ቀቢፀ-ተስፈኛው ፕሬዚዳንት
ዘሩባቤል ማትያስ
ክፍል አንድ
አቶ ኢሳያስ አፈወርቂ ኣብርሃ። የሀገረ- ኤርትራ ብቸኛውና ፈላጭ ቆራጩ መሪ። ከሳሹ፣ ፖሊሱ፣ ዳኛው፣ አሳሪው፣ ፈቺው፣ መሐንዲሱ፣ ሐኪሙ፣ ጋዜጠኛው፣ ጠያቂው፣ ተጠያቂው፣ አስጠያቂው፣ የሁሉም መስሪያ ቤቶች ሚኒስትሩ…ሌላ ሌላም—‘ወዲ አፎም።’ በአንድ ወቅት “ከእኔ ወዲያ ኤርትራን የሚመራትን ሰው ፈጣሪም እንኳን አያውቀውም” ያሉን እኚህ ግለሰብ፤ ከመሰንበቻው አዲስ መለያ ለብሰው እና ላለፉት 26 ዓመታት በህቡዕ ሲያደርጉት የነበሩትን በገሃድ አምነው ፔትሮ ዶላር በፈጠረባቸው ቀቢፀ-ተስፋ ታብየው ብቅ ብለዋል።
ምንም እንኳን ሰውዬው የለበሱት አዲስ መለያ ከምን እንደተሰራና የትኛውን ዶላር ከፋይ ሀገር እንደሚወክል የሚያውቁት እርሳቸውና የላካቸው አካል ብቻ ቢሆኑም፤ እኔ ግን እላለሁ…የእኚህ ግለሰብ አዲሱ መለያ ከቁርበት የተሰራ ሆኖ አልባሾቹም የመካከለኛው ምስራቅ የፖለቲካ ቀውስ በጊዜያዊነት ያቧደናቸውና በቀጣናችን ላይ የራሳቸው ፍላጎት ያላቸው ወረፈኞች ናቸው። እናም አዲሱን ቁርበት “ተቆርብተው” እና እንደ ሩቅ አላሚና ተመራማሪ ጣራ…ጣራውን እያዩ፣ የተነገራቸውን እያስታወሱ…ሰሞኑን የኤርትራ ቴሌቪዥን የሰርክ ጋዜጠኞች ለሆኑትና ምናልባትም ራሳቸው በእጃቸው ፅፈው የሰጧቸውን ጥያቄ እንደ መፅሐፍ ቅዱስ ቃላት ሳይቀንሱና ሳይጨምሩ ለሚያንበለብሉት ለእነ ዑስማን ኢድሪስ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
በዚህ መግለጫቸው ሰውዬው የመካከለኛው ምስራቅ ፖለቲካ በፈጠረባቸው ቀቢፀ- ተስፋ ተሞልተውና ቀደም ሲል ሲያልሙት የነበረውን የቀጣናው አውራ የመሆን ቅዥት ተንተርሰው፤ የምስራቅ አፍሪካን ችግር ለመፍታት መደረግ ስላለበት ጉዳይ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ለተፈጠረው ችግር የሀገራችን ህገ መንግስት አንቀፅ 39 ምክንያት ስለመሆኑ፣ ‘ግብፆች በሳዋ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ውስጥ ጦራቸውን አስፍረዋል’ በማለት አልጀዚራ ቴሌቪዥን ስለዘገበው ሃቅ እንዲሁም ስለ ሌሎች ተያያዥ ጉዳዩች የቀጣናው አዋኪ የሆኑት ግለሰብ ማብራሪያ ሰጥተዋል። ነገሩ “ጅራፍ ራሱ ገርፎ፤ ራሱ ይጮሃል” እንዲሉት ዓይነት መሆኑ ነው።
ራሱን ገራፊ ሆኖ ራሱ የሚጮኸው የሆነው የአቶ ኢሳያስ የመግለጫ ጅራፍ፤ የኢትዮጵያን ችግር ለመፍታት ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር አብረው እንደሚሰሩ ነግረውናል። በሌላ ቋንቋ ‘የኢትዮጵያን መንግስት ከማንም ጋር ቢሆን ተቧድኜ አስወግደዋለሁ’ ማለታቸው ነው። የዚህ ፅሑፍ አንባቢ ይህን የ‘ወዲ አፎም’ን አቅምን ያላገናዘበና ‘አዛኝ መሳይ ቅቤ አንጓች’ ዲስኩር “ቀቢፀ-ተስፋ አንድ” ብሎ ሊመዘግብልኝ ይችላል።
ታዲያ አንባቢው ሲመዘግብልኝ ግን የሻዕቢያን ማንነት በእዝነ አዕምሮው ማስታወስ ያለበት ይመስለኛል። ሻዕቢያ በመንግስትነት ከመዋቀሩ በፊት በሳህል ድንጋያማ ተራራዎች ላይ መሽጎ በጥገኝነት፣ በጦረኝነትና በፀረ- ዴሞክራሲያዊነት ዳንኪራ ሲውረገረግ የነበረ ኃይል ነው። ያም ሆኖ መንግስት ከሆነ በኋላ እንደ ተውሳክ የተጣቡትን እነዚህን የጥገኝነት፣ የጦረኝነትና የፀረ ዴሞክራሲያዊነት ደዌ በመተው ከዳንኪራ ተወዛዋዥነቱ ሰክኖ ምራቁን ይውጣል ብለው ያሰቡ የቀጣናው ሀገራት በርካታ ነበሩ።
ግና እንደ አለመታደል ሆኖ አሊያም ያደቆነው የሳህል ተራራ ሰይጣን አልለቅም ብሎት ሻዕቢያ እግሩን ሰዶ እና ተንፈላሶ የነገር አንቴናውን በመያዝ በምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ውስጥ በጠብ አጫሪነት ይራወጥ ጀመር። የዳንኪራውን ዙር በማፍጠንም እንደ አጭር ርቀት ተወዳዳሪ የመንን፣ ሱዳንን፣ ኢትዮጵያንና ጂቡቲን ያተረማምሳቸው ያዘ። ለዚህ ፍጥነት ላልተለየው የትርምስ ሩጫው ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የሰጠው ምላሽ ግን ሁለት የማዕቀብ ሜዳሊያዎችን አንገቱ ላይ ማንጠልጠል ነው።
ታዲያ እኚህ ሰው ናቸው—ዛሬ የቀጣናውን ችግር ለመፍታት ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ችግር መፍታት እንደሚገባ ለጋዜጠኞቻቸው ሲነግሩ የነበሩት። ይህ የአቶ ኢሳያስ የተገላቢጦሽ አባባል “ጅብ የማያውቁት ሀገር ሄዶ ቁርበት አንጥፉልኝ አለ” የሚለውን ይትብሃል ያስታውሰኛል። ለነገሩ በመግቢያዬ አካባቢ እንደገለፅኩት፤ የሰውዬው አዲሱ መለያ ቁርበት በመሆኑ እርሱኑ መልሰን ልናነጥፍላቸው አንችልም። ‘ወዲ አፎም’ ማንና ምን እንደነበሩ ከቀጣናው ሀገራት በተለይም ከኢትዮጵያዊያን የተሰወረ አይደለምና።
እናም በእኔ እምነት የምስራቅ አፍሪካን ችግር ለመቅፍ በቅድሚያ መወገድ ያለበት የአሸባሪዎች አዝማች በመሆን እንደ ጋጣ በሬ ቀጣናውን በማተረማመስ ላይ የሚገኘውና በዚህ ጠብ አጫሪ ባህሪውም ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ማዕቀቦችን የጣለበት በአቶ ኢሳያስ አምባገነናዊ አመራር የሚተዳደረው የኤርትራ መንግስት ነው። ምስራቅ አፍሪካ ሰላም አግኝታ በትብብር ልማት እንድታድግና ህዝቦቿም ከሽብርና ከጦርነት አደጋ እንዲላቀቁ ‘የወዲ አፎም’ ጦር ሰባቂና ጥገኛ መንግስት ማክተም ይኖርበታል።
ሻዕቢያ ከተወገደ፤ በሱዳን በኩል የቤጃ እንቅስቃሴ በሚል የሚታወቁ የዚያች ሀገር አማፂያንን የማደራጀትና ለሌሎች በተላላኪነት የመስራት ተግባሩ ያበቃል። ሻዕቢያ ከተወገደ፤ የኢትዮጵያንና የህዝቦቿን ሰላም ለማወክ ያዘጋጃቸው እነ ግንቦት ሰባት፣ እነ ኦነግ፣ እነ ኦብነግና እነ አልሸባብ የሚረዳቸው አይኖርም። ሻዕቢያ ከተወገደ፤ ፍሩድ የሚሰኘውን የጂቡቲ አማፂ ቡድን እያስታጠቀ ሰላሟን የሚነሳት ሃይል አይኖርም። ሻዕቢያ ከተወገደ፤ ወንድም የሆነው የሶማሊያ ህዝብ ከአልሸባብ የሽብር ጥቃት ድኖ የሰላም አየርን ይተነፍሳል። ከቀጣናው ህዝቦች ጋር በልማት ተሳስሮ ወደፊት ይገሰግሳል። ሻዕቢያ ከተወገደ፤ አዲሷ ሀገር ደቡብ ሱዳን በኤርትራው መንግስት ‘የቀይ ባህር ኮርፖሬሽን’ አማካኝነት በአጅ አዙር ከመበዝበዝና ሰላሟንም ከማጣት ትድናለች። በአጠቃላይ ሻዕቢያ ከተወገደ፤ ቀጣናው ሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ የሰፈነበት ይሆናል። የሰሜኑ የሀገራችን ህዝብ እንደሚለው ‘ሀገር ጫታ’ ይሆናል።
እዚህ ላይ ስድስት ሚሊዩን የሚጠጋ ህዝብን የሚመሩት የኤርትራው ፕሬዚዳንት (ግማሽ የሚሆነው የርሳቸውን አገዛዝ በመፍራት እየተሰደደ መሆኑን ልብ ይሏል!) የኢትዮጵያን መንግስት ለመጣል በህልማቸው ስለማሰባቸው ምንም ማለት የሚያስፈልግ አይመስለኝም። ምክንያቱም የርሳቸው ሃሳብ የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ መለስ ዓለም እንዳሉት ‘የባህረ ሰላጤው ቀውስ የፈጠረው ቀቢፀ-ተስፋ’ ስለሆነ ነው። የሀገራችን አርሶ አደር “ድሃ በህልሙ ቅቤ ባይጠጣ ኖሮ፣ ንጣት ይገድለው ነበር” እንደሚለው፤ ርሳቸውም በህልማቸው የኢትዮጵያን መንግስት እየጣሉ ማደራቸው ከምኞት የዘለለ ትርጓሜ የሚሰጠው አይሆንም።
ዳሩ ግን ወደ እውኑ ዓለም ሲመለሱ ምናልባት ለአረቦች ያከራዩት የአሰብ ወደብ ያስገኘላቸው ዶላር አሊያም የአንዳንድ የኢትዮጵያ ጠላቶች “አይዞህ” ባይነት በድቡሽት ላይ እንደተገነባ ቤት መሰረት አልባ መሆኑን ማወቃቸው የሚቀር አይመስለኝም። “ለምን?” ቢሉ፤ ይህ የህልም ዓለም ወሬያቸው አንድም፣ በኢትዮጵያ መንግስትና ህዝብ ለውጭ ኃይሎች ያለውን የማይታጠፍ ምልከታ ስለሚያውቁት፣ ሁለትም ህዝባዊውን የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊትን ማንነት ከሻዕቢያና ሞራሉ ላሽቆ በየቀኑ በስደት ለኢትዮጵያ የፀጥታ ሃይሎች እጁን ከሚሰጠው ሰራዊቱ በላይ እማኝ የሚያውቀው ስለማይገኝ ነው። እናም ያኔ የህልም ቅቤያቸው ሳያወዛቸው ቀርቶ ንጣት በንጣት እንዳደረጋቸው ይገነዘቡታል ብዬ አስባለሁ።
ያም ሆነ ይህ አቶ ኢሳያስ አፈወርቂ ዛሬ ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያዊያን አሳቢ መስለው የማናነጥፍላቸውን አዲስ ቁርበት እንደ ኩታ ደርበው ቢመጡም፤ በትጥቅ ትግሉ ወቅት የትግራይ ህዝብ በረሃብ አደጋ ሲጠቃ ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) የህዝቡን ህይወት ለመታደግ ሻዕቢያ በተቆጣጠራቸው የሱዳን ድንበር በኩል እህል ለማስገባት ሲሞክር አካባቢውን በመዝጋት በሰው ልጅ ስቃይ ሲሳለቅ የነበረ ፀረ ህዝብ ኃይል ነው። ከነፃነት በኋላም ቢሆን ኤርትራ ውስጥ የነበሩ ዜጎቻችንን ንብረቶች እንዲሁም ፈፅሞ ኢ- ሰብዓዊነት በተሞላበት ሁኔታ የጥርስ ወርቆቻቸውን ሳይቀር በፒንሳ አስወልቀው የዘረፉና ያስዘረፉ፣ በጠብ አጫሪነት ባህሪያቸው ባድመንና አካባቢውን በመውረር በአስር ሺህዎች ለሚቆጠሩ የሁለቱ ሀገራት ዜጎች ሞትና አካል ጉዳት ምክንያት የሆኑ፣ ኢትዮጵያን ለመበታተን ከአሸባሪዎችና ከፀረ ሰላም ሃይሎች ጋር ሲሰሩ የነበሩ እንዲሁም ታሪካዊ ጠላቶቻችን ለሆኑ የውጭ ኃይሎች ተወርዋሪ ድንጋይ በመሆን “በኮሚሽን” እየሰሩ ያሉ የሀገራችንና የህዝቦቿ ደመኛ ጠላት ናቸው።
እናም ትናንትም ይሁን ዛሬ እኚህ ግለሰብ የኢትዮጵያዊያንና የህዝቦቿ ጠላት ሆነው ሲያበቁ፤ በምንም ዓይነት ፖለቲካዊ ቀመር ለእኛ ሊያሰቡልን አይችሉም። ሰውዬው የኢትዮጵያ ህዝቦች ዕድገት ለማወክ ሲሰሩና ሲያሰሩ የመጡ፣ ገፅታችንን ለማጉደፍ ወደ ሀገራችን አሸባሪዎችን ቦንብ አስታጥቀው አስርገው ለማስገባት የሚጥሩ፣ ‘ምናልባት ኢትዮጵያና ግብፅ በህዳሴው ግድብ ሳቢያ ጦርነት ውስጥ ሊገቡ ይችላሉ’ በሚል ቀሽም ስሌት የለመዱትን “የኮሚሽን ስራ” ለማከናወን ካይሮ እንደ ውሃ ቀጂ በግልፅና በስውር ሲመላለሱ የነበሩ ናቸው። እናስ እኚህ ግለሰብ እንደምን ዛሬ የእኛ አሳቢ ሆነው ‘የኢትዮጵያ ህዝብን እደግፋለሁ …ምንትስ’ ሊሉ ይችላሉ?—ርግጥ የዚህን ጥያቄ ምላሽ የሚያውቁት እርሳቸውና የሳህል በረሃው ሰይጣን ብቻ ይመስለኛል።
ሰውዬው ማንነታቸውን አብጠርጥሮ የሚያውቀውን የኢትዮጵያን ህዝብ ባልፈጠረባቸውና በሌለ ማንነታቸው ለመሸንገል ከመሞከር ይልቅ፤ እንደለመዱት አረቦቹን ‘ወላሂ…በእናንተው መጀን ይሁን!’ እያሉ ዶላራቸውን በመቃረም ጥገኛ ፍላጎታቸውን ቢወጡ የሚበጃቸው ይመስለኛል። ምክንያቱም ርሳቸው በጉያቸው አቅፈው ከያዟቸው አሸባሪዎችና ፀረ ሰላም ኃይሎች በስተቀር እዚህ ሀገር ውስጥ ኢትዮጵያን ለባዕዳን አሳልፎ የሚሰጥና አስመራ ቁጭ ብሎ እንደፈለገው በሚያወራ ግለሰብ የህልም ቅዥት እንደ ቦይ ውሃ የሚነዳ ዜጋ ስለሌለ ነው። እኛ ኢትዮጵያዊያን እንደ ርሳቸው ስራ ፈት አይደለንም። በላባችንና በአንጡራ ሐብታችን ደክመን በመስራት እየተለወጥን የምንገኝ ህዝቦች ነን። እንደ ርሳቸው በጥገኝነት አስተሳሰብ ተውጠን በሌሎች ዕድገት ላይ ዓይናችን ደም የሚለብስ አይደለንም። ለእንዲህ ዓይነቱ ዘበዘባ ዲስኩርም ጆሯችን መስሚያው ጥጥ ነው። በቃ! ኦሮማይ!…
በክፍል ሁለት ፅሑፌ ‘ወዲ አፎም’ በመግለጫቸው ላይ ስለ ጠቃቀሷቸው ሌሎች ጉዳዩች ምላሽ የሚሆኑ እውነታዎችን ይዤ እቀርባለሁ።…