Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ስለፌዴራል ሥርዓቱ ተመራጭነት ምኑ ተወርቶ!

0 361

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ስለፌዴራል ሥርዓቱ ተመራጭነት ምኑ ተወርቶ!

ወንድይራድ ኃብተየስ

 

ኢትዮጵያ ላስመዘገበችው ዘርፈ ብዙ ስኬቶች የፌዴራል ሥርዓቱ መሠረት ሆኗል።  አገሪቱ ለዘመናት ቀፍድዶ ይዟት የነበረውን ችግሯን መፍታት የቻለችው በዚህ  የፌዴራል ሥርዓት ነው። ጥቂቶች አልፎ…አልፎ እዚያና እዚህ የሚነሱ ትናንሽ ግጭቶችን፣  አለመግባባቶችን እንደ ማሣያ በማቅረብ ፌዴራል ሥርዓቱ ያመጣው ጦስ አድርገው ለማቅረብ ጥረት ሲያደርጉ ይስተዋላሉ።

 

ጽንፈኛው አካል የፌዴራል ሥርዓቱ ካስገኛቸው በርካታ ትላልቅ ጠቀሜታዎች ይልቅ በየአካባቢው የሚከሰቱ ትናንሽ ግጭቶችን በማነፍነፍ የሥርዓቱ ውጤት አድርገው ለማቅረብ ነገሮችን ሲያጎኑ ይታያሉ። ለዚህም ሲሉ ከወዲህ ወዲያ ሲሯሯጡ ይታያሉ። ይህ ሁኔታ ለማንም የሚበጅ አይደለም። ኢትዮጵያ የበርካታ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች፣ የብዙ ኃይማኖቶች፣ የተለያዩ አስተሳሰቦች፣ የድንቅ ባህሎች ወዘተ…ባለቤት አገር ናት።

 

እናም ኢትዮጵያ እነዚህን በርካታ ልዩነቶች ሊያስተናግድ የሚችል የአስተዳደር ሥርዓት መከተል የግድ ይላታል። ይህ ደግሞ ከነእጥረቱም ቢሆን  ዛሬ ላይ ተመራጭ ሆኖ ሊቀርብ የሚችለው የፌዴራል ሥርዓት ነው።   

    

በኢትዮጵያ የብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦችን ማንነት፣ እኩልነትና ነጻነት አሁን በተግባር ከሚታየው የፌዴራል ሥርዓት በተሻለ ሊያረጋግጥ የሚችል ሌላ አማራጭ ያለ አይመስልም።  ወደኋላ መለስ እንበል። በደርግ ሥርዓት ውድቀት ማግሥት የአብዛኛውን  ህዝቦች ፍላጎት ሊያሟላና የአገሪቱን  አንድነት  ሊያስቀጥል የሚችል ይህ የአስተዳደር ሥርዓት ብቻ ነበር።  

 

ለማስታወስ ያህል በዚያን ወቅት ከ17 በላይ የታጠቁ ኃይሎች በነበሩበት ሁኔታ  ሁሉንም ፍላጎቶች ማጣጣም የሚችል የአስተዳደር ሥርዓት  መተግበር ይግድ ይል ነበር። ከዚህ ውጪ የተሻለ አማራጭም አልነበረም። ያ ሥርዓት ደግሞ ይህ አገሪቱ የመረጠችው የፌዴራል  የአስተዳደር ሥርዓት ነበር። ይህ የፌዴራል ሥርዓት ምንም ችግር የለበትም ፍጹም ነው አይባልም። ከአሃዳዊ የአስተዳደር ሥርዓት ግን እጅጉን የተሻለና በአገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ ተጨባጭ ለውጦችን ማምጣት የቻለ፤ አገሪቱንም ወደ ላቀ ከፍታ ያሸጋገረ ነው ብሎ መሞገት ይቻላል።  

 

የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በዚህ የፌዴራል ሥርዓት በማንነታቸው እንዲኮሩ፣ ባህላቸውን እንዲያሳድጉ፣ ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ ወዘተ…  በማድረግ  ሁኔታዎችን አመቻችቷል።  የፌዴራል ሥርዓቱ  የአገሪቱን ሠላም  ዘላቂና አስተማማኝ አድርጓል። የአገሪቱ አንድነት በጠንካራ አለት ላይ እንዲመሠረት አስችሏል። አገሪቱን ከብተና አደጋ ታድጓል። የብልጽግናና የዕድገት ጎዳናን እንድትያያዝ ያደረገው ይህ የፌዴራል ሥርዓት መሆኑም መታወቅ አለበት።

 

በተለያየ ምክንያት ግጭቶች ሲከሰቱ፣ ድንገቴ ችግሮች ሲያጋጥሙ የፌዴራል ሥርዓቱን  እንደ ምክንያት አድርጎ መነሳሳት አሳማኝ አይደለም። ትናንት የአካባቢ ግጭቶች   በቀድሞዎቹ አሃዳዊ ሥርዓቶችም ነበሩ፤ ምናልባትም  ነገም ይኖራሉ። የግጭቶች መንስዔ በርካታ ጉዳዮች ሊሆኑ ይችላሉና።  

 

ኢትዮጵያ የመረጠችው ያልተማከለ አስተዳደር የህዝቦች ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶችን ከማረጋገጥ ባሻገር አገሪቱን በፈጣን የምጣኔ ሀብት ለውጥ ምህዋር ውስጥ አስገብቷታል። ባለፉት 27 ዓመታት አገሪቱ በዓለም አቀፍ መድረክ የነበራት ገጽታም ሆነ  ተሰሚነት እጅጉን ተለውጧል። ትናንት ትታወቅበት የነበረው ድርቅ፣ ረሃብና ጦርነት ዛሬ የለም። በአገሪቱ አስተማማኝና ዘላቂ ሠላም ሰፍኗል። ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀዳሚ የኢንቨስትመንት መዳረሻ እየሆነች መጥታለች። በአገሪቱ ከባድ ድርቅ ለተከታታይ ዓመታት ቢከሰትም ችግሩን በራስ አቅም መቋቋም ተችሏል። ዛሬ ላይ ኢትዮጵያ ውስጥ   በረሃብ ምክንያት የሚሞት ዜጋ  የለም። ሥራ የማማረጥ ጉዳይና የክፍያ ማነስ ካልሆነ በስተቀር ማንም መሥራት የሚችልና የሚፈልግ ዜጋ ጦሙን የማያድርባት አገር መፍጠር እየተቻለ ነው። ይህ እውነታ በአትኩሮት ለተመለከተው ትልቅ ጥንካሬ ነው። ይህ የፌዴራል ሥርዓቱ ስኬት ሆኖም ሊጠቀስ የሚችል ነው።

 

ኢትዮጵያ ዛሬ ላይ በአፍሪካ ሆነ በዓለም አቀፍ መድረክ ተሰሚነቷ እያደገ መጥቷል።  በአገሮች መካከል ግጭት ወይም ያለመግባባት ሲከሰት ኢትዮጵያ በአደራዳሪነት ወይም በሸምጋይነት ግንባር ቀደም ተመራጭ እየሆነች መጥታለች። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አገሪቱ በተባበሩት መንግሥታት ያላት ተሰሚነትም ጨምሯል። በአፍሪካ ህብረት ያላት የመሪነት ሚናም እንዲሁ ጎልብቷል። በኢጋድና በሌሎች ትላልቅ መድረኮች ያገኘችው ሥፍራም ከተግባሯ የመነጨ ነው።

 

ባለፈው ዓመት ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ አባል እንዲሁም የዓለም የጤና ድርጅት አመራር ለመሆን መብቃቷ አይዘነጋም። ይህም የሆነው በስኬታማ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲዋ ሣቢያ ነው። ይህ የፌዴራል ሥርዓቱ ስኬት ተደርጎ ሊወሰድ ይቻላል። እነዚህ ትላልቅ የፌዴራል ሥርዓቱ ስኬቶች ወደ ጎን ተጥለው በጥቃቅን ጉዳዮች ላይ ማጠንጠን ስለምን ይመረጣል፣ ስለምን ትናንሽ ነገሮችን ብቻ ለማጎን እሽቅድምድም ይያዛል?

 

ከጥቂት ዓመታት በፊት  የድርቅና ረሃብ ተምሣሌት ተደርጋ ትጠቀስ የነበረች ይህች አገር ዛሬ ላይ ባለ ብዙ ቢሊዬን ዶላር ወጪን የሚጠይቁ  ትላልቅ ሜጋ ፕሮጀክቶችን ሳይቀር በራስ አቅም የመገንባት አቅም መፍጠር ችላለች። ባለተስፋ አገር ለመሆንም በቅታለች።  አሁን ላይ በመላ አገሪቱ በርካታ ትላልቅ መሠረተ ልማቶች በመስፋፋት ላይ ናቸው።  መዲናችን ለዚህ ጥሩ ማሣያ ናት።  

 

የዓለም አቀፍ  ተቋማትና ዲፕሎማቶች መኖሪያ  የሆነችው አዲስ አበባ ፈርሳ እንደገና በመገንባት ላይ ያለች ከተማ ሆናለች። በየትኛውም  የአዲስ አበባ ክፍል የሚዘዋወር ጎብኚ አዳዲስ ህንጻዎችንና መንገዶችን መመልከት አዲስ ነገሩ አይሆንም። ማየት ለማይሹት ፈርሳ በአዲስ መልክ እየተገነባች ያለችውን የአዲስ አበባ ለውጥ ቁም ነገራቸው አይደለም። አዲስ አበባ እንደስሟ አዲስ  በመሆን ላይ ነች። ይህ ስኬት  የተመዘገበው  በፌዴራል ሥርዓታችን ምክንያት ነው።  

ኢትዮጵያ ዛሬ ከራሷ አልፋ ለቀጠናው አገራት ሊተርፍ የሚችል ትላልቅ ፕሮጀክቶችን በመገንባት ላይ ነች።  በታዳጊ  አገር  አቅም ለመገንባት አይታሰብም የሚባለውን ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ጥረት ከ63 በመቶ  በላይ ደርሷል። ይህ ፕሮጀክት ለኢትዮጵያ ከሚያስገኘው ምጣኔ ሀብታዊ ፋይዳ ባሻገር   የአካባቢው አገራት የምጣኔ ሀብት ትስስሩንም  የበለጠ ያሳድገዋል። ይህም የፌዴራል ሥርዓቱ ውጤት ሆኖ ይመዘገባል።  

ኢትዮጵያ አህጉሩን እየመራች ያለችው በምጣኔ ሀብት ብቻ አይደለም። በአካባቢው አገሮች የነበሩትን ግጭቶች እልባት እንዲያገኙ መፍትሄ በማፈላለግ ጭምር ነው።  ሽብርተኝነትንም  በመዋጋት ረገድ  ኢትዮጵያ ለዓለም አቀፉ  ማኅበረሰብ  ግንባር ቀደም ተዋናይ ነች።  የአልቃይዳ ክንፍ የሆነው ጽንፈኛ አልሸባብ በሶማሊያና በአካባቢው አገሮች እያደረሰ ያለውን ጥፋት ለመከላከል ኢትዮጵያ የአንበሣውን ድርሻ  በመወጣት ላይ ነች።  የመከላከያ ኃይላችን  የህዝቦችን  ደህንነት  ከመጠበቅ ባለፈ ለአፍሪካ ህዝቦች ደህንነት መረጋገጥ ድንበር ተሻግሮ በመሥራት ስኬታማነቱን አረጋግጧል። በዚህ ሠራዊት ኢትዮጵያዊያን ብቻ ሳይሆኑ አፍሪካዊያን ጭምር የሚኮሩበት ሠራዊት ነው።     

ኢትዮጵያ ለሁሉም ጎረቤት አገራት ዜጎች እንደሁለተኛ አገር በመቆጠር ከሰሐራ በታች ካሉ የአፍሪካ አገራት ከፍተኛ ቁጥር ያለውን ስደተኞች አስጠልላለች። ለስደተኞች ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጭምር ሙገሣ ተችሯታል። በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ከሶማሊያ፣ ከደቡብ ሱዳንና ከኤርትራ የተሰደዱ ከስምንት መቶ ሀምሳ  ሺህ በላይ ለሚሆኑ ስደተኞች መጠለያ ሆናለች። ከሁለት አሥርት ዓመታት በፊት የነበረውን የአገሪቱን ሁኔታ ስናስታውስ ኢትዮጵያ ለሌሎች አገሮች ዜጎች መጠለያ ልትሆን ይቅርና የራሷ ህዝቦችም በጦርነትና በረሃብ ሣቢያ ዜጎቿ የትውልድ ቀያቸውን  ጥለው የሚሰደዱባት አገር ነበረች።  

ይሁንና ባለፉት ጥቂት ዓመታት በተመዘገቡ ፖለቲካዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊና ማህበራዊ ለውጦች ምክንያት ለአገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን ለአካባቢው አገራት ህዝቦች ጭምር  መጠጊያ ለመሆን በቅታለች።  ከፍተኛ ቁጥር ያለው  ስደተኛ የሚፈጥረው  ጫና ከባድ ቢሆንም ኢትዮጵያ አቅም በፈቀደ ሁሉ ለስደተኞች ሁኔታዎች እንዲሟሉላቸው እያደረገች ትገኛለች። እነዚህ ሁሉ መልካም ነገሮች የመነጩት አገሪቱ የምትከተለው የፌዴራል ሥርዓት ውጤት መሆኑን መገንዘብ አያዳግትም። የፌዴራል ሥርዓቱ ስላስገኛቸው ጠቀሜታዎች ምኑ ተዘርዝሮ ያልቃል።  

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy