቶች፣ የበርካታ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች፣ የበርካታ ፍላጎቶችና አስተሳሰቦች እንዲሁም የበርካታ ባህሎች መገኛ ናት። አገራችን ይህን ልዩነት ማስተናገድ የሚችል ስርዓት መተግበር ከተሳናት  ኢትዮጵያ እንደአገር ልትቀጥል አትችልም። አሁን ላይ ዓለም በበርካታ ነገሮች ተቀይራለች። ዴሞክራሲ የአገሮች የህልውና ካስማ በሆነበት ጊዜ የቀድሞው ጠቅልለህ ግዛ አካሄድ  የሚያስኬድ አይደለም። ብዝሃነት በአግባብ ማስተናገድ ከተቻለች የጥንካሬና የዕድገት  መሰረት እንደሆነ ኢትዮጵያ ጥሩ ማሳያ ያለ አይመስለኝም። የዘመናት የአገራችን የቁልቁለት ጉዞ  የተገታው አገራችን ብዝሃነትን ማስተናገድ በመጀመሯ ነው። አገራችን  ባለፉት 27 ዓመታት ዴሞክራሲያዊ  ስርዓት  መገንባት በመቻሏ ዘርፈ ብዙ ስኬቶችን ማስመዝገብ ችላለች።

ብዝሃነት የግጭትና የቀውስ  ምክንያት ሊሆን እንደማይችል ባለፉት 27 ዓመታት  የአገራችን ጉዞ ጥሩ ማረጋገጫ ነው። በርካታ የዓለማችን አገሮች አንድ ሃይማኖት፣ አንድ ብሄር፣ አንድ ቋንቋ ኖሯቸው እንኳን ለከፋ ቀውስ ተጋልጠው ተመልክተናል። ብዝሃነት በአግባብ ማስተናገድ ከተቻለ የግጭት ምክንያት ሊሆን እንደማይችል የባለፉት 27 ዓመታት የአገራችን ሁኔታ ጥሩ ማሳያም ነውም። በአዲሲቷ ኢትዮጵያ  የህዝቦችን መብት ወይም በህዝቦች መካከል አድልዖ ሊፈጥር የሚያስችል ሁኔታም የለም። ይሁንና በኢህአዴግ አመራሮች ግምገማ የተስተዋሉ የጥገኞች አካሄድ ግን የለም ማለት አይቻልም።  

በአገራችን ሰላማዊ በሆነ መንገድ ማንም በግልም ይሁን በቡድን ሃሳቡን የመግለጽ ህገመንግስታዊ መብቱ የተረጋገጠ ነው። ለመደገፍም ይሁን ለመቃወም ምክንያታዊ  መሆን እጅግ አስፈላጊ ነው። አገር በምክንያታዊነት ታድጋለች፤ በስሜታዊነት ደግሞ ትፈርሳለች። እንደእኔ እንደኔ ጽንፍ የወጣ ድጋፍም ሆነ ተቃውሞ ለአገራችን ፖለቲካ መጎልበት የሚበጅ አካሄድ አይደለም። ሁለቱም ጽንፎች  ዋጋ አስከፍለውናል። እስካሁን ባለው ሁኔታ ልማታዊ ጋዜጠኝነት በአግገባብ ተተርጉሟል የሚል አቋም የለኝም። የህዝብ ሚዲያዎች አዎንታዊ ዘገባዎችን ብቻ ያቅርቡ እንደተባለ ሁሉ ይቀርቡ የነበሩ ዘገባዎች በአብዛኛው ድክመትን ለማረም የሚያግዙ ሆነው አላገኘኋቸውም። በእኔ እሳቤ ይህ ህብረተሰቡን የተሟላ መረጃ እንዳይኖረው ስለሚያደርገው ይህን ሚዛናዊ ለማድረግ  ወደሌላ ሚዲያዎች እንዲሄድ አድርጎታል።   

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሚዲያዎች እየተመለከትን ያለነው  ነገር ይበል የሚያሰኝ ነው። ሁሉም በልክ በልክ እየተስተናገደ ነው። ይህ አካሄድ ጽንፈኝነት ቦታ እንዳይኖረው፣ የጽንፈኛው ሚዲያዎች አድማጭና ተከታይ እንዳይኖራቸው ከማድረጉም ባሻገር ምክንያታዊነት በህዝቦች ውስጥ እንዲጎለብት ያግዛል። ምክንያታዊነት በኢትዮጵያ ህዝቦች ዘንድ እየጎለበተ መምጣት ጀምሯል። ማንም ጽንፈኛ እየተነሳ እንዲህ አድርግ ወይም እንዲህ አታድርግ ስላለው ብቻ በጅምላ የሚነዳ እንዳልሆነ አንዳንድ አብነቶችን ማንሳት ይቻላል።

ከዚህ በፊት የሙስሊም መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ በሚል ራሱን አደራጅቶ ይንቀሳቃሰ የነበረ ቡድን ምክንያታዊ መሆን ባለመቻሉ የህብረተሰቡን ድጋፍ ማግኘት አልቻለም። በዚህም ሳቢያ ህገወጦችን  ህብረተሰቡ ራሱ ለህግ አሳልፎ ሰጥቷቸዋል።   በተመሳሳይ ቅንጅት ድህር 1997 ዓ ም ምርጫ ወቅት  ይከተል የነበረው አካሄድ ምክንያታዊ ባለመሆኑ ህዝባዊ ድጋፍ ማግኘት ባለመቻሉ ተንኮታኩቶ ሊወድቅ ችሏል።  በቅርቡ በአገራችን የተከሰተውን ሁከት አስመልክቶም  እየተካሄዱ ካሉ ኮንፍረንሶች መረዳት የሚቻለው ይህንኑ ነው።

የምክንያታዊነት አስተሳሰብ  ሲነግስ ዜጎች  መብታቸውን መጠየቅ ብቻ ሳይሆን  ግዴታቸውን ከመወጣት ባሻገር ለሌሎች መብቶች መረጋገጥ እንዲሁም  ለህግ የበላይነት  መረጋገጥ  ይታገላሉ። በጭፍንና ጥልቅ  ጥላቻ ናላቸው የዞረ አሊያም የግል የፖለቲካ ፍላጎታቸውን  በድብቅ ለማሳካት  የሚፈልጉ አካላት አገር ሊያፈርሱና ህዝብን ለማጋጨት የሚያደርጉትን መሯሯጥ ማጋለጥ የሁሉም ሃላፊነት ነው። ሚዲያዎቻችን በራሳቸው ያለባቸውን ህጸጽ ለመቅረፍ የጀመሩት አካሄድ ይበል የሚያሰኝ ነው።   

በግጭት ሳቢያ ዜጎች ያለሃጢያታቸው ሲገደሉ፣ ሲቆስሉ፣ ሲንገላቱ፣ ንብረታቸው ሲዘረፍና ሲወድም፣ ለበርካታ  ለዜጎች የስራ እድል የፈጠሩ ፋብሪካዎችና ህዝብ  የሚገልገልባቸው  መሃበራዊ ተቋማት ሲወድሙ  ጽንፈኛው የዳያስፖራ ፖለቲከኞች  ጮቤ ሲረግጡ እንደነበር  ተመልክተናል። ጽንፈኛ የዳያስፖራ ፖለቲከኞች አገር በተረጋጋች፣ ልማት የተቀላጠፈ ጊዜ ሁሉ ጥሩ ስሜት እንደማየኖራቸው ከዚህ የተሻለ ማረጋገጫ የለም። ጽንፈኛ የዳያስፖራ ፖለቲከኞች አንዱ የጥፋት በር ሲዘጋባቸው ሌላውን ማማተራቸው የማይቀር ነው። ለአብነት የኤርትራን መንግስት ተልዕኮ ለማሳካትና  አገራችንን የትርምስ ቀጠና ለማድረግ የመላላክ ፖለቲካ ፈጻሚዎች ሆነው  ተመልክተናል። በተመሳሳይ ለግብጽ መንግስት ተቆርቋሪ መስለው  የኢትዮጵያ ህዝቦች የትብብር ማሳያ የሆነውን የታላቁን የህዳሴ ግድብ ለማወክ ሲሯሯጡ ነበር።

የሚያስገርመው ጽንፈኛው የዳያስፖራ ፖለቲከኞች አገር እንደፈረሰች መንግስት እንደሌለ አስመስለው የሚችሉትን ያህል ቢቀሰቅሱም አድማጭና ተመልካች አላገኙም። ለዚህ ሁለት ተጨባጭ ማረጋገጫዎችን ማንሳት ይቻለል። የመጀመሪያው የጥፋት ሃይሎች ህብረተሰቡን በብሄር በመከፋፈል አንዱ ሌላውን እንዲያጠቃ ያደረጉት ሰፊ ፕሮፓጋንዳ ተቀባይነት ባለማግኘቱ አገራችን ወደ እልቂት ሳታመራ ቀርታለች። ሁለተኛው ማረጋገጫ ደግሞ ጽንፈኛው ሃይል ኢትዮጵያ  የግጭት አውድማ እንደሆነች አድርጎ ለውጩ ዓለም ለማቅረብ  ቢሯሯጥም ሰሚ ጆሮ የሰጠው አካል ባለመኖሩ ወደ አገራችን  የሚደረገው የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትም ሆነ የቱሪስት ፍሰት እንደቀድሞው  ቀጥሏል። የጽንፈኛው ዳያስፖራ ፖለቲከኛ ቅስቀሳ አድማጭና ተመልካች ያጣው አገራችን ባለፉት 27 ዓመታት መገንባት በቻለችው መልካም ገጽታ ነው። አሁንም የጥፋት ሃይሎች የብሄር የግጭት  ታክቲካቸው  አልሆን ሲላቸው፤ ሃይማኖትን ከሃይማኖት እንዲሁም ይህ አልሆን ሲላቸው በመንግስት ላይ ቅሬታ ይኖራቸዋል  የሚሏቸውን ሃይሎች በማሰባሰብ ሁከትና ነውጥ  ለማነሳሳት መሞከራቸው አይቀርም።  በመሆኑም ህብረተሰቡ የእነዚህን የጥፋት ሃይሎች ድብቅ የፖለቲካ ፍላጎት ተረድቶ  የእነሱ መጠቀሚያ እንዳይሆን ሊጠነቀቅ ይገባል።