Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ሰላም መሰረት ነው

0 660

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ሰላም መሰረት ነው

ኢብሳ ነመራ

ሰላም በውስጡ ሲኖርበት ጣዕሙ ይዘነጋል። የሰላም ጣዕምና ዋጋ የሚታወቀው ሲታጣ ነው። በአሁኑ ጊዜ በዓለማችን የሶሪያን ህዝብ ያህል የሰላምን ዋጋና ጣዕም የሚያውቅ የለም።  ሶሪያውያን በሰላም ሰርተው ይገቡበት የነበረበት፣ ሰርተው ባገኙት ምንዳ ቤተሰባቸውን ያስተዳድሩ የነበረበትን፣ ሃብት ያፈሩበት፣ ቤተሰብ መስርተው ልጆች ወልደው ያሳደጉበት፣ ድረው ወግ ያዩበት . . . የሰላም ዘመን ትዝታው ብቻ ነው የተረፋቸው። አሁን በእጃቸው የለም። ሳያስቡት ከእጃቸው ያመለጠውን ጊዜ በቁጭት ያስታውሳሉ። ልጆቻቸው ይፈነድቁ፣ ይቦርቁ የነበረበትን፣ ትምህርት ቤት ውለው ይመለሱ የነበሩበትን ጊዜ ያስታውሳሉ። አሁን ምንም የላቸውም። ይህ እንዲሆን በማድረግ ረገድ ቀዳሚዎቹ ተጠያቂዎች ራሳቸው ሶሪያውያን ናቸው።

እርግጥ ነው ሶሪያውያን መንግስታቸው ላይ ተቃውሞ ሊኖራቸው ይችላል፣ የስርአት ለውጥም ይፈልጉ የነበሩ ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ ይህን ሊቆጣጣሩት በሚችሉት ሰላማዊ ሂደት ማድረግ ሲችሉ፣  ለሶሪያውያን ሳይሆን ለራሳቸው ርዕዮተዓለማዊ የበላይነት ለሚራወጡ ምዕራባውያን ቀዳዳ ከፈቱ። በዚህ ቀዳዳ የገቡት የዴሞክራሲ ጠበቃ ነን ብለው የሲቪክ ማህበራት ካባ የለበሱ ወገኖች በሁከትና በግርግር የስርአት ለውጥ እንዲመጣ ሶሪያውያንን መጠቀሚያ አደረጓቸው። በከተሞች የሚኖሩ የተወሰኑ ሶሪያውያን በዚህ ሁኔታ ግጭት ውስጥ ገቡ። ይህ የከተማ ግጭት አድሮ ውሎ ሶሪያን እዚህ አድርሷታል። አሁን ምንም የላቸውም። ሶሪያ ሶሪያውያን የመብት ጥያቄ የሚያነሱባት ምድር ሳትሆን የተለያዩ አካላት የየቤታቸውን የቆየ ቂም የዘው የሚፋለሙባት የውጊያ መድረክ ነች።

ሰላም እንዲህ ድንገት ከእጅ ሊያመልጥ ይችላል። ስለዚህ ከማንም በላይ የሰላም ባለቤትና ተጠቃሚ የሆነው ህዝብ ለሰላሙ ቃፊር ሊቆም ይገባል። ህዝብ ያልጠበቀውን ሰላም መንግስት ሊጠብቀው አይችልም። የውጭ ሃይሎች የሌላን ሃገር ሰላም ያስጠብቃሉ ብሎ ማሰብም የዋህነት ነው። በሰላም እጦት በቀጥታ የማይጎዱ በውጭ ሃገራት የሚኖሩ ለህዝብ ተቆርቋሪ የሚመስሉ ወገኖችም ሰላምን ሊያስጠብቁ አይችሉም። ከሁከቱ የፖለቲካ ትርፍ ካገኙ ይፈልጉታል። ይህን ትርፍ ለማግኘት በሚፈጥሩት የሰላም እጦት ተጎጂዎች ስለማይሆኑ የሰላም መደፍረስ ብዙም አያስጨንቃቸውም። ብዙሆቹ የሌላ ሃገር ዜግነት ያላቸው፣ የትውልድ ሃገራቸው በትርፍነት የሚጫወቱበት ነው። የትውልድ ሃገራቸውን ቢበሉ ስለማይከስሩ ውጤቱ ሃገርን የሚያጠፋ ቢሆንም ከመቆመር አይመለሱም።

ኢትዮጵያውያንም በእጃቸው ያለውን ሰላም እንቅልፍ አጥተው ሊጠብቁ ይገባል። ኢትዮጵያ በተቀናቃኞች የተከበበች ሃገር ነች። እነዚህ ተቀናቃኞች ግን ኢትዮጵያ ላይ እጃቸውን ሰንዝረው የማጥቃት ምንም አቅም የላቸውም። ኢትዮጵያን ሊያጠቀቁ የሚችሉት ኢትዮጵያውያን ብቻ ናቸው። የኢትዮጵያ ተቀናቃኞች በኢትዮጵያውያን ላይ ተንጠልጥለው ብቻ ነው ሊያጠቁ የሚችሉት። በቀጥታ ኢትዮጵያ ላይ እጃቸውን መሰንዘር የሚጀምሩት በሃገሪቱ ሰላም ጠፍቶ ኢትዮጵያውያን ክንዳቸው ከዛለ በኋላ ብቻ ነው። ያኔ የማንም መፈንጫ ተሆናለች፤ የውጊያ መለማመጃ፣ የመሳሪያ መሞከሪያ። አሁን ሶሪያ እንደሆነችው ማለት ነው። እናም ኢትዮጵያውያን ድንገት ከእጃችሁ ሊያመልጥ የሚችለውን ሰላም ጠብቁ። የኢትዮጵያ ህዝብ ያልጠበቀውን ሰላም መንግስት ሊጠብቀው አይችልም።

ባለፉ ሁለት ዓመታት በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች የሰላም እጦት ስጋቶች አጋጥመዋል። ለሰላም እጦት ስጋት ምንጭ የሆነው ሁከትና ግርግር በቀዳሚነት የመንግስት አፈጻጸም ችግር ነው። ይህን መንግስትም በተደጋጋሚ ህዝብን ይቅርታ እስከመጠየቅ በዘለቀ ሁኔታ ተቀብሎታል። ይህ የመንግስት የአፈጻጸም ችግር – የመልካም አስተዳደርና የፍትህ እጦት፣ የመንግስትና የህዝብ ሃብት ዘረፋ፣ የስራ አጥነት ችግር ክምችት የፈጠረው ምሬት ድንገት በህዝባዊ ተቃውሞ መልክ ፈነዳ። በዚህ ሁኔታ ህዝቡ ለተቃውሞ መውጣቱ የሚጠበቅ ነው።  መንግስት ሃላፊነቱን በአግባቡ ካልተወጣ ይህ መሆኑ አይቀሬ ነው።

ይሁን እንጂ፣ ይህ ተቃውሞ መንግስት ችግሮቹን ለማስተካከል ቃል ከገባ፣ እርምጃዎች መወሰድና ተስፋ መታየት ከጀመረ በኋላም ወደሰገባው አልተመለሰም። መንግስት ችግሮቹን ለማስተካከል የገባውን ቃል መፈጸም እንዳይችል በሚያሰናክል አኳኋን ሃገርን የሚያወድምና ለመፍረስ የመያጋልጥ ሆኖ ቀጠለ። ይህ የኢትዮጵያ ህዝብ ፍላጎት አልነበረም። ሁኔታው የህዝብ ተገቢ ቅሬታ የፈጠረውን ተቃውሞ በመጠቀም በቀጥታ ሊያጠቋት ያልቻሉትን ሃገር በኢትዮጵያውያን እጅ ለማጥቃትና ለማፍረስ የሰረጉ  የሃገሪቱ ጠላቶች ተግባር ነበር። በኤርትራ መንግስት የፕሮፓጋንዳ አቅጣጫ እየተሰጣቸው የሚንቀሳቀሱ ሚዲያዎችን፣ በተለይ ማህበራዊ ሚዲያዎችን መመልከት ለዚህ በቂ አስረጂ ነው።

በዚህ ላይ በክልሎች መሃከል የወሰን ጥያቄዎችን መነሻ ያደረገ ሁከትና ግጭት ታክሎበት የሃገሪቱ ሰላም እጅግ አስፈሪ ስጋት ላይ ወደቀ። በቅድሚያ በትግራይና በአማራ ክልሎች በኋላም በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሱማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች የነበረን የወሰን ጉዳይ ሰበብ ያደረገ ግጭት ተቀሰቀሰ። በተለይ በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሱማሌ ክልሎች መሃከል የተፈጠረው ግጭት በሃገሪቱ ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በመቶ ሺህ ለሚቆጠሩ ዜጎች መፈናቀል እንዲሁም ቁጥራቸው በውል ላልታወቀ ዜጎች ህይወት መጥፋት ምክንያት ሆኗል።

በዚህ አኳኋን የተቀሰቀሰው ሁከትና ግጭት እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ቀጥሎ ቆይቷል። በዚህ ሁኔታ ብዙዎች የሃገሪቱ ሰላም ከእጅ ሊያመልጥ ይሆን? የሚል ስጋት አድሮባቸዋል። የሃገሪቱ ጠላቶች ደግሞ ደካማና የፈረሰች ሃገር የሚያዩበት ጊዜ እየተቃረበ መሆኑን በማሰብ በጉጉት ውስጥ ቆይተዋል። ያም ሆነ ይህ በተለይ ባለፈው አንድ ወር ገደማ ጊዜ ውስጥ ሰላምና መረጋጋት የሰፈነ ይመስላል። ሰሞኑን በወልዲያ ከተማ ካጋጠመው ሁከት ውጭ በተቀሩት የሰላም ስጋት በነበረባቸው የሃገሪቱ አካባቢዎች ከሞላ ጎደል ሰላም ሰፍኗል። አስፈሪ የሰላም ችግር የነበረባቸው የኦሮሚያና የኢትዮጵያ ሱማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎችም እጅግ የተሻለ ሊባል የሚችል የሰላም ሁኔታ ውስጥ ናቸው።

ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የተሻለ ሰላም እንዲሰፍን በማድረግ ረገድ ህዝቡ ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክቷል። በትግራይና በአማራ ክልሎች መሃከል የነበረውን የወሰን ችግር ተወያይቶ እልባት ያበጀው ችግር በነበረበት  አካባቢ የሚኖረው የሁለቱ ክለሎች ህዝብ ነው። የሁለቱ ክልሎች መንግስታት ለህዝቡ መድረክ ከማዘጋጀትና የህዝቡን ውሳኔ ህጋዊ ስርአት ከማስያዝ ያለፈ ድርሻ አልነበራቸውም። በዚህም በተለይ ከሰሜን ጎንደር አካባቢ እየተቀሰቀሰ በማህበራዊ ሚዲያ አራጋቢነት ወደሌሎቹም ዞኖች ሲዛመት የቆየ የሰላም እጦትና ስጋት ለመቃለል በቅቷል።

በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሱማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ተቀስቅሶ የነበረውም ግጭት አሁን ጋብ ብሏል። መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በግጭቱ ሳቢያ ተራርቀው የነበሩት አዋሳኝ አካባቢ የሚኖሩ ህዝቦች የቀድሞ ግንኙነታቸውን እያደሱ ነው። በኦሮሚያ ምስራቅ ሃረርጌ ዞን የምትገኘው የጫት ንግድ ማዕከል የሆነችው አወዳይ ከተማ ሰሞኑን ወደወትሮው የሞቀ የንግድ እንቅስቃሴዋ ተመልሳለች። በግጭቱ ሳቢያ ቀዳሚ ተጎጂ የሆነው የአወዳይ ከተማና የአካባቢው ህዝብ አሁን መጠንቀቅ እንዳለበት ተረድቷል። ሰላሙን ሲያጣ ጣዕሙንም በደንብ አወቀ። እናም አሁን በግጭቱ ሳቢያ ከመፈናቀልና ከሞት ከተረፉት በመሃከላቸው ይኖሩ ከነበሩ የኢትዮጵያ ሱማሌ ተወላጆች ጋር እንደወትሮው እየሰሩ ይገኛሉ። ይህ በአካባበቢው ተፈጥሮ የነበረው ስጋት እየተገፈፈ መሆኑን ያመለክታል።

ሰላም በማስከበር እንቅስቃሴ ውስጥ ቀዳሚውና የማይተካ ሚና ያለው ህዝብ ቢሆንም የመንግስት የሰላም አስከባሪ ሃይል ድጋፍ ማስፈለጉ አይካድም። በዚህ ረገድ በሃገሪቱ ዘላቂና አስተማማኝ ሰላም ለማስፈን የተቋቋመው ብሄራዊ የደህንነት ምክር ቤት ከክልሎች ጋር በመተባበር ያከናወነው  ተግባር ለተገኘው የሰላም ውጤት ትልቅ ድርሻ ነበረው።

ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሱማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች የተቀሰቀሰው ግጭት በመቶ ሺህ ለሚቀጠጠሩ ዜጎች መፈናቀል ምክንያት ሆኗል። በግጭቱ ሳቢያ በክልላቸው ውስጥ ይኖሩበት ከነበረው መንደር ተፈናቀለው በጊዜያዊ መጠለያ የሰፈሩም አሉ። ዘላቂ አስተማማኝ ሰላም እንዲሰፍን እነዚህ ዜጎች መረዳትና በዘላቂነት ወደመደበኛ ህይወታቸው እንዲመለሱ ማድረግ ያስፈልጋል። ይህን በተመለከት ሁለቱ ክልሎችና የፌደራል መንግስት ተጨባጭ ተግባር እያከናወኑ ነው።

የፌደራል መንግስት በግጭቱ ሳቢያ ለተፈናቀሉ ዜጎች የአስቸኳይ ጊዜ ደራሽ እርዳታ ለማቅረብ ከመደበው 800 ሚሊየን ብር በተጨማሪ፣ ተፈናቃዮቹን ለማቋቋም 900 ሚሊየን ብር መመደቡን መረጃዎች ያመለክታሉ። የፌደራል መንግስት እስካሁን ይህን ያከናወነ ቢሆንም፣ ምን እንዳከናወነና ምን ለመስራት እንዳቀደ ለህዝብ በተገቢ መንገድ የማሳወቅ ክፈተት ታይቷል። ይህ የኮሚኒኬሽን ችግር ህዝብ የፌደራል መንግስቱን በቀና አይን እንዳያይ ያደረገ መሆኑን የሚመለከተው አካል ሊገነዘብ ይገባል።

በሌላ በኩል በተለይ የኦሮሚያ ክለላዊ መንግስት ከህዝብ ጋር በመተባባር ተፈናቃዮቹን ለመርዳትና በዘላቂነት ለማቋቋም ከፍተኛ እንቅስቃሴ እያደረገ ይገኛል። በኦሮሚያ ከሃገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ምሁራን ወዘተ የተወጣጣ ህዝባዊ የእርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴ ተዋቅሮ ለወደፊትም በሃገር አቀፍ ደረጃ ተሞክሮ ሊሆን የሚችል የወገን ለወገን ደራሽነት ስራ እያከናወነ ነው። እስካሁን በዚህ ኮሚቴ አማካኝነት ተፈናቃዮቹን በቋሚነት ለማቋቋም የሚውል ከ6 መቶ ሚሊየን ብር በላይ ገንዘብ ተሰባስቧል። ወደነበሩበት የኢትዮጵያ ሱማሌ ክልል መመለስ የሚፈልጉትን ተፈናቃዮች ለመሸኘት ከሚደረገው እንቅስቃሴ በተጨማሪ፣ በክልሉ መኖር የሚፈልጉትን ለማቋቋም ከህዝብ ጋር በመተባበር በተለያዩ ከተሞች የመኖሪያ ቤቶች እየተገነቡ ነው።

በዚህ ረገድ በኢትዮጵያ ሱማሌ ክልል አካባቢ ተመሳሳይ እንቅስቃሴ መኖሩ ቢሰማም እንውስቃሴው ምን እንደሚመስል የተሟላ መረጃ እየተሰራጨ አይደለም። ባለፈው ወር ክልሉን ጎብኝቶ የነበረው በርካታ የሃገሪቱን የግል ሚዲያዎች ያቀፈ የጋዜጠኞች ቡድንም በዚህ ረገድ ያለውን እንቅስቀሴ የተመለከተ መረጃ አላቀረበም። ያም ሆነ ይህ ክልሉ የሚችለውን እያደረገ እንደሆነ ይታወቃል።

በሁለቱ ክልሎች መሃከል ዘላቂ ሰላም ለማስፈን በቅድሚያ የተፈናቃዮቹ ጉዳይ እልባት ማግኘት አለበት። በሁለቱ ክልሎች መሃከል ህዝባዊ የሰላም ኮንፈረንስ ማካሄድ የሚቻለው የተፈናቃዮቹ ሁኔታ እልባት ካገኘና የህግ የበላይነት ከተረጋገጠ በኋላ ብቻ መሆኑ መታወቅ አለበት። በህዝባዊ የሰላም ኮንፈረንስ በሁለቱ ህዝቦች መሃከል ለክፍለ ዘመናት የነበረው መልካም ግንኙነትና ጥብቅ ወዳጅነት ከታደሰ በኋላ የወሰን ማካለሉ ስራ በህዝቡ በራሱ ይከናወናል። የዘላቂ ሰላም መንገድ ይህ ነው።

በአጠቃላይ አሁን በሃገሪቱ የተገኘውን ሰላም የሰላሙ ባለቤት፣ በሰላም መስፈኑ ቀዳሚ ተጠቃሚ፣ ሰላም በመታጣቱም ብቸኛ ተጎጂ የሚሆነው ህዝብ ከእጁ እንዳይሾልክ በአስተዋይነት ሊጠብቅ ይገባል። ሰላም የልማት፣ የተረጋጋና የተሻለ ህይወት፣ የደስታ፣ የተስፋ መሰረት ነው። ሰላም የሃገር ዘላቂ ህልውና ጉዳይ ነው። እናም ይህን የሁሉ መሰረት የሆነ ሰላም ነቅተን እንጠብቅ።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy