Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

በቤተሰብ ደረጃም ይደገማል!

0 279

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

በቤተሰብ ደረጃም ይደገማል!

አባ መላኩ

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ መሰረት የግብርናው ዘርፍ ነው። በዚህ ዘርፍ የተመዘገበው ዕድገት ለአገሪቱን  ኢኮኖሚ መስፈንጠር የአንበሳውን ድርሻ አበርክቷል። የዚህ ዘርፍ መለወጥ ለአገራችን ኢኮኖሚ ዕድገት መሰረት ከመሆኑ ባሻገር ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ማለት በሚቻል ደረጃ ቀጥታ ተጠቃሚ እንዲሆን አድርጎታል። የበርካታ አርሶና አርብቶ አደሮች ህይወት እጅጉን ተለውጧል። አርሶና አርብቶ አደሩ ጥሪት መቋጠር በመቻሉ ዘመናዊ የአኗኗር ዘይቤ በመላመድ ላይ ነው። ይህ ሲባል ግን  አንድም ችግርተኛ የለም ማለት አይደለም። እንኳን እኛ አገር ይቅርና የነፍስ ወከፍ ገቢያቸው ጣሪያ ነክቷል የሚባሉት አገራትም ቢሆኑ ቀላል የማይባሉ ዜጎቻቸው የዕለት ጉርሳቸውን አጥተው በየጎዳናው ሲንከላወሱ መመልከት አዲስ ነገር አይደለም።

ይህን ጉዳይ በተመለከተ አንዳንድ ግለሰቦች በተለይ ጽንፈኛ ዳያስፖራዎች የመንግስትን ስኬታማነት ለማጣጣል ወይም መንግስትን ለማሳጣት ስኬታማ  ያልሆኑ ግለሰቦችን  በማሳያነት በማቅረብ  የህብረተሰቡ ህይወት የከፋ እንደሆነ አድርገው ለማቅረብ ሲሯሯጡ  ይታያሉ። እንደእኔ እንደእኔ ይህን አይነት አካሄድ ለማንም አይበጅም ምክንያቱም  አስተማሪ አይደለምና። መንግስት ባስመዘገባቸው ስኬቶች ይወደስ፤ በግድፈቱም ይወቀስና በቀጣይ ለተሻለ ነገ እንዲተጋ እናድርገው። ይህ ነው ለሁላችንም የሚበጀን።  

በአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ሁሉም የግብርና ምርቶች የአርሶና አርብቶ አደሩ ውጤቶች ናቸው። ይህ እውነታ ነው።  በዘንድሮው የመኸር ምርት በዋና ዋና ሰብሎች ብቻ  ከ345 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ሰብል መሰብሰብ እንደሚቻል ቅድመ ትንበያዎች ያመላክታሉ። አሁን ላይ ከ85 በመቶ የሚበልጠው ምርትም ተሰብስቧል። በበልግ የዝናብ ወቅት የሚገኝ ምርትና እና በመስኖ የሚለማ መሬት ምርት ሲታከልበት ደግሞ ይህ አሃዝ ከፍ እንደሚል በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል። በመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ማብቂያ ላይ በአገር ደረጃ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ተችሏል። እንደእኔ እንደኔ ይህ ትልቅ ስኬት ነው። በስንዴ ልመና ትታወቅ የነበረች አገር ዛሬ ላይ ይህን ያህል ለውጥ ማስመዝገብ መቻሏ ትልቅ ስኬት ነው። አገራችን  የምግብ ሰብል ፍላጎቷን  ማረጋገጥ በመቻሏ  በቅርቡ በአገራችን መጠነ ሰፊ ድርቅ ቢከሰትም ድርቁ በዜጎች ላይ የከፋ ጉዳት አላደረሰም።

አገራችን በታሪክ ከገጠሟት ከባድ ድርቆች መካከል አንዱ በ2008 ዓ ም ጀምሮ እስካሁን ድባቡ ያልተላቀቀን ድርቅ አንዱ ነው። ይህን የድርቅ በአብዛኛው መቋቋም የተቻለው  በመንግስት አቅም ነው። እዚህ ላይ የአጋር ድርጅቶችንና መንግስታትን ድጋፍ ለማሳነስ ፈልጌ ሳይሆን እውነታው መታወቅ ስላለበት ነው። የኢትዮጵያ መንግስት ዜጎችን ከማንኛውም ነገር መታደግ እንደሚችል ያረጋገጠበት ወቅት ቢኖር ይህ የድርቅ ወቅት አንዱ ነው። አንድም ዜጋ በድርቅ ሳቢያ በምግብ እጦት ህይወቱ አላለፈም። ከፍተኛ የዜጎች መፈናቀል አልተከሰተም። ይህ ትልቅ ድል ነው።  

በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ማጠናቀቂያ ላይ ደግሞ (በ2012 ዓ ም) መንግስት ሌላ ትልቅ ስኬት ለማስመዝገብ  በመሰራት ላይ ነው። በአገር ደረጃ  የምግብ ዋስትናችን ማረጋገጥ እንደተቻለ ሁሉ እያንዳንዱ ቤተሰብ የምግብ ፍላጎቱን ማረጋገጥ እንዲችል ለማድረግ በመሰራት ላይ ነው። ይህን ዕቅድ ማሳካት እንደሚቻል ካለው ነባራዊ ሁኔታ መገመት የሚከብድ አይሆንም። የግብርናው ዕድገት ከኢንዱስትሪው ማስተሳሰር  ለተጀመረው ዕድገት ቀጣይነት ዋንኛ መሰረት ነው። አሁን ባለው ሁኔታ የግብርና ውጤቶችን የሚጠቀሙ ኢንዱስትሪዎች  በፍጥነት ማስፋፋት ካልተቻለ የግብርናው ዕድገት በራሱ አደጋ ላይ ይወድቃል። ምክንያቱም አሁን ላይ የአርሶና አርብቶ አደሩ  ትኩረት ወደ ካሽ ክሮፕ ምርቶች በመሸጋገር ላይ ነው። ለዚህም ይመስለኛል መንግስት ግብርናውንና ኢንዱስትሪውን ለማመጋገብ የሚያስችሉ የተለያዩ ተግባራትን በማከናወን ላይ የሚገኘው።

የኢፌዴሪ መንግስት የኢንዱስትሪውን ዘርፍ ለማስፋፋት የሚያግዙ የተለያዩ  ፖሊሲዎች፣ ስትራቴጂዎች፣ ህጎችና ደንቦች አዘጋጅቶ እንዲሁም የተለያዩ አደረጃጀቶችና አሰራሮችን ፈጥሮ ለተግባራዊነታቸው ጥረት በማድረግ ላይ ነው። የመንግስት የትኩረት አቅጣጫ ከሆኑት የኢንደስትሪ ዘርፎች መካከል የግብርና ምርትን በስፋት በግብዓትነት በሚጠቀሙ፣ ሰፊ ሰው ኃይል ሊሸከሙ በሚችሉ፣ የሀገሪቱን የቴክኖሎጂ አቅም ግምት ውስጥ ያስገቡና ለቴክኖሎጂ ሽግግር ምቹ በሆኑ ኢንዱስትሪዎች ላይ ነው።

ለኢንዱስትሪው  ዘርፍ መስፋፋት የመሰረተ ልማት መሟላት ቀዳሚውና ዋናው ነገር ነው። መንግስት በዚህ ረገድ ከፍተኛ ርብርብ በማድረግ ላይ ነው። ባለፉት አስርት ዓመታት መንግስት ከበጀቱ ከፍተኛውን ድርሻ እየመደበ ያለው ለመሰረተ  ልማት ማስፋፋት  በመሆኑ በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች በርካታ ሰፋፊ አውራ ጎዳናዎችንና የገጠር መንገዶችን በመገንባት ላይ ነው፤ አገሪቱን ከወደብ ጋር የሚያገናኝ የባቡር ሃዲድ ዘርግቷል፤ እንዲሁም ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ጋር የሚያገናኙ  የባቡር ሃዲዶችን  በመገንባት ላይ ይገኛል፤ ዘመናዊ ኤርፖርቶች በማስፋፋት ላይ ነው፤ የባህር ትራንስፖርትን ለማቀላጠፍ የሚያስችሉ በርካታ  መርከቦችን  ገዝቷል፤ ለኢንዱስትሪ መስፋፋት የደም ስር ነው የሚባለውን የሃይል አቅርቦት ለማሳደግ እጅግ ውጤታማ ስራዎች በመከናወን ላይ ናቸው እንዲሁም የቴሌኮሙዩኒኬሽን አውታሩን በከፍተኛ ሁኔታ አሳድጎታል።

ከላይ ለማንሳት እንደሞከርኩት የመንገድ ግንባታ ከፍተኛ አቅም የሚጠይቅ ቢሆንም ዘርፉ ካለው ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ በ1983ዓ.ም በመላ ሀገሪቱ 18 ሺ 81 ኪሎ ሜትር የነበረውን የመንገድ  አውታር  በአሁኑ ወቅት ወደ ከ128 ሺ ኪ.ሜ በላይ ማድረስ ተችሏል። ለግብርናው ዘርፍ አንዱ ስኬት ተብሎ የሚጠቀሰው  የመንገድ ልማት በአርሶና አርብቶ አደሩ አካባቢዎች መስፋፋት በመቻላቸው አርሶና አርብቶ አደሩ የግብርና ግብዓቶችን በወቅቱና በተመጣጣኝ ዋጋ  እንዲያገኝ እንዲሁም  ምርቶቹን የተሻለ ገበያ ወደ ሚያገኝበት  አካባቢ ማቅረብ   እንዲችል አግዘውታል።

ኤሌክትሪክፊኬሽን ማስፋፋት ሌላው የመንግስት ስኬት የተመዘገበበት ዘርፍ ነው። በ1983 ዓ.ም በአገራችን የነበረው የሀይል አቅርቦት  ከ30 ሜጋ ዋት ብዙም ያልበለጠ ነበር። ይሁንና በዚያ ወቅት በአገራችን የኤሌክትሪክ  ሃይል እጥረት የህዝብ አጀንዳ አልነበረም። ምክንያቱም በዚያን ወቅት በአገራችን ኢንዱስትሪዎች ካለመኖራቸው ባሻገር የህብረተሰቡ የሃይል አጠቃቀምም  እጅግ ውሱን በመሆኑ ነው። በአሁኑ ላይ  ከ4 ሺህ ሶስት መቶ ሜጋ ዋት  በላይ ሃይል ማመንጨት ተችሏል። ይሁንና የኤሌክትሪክ አቅርቦት እጥረት የባለሃብቱም ሆነ የህዝቡ ትልቅ አጀንዳ ነው።  በቀጣዮቹ  ዓመታት የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ ጨምሮ የሌሎች ፕሮጀክቶች ግንባታ ሲጠናቀቅ የአገራችን የሃይል አቅርቦት  ከ11 ሺህ ሜጋ ዋት በላይ  ይደርሳል። ከዚያም ባሻገር በሁለተኛው የዕትዕ የተያዙ ፕሮጀክቶች ሲጠናቀቁ  ደግሞ የአገራችን የሃይልል አቅርቦትወደ 17 ሺህ ከፍ ይላል። በዚያ ወቅት የአገራችን የሃይል አቅርቦት እጥረት ምላሽ ያገኛል።

እንግዲህ መንግስት ለኢንዱስትሪ መስፋፋት አስፈላጊ የሆኑ መሰረተ ልማቶችን አሟልቶ ነው ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት የተሸጋገረው። አሁን ላይ 13 የኢንዱስትሪ ፓርኮችንና ወደ 17 የሚሆኑ  የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎችን ለመገንባት ጥረት በማድረግ ላይ ነው። እስካሁን ባለው ሁኔታ የአዲስ አበባ፣ የሃዋሳ፣ የኮምቦልቻ፣ የመቀሌ፣ ፓርኮች ግንባታቸው ተጠናቆ ለባለሃብቶች ክፍት የተደረጉ ሲሆን፤ የሃዋሳው ስራ ጀምሯል፤ የአዳማ፣ ድሬዳዋ ባህርዳር፣ ጅማ ደግሞ ግንባታቸው በመፋጠን ላይ ነው። ኢንዱስትሪ ፓርኮችን  አሁን ላይ እየለሙ ይሁን እንጂ ከዚህ ቀደም በርካታ የኢንዱስትሪ ዞናች ተቋቁመው  ስኬታማ መሆን ችለዋል።

አዳዲሶቹ የኢንደስትሪ ፓርኮች ከቀድሞዎቹ የኢንደስትሪ ዞኖች ተብለው ይጠሩ ከነበሩት በበርካታ ነገሮች የተለዩ ናቸው። ለአብነት አዳዲሶቹ የኢንደስትሪ ፓርኮች የተደራጁት በመንግስት መሆኑና ሁሉም መሰረተ ልማት የተሟሉላቸው መሆናቸው፣ ዓለም ዓቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ በመሆናቸው ከአካባቢ ብክነት  ነጻ መሆናቸው፤ ተመጋጋቢ እንዲሆኑ ታስበው በክላስተር የተደራጁ መሆናቸው ማለትም  ተመሳሳይ ምርት ሊያመርቱ የሚችሉ ፋብሪካዎች ለአብነት የጨርቃ ጨርቅ፣ ጋርመንትና ማቅለሚያ ኬሚካሎችን የሚያመርቱ በአንድ ክላስተር  እንዲሁም  ፋርማሲዩቲካልና ምግብ ነክ የሆኑ ውጤቶችን የሚያመርቱ በአንድ ላይ እንዲደራጁ ተደርጓል።  ከዚህም ባሻገር ባለሃብቱ የሚፈልጋቸው ማንኛውም አገልግሎቶች በአንድ ቦታ እንዲሟሉ በመደረጉ ባለሃብቱ ጊዜውን እንዲቆጥብና ከተጨማሪ ወጪ እንዲድን ያደርገዋል።

ሌላው መንግስት እያከናወነ ያለው ሰፊ ተግባር የሰው ሃብት ልማት ስራዎች ናቸው። ኢትዮጵያ ከአጠቃላይ የህዝብ ቁጥሯ (አሁን ላይ ያለው ትንበያ የሚያመላክተው 105 ሚሊዮን)  ወደ  70 በመቶ አካባቢው በወጣትነት የዕድሜ ክልል ውስጥ  የሚገኝባት አገር ናት።  ይህን ሃይል በአግባቡ መያዝ ከቻለች አገራችን የጀመረችው ባለሁለት አሃዝ የኢኮኖሚ ዕድገትን  ማስቀጠል የሚከብድ አይደለም። አሁን ላይ በመንግስት ብቻ የተገነቡ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ወደ ሃምሳ ደርሰዋል። እነዚህ ተቋማት የኢንዱስትሪ ልማቱን ለማፋጠን በከፊል የሰለጠነ ወይም በቀላል ስልጠና የተፈለገውን ስራ ማከናወን የሚችል የሰው ሃይል  በስፋት በማቅረብ ላይ ናቸው። ይህ የሰው ሃይል አቅርቦት አገራችንን ለውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ተመራጭ ያደርጋታል።

ከላይ ከተዘረዘሩት ነጥቦች በተጨማሪ አገራችን ሰፊ የገበያ አማራጭ ያላት አገር ናት። በአገራችን ሰፊ መሰረት ያለው መካከለኛ ገቢ ያለው የህብረተሰብ ክፍል  በመፈጠር ላይ በመሆኑ የዜጎች የአኗኗር ዘይቤ ለውጥ በማሳያት ላይ ነው። ይህም ማለት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገራችን እሴት የተጨመረባቸው የግብርና ምርቶችን የመጠቀም ልምድ  በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ መጥቷል። ይህ ደግሞ ለባለሃብቱ በርካታ አማራጮችን ይዞለት እንደሚመጣ ዕሙን  ነው። ከዚህም ባሻገር አገራችን በተለይ ለመካከለኛው ምስራቅ እንዲሁም ለምስራቁም ሆነ ለምዕራቡ ዓለም ቀረቤታ ባለው አካባቢ የምትገኝ በመሆኑ ለኢንቨስትመንት ተመራጭ ያደርጋታል። በ2007 ዓ ም  በአገር ደርጃ ያሳካነውን  በምግብ ሰብል ራስን የመቻል ዕቅድ፤ በተመሳሳይ በ2012 ዓ ም ማለትም በዕትዕ ሁለት ማብቂያ ላይ ደግሞ  በቤተሰብ ደረጃ ይደገማል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy