Artcles

በሀገራችን መንግስታዊ ስርአት ተዘርግቷል

By Admin

January 23, 2018

በሀገራችን መንግስታዊ ስርአት ተዘርግቷል

 

ስሜነህ

 

መንግሥት ሰሞኑን በመጀመርያ ዙር 528 ሰዎች ክሳቸው ተቋርጦ ከእስር እንደሚለቀቁ ባስታወቀው መሰረት በመቶ አስራዎች የሚቆጠሩቱ በመጀመሪያው ዙር በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት በተደረገ ስነ ስርአት ከእስር ተፈተዋል፡፡ እዚህ ውሳኔ ላይ የተደረሰው ደግሞ የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ለ17 ቀናት ያደረገውን ግምገማ ካጠናቀቀ በኋላ ባወጣው ባለ ስምንት ነጥብ ውሳኔ መሠረት ነው፡፡ ከፖለቲካ ጋር በተገናኘ ክሳቸው እንዲቋረጥ የተደረጉ ሰዎች ከእስር መፈታታቸው መልካም ጅምር ነው፡፡ በዚህ መሠረት ሒደቱ ቀጥሎ በርካቶች ከእስር እንደሚለቀቁ ይጠበቃል፡፡ አገሪቱም እስርና ከመሳሰሉ ደስ የማይሉ ድርጊቶች ተላቃ ሁሉም ነገር በሕግ የበላይነት ሥር በብሔራዊ መግባባት እንደሚከናወን በመንግስት በኩል አቋም ተይዟል። ይህ አቋም የተያዘበትም ምክንያት በማወቅም ይሁን ባለማወቅ የተፈጸሙ ስህተቶች በይቅርታና በምሕረት እንዲታለፉና፣ በዚህም ኢትዮጵያውያን እጅ ለእጅ ተያይዘው በፍቅርና በመተሳሰብ አገራቸውን ከገባችበት ቀውስ እንዲታደጓት ሲባል ነው። ውሳኔው ከእስር መልቀቅን የውሳኔው መጀመሪያ ያድርግ እንጂ፤ የአገሪቱ የሕግ ማስከበር አገልግሎት ይዞታን ማሻሻል፤ በሕግ ጥላ ሥር ያሉ ሰዎች አካላዊም ሆነ ህሊናዊ ችግር ሳያጋጥማቸው በሕግ የሚዳኙበትን ሥርዓት ማጠናከርና፤ ከሕግ የበላይነት ጋር የተያያዙ ዋና ዋና ጉዳዮችንም የሚያካትት ነው፡፡ ውሳኔውን ጥሩ ጅምርና ቁርጠኝነት የታየበት ሲሉ አንዳንዶች የማወደሳቸውን ያህል አንዳንዶች ሃሳብ ለማስቀየርና የፖለቲካ ቁማር ለመቆመር ሲባል የህግ የበላይነት ላይ የተያዘ የልጅ ጨዋታ ነው ሲሉም ኮንነውታል። ስለሆነም የኩነናውን ተገቢነት ማሄስ የዚህ ተረክ ዓብይ ጉዳይ ነው።

 

የፌዴራል ዋና ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ አቶ ጌታቸው አምባዬ ሰኞ ጥር 7 ቀን 2010 ዓ.ም በጽሕፈት ቤታቸው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንደተናገሩት፣ አንዳንድ ወገኖች የሕግ ማስከበር ሥራ የሚቆምና ወደኋላ የሚመለስ አድርገው ያስባሉ፡፡ ተጠርጣሪዎችንና ፍርደኞችን ክስ በማቋረጥም ሆነ ምሕረት በማድረግ እንዲለቀቁ ይደረጋል ማለት ግን፣ የሕግን የበላይነት ማስከበር ይቆማል ማለት አይደለም የማለታቸውን ህጋዊ ተጠየቅ ከላይ ስለተመለከተው ኩነኔ መጀመሪያ ማጤን ተገቢ ይሆናል፡፡

 

ጉዳዩ በኩነኔ ብቻ አላበቃም፤ አንዳንዶች ፍርድ ቤቶች መደበኛ ሥራቸውን እየሠሩ በተከሳሾች ላይ ፍርድ ሲሰጡ “መንግሥት እስረኞችን እለቃለሁ እያለ ለምን ይህንን ያደርጋሉ?” በማለት የፍርድ ቤቱን ሥራ የሚቃወሙ አሉ፡፡ ዓቃቤ ሕግስ ለምን ክስ ይመሠርታል? ፖሊስስ ለምን ምርመራ ያደርጋል? የሚሉ የተለያዩ ወገኖች መኖራቸውንም የፌደራል ዋና አቃቤ ህግ አመልክቷል፡፡ ነገር ግን አንድ ተጠርጣሪ ተከሶ በፍርድ አደባባይ ከቀረበ በኋላ፣ ነፃነቱን ማረጋገጥና ማስከበር የሚችለው ሕጋዊ አካሄዶችን ተከትሎ፣ የተጠረጠረበትን የወንጀል ድርጊት በበቂ የመከላከያ ማስረጃ ማስተባበልና ነፃ መሆኑን ሲያረጋግጥ ብቻ  የመሆኑን የህግ ማእቀፍ ውሳኔው አልሻረም፡፡ ፍርድ ቤቶችን በማወክ፣ በመበጥበጥ፣ ተገቢ ያልሆነ ዛቻና ማስፈራሪያ ቃላትን በማውጣት ከሕግ አደባባይ ለማምለጥ የሚደረግ ነገር  ሁሉ ስህተት መሆኑንም ውሳኔው አልሰረዘም፤ አልደለዘም፡፡

 

በህገ መንግስቱ አግባብ መቼም ቢሆን የዚህ ዓይነት አካሄድና ተግባር ለድርድር አይቀርብም፡፡ አጥፊዎች ምን ጊዜም ቢሆን ከመጠየቅ አይድኑም፡፡ ሊታረሙና ሊስተካከሉ የሚገቡ መሆኑ የህግ የበላይነት የመጀመሪያው መስፈርትና መነሻ ነው፡፡ የፌደራል ዋና አቃቤ ህግ ሁከትና ብጥብጥን እንደ መፍትሔ አይቶ የሚቀጥል ኃይል ካለ፣ ሕግን ለማስከበር የፍትሕ አካላት ያላሰለሰ ጥረት የሚያደርጉ መሆኑን ያስገነዘበውም ስለዚህ ተጠየቅ ነው፡፡

 

ዋና ዓቃቤ ሕጉ በቅርቡ የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ “የፖለቲካ ምኅዳሩን ለማስፋትና አገራዊ መግባባትን ለመፍጠር” በማለት የተከሳሾችን ክስ በማቋረጥና ፍርደኞችን በምሕረት ለመልቀቅ ውሳኔ ላይ መድረሱን መነሻ በማድረግ መንግሥት የፍትሕ ዘርፉንና ሌሎች የተቀመጡ አቅጣጫዎችን ለመፈጸም ግብረ ኃይል እንዲቋቋም አድርጓል። ግብረ ኃይሉም የአጭር፣ የመካከለኛና የረዥም ጊዜ ዕቅድ አፈጻጸም ተግባራትን ለይቶ ሥራውን ጀምሯል፡፡

 

ግብረ ኃይሉ በአጭር ጊዜ ዕቅዱ በሚቀጥሉት ሁለት ወራት የሕግ የበላይነትን ባከበረ መንገድ ክሳቸው በመታየት ላይ ያሉ ተጠርጣሪዎችን ክስ የማቋረጥ፣ በተመሠረተባቸው ክስ ጥፋተኝነታቸው ተረጋግጦባቸው የተፈረደባቸውን ፍርደኞች ምሕረት የመስጠት ሥራ የሚያከናውን እንደሆነ ተገልጿል፡፡ ክስ ለማቋረጥና ምሕረት ለማድረግ ተከሳሹ ወይም ተከሳሿ በአገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች በተደረጉ ሁከቶች፣ ብጥብጦችና ሌሎች ጉዳዮች ላይ የሰው ሕይወት ያላጠፋና ከባድ የአካል ጉዳት ያላደረሰ፣ ትልልቅ የኢኮኖሚ አውታሮችን በማውደም ተግባር ላይ ቀጥተኛ ተሳትፎ ያልነበረው፣ ሕገ መንግሥቱንና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል ለመቀልበስ በተደጋጋሚ አመፆችን ያልመራ መሆኑን ግብረ ኃይሉ በመሥፈርትነት ይዞ እየሠራ መሆኑንም ዋና አቃቤ ህግ በግልጽ ይፋ ባደረገበት አግባብ የህግ የበላይነት ላይ ቁማር እየተቆመረ እንደሆነ አስመስሎ ማራገብ ይልቁንም ምህዳሩ የጠበበው ከገዥው ፓርቲና በመንግስት ሳይሆን በተቃዋሚውም ሆነ ይብዛም ይነስ በህዝቡም ዘንድ እንደሆነ የሚያጠይቅ ነው፡፡

 

ሌሎች ክሳቸው የሚቋረጥላቸው ተከሳሾች ደግሞ፣ የሥርዓቱ ተጠቃሚ የሆኑ ነገር ግን መንግሥት መሥራት የሚገባውን ሥራ ባለመሥራቱ የተነሳ በሌሎች ኃይሎች ፍላጎትና ዓላማ ተነሳስተው በጥፋትና በውድመት ላይ የተሳተፉ በመንግሥት ጥፋት ወደ ስህተት የገቡ ስለሆኑ፣ ክሳቸው እንደሚቋረጥና የምሕረቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ እንደሚደረግ ዋና አቃቤ ህግ ማስታወሱ መንግስት ምህዳሩን ለማስፋት ከግማሽ መንገድ በላይ እየሄደ መሆኑን የሚያረጋግጥ እንጂ በህግ የበላይነት ላይ እየተደራደረ አለመሆኑን ነው፡፡

 

መንግሥት በመካከለኛ ጊዜ ሊተገብራቸው ያቀደው ሦስት የሕግ ድንጋጌዎችን ማሻሻል ቀዳሚው ተግባር መሆኑን ዋና አቃቤ ህግ ይፋ አድርገዋል፡፡ ይህም ከ50 ዓመታት በላይ በማገልገል ላይ የሚገኙትን የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግንና የንግድ ሕግን ማሻሻልን የተመለከተው አንዱ ነው፡፡ ሌላው በረቂቅ ደረጃ ላይ ያለው ሕግ ደግሞ፣ የኃይል አጠቃቀም አዋጅ ነው፡፡ የፌዴራል ፖሊስ ማቋቋሚያ አዋጅ ሕግ ለማስከበር ተመጣጣኝ የኃይል ዕርምጃ መውሰድ እንደሚቻል የሚገልጽ ቢሆንም፣ “ተመጣጣኝ የሆነ ኃይል ማለት ምን ማለት ነው?” የሚለውን ለመወሰን የሕግ ማዕቀፍ አስፈላጊ በመሆኑ ረቂቁ ተዘጋጅቷል፡፡ ሌላው መንግሥት በመካከለኛ ጊዜ ዕቅዱ ማለትም እስከ በጀት ዓመቱ ማጠናቀቂያ ድረስ ሊተገብራቸው ያቀዳቸው ነገሮች፣ በዓቃቤ ሕግ ተቋምና በፍርድ ቤት ተቋም የሚሠሩ ተግባራትን የሚመለከቱ ናቸው፡፡ የእስረኞች የቀጠሮ አያያዝ፣ የጉዳዮች አፈጻጸምና አጨራረስ ላይ የሚታዩ መሠረታዊ ችግሮችን፣ ኅብረተሰቡ በምሬትና በብሶት የሚያነሳቸው የቀጠሮዎች መጓተትና ሌሎችንም ችግሮች የመፍታት ሥራ እንደሚያከናውን ዋና ዓቃቤ ሕጉ ጠቁመዋል፡፡

 

ግለሰቦች ባላቸው የሙያ ተሳትፎ የፖለቲካ ፓርቲ አመራር ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ጋዜጠኞችም ባላቸው የሙያ ተሳትፎ ዓምደኛ ሊሆኑ እንደሚችሉ፣ ነገር ግን እስካሁን ድረስ የፖለቲካ አባልና አመራር በመሆኑ የታሰረ የሌለ እንደሆነም በዋና አቃቤ ህጉ በኩል ተገልጿል፡፡ የታሰረው የፖለቲካ ድርጅቱን ከለላ በማድረግ በፈጸመው ወንጀል ነው፡፡ ሐሳቡን በመግለጹ የታሰረ ጋዜጠኛ እንደሌለ፣ የታሰረውም ቢሆን በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 9(6) ሥር የተደነገገውን ተላልፎ ቀስቃሽና ግጭት ፈጣሪ የሆኑ ጽሑፎችን በመጻፉ በፈጸመው ወንጀል ነው፡፡  

 

የአገሪቱ ሕገ መንግሥት የሕይወት፣ የአካል ደኅንነትና የነፃነት መብትን በተመለከተ በአንቀጽ 14፣ 15 እና 16 ድንጋጌዎች አሉት፡፡ ማንኛውም ሰው ሰብዓዊ በመሆኑ የማይደፈርና የማይገሰስ በሕይወት የመኖር፣ የአካል ደኅንነትና የነፃነት መብት አለው ይላል፡፡ በሕይወት የመኖር መብት ያለው ሰው በሕግ በተደነገገ ከባድ የወንጀል ቅጣት ካልሆነ በስተቀር ሕይወቱን አያጣም፡፡ ማንኛውም ሰው በአካሉ ላይ ጉዳት እንዳይደርስበት የመጠበቅ መብት አለው፡፡ ይህንን የመሰለ ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌ ባለበት አገር ውስጥ  የህግ የበላይነት ለድርድር አይቀርብም ። ስለምህዳሩ መስፋት ሲባል የተወሰደውን ከላይ የተመለከተ እርምጃም በዚህ አግባብ መገንዘብና ባይሆን ደግሞ በኛም መንደር የጠበበ ካለ ማስፋት ተገቢ ይሆናል። የማስፋቱ ስራም የተወሰደውን እርምጃ ከማድነቅና እውቅና ከመስጠት መጀመር ይገባል።

 

በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 18 መሠረት ኢሰብዓዊ አያያዝ ክልክል ነው፡፡ ማንኛውም ሰው ጭካኔ ከተሞላበት፣ ኢሰብዓዊ ከሆነ ወይም ክብሩን ከሚያዋርድ አያያዝ ወይም ቅጣት የመጠበቅ መብት እንዳለበት ተደንግጓል፡፡ ስለሆነም ይህንንም ማስተካከል የሚያስችል እቅድ ከላይ በተመለከተው አግባብ ሲያዝ ነገሩን ማጣጣል የሚሆነው ምህዳርን የማጥበብ ሴራ ነው።  

 

የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ግምገማ ሲጠናቀቅ መግለጫ የሰጡት የአራቱ ብሔራዊ ድርጅቶች አመራሮች፣ በአገሪቱ ለደረሰው ቀውስ ተጠያቂ አመራሩ መሆኑን አስታውቀው ለሕግ የበላይነት አፅንኦት መስጠታቸው  ስለምህዳሩ መስፋት ያላቸውን ቁርጠኝነት የሚያመላክት ነው፡፡ ስለሆነም ተቃዋሚዎቹም ይሰረዝ፤ ይደለዝን ብቻ ሳይሆን በቤታቸው የጠበበውንም ማስፋት ይጠበቅባቸዋል።  

 

ባጠቃላይ፣ በሃገሪቱ በሚራገበው መልክ ሳይሆን ወይም ለግለሰብ ወይም ለቡድን የሚታዘዝ ቢሮክራሲ ሳይሆን፣ በሕግና ሥርዓት እየተመራ አገር የሚያገለግል መንግሥታዊ ስርአት ተዘርግቷል። ስርአቱም ለሕግ የበላይነት ልዕልና የሚኖር ነው፡፡ በሥልጣን መባለግን አይፈቀድም፤ ዜጎች ሕግ እንዲያከብሩና፣ በሕግ እንዲዳኙ ብቻ የሚፈቅድ ነው፡፡ ይህም ለሕገወጥነት ክፍተት ሳይሰጥ ሰላምና መረጋጋትን የሚያሰፍን ስርአት ነው ማለት ነው።