ሥነ ምግባርና ህግን አጣምረን ሠላማችንን እናረጋግጥ
ብ. ነጋሽ
የሃገር ሽማግሌዎች፣ የጎሳ መሪዎች፣ በኦሮሞ ባህል ደግሞ አባገዳዎች፣ የሃይማኖት መሪዎች የአካባቢን ሰላም በማስከበር ረገድ ትልቅ ድርሻ አላቸው። በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ጥብቅ ማህበራዊ ትስስር ባለባቸው ሃገራት የስነምግባር ደንቦች (moral norms) ከህግ ጋር የተመጣጣነ አልፎ አልፎም የበለጠ ጉልበት ይኖራቸዋል። በመሆኑም የስነምግባር ደንቦችን የማስጠበቅ ሚና ያላቸው የሃገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የጎሳ መሪዎች (አባ ገዳዎች) የአካባቢ ሰላምን በማስከበርና እርቅ በማውረድ ረገድ ትልቅ ድርሻ ይኖራቸዋል። ኢትዮጵያ ውስጥ በሁሉም ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ውስጥ ባሉ ማህበረሰቦች ዘንድ የሃገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች እንዲሁም የጎሳ መሪዎችና አባገዳዎች ትልቅ ስፍራ ይሰጣቸዋል። የሃገር ሽማግሌዎች በትውልዶች ውስጥ በማለፍ የካበተ የህይወት ልምድና ገጠመኞች አላቸው። በየትውልድ ቅብብሎች ክፉ ደጉን አስተውለዋል። ከዚህ ማስተዋል የነገሮችን አካሄድ አስቀድመው መተንበይ፣ አደጋን አስቀድሞ መረዳት፣ ከስሜት ይልቅ እውነት የሚገዛቸው የሰከነ አቋም ያላቸውው የትውልድ አንጋፋዎች ናቸው።
በመሆኑም የሃገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና ባህላዊ መሪዎች በቤተሰብ ውስጥ፣ እንዲሁም በግለሰቦች መሃከል የሚፈጠርን አለመግባባት የማህበረሰቡን የስነምግባር ደንብ መሰረት አድርገው በእርቅ ከመዳኘት ጀምሮ በማህበረሰቦች መሃከል የሚፈጠሩ አለመግባባቶችንና ግጭቶችን በመፍታትና በማስታረቅ ረገድ ትልቅ ሃላፊነት ሲወጡ ኖረዋል። በአጠቃላይ በተለይ በኢትዮጵያ የተለያዩ ማህበረሰቦች ውስጥ በከተሞች ጭምር ከግለሰባዊነት ይልቅ ማህበራዊ ትስስር ጥብቅ በመሆኑ የስነምግባር ደንቦች የሰዎችን አኗኗር በመወሰን ረገድ ያላቸው ድርሻ ከፍተኛ ነው። እናም የስነምግባባር ደንቦችን የሚያስጠብቁ የሃገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች ሰላምና እርቅን በማውረድ ረግድ ጉልህ ድርሻ አላቸው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሃገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የሚያጋጥሙ የሰላም መደፍረስን በማረገብና ግጭቶችን በመዳኘት ድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል።
በሃገራችን በተለይ ከ2008 ዓ/ም ጀምሮ በአንዳንድ የሃገሪቱ አካባቢዎች የሰው ህይወት የሚጠፋባቸውና ንብረት የሚወድምባቸው ግርግሮች ሲያጋጥሙ ቆይተዋል። እነዚህ ግርግሮች አሁንም አልበረዱም። ለግርግሮቹ ምክንያት የሆነው፣ ህዝብ በተለይ ወጣቶች በመንግስት ላይ የነበራቸው ቅሬታ መሆኑ ይታወቃል። የመልካም አሰተዳደር መጓደል፣ የፍትህ ስርአት መዛባት፣ የኪራይ ሰብሳቢነትና ሙስና፣ የስራ አጥነት ችግሮች ወዘተ ከግዜ ወደጊዜ እየተባበሱ መሄድ ጋር ተያይዞ ቅሬታው ወደአደባባይ ተቃውሞነት የተቀየረበት ሁኔታ እንደነበረም ይታወሳል። ህዝብ በመንግስት ላይ ቅሬታ እንዲያድርበት ያደረጉት ችግሮች ተጨባጭ ናቸው። ከችግሮቹ ስፋት አንጻር ሲታይ የሚያስገርመው ህዝብ ቅሬታ ያደረበት መሆኑ ሳይሆን፣ ረጅም ጊዜ በትእግስት ማለፉ ነው። ህዝብ ላይ ቅሬታዎች የፈጠሩ ችግሮች ከመቃለል ይልቅ እየደነደኑ ልማዳዊ ተግባር እየሆኑ ዘልቀው ኮርኳሪ አጋጣሚ ሲያገኝ፣ በድንገት የአደባባይ ተቃውሞ ሆነው ወጥተዋል።
ይሁን እንጂ የአደባባይ ተቃውሞዎቹ የቅሬታ ድምጾችን በማሰማትና መንግስት ለችግሮቹ ምላሽ እንዲሰጥ ጫና በማሳደር ተገድበው አልቀሩም። ከዚህ ይልቅ ወደየሃይል ጥቃት የተቀየሩበት ሁኔታ ተስተውሏል። በዚህ የሃይል ጥቃት ለተቃውሞ አደባባይ በወጡ ሰዎችና በጸጥታ አስከባሪዎች መሃከል ግጭት አጋጥሟል። በዚህም የሰው ህይወት ጠፍቷል። አደባባይ ላይ በድንገት ወደሃይል እርምጃ ወይም ሁከትነት የተቀየረው ተቃውሞ ለግለሰቦች፣ ለህዝብና ለመንግስት ንብረት መዘረፍና ውድመት ምክንያት ሆኗል።
ይህን ተከትሎ መንግስት፣ ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግና አባል ድርጀቶቹ የችግሮቹን ምንጭ ፍለጋ ወደውጭ ከማማተር ይልቅ ወደውስጥ መመለከትንየመረጡበት ሁኔታ ነው ያለው። ህዝቡን ለተቃውሞ አደባባይ ያወጣው ቅሬታ ተጨባጭ ምክንያት ያለው መሆኑን፣ ቅሬታዎቹ ከመንግስት የአፈጻጸም ድክመቶች የመነጩ መሆናቸውን፣ በተለይ ስር የሰደደ የመልካም አሰተዳደር መጓደል፣ የኪራይ ሰብሳቢነት፣ የህግ የበላይነት መጓደል፣ የስራ አጥነት ችግሮች መኖራቸውን አምነው ተቀብለዋል። አመነው መቀበል ብቻ ሳይሆን፣ በመንግስትና በድርጅቱ ውስጥ ጥልቅ ተሃድሶ በማካሄድ የአመለካከት ለውጥ በማምጣት በውክልና በተሰጣቸውን ስልጣን ህዝቡን በአግባቡ ለማገልገልና እርካታ ለመፍጠር ቃል ገበተው ተግባራዊ እንቅስቃሴ ጀምረዋል። ይህ እንቅስቃሴ ከቀበሌ እሰከ የፌደራል መንግስት ካቢኔ ያሉ አመራሮችን በማንሳት በአዲስ በመተካትና የህግ እርምጃዎች በመውሰድ ተገልጿል።
ይህ ብቻ አይደለም። በከተሞች ያለውን የከፋ የወጣቶች የስራ አጥነት ችግር ለማቃለል ቀደም ሲል በስራ ላይ የነበረውን የወጣቶች የልማት ተሳትፎና ተጠቃሚነት ፖሊሲ እንዲሻሻል ተደርጓል። ወጣቶችን ቀደም ሲል ከነበረው በበለጠ ሁኔታ በስራ ፈጠራ ፕሮግራም ስራ ላይ ለማሰማራት የሚያስችል ልዩ የተንቀሳቃሽ ፈንድ በፌደራል መንግስት ተመድቧል። ይህ በፌደራል መንግስት የተመደበ ገንዘብ ስራ ላይ የሚውለው በክልሎች ነው። ክልሎችም የየራሳቸውን ለወጣቶች በብድር የሚሰጥ የስራ ፈጠራ ፈንድ ከመመደብ በተጨማሪ፣ መሬትን ጨምሮ የመስሪያ ዎርክ ሾፕ ዳሶችንና የመሸጫ ቦታዎችን በማዘጋጀት ድጋፍ የማድረግ ሃላፊነት ተረክበዋል።
እነዚህ ተጨባጭ እውነታዎች መንግስት በተቃውሞ የቀረበውን የህዝብ ጥያቄ ማዳመጡንና ምላሽ ለመስጠት መወሰኑን ያረጋግጣሉ። ይሁን እንጂ በመንግስት አስፈጻሚዎች ዘንድ ያለው የአመለካከትና የብቃት ችግር እንዲሁም በህዝቡ ላይ ያሉት ችግሮች ከፍተኛና ስር የሰደዱ በመሆናቸው በጥቂት ወራት ውስጥ ብን በለው ይጠፋሉ ተብሎ አይጠበቅም። አብዛኞቹ ኢኮኖሚያዊ ችግሮች አሁን ስልጣን ላይ ባለው መንግስት የተፈጠሩ ሳይሆኑ ከባለፉት ስርአቶች እየተንከባለሉና እየተከማቹ የመጡ፣ በጉልህ ለማቃለል አጠቃላይ የሃገሪቱን ኢኮኖሚ ማሻሸል የሚጠይቁ ናቸው። በመሆኑም ጊዜ ይጠይቃል፤ ትዕግስትም ይፈልጋል።
በአጠቃላይ አሁንም የህዝብ ቅሬታ ሙሉ በሙሉ ምላሽ አለማግኘቱና አንዳንድ አዳዲስ ችግሮችም የሚፈጠሩበት ሁኔታ መኖሩ ባይካድም፣ መሰረተ ቢስ ምክንያቶችን በማንሳት አልፎ አልፎም ጸያፍ የዘረኝነት አመለካከትን የተላበሱ አውዳሚ ሁከቶችና የእርስ በርስ ግጭቶች ማጋጠማቸው እንደቀጠለ ነው። መንግስት እነዚህን ሁከቶች ህግን በማስከበር እርምጃ የመከላከል ሃላፊነት ቢኖርበትም፣ በመንግስት ህግን የማስከበር እርምጃ ብቻ በሚፈለገው ልክ ውጤታማ ሊሆን አይችልም። ሰላምን የማረጋገጥ እርምጃ በሃገር ሽማግሌዎችና በሃይማኖት አባቶችም መታገዝ አለበት። ቀደም ሲል እንደጠቀስኩት ኢትዮጵያውያን ጠንካራ ማህበራዊ ትስስር ያላቸው በመሆኑ የስነምግባር ደንቦች የህግን ያህል አልፎ አልፎም የበለጠ ጉልበት አላቸው። በመሆኑም ሰላምን በማረጋገጥና እርቅ በማውረድ ረገድ የሃገር ሽማግሌዎች ተሳትፎ አስፈላጊ ነው። እናም በየአካባቢው የሃገር ሽማግሌዎችንና የሃይማኖት አባቶችን የሚያሳትፉ የሰላምና እርቅ መድረኮች ሊዘጋጁ ይገባል።
ሰሞኑን በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት አምቦ ከተማ የሃገር ሽማግሌዎች ምክር ቤት መቋቋሙን ሰምተናል። የሃገር ሽማግሌዎቹ የአካባቢያቸው ሰላም የሚከበርበትና ልማት የሚፋጠንበት ሁኔታ ላይ የመስራት አደራ እንደተሰጣቸውም ሰምተናል። የሃገር ሽማግሌዎቹ ሃላፊነታቸውን ለመወጣት ቃለ መሃላ ፈጽመዋል። ይህ የአምቦ ከተማ ጅምር በሌሎቹም አካባቢዎች ሊቀጥል ይገባል። ከሃገር ሽማግሌዎቹ ጎን ለጎን በተለይ በኦሮሚያ ውስጥ አባገዳዎች ሰላምና መረጋጋትን በማስፈን በኩል የተቀናጀ ድጋፍ ቢያደርጉ መልካም ይሆናል። የሃይማኖት አባቶችም በተለይ ከሰላምና መረጋጋት ጋር የተያያዘው ነባራዊ ሁኔታ ላይ አተኩረው መንፈሳዊ አስተምህሮዎች ላይ የተመሰረተ የስነምግባር ማነጽ ስራ መስራት ይጠበቅባቸዋል። ይህ ካልሆነ ሃገራችንን በራሳችን ወጣቶች ቦርቡረን አዳክመን ለጠላት አጋልጠን ዘላቂ ሰላማችንን አደጋ ላይ ልንጥል እንችላለን። እናም የሃገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና አባገዳዎች ተቻችሎ በሰላም የመኖርን ነባር የህዝቡን የስነምግባር ደንብ መሰረት አድርገው የመንግስትን ሰላምን በህግ የማስጠበቅ ተግባር ሊያግዙ ይገባል።