Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ሰላማችን በእጃችን የሚሆነው

0 382

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ሰላማችን በእጃችን የሚሆነው

 

ስሜነህ

 

ከሁለት ዓመት በፊት የተከሰተውን ችግር ለመፍታት ለአሥር ወራት ያህል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጆ እንደነበር ይታወሳል፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በተነሳ በሁለት ወራት ልዩነት ውስጥ በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች በተቀሰቀሰ ግጭት የበርካታ ዜጎች ሕይወት አልፏል፡፡ በመቶ ሺሕ የሚቆጠሩ ከቀዬአቸው ተፈናቅለዋል፡፡ በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች የተከሰተው ግጭት ከፍተኛ ቀውስ ያስከተለበት ምክንያት፣ የሁለቱ ክልሎች አመራሮችና የፀጥታ አካላት እጅ ያለበት በመሆኑ እንደሆነ በተደጋጋሚ ጊዜ ተነግሯል፡፡ በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ያለው ግጭት ሳይበርድ፣ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በሚማሩ ተማሪዎች መካከል በተፈጠረ ብሔር ተኮር ግጭት የተማሪዎች ሕይወት አልፏል፡፡ ይህን ግጭት ተከትሎ በአንዳንድ ዩኒቨርሲቲዎች ተማሪዎች ሙሉ በሙሉ ለቀው ሲወጡ ተስተውሏል፡፡ በዚህ ምክንያት እስካሁን ሶስት በሚሆኑ ዩኒቨርስቲዎች የመማር ማስተማር ሂደቱ አሁንም ተቋርጦ እንደሚገኝ እየተነገረ ነው።   

 

መንግሥት መጠነ ሰፊ የሆነውን ቀውስ ለማስቆም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አቋቁሞት እንደነበረው ኮማንድ ፖስት ሁሉ፣ የፌዴራልና የክልሎች የጋራ የፀጥታ ምክር ቤት በማቋቋም ወደ ሥራ ከገባ ከአንድ ወር በላይ አስቆጥሯል፡፡ የፌዴራልና የክልሎች የጋራ የፀጥታ ምክር ቤት ተቋቁሞና የጋራ ዕቅድ አውጥቶ ወደ ሥራ በመግባቱ ምክንያት በአገሪቱ የተሻለ መረጋጋት ተፈጥሯል፡፡

 

በወቅቱ ከነበሩ ዋና ዋና ችግሮች መካከል የዜጎች በነፃነት የመንቀሳቀስ፣ የትም አካባቢ ሆኖ ሀብት አፍርቶ የመኖር መብቶች ሲገደቡ እንደቆዩ፣ በተለያዩ አካባቢዎች ሰበቦችን በመፈለግ ሕገወጥ ሠልፎችን ማካሄድ፣ ሕገወጥ መሣሪያዎች ማዘዋወር፣ እንዲሁም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ግጭቶች መቀስቀስ የተለመዱ ጉዳዮች ሆነው ቆይተዋል፡፡ በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ባለው ግጭት የዜጎች በነፃነት የመንቀሳቀስና ሀብት የማፍራት ሕገ መንግሥታዊ መብት ሲጣስ መቆየቱን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ከአወዳይ ወደ ጅግጅጋና ሌሎች አካባቢዎች አትክልትና ፍራፍሬ ይዘው የሚንቀሳቀሱ ተሽከርካሪዎችን መስታወት ከመስበር ባሻገር፣ በሾፌሮችና በባለሀብቶች ላይ የአካል ጉዳትና የንብረት ዘረፋ ሲካሄድ ተስተውሏል፡፡   

 

በእርግጥ በዚህች አገር ሰላማዊ ሠልፍ በማድረግ የፈለጉትን መቃወምና መደገፍ የሚቻልበት ስርአት ተዘርግቷል፤ ለዴሞክራሲ ሥርዓት መጎልበት አስተዋጽኦ ስላለው፡፡ ዋጋ ያስከፈሉን ሕገወጥ ሠልፎች ግን የሚመለከተውን ሕጋዊ አካል በማሳወቅ የተካሄዱ አይደሉም፡፡ የተለያዩ ምክንያቶች በመፍጠር የሚካሄዱ እንጂ፡፡ የሠልፎቹ አዘጋጆች ወይም ባለቤቶች በቅጡ አይታወቁም፡፡ ማን እንደሚያደራጃቸው አይታወቅም፡፡ ሠልፎቹ ከተካሄዱ በኋላ ደግሞ የሕዝብን ሀብትና ንብረት የሚያወድሙ መሆናቸው ታይቷል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ሠልፎቹ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሸባሪ ተብለው የተፈረጁ ድርጅቶችን ዓርማ ይዘው የሚደረጉ መሆናቸውንም ተመልክተናል ፡፡

 

በዩኒቨርሲቲዎች ተቀስቅሶ በነበረው ብሔር ተኮር ግጭት የመማር ማስተማሩ ከመስተጓጎሉ በላይ፣ በርካታ ተማሪዎች ግጭቱን በመፍራት ትምህርታቸውን እያቋረጡ ወደ ቤተሰቦቻቸው  ሄደው የነበረ መሆኑም ይታወሳል። ይህ ዘግናኝና ሁል ጊዜም ሊያሳፍር የሚገባ፣ መቼውንም ቢሆን መሆን የሌለበት ተግባር ነው። በዩኒቨርሲቲዎች አጋጥሞ በነበረው ግጭት አንዳንድ የዩኒቨርሲቲ አመራሮች ተሳታፊ እንደነበሩ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ የጋራ ምክር ቤቱ እንዳወጣው መረጃም ከሆነ በዲሲፕሊንና በአካዳሚክ ውጤታቸው የተባረሩ ተማሪዎች ዩኒቨርሲቲውን ሳይለቁ ውስጥ ሆነው ይፈጠሩ የነበሩ ግጭቶችን ሲያባብሱ ነበር ብለዋል፡፡ ‹‹ለማጥራት በተሠራው ሥራም በኦሮሚያ ብቻ 980 ተማሪዎች ተገኝተዋል፡፡ በዚህ መልክ ተባረው መውጣት የነበረባቸው ግን ቁጭ ብለው ሁከቱንና ብጥብጡን ሲያባብሱ የነበሩ ናቸው፡፡ ትግራይ ውስጥ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ብቻ 41 ተማሪዎች በዚህ ሁኔታ ውስጥ ተገኝተዋል፡፡

 

አሁን የፌዴራልና የክልሎች የጋራ የፀጥታ አካላት፣ እንዲሁም የአገር ሽማግሌዎችና አባ ገዳዎች ባደረጉት ጥረት መረጋጋት እንዲፈጠርና የማስተማር ሥራው እንዲጀመር ተደርጓል፡፡ በግጭቱ ሳቢያ ከቀዬአቸው የተፈናቀሉ ዜጎችን መልሶ የማቋቋም ስራው ቢጀመርም ቀላል ግን አልሆነም። የመንግስትን ብቻ ሳይሆን የሁሉንም ርብርብ የሚጠይቅ ነው። በኦሮሚያ እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴ የሚያበረታታ ቢሆንም በደረሰው ጥፋት ልክ ግን አይደለም። ይልቁንም ወጥ ያልሆነው የድጋፍ አሰባሰብ፤ አንዳንድ አካባቢዎችም ላይ ማስገደደን ጭምር ታሳቢ ያደረገው እና ከደረሰኝ ውጭ እየተደረገ ያለው የድጋፍ አሰባሰብ ሰዎችን ስልቹ እንዳያደርግና፤ ለኪራይ ሰብሳቢ ሃይሎች ተጋላጭ እንዳይሆን መጠንቀቅ ያስፈልጋል።  በጸጥታው በኩል ያለውም በተመሳሳይ ነው። ገና ያልተፈታ ብዙ ችግር አለና የሁሉንም ጥረት ይፈልጋል።

 

የአገር መከላከያ ሚኒስትርና የብሔራዊ ደኅንነት ምክር ቤት ጸሐፊ አቶ ሲራጅ ፈጌሳ ዓርብ ታኅሳስ 27 ቀን 2010 ዓ.ም በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የመሰብሰቢያ አዳራሽ፣ የፌዴራልና የክልል የፀጥታ ምክር ቤቶች የተካሄደው የጋራ ስብሰባ ከተጠናቀቀ በኋላ በሰጡት መግለጫ ያረጋገጡትም ይህንኑ ነው፡፡ ከአንድ ወር በፊት በአገሪቱ ያለውን የፀጥታ ችግር ለመፍታት በፌዴራልና በክልሎች የጋራ ምክር ቤት ዕቅድ ወጥቶና መግባባት ተፈጥሮ ወደ ሥራ በመግባት በርካታ ለውጦች ቢመዘገቡም፣ ሕገወጦችን በቁጥጥር ሥር ከማዋል አኳያ የሚቀሩ ሥራዎች መኖራቸው በዚሁ መግለጫ ተመልክቷል፡፡

 

በኦሮሚያ፣ በአማራና በትግራይ ክልሎች ውስጥ በሚገኙ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ ተከስተው የነበሩ የፀጥታ ችግሮችን በፌዴራልና በክልሎች የፀጥታ አካላት፣ እንዲሁም በአገር ሽማግሌዎችና በሃይማኖት አባቶች አማካይነት የማስተማር ሒደቱ እንዲቀጥል መደረጉን በመግለጫቸው ላይ ያወሱት አቶ ሲራጅ፤ ይሁንና ሦስት ዩኒቨርሲቲዎች አሁንም ድረስ የማስተማር ሥራ እንዳልጀመሩ ተናግረዋል፡፡ የማስተማር ሥራቸውን ያልጀመሩት ዩኒቨርሲቲዎች እነማን እንደሆኑ ግን ይፋ አላደረጉም፡፡

 

በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች በተፈጠረው ግጭት የሁለቱ ክልሎች አመራሮችና የፀጥታ አካላት እጅ እንዳለበት የጠቆሙት ሚኒስትሩ፣ በተሠራው ከፍተኛ ሥራ በአንፃራዊነት የተሻለ ሰላም ለመፍጠር መቻሉን አመልክተዋል።  

 

ሰላማችን የሚገኘው አሁንም በእጃችን ላይ ነው። ግን አሁንም  የመላውን ሕዝብ ድጋፍ ይሻል፡፡ የአገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ አዛውንት፣ ምሁራን፣ ወጣቶች፣ ሴቶችና የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ገዥው ፓርቲ የያዘው አዲስ መንገድ በተግባር ጎልብቶ ውጤት ያፈራ ዘንድ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ሊያበረክቱ ይገባል፡፡ ሰላማችን በእጃችን የሚቆየው በማኅበራዊ ሚዲያዎች አማካይነት ሃሳባቸውን የሚያካፍሉ ዜጎች ከጨለምተኛ አስተሳሰቦች በመላቀቅ ጠቃሚ ምክሮችንና ልምዶችን እስካጋሩ ድረስ ብቻ ነው፤ ሰላማችን በእጃችን የሚቆየው በተለያዩ ጎራዎች በመሠለፍ የቡድን ጥቅምን ታሳቢ ያደረጉ ጭቅጭቆችና ውዝግቦች እስከተወገዱ ድረስ ብቻ ነው። እንዲህ ያሉት ውዝግቦች ጭቅጭቆችና ምክሮች ለአገርም ሆነ ለሕዝብ ፋይዳ የላቸውም፡፡ ሰላማችን በእጃችን የሚቆየው ወደፊት የሚያራምዱ የለውጥ ሃሳቦች ማፍለቅ እስከተቻለ ድረስ ብቻ ነው፡፡

 

በተቃውሞ ጎራ ያሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች አባላትና አመራሮችም ገዥው ፓርቲ ለተያያዘው አዲስ መንገድ የሚጠቅሙ ነገሮች ላይ በማተኮር ድጋፍ እስካደረጉ ድረስ ብቻ ነው ሰላማችን በእጃችን የሚሆነው። ወቅቱ አገርን ከውድቀት የመታደጊያ እንጂ፣ የቆዩ ቁስሎችን እያነካኩ ማመርቀዝ አይደለም፤ ይህ ደግሞ ለማንም አይጠቅምም፡፡ ተቃዋሚዎቹ  በተለይ ከተበላሸው የፖለቲካ ግንኙነት ጋር የተያያዙ ችግሮችን በማስወገድ፣ እና እራሳቸውንም በማደስ ለአዲሱ ጅማሬ የሚጠቅሙ ግንኙነቶችን ስለሰላማችን ለመፍጠር ራሳቸውን ሊያዘጋጁልን ይገባል፡፡ ሌሎችን ከመውቀስ ባልተናነሰ ራሳቸውንም ስለሰላማችን ሊፈትሹ ይገባል፡፡  

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy