Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

በባዶ ሜዳ የመዳከር አባዜ

0 364

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

በባዶ ሜዳ የመዳከር አባዜ

                                                     ታዬ ከበደ

በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ ቦታዎች በተከሰተ ግጭት ሳቢያ የተፈናቀሉ ዜጎች በክልሎቹና በፌዴራል መንግስት አማካኝነት አበረታች ተግባሮች እየተከናወኑ ናቸው። በተለይ በፌዴራል መንግስት በኩል ለተፈናቃዩቹ በቂ ድጋፍ እየተሰጠ ነው።

የፌዴራል መንግሥት ቀደም ሲል 800 ሚሊዮን ብር ከመደበ በኋላ፤  ለዘላቂ ማቋቋሚያ የሚሆን ተጨማሪ 900 ሚሊዮን ብር መድቧል። ይሁንና ይህን መሰሉ የጋራ ስራዎች ባሉበት አገር ውስጥ፤ ጽንፈኛው ሃይል ሆን ብሎ የፌዴራል መንግሥትንና የክልል መንግሥታትን ለመነጣጠል በባዶ ሜዳ ላይ ሲዳክር ይስተዋላል። ይህ የጽንፈኛው ሃይል በባዶ ሜዳ ላይ የመዳከር አባዜ በተጨባጭ ካለው ነባራዊ እውነታ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት የሌለው ነው።

በባዶ ሜዳ ላይ ለመዳከር የሚከጅለው ፅንፈኛ ሃይሎች በፌዴራል መንግስትና በክልሎች መካከል ያለውን አንድነት እንኳን በቅጡ የሚገነዘብ አይደለም። የእነዚህ ሃይሎች ተራ አሉባልታን የማራገብ ተግባር ለየትኛውም ክልል የሚጠቅም አይደለም።

የፅንፈኛና የፀረ ሰላም ሃይሎች አሉባልታ የሰላም ወዳዱና ከሌሎች የሀገሪቱ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ጋር በአንድነት የማደግ ፍላጎት ያለው የኦሮሞም ይሁን የኢትዮጵያ ሶማሌ ህዝብ አጀንዳ አይደለም። የሁለቱ ህዝቦች ፍላጎት ከሌሎች የሀገሪቱ ህዝቦች ጋር በመተሳሰብና በመደጋገፍ በጋራ የመልማት፣ ከአጎራባች ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች ጋር በፍትሐዊ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ ግንኙነት እንዲሁም ባደረገው መራር ትግል ዕውን እንዲሆን ባስቻለው ህገ መንግስት ላይ የሰፈሩት መብቶቹ ሳይሸራረፉ እንዲተገበሩላቸው ነው።

በግጭት አራጋቢዎች አሉባልታ ጠቅለል ተደርጎ ሲታይ፤ ሴራው ሆን ተብሎ ሁለቱ ህዝቦች አገራዊና ክልላዊ ተጠቃሚነት ለማደናቀፍ እንዲሁም ክልሎቹ በትግላቸው ያገኟቸውንና እያጎለበቷቸው የሚገኙትን ሁለንተናዊ ህገ-መንግስታዊ መብቶች ለመሸርሸር ብሎም ህዝቡ ተረጋግቶ በልማት ስራው ላይ እንዳያተኩር ለማድረግ የታለመ ነው።

እንደሚታወቀው ሁሉ የኦሮሚያና የኢትዮጵያ ሶማሌ ህዝቦች ባለፉት ዓመታት በተጎናጸፏቸው የልማትና የዕድገት ዕድሎች በብቃት በመጠቀም ከፍተኛ ለውጥ ማስመዝገብ ችለዋል። በህዝቦች ይሁንታ የተመሰረተው ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት በህዝቦች ቀጥተኛ ተሳትፎ መገንባት ከጀመረበት ወዲህ በሁለተም እየታየ ያለው ለውጥ ከፍተኛ ነው።

ከለውጦቹ መካከል በመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን በተመዘገቡ ለውጦች አጠቃላይ የሀገራችን የኢኮኖሚ ዕድገት በሁለት አሃዝ እንዲያድግ አስችሏል። በዚህ ሂደት ውሰጥ የህዝቡ ቀጥተኛ ተሳታፊነትና ባለቤትነት ነበር። ያለ ህዝቡ ይሁንታና ፈቃድ የተከናወነ ነገር የለም። ምናልባት በአፈፃፀም ረገድ የሚታዩ ጉድለቶች ካሉ ህዝቡ ከመንግስት ጋር ሆኖ የሚያስተካክላቸው ናቸው።

ይሁን እንጂ የፖለቲካ ኪሳራ የደረሰባቸው ፅንፈኞች ሁሌም በክልሉ ላይ በማተኮርና በሽብርተኝነት ከተፈረጁ እንደ ኦነግ፣ ኦብነግና ግንቦት ሰባት ያሉ የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር በመቀናጀትና በጸረ ሰላም ሚዲያዎች የሀሰት ወሬ በመንዛት ፌዴራል መንግስት ለተፈናቃዩች ምንም እንዳላደረገ ይለፍፋሉ። ሃቁ ግን ክልሎችና ፌዴራል መንግስት ተቀናጅተው በግጭት ለተፈናቀሉ ወገኖ ድጋፍ ማድረጋቸው ነው።

እነዚህ ኮንትሮባንዲስቶችና ኪራይ ሰብሳቢዎች እንዲሁም ሽብርተኛዎቹ ኦነግና ግንቦት ሰባትና ኦብነግ ቀደም ባሉት ጊዜያት በፈጠሩት እኩይ ሴራ አንድም ስንዝር መራመድ ያቃታቸው ናቸው። በዘመናት የትስስር ድር የተጋመዱት የሁለቱ ክልል ህዝቦች የአእምሮ ዕድገትና የፈጠራ ክህሎት እንዳይዳብር፣ ተወዳዳሪነታቸው እንዲደናቀፍና ድህነትና ኋላቀርነት በክልሉ ስር ሰዶ እንዲቆይ ያላቸውን ክፉ ምኞት ለመተግበር ጥረት አድርገዋል። ሆኖም ጊዜያዊ ችግር ከመፍጠር በዘለለ ሌላ ተሳክቶላቸው አያውቅም።

እንደ እውነቱ ከሆነ የሁለቱ ክልል ህዝቦች በተፈጥሮ በተቸራቸው ቋንቋ የመጠቀም መብታቸው ለዘመናት ተነፍጎ ከኖረበት ሁኔታ ራሳቸውን በማላቀቅ ዛሬ ላይ ቋንቋቸው የሳይንስ፣ የጥናትና ምርምር እንዲሁም የእድገት ምንጭ በመሆን ከፍተኛ ለውጥ እያስመዘገበ ይገኛል። ከሌሎች የሀገራችን ህዝቦች ጋር በመሆንም ባካሄዱት መራርና እልህ አስጨራሽ ትግል ዘርፈ ብዙ ለውጦችን በማምጣት የየክልላቸውን ህዝቦች በየደረጃው ተጠቃሚ ማድረግ ችለዋል።

ይህ በክልሎቹ እየተመዘገበ ያለው ዕድገት የሚያሳበዳቸው እነዚህ ፅንፈኞች የልማቱን ግስጋሴ ባዩ ቁጥር እንዲሁም መንግስት በኪራይ ሰብሳቢዎች ላይ እየወሰደ ያለው ርምጃን ሲመለከቱ ጥቅሞቻችን ከመቃብር በታች ይውሉብናል በሚል ስጋት የሞት ሽረት ትግል ማድረጋቸው የማይቀር መሆኑን በገሃድ አሳይተዋል። ይህ ተግባራቸው አንድም ስንዝር ባያራምዳቸውም አሁን ደግሞ ፌዴራል መንግስትንና ክልሎችን ‘ምንም ድጋፍ አልተደረገም’ በሚል ለመለያየት ጥረት እያደረጉ ነው። እውነታው ግን ከላይ በመግቢያዬ አካባቢ የጠቀስኩት ነው።

ሐሰት ማውራት ስራችን ነው በሚል ስጋት አሉባልታን በማውራት ስራ ላይ የተጠመዱት እነዚህ ፅንፈኞች የህዝቡ ፍላጎት ያልሆነን አጀንዳ በመምዘዝ በሁለቱም ክልሎች ውስጥ ምንም ዓይነት ድጋፍ እንዳልተደረገ እየለፈፉ ነው። በዚህም በአንድ በኩል ሁለቱን ክልች ለማለያየት በሌላ በኩል ደግሞ ክልሎቹን ከፌዴራል መንግስቱ ጋር የተለያዩ እያስመሰሉ ያቀርባሉ።

ሆኖም በሁለቱ ክልሎች ውስጥ የሚገኘው ህዝብ እንደ ሌሎቹ የሀገራችን ህዝቦች አንድ የጋራ ፖለቲካል ኢኮኖሚ ስርዓትን ለመገንባት በህገ መንግስቱ ቃል የገባ ነው። ከፌዴራል መንግስት የሚያገኘውና እያገኘ ያለውን ድጋፍ በሚገባ ያውቃል። ማንም ነጋሪና አስታዋሽ አያስፈልገውም።

መንግስትም ተፈናቃይ ለሆኑት የየክልሎቹ ነዋሪዎች የሚያደርገውን ድጋፍ ወደፊትም አጠናክሮ ይቀጥላል። የሁለቱም ክልሎች ተፈናቃዩች እየመሰከሩ ያሉት መንግስት እያደረገላቸው ያለውን ድጋፍ እንጂ ፅንፈኞቹ የሚያወሩትን የመለያየት ፖለቲካ ባለመሆኑ የፅንፈኞቹ ተስፋ በባዶ ሜዳ ላይ ከመዳከር የዘለለ የሚሆን አይመስለኝም።

ለዚህ አባባሌ በቅርቡ የሁለቱንም ክልሎች ተፈናቃዩችን ጎብኝቶ የተመለሰው የፌዴራል መንግስት የሱፐርቪዥን ቡድን ለህዝብ ተወካዩች ምክር ቤት ያቀረበውን መረጃ ማቅረብ እችላለሁ። ኮሚቴው “…የኦሮሚያ ክልል ተፈናቃዮች ባሉባቸው መጠለያ ጣቢያዎች በተወሰኑት ብቻ ጊዜያዊ የጤና ተቋም ወይም ማዕከል በመክፈት ሙያተኛና መድኃኒት በማቅረብ የጤና አገልግሎት ለመስጠት ጥረት ተደርጓል፡፡ ሌሎች ደግሞ በአቅራቢያቸው በሚገኝ ጤና ተቋም እየሄዱ አገልግሎቱን እንዲያኙ ሲያደርጉ ተመላላሽ ሙያተኛ በመመደብም የሕክምና አገልግሎት ለመስጠት ጥረት ተደርጓል፡፡…በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ተፈናቃዩች በኩልም የግልና የአካባቢያቸው ንፅህና እንዲጠበቁ የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁሶች የቀረቡላቸው መሆኑንና መፀዳጃ ቤቶችም ምቹ መሆናቸውን ተፈናቃዮች ይገልጻሉ፡፡ በመጠለያ ጣቢያዎች አካባቢም የጤና ተቋም ወይም ማዕከል ተከፍቶ የባለሙያና የመድኃኒት አቅርቦትም መኖሩን ቡድኑ አረጋግጧል፡፡…” የሚል ነው። ይህ በሁለቱም ክልሎች ተፈናቃዩች አካባቢ እየተደረገ ያለው ተጨባጭ እውነታ የፅንፈኞቹን አሉባልታ ባዶ ሜዳ ላይየሚያስቀረው ነው።  

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy