Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

“ሲሮጡ የታጠቁት…” እንዳይሆን

0 388

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

“ሲሮጡ የታጠቁት…” እንዳይሆን

                                                      ቶሎሳ ኡርጌሳ

የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ከመሰንበቻው የሰጠውን መግለጫ ተንተርሰው አንዳንድ ፅንፈኛ ሃይሎች መግለጫውን ገና ከመስማታቸው የተለመደውንና ህብረተሰቡን ያደናግርልኛል የሚሉትን “ኢትዮጵያ ፈርሳለች” ዲስኩር ሲያስደምጡን ሰንብተዋል። ይህ በእውነቱ እጅግ አስገራሚና አስቂኝ ጉዳይ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። እነዚህ ሃይሎች ወትሮም ቢሆን “ወደቀ” የሚል ጉዳይ ሲሰሙ ተሰበረ የሚሉ ናቸው።

ርግጥ የ“ኢትዮጵያ ተበታተነች” ሟርት ዛሬ የተጀመረ አይደለም። እነዚህ ፅንፈኞች ከዛሬ 26 ዓመት በፊት ተመሳሳይ ነጠላ ዜማን በአንድ ዓይነት ቅላፄ ሲያቀነቅኑ የነበሩ ናቸው። ልዩነቱ ከዛሬ 26 ዓመት በፊትና ዛሬ መባሉ ነው። ግና ኢህአዴግ ኢትዮጵያን ከብተና ያዳነ ድርጅት እንጂ ሀገርን ወደ ብተና የሚመራ ሃይል አይደለም።

እንኳንስ ዛሬ ይህ ያኔም ቢሆን ድርጅቱ ችግሮችን ከህዝቡ ጋር በመሆን እንደ አመጣጣቸው የመፍታት ጥንካሬ ይዞ ያደገ ነው። የኢህአዴግ መስመር በደርግ ውድቀት ማግስት ‘ኢትዮጵያ ልትበታተን ነው’ በማለት ሲያሟርቱ የነበሩ ተንታኝ ተብዬዎች ጥንቆላ መና እንዲቀር ያደረገ የሰላም ጎዳና ነው። መስመሩ ሀገራችን ሰላም እንድትሆን ያደረገ ብቻ ሳይሆን፤ ከብተናም እንድንድን ያደረገን መሆኑን ማንም መዘንጋት የለበትም። ያም ሆኖ ግን መግለጫው ፅንፈኞች እንደሚሉት ዓይነት አይደለም።

ርግጥ መግለጫው በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ በአንዳንድ አካባቢዎች ግጭቶች ሊኖሩ ቢችሉም፤ ኢህአዴግና መንግስት ግን በመግለጫው ላይ ችግሩን ለመፍታት ቁርጠኛ አቋም መያዛቸውን የሚያስረዳ እንጂ ስለ ሀገር ብተና የሚያወራ ነገር የለውም። ምንም እንኳን እያንዳንዱ ጉዳይ በመግለጫ ውስጥ ሊዘረዘር የሚችል ባይሆንም፤ ፅንፈኞቹ ስለ መግለጫው አንዳች እውቀት ሳይኖራቸው ተሽቀዳድመው “ሲሮጡ የታጠቁት…” ዓይነት በመሆን ‘በቃ! ሁሉም ነገር አበቃለት!’ የሚል የማደናገሪያ ስልት መያዛቸው መልሶ ራሳቸውን ግምት ላይ የሚጥላቸው ይመስለኛል።

እንደ እውነቱ ከሆነ ፅንፈኞቹ የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ለ17 ቀናት ግምገማ ሲቀመጥ ምንም ዓይነት ፍንጭ ሊያገኙ ባለመቻላቸው ይይዙትና ይጨብጡት ነገር አጥተው እንደነበር ግልፅ ነው። በ“ይሆናል” መላ ምት ሲታመሱ እንደነበር ማንም አይዘነጋውም። ገሚሱ ፅንፈኛ ‘የአነ እገሌ ድርጅት አልተስማማም’ ሲል፤ ሌላው ደግሞ ‘እነ እገሌና እነ እገሌ ተጣሉ’ የሚል የመንደር አለሉባልታን በየማህበራዊ ሚዲያው ላይ ሲደሰኩሩ ነበር። መግለጫው እንደ ወጣም ‘በቃ አከተመለት’ የሚል ልቦለዳዊ ድርሰትን ደረሱ።

ከድርሰታቸው ውስጥ እጅግ ያሳቀኝ ጉዳይ ቢኖር ‘የሽግግር መንግስት መስርተናል’ የሚሉና የሀገራችንን ህዝብ የማይመጥኑ በውጭ የሚኖሩ አስቂኝ ፅንፈኞች ናቸው። በእነርሱ ቤት ውጭ ሆነው የሽግግር መንግስት ለመመስረት ተፈራርመው ያለ አንዳች ሃፍረት ጃኬታቸውን ‘ተጃክተው’ እና በከራቫታቸው ታንቀው በቦሌ በኩል ‘ጉሮ ወሸባየ’ እያልን እንድንቀበላቸው እየነገሩን ነው።

እንግዲህ በወረቀት ላይ ፊርማ አራት ኪሎ በተ መንግስት ሊገባ መሆኑ ነው። ለእነርሱ የህዝብ ሉዓላዊ የስልጣን ባለቤትነት፣ የሀገር ውስጥ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ትግል እንዲሁም ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ምናቸውም አይደሉም። የቀን ቅዠታቸው ስልጣንና ስልጣን ብቻ ነው። መቼም ‘ጆሮ አይሰማው የለ’ ከማለት ውጭ ከቶ ምን ማለት ይቻል ይሆን?—ምንም። የእነዚህን “ላም አለኝ በሰማይ…” ባዮች የህልም እንጀራ እዚህ ላይ ልግታውና ወደ ኢህአዴግ መግለጫ ላምራ።…

ቀደም ሲል እንዳልኩት ኢህአዴግ በአመራሩ ውስጥ በነበረው ችግር ምክንያት በሀገራችን ውስጥ በጊዜያዊነት የተከሰተውን ግጭት በቁርጠኝነት ለመፍታት ግልፅ አቋም ወስዷል። ይህ አቋም የወሰደውም አመራሩ በችግሮቹ ላይ ተማምኖ የጋራ አንድነት ፈጥሮ እንደ ቀድሞው አንድ ዓይነት ስምምነት ላይ በመድረሱ ነው። ተበታትኖና ተለያይቶ አሊያም ፅንፈኞች እንደሚሉት ‘እገሌ ከእገለሌ ጋር ተጣልቶ’ አይደለም።

ታዲያ ይህን እውነታ ከመግለጫው ላይ “የድርጅታችን ግምገማ በመላው የአገራችን ህዝቦች ከባድ ተጋድሎ የተመዘገቡ ስኬቶችን ለመጠበቅና ለማስፋት እንዲሁም ከምንም ነገር በላይ በአመራር ድክመት የተፈጠሩትን አደጋዎችና ስጋቶች ለመቅረፍ በሚያስችል ስምምነትና መግባባት ተጠናቋል” በማለት ያሰፈረውን አቋም መግለፅ የተነሳሁበትን ነጥብ ይበልጥ የሚያደረጅልኝ ይመስለኛል።

የድርጅቱ መግለጫው በተፈጠው የአመራር ስህተት የኢትዮጵያን ህዝብ ለመካስ ቁርጠኛ መሆኑንም አስታውቋል። ይህ ማለት በድርጅቱ ፈጣን አመራር የመስጠት ችግር ምክንያት ሀገራችን ውስጥ የተፈጠሩ ችግሮች ይስተካከላሉ፣ ከእንግዲህም የህዝብ ግጭት መነሻ የማይሆኑበት ደረጃ ለማድረስ በቁርጠኝነት እንሰራለን ማለት ይመስለኛል። ይህንን ሁኔታም የአራቱ ብሔራዊ ድርጅቶች ሊቃነ መናብርት በመገናኛ ብዙሃን ሲገልፁ አድምጠናል።

እንደ እውነቱ ከሆነ ኢህአዴግ አንድን ነገር “ፈፅማለሁ” ካለ እንደተፈፀመ መቁጠር የሚያስፈልግ ይመስለኛል። ምክንያቱም ከድርጅቱ ቀዳሚ ታሪክ እንደምንረዳው፤ ገዥው ፓርቲ አደርገዋለሁ ብሎ ያልፈፀመው ነገር አለመኖሩ ነው። ይህ ማንነቱም በህዝቡ ውስጥ እንደ ፅንፈኞቹና እንደ አንዳንድ ሁሌም ከል ደመና ብቻ የሚታያቸው የሀገር ውስጥ ተቃዋሚ ፖለቲከኞች ምራጭ ሳይሆን፣ ተመራጭ ያደረገው ነው ብዬ አስባለሁ።

በእኔ እምነት ኢህአዴግ የማያደርገውን ነገር አደርጋለሁ ብሎ ቃል አይገባም። ይህን ማንነቱን ከዛሬ 16 ዓመት በፊት አሳይቶናል። በወቅቱ ለመታደስ ቃል በገባው መሰረት መታደስ ብቻ ሳይሆን ከተሃድሶው በኋላ በተከተላቸው ትክክለኛ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ሀገራችንን የልማት ተምሳሌት ማድረግ ችሏል። የዓለም ሀገራት ዘንድ ተፈላጊ እንድትሆንም አድርጓታል።

ዛሬ የኢህአዴግን መስመር አፍሪካዊ ወንድሞቻችን እንደ “ሞዴል” እየተወሰደ ነው። ድርጅቱ ከትናንት ችግሮቹ እየተማረና ፈተናውንም በአጥጋቢ ውጤት እያለፈ የመጣ ህዝባዊ ኃይል በመሆኑ፤ ነገም ዛሬ የገባውን ህዝብን የመካስ ቃል እንደሚፈፅም በርግጠኝነት መናገር የሚቻል ይመስለኛል። ምክንያቱም ድርጅቱ የህዝብን የለውጥ ፍላጎት ሲመራ የመጣና ወደፊትም የሚመራ የህዝብ አገልጋይ በመሆኑ ነው።

በመሆኑም ራስን አሂሶ የህዝብን ችግር በቁርጠኝነት ለመፍታት ቃል በመግባትና በመግለጫውም ላይ “ከውስጠ ድርጅት ዴሞክራሲ አኳያ አሁን የተጀመረውን ግምገማ መሰረት በማድረግና የትራንስፎርሜሽን አጀንዳችንን በውጤት ለማስፈፀም እያንዳንዱ ብሔራዊ ድርጅት በከፍተኛ አመራር ደረጃ የሚታይበትን ድክመት በጥልቀት ገምግሞ በግልጽነትና በተጠያቂነት ላይ የተመሰረተ የማስተካከያና የእርምት ርምጃ እንዲወስድ ወስኗል” ብሎ ተገቢ መንገድን መከተል ለፅንፈኞቹ እንዴት “ኢትዮጵያ አበቃላት” የሚል የማደናገሪያ ሰበዝ ሊያስመዝዝ እንደቻለ የሚገባው ለእነርሱ ብቻ ይመስለኛል። ገና ለገና ምኑንም ሳያዩና ተሽቀዳድመው ተረት-ተረት ለማውራት መሞከራቸው እነዚህ ሃይሎች ምን ያህል እዚህ ሀገር ውስጥ ካለው የፖለቲካ ተጨባጭ ሁኔታ የራቁ መሆኑን አመላካች ነው። እናም ነገረ ስራቸው “ሲሮጡ የታጠቁት…” ሆኖ፤ ለላኪዎቻቸው የሚሯሯጡት ፅንፈኞች በሚያራምዱት ባዶ ሃሳብ ሊያፍሩ የሚገባቸው ይመስለኛል። ህሊና ላለው ሰው ከዚህ በላይ ውርደት አይኖርም።  

ያም ሆኖ እነርሱና አንዳንድ ፀረ ኢትዮጵያ ሃይሎች እንደሚመኙት የምትበታተን ሀገር የለችንም። ኢትዮጵያ ዛሬም ይሁን ነገ በህዝቦች የመስዕዋትነት ድል ያገኘችውን ሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ በማጠናከር ዓለም አቀፋዊ ተሰሚነቷን እየጨመረች ነገ ይበልጥ ከፍ ያለ ቦታ ላይ መገኘቷ አይቀሬ ነው። የዚህ አባባል መሰረቱ ኢህአዴግና ህዝቡ ያላቸው የማይላላ ግንኙነት ነው። እናም እውነታውን ፅንፈኞቹም ይሁኑ ላኪዎቻቸው ሁሌም ሊያውቁ የሚገባ ይመስለኛል።       

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy