Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ተመራጭ ነው የሚያሰኙት እውነታዎች…

0 340

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ተመራጭ ነው የሚያሰኙት እውነታዎች…

አባ መላኩ

የኢትዮጵያ ፌዴራል ሥርዓት በዓለም እምቦቃቅላ ዕድሜ ካላቸው አዳጊ ሥርዓቶች ውስጥ የሚመደብ ነው። ይህ ሥርዓት በኢትዮጵያ ውስጥ ሲጀመር ከአስከፊ የድህነትና የዴሞክራሲ እጦት ደረጃ ላይ በመነሳት ነው። ይህ ብቻም አይደለም! ሥርዓቱ ሲጠነሰስ በፀጥታና መረጋጋት ችግር ውስጥ ይታመስ ከነበረው የምሥራቅ አፍሪካ ጂኦፖለቲካ ውስጥ ሆኖ ነበር። ይህም ሆኖ ሳለ ግን የኢትዮጵያ ፌዴራል ሥርዓት በርካታ ፖለቲካዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊና ማህበራዊ ስኬቶችን በማስመዝገብ ለሌሎች አገራት የሚተርፍ ልምዶችን ሊያበረክት ችሏል።

የኢትዮጵያ ፌዴራል ሥርዓት ሁሉም የዓለም ፌዴራል አገራት የሚከተሏቸውን የጋራ ባህሪያት ያሟላ ነው። የኢትዮጵያ ፌዴራል ሥርዓት ከራሱ ታሪካዊና ነባራዊ ሁኔታዎች የመነጩ ልዩ ባህሪያት አሉት። የኢትዮጵያ ፌዴራል ሥርዓት በሁሉም የዴሞክራሲያዊ ይዘት መስፈርቶች ሲመዘን የላቀ ዴሞክራሲያዊነት ያለውን ህገ መንግሥት በማፅደቅ እየተመራ የሚገኝ ነው፡፡

በኢትዮጵያ ፌዴራል ሥርዓት የተረጋገጡ መብቶችና የአፈፃፀም አቅጣጫዎችን በተመለከተ ከብዝሃነት አያያዝ አንጻር ሲገመገም በጥልቀት አልተመረመረም፤ በቂ ትምህርትም አልተወሰደበትም የሚሉ አስተያየቶች ይደመጣሉ።  

አንዳንዶች የፌዴራል ሥርዓቱ የብዝሃነት አያያዝ አፈፃፀሞች ግጭቶችን እያባባሱና አንድነትን አደጋ ላይ እየጣሉ፣ ለብሄር ቅራኔዎች መጧጧፍ ምክንያት እየሆኑ ናቸው የሚሉ ሃሳቦችን ያራምዳሉ። በአሁኑ ጊዜ የህብረ ብሄራዊነት ግንባታ ሂደትን የሚፈታተኑ ተግዳሮቶች ጎልተው እየታዩ ናቸውም ይላሉ፡፡ በሌላ ወገን በኢትዮጵያ ፌዴራል ሥርዓት የህብረ ብሄራዊነትን ምንነት በመገንዘብ የግንባታ ሂደቱን ማሳካትና ችግሮችን በመታገል የኢትዮጵያን የህዳሴ ጉዞ እውን ማድረግ ያስፈልጋል የሚሉም አሉ።

ህገ መንግሥት የአንድ አገር መሠረታዊ ህግ ነው በሚለው ትርጓሜ ብዙዎች ግን ይስማማሉ። አገላለፃቸው ይለያይ እንደሆን እንጂ ሁሉም ፀሃፊዎች ህገ መንግሥት የህጎች ሁሉ የበላይ ህግ መሆኑን ይስማማሉ፡፡ ህገ መንግሥት የአንድ አገር ህዝብ ስለፖለቲካዊ ሥርዓቱና አስተዳደሩ ያሳለፈውን ውሣኔና ስምምነት የሚወክል የህግ ማዕቀፍ ነው፡፡ የህዝቦች የስምምነት መንፈስና ለስምምነቱ የተሰጠውን ክብደት፣ የመንግሥትን የሥልጣን ህጋዊነት፣ የሥርዓቱን ባህሪያት የሚወስን ነው፡፡ በመሆኑም ሌሎች ህጎች የሚመነጩት፣ እውቅናና ተፈፃሚነት የሚያገኙት ከዚሁ ህገ መንግሥት ነው፡፡

ከህገ መንግሥት ጋር ተያይዞ የሚነሳው ሌላው ጉዳይ ህገ መንግሥታዊነት ነው፡፡ ብዙውን ጊዜ ህገ መንግሥታዊነት ከአስተሳሰብና እምነቶች፣ ከእሴቶችና መርሆች ጋር የተያያዘ ትርጉም ሲሰጠው ይታያል። በህገ መንግሥት የመገዛትን እምነት፣ ዜጎች ሊላበሷቸውና ወደቀጣይ ትውልዶች ሊያስተላልፏቸው የሚገቡ ህገ መንግሥታዊ መርሆዎችንና እሴቶችን ወዘተ…ወደ ባህል ደረጃ በማሳደግ የተረጋጋ ኅብረተሰብንና ዋስትና ያለው የፖለቲካ ሥርዓት ግንባታን ለማሳካት የሚያስችል መሣሪያም ስለመሆኑ ስምምነት አለ።

ከዚሁ ጋር ተያይዞ የሚነሳው ሌላው ቁም ነገር ደግሞ ህገ መንግሥታዊ ሥርዓት ህገ መንግሥትና ህገ መንግሥታዊነት በተግባር የሚተረጎሙበት መሆኑ ነው፡፡ በአንድ በኩል በህገ መንግሥት የተደነገጉትን ዓላማዎች፣ እሴቶች፣ መርሆዎች፣ መብቶች፣ ግዴታዎች እና ሌሎችም ድንጋጌዎች በተግባር ተፈፃሚ የሚደረጉበት ሥርዓት ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ህገ መንግሥታዊነትን ለማስፈን የሚከናወኑ ቀጣይነት ያላቸው ሥራዎችን ለመተግበር ምቹ ምህዳር የሚፈጠርበት ነው፡፡

በኢትዮጵያ የነበሩት ህገ መንግሥቶች የተሟላ ቅርፅ ባይኖራቸውም የበላይ ህግ ተደርገው ሥራ ላይ የዋሉ የተለያዩ ህጎች በተለያዩ ወቅቶች ነበሩ፡፡ ከእነዚህ ህጎች ውስጥ ፍትሃ ነገሥት እና ክብረ ነገሥት ተጠቃሾች ናቸው። ከ1923 ዓ.ም አንስቶ የተለያዩ ይዘቶች ያሏቸው ሦስት ሕግጋተ መንግሥት ሥራ ላይ ውለዋል፡፡ እነዚህም ለመጀመሪያ ጊዜ በ1923 ዓ.ም ሥራ ላይ የዋለው የንጉሰ ነገሥት ህገ መንግሥት ነው። ይህንን ህግ በማሻሻል በ1948 ዓ.ም የፀደቀው እና በወታደራዊ ደርግ መንግሥት ሥራ ላይ የዋለው የ1980 ዓ.ም ህገ መንግሥቶችም ቀሪዎቹ ናቸው፡፡

በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በመንግሥትና በዜጎች መካከል የሚኖርን ግንኙነት፣ የሥልጣን ባለቤትነትና የመንግሥት አወቃቀር መልክ የወሰነው ህግ የአፄ ኃይለሥላሴ ህገ መንግሥት ነው፡፡ ይህ ህገ መንግሥት ንጉሰ ነገሥቱ በመለኮታዊ ኃይል ተመርጠው እንደተሾሙና በፈቃዳቸው ህገ መንግሥቱን ለሕዝቡ እንደሰጡ በግልፅ የተደነገገ ህገ መንግሥት እንደነበር የታሪክ ድርሣናት ያስረዳሉ። የሥልጣን ምንጭ መለኮታዊ ኃይል በመሆኑ የህዝብ ይሁንታ እንደማያስፈልግና ህገ መንግሥቱም የህዝቦች የቃል ኪዳን መገለጫ ሳይሆን በመለኮታዊ ኃይል የተሰየሙት ንጉሰ ነገሥት በፈቃዳቸው ለህዝቡ ያበረከቱለት ስጦታ እንደነበር ያመለክታል፡፡ የሥልጣን ባለቤትነት ከነገሥታቱ ሳይወጣ በዘር ሐረግ የሚተላለፍ እንጂ ህዝብ ለመረጠው አካል አይሰጥም። ከዚህም ባለፈ ሥርዓቱ ያነገሰው አስተሳሰብ ህዝቡ የንጉሱ ሐብት ንጉሱም የፈጣሪ ተወካይ መሆናቸውን እንዲታመን ማድረግ ነው፡፡

በ1948 ዓ.ም ተሻሽሎ የፀደቀው ህገ መንግሥትም ቢሆን መሠረታዊ የይዘትና የዴሞክራሲያዊነት ለውጥ አላመጣም፡፡ ኢትዮጵያን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አባል ለማድረግ፣ ኤርትራን ከኢትዮጵያ በኮንፌዴሬሽን ለማቀላቀልና ምዕራባዊ አስተሳሰብ የህገ መንግሥቱ እሴት መሆኑን ለማመላከት ሲባል ብቻ ህገ መንግሥቱ እንደተሻሻለ ይገልፃል፡፡ በሁለቱም ህገ መንግሥታት ንጉሱ የህግ አውጪነት፣ የህግ አስፈፃሚነትና የህግ ተርጓሚነት ሥልጣን ባለቤት ነበሩ፡፡

የደርግ ወታደራዊ ጁንታ ወደ ሥልጣን የመጣው በ1967 ዓ.ም ላይ ነበር። ደርግ ህገ መንግሥት ያወጣው ደግሞ በ1980 ዓ.ም ነበር፡፡ ደርግ ፍፁም ፀረ ዴሞክራሲያዊ ስለነበር ህዝቡ በተወካዮቹ አማካይነት በህገ መንግሥቱ ማርቀቅም ሆነ በረቂቁ ላይ በቀጥታ በመምከር ወይም በወኪሎቹ በኩል በህገ መንግሥታዊ ጉባዔ ህገ መንግሥቱን በማፅደቅ ሂደት ያደረገው ተሳትፎ አልነበረም፡፡ ደርግ ይከተለው በነበረ ርዕዮተ ዓለም ምክንያት በህገ መንግሥቱ የሰርቶ አደር ህዝብን (የላብ አደርን) የበላይነት ቢደነግግም የርዕዮቱ መሠረት ሊሆን የሚችል ላብ አደር አልነበረም። በተጨማሪም ደርግ የደነገገውን የላብ አደሩን የሥልጣን ባለቤትነት ከህገ መንግሥቱ በፊትና በኋላ በወጡ ህጎች በግላጭ አግዷል፡፡ በቀጣይ ወደ ኢፌዴሪ ህገ መንግሥት መለስ ብለን ልዩ ባህሪያቱን በጥቂቱ እንዳስስ።

የኢፌዴሪ ህገ መንግሥት የአገሪቱን ታሪካዊና ነባራዊ ሁኔታ መሠረት ያደረገና የህዝቦችን መሠረታዊ እምነቶችና ፍላጎቶች የሚወክል ህግ በመሆኑ ከሌሎች የዓለም ምርጥ ህገ መንግሥት አንዱ ያደርገዋል፡፡ ህገ መንግሥቱ ከአገሪቱ ታሪካዊና ነባራዊ ሁኔታ የመነጩ ልዩ ባህርያትንም ይዟል፡፡ ከእነዚህም መካከል የዴሞክራሲያዊ ገፅታ መገለጫዎቹ ተጠቃሽ ይሆናሉ።

የኢፌዴሪ ህገ መንግሥት ከቀደሙቱ በመሠረቱ የተለየና ዘመናዊ ነው፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ የኢትዮጵያ ህዝቦች በየአካባቢያቸው ተወያይተውና ተከራክረው የተስማሙበትና በመረጧቸው ወኪሎች አማካይነት በተቋቋመው ህገ መንግሥታዊ ጉባዔ የበላይ ህግ ሆኖ እንዲፀድቅ ማድረጋቸው ልዩ ያደርገዋል፡፡ ይህም በዓለም አቀፍ መስፈርት ሲመዘን ዘመናዊ የአቀራረፅ ሂደት የተከተለ መሆኑን ያሳያል፡፡ በህገ መንግሥቱ መግቢያ ላይ እንደተገለፀው ሥርዓቱ የተመሠረተበት አስተሳሰብ ወይም ፍልስፍና፣ የሚመራባቸው ራዕይና ዓላማዎች ካለፈው የታሪክ ምዕራፍ በዓይነቱ የተለየ ነው፡፡ ህገ መንግሥቱ ያረጋገጣቸው መብቶች በዓለም አቀፍ መስፈርት ሲታዩ የላቀና ዘመናዊ መሆኑን ያሳያሉ፡፡ በህገ መንግሥቱ ከሰፈሩት 106 አንቀፆች ውስጥ አንድ ሦስተኛው ገደማ ስለሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች የተደነገጉበት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ያፀደቀቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶችም የህገ መንግሥቱ አካል ሆነዋል፡፡ በተጨማሪም የህገ መንግሥቱ የማሻሻያ ሥርዓት ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በቀላል ማሻሻያ እንዳይሸራረፉ ዋስትና ሰጥቷል። የዚህ ህገ መንግሥት ሌላው ባህሪያቱ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን እስከ መገንጠል መብት መፍቀዱ ነው።

ይኸውም የህገ መንግሥቱ አንዱ ልዩ ባህሪ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን እስከ መገንጠል መብት ማረጋገጡ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ህዝቦች የታገሉለት ዋነኛው ዓላማ የራስ አስተዳደርና የጋራ አስተዳደርን የመመሥረት መብት ለመጎናፀፍ፣ ይህም ከተፅዕኖ ነፃ በሆነ መንገድ በፈቃደኝነትና በመተማመን ላይ የተደራጀ ዘላቂ አብሮነት መመሥረት ነው፡፡ ሁለተኛው ዓላማ ይህን መብት በማንኛውም አጋጣሚ ሲቀለበስ ወደቀድሞው የአፈና ሥርዓት ላለመመለስና በሠላማዊ መንገድ ለመፋታት የሚያስችል ፖለቲካዊ ምህዳር ለመፍጠር ነው፡፡

የድንጋጌው መነሻ አብሮ ለመኖር አፈና እንደማያስፈልግ፣ አብሮነቱን ያልፈለገ ማኅበረሰብ ደግሞ ከህብረቱ ለመውጣት በግጭትና በጦርነት መሸኘት የለበትም የሚል መሠረታዊ እምነት ነው፡፡ የመገንጠል መብት ሲያነሱ የነበሩ ማህበረሰቦችና ኃይሎች ይህ መብት በህገ መንግሥት ከተረጋገጠ በኋላ በተግባር በህብረቱ መቀጠላቸውን፣ በጠባብነት አጀንዳ በመሰለብ የመገንጠል ጥያቄ አለን የሚሉ ግለሰቦችና ቡድኖች ፍላጎትም የህዝብ አመኔታ እያጣ መምጣቱ የሚያረጋግጠው ጉዳይ በእኩልነትና በነፃነት ላይ የተመሠረተ አብሮነትና ሕብረ ብሄራዊነት ፖለቲካዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊና ማህበራዊ ጥቅሞች ማምጣት እንደቻለ ነው፡፡

የግለሰብና የጋራ መብቶችን ያጣመረ መሆኑም ሌላው የኢፌዴሪ ህገ መንግሥት ባህሪያት ሆነው ይቀርባሉ። የግለሰብና የጋራ መብቶች በበርካታ አገራት ህገ መንግሥታት ጥበቃ ለማድረግ ይሞከራል፡፡ ነገር ግን በአተገባበራቸው ላይ ከአገር አገር ሰፊ ልዩነቶች ይታያሉ፡፡ የግለሰብ መብት ሲከበር እግረ መንገዱን የጋራ መብትም ይከበራል የሚልና የጋራ መብቶች ተለይተው ከተረጋገጡ የግለሰብን መብቶች ለማፈን መሣሪያ ይሆናሉ የሚል አስተሳሰብ ገዥ ቦታ ይዞ ይገኛል፡፡

የኢፌዴሪ ህገ መንግሥት ከዚህ አስተሳሰብ በዓይነቱ የተለየ እምነትን መነሻ በማድረጉ ሁለቱን መብቶች ሙሉ ጥበቃ ያደርግላቸዋል፡፡ ህገ መንግሥቱ በአንድ በኩል እነዚህ መብቶች በአገሪቱ ሁኔታ ተነጣጥለው ሊሄዱ የሚችሉ አይደሉም ብሎ ይወስዳል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በአንዱ መብት መከበር ስም የሌላው መብት እንዲረገጥ ቦታ የሚሰጥ አይደለም፡፡ በአፈፃፀም ሂደትም አንዱን መብት ለማስጠበቅ ሲባል ሌላውን መብት መደፍጠጥ አያስከትልም፡፡ የቡድን መብቶች የሚፈለጉትና ፋይዳ የሚኖራቸው እንደ ቡድን ተገቢውን የፖለቲካ፣ የምጣኔ ሀብትና የማህበራዊ ጥቅሞችን ለማረጋገጥ ነው፡፡ የቡድን መብቶች የማንነት የጋራ መገለጫዎች በመሆናቸው በተናጠል በግለሰብ ደረጃ ተጠይቀው መልስ ሲሰጣቸውና በዚህ አማካይነትም የቡድን መብቶች መፍትሄ ሊያገኙ አይችሉም፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብ የመሬት ባለቤትነት ጥያቄ አንስቶ ‘መሬት ላራሹ’ በሚል መፈክር ወሣኝ ትግል አካሂዷል፡፡ ህገ መንግሥቱ ይህንን ጥያቄ የመለሰበት መንገድ በዓለም ከታዩ ልምዶች በዓይነቱ የተለየ ነው ማለት ይቻላል፡፡ የመሬትና የተፈጥሮ ሐብት ባለቤትነት የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት መሆኑን በመጥቀስ “መሬት የማይሸጥ የማይለወጥ የኢትዮጵያ ብሄሮች ብሄረሰቦች ህዝቦች የጋራ ንብረት ነው” የሚል ድንጋጌ አስፍሯል፡፡ በአገሪቱ ሁኔታ መሬት ዋነኛ የሐብት ምንጭ በመሆኑ አርሶ እና አርብቶ አደሮች በመሬት ላይ ያልተገደበ የመጠቀም መብት ተጎናፅፈዋል፡፡ ተጠቃሚው አርሶ አደር ወይም አርብቶ አደር ራሱ ተጠቅሞ ለልጆቹ የማስተላለፍ መብትም ተረጋግጦለታል፡፡ በመሬቱ ላይ ሰርቶ፣ ጥሮና ግሮ ገደብ የሌለው ምርት የማፍራትና ምርቱን በነፃ ገበያ በመረጠው ዋጋ የመሽጥ መብቱ ያለገደብ ተረጋግጦለታል፡፡ መሬት የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የጋራ ንብረት በመደረጉ ከመሬት ያለመነቀል ዋስትና የሚሰጥና የፍትሃዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጫ መሣሪያ ሆኗል፡፡

ሌላው የኢፌዴሪ ህገ መንግሥት ባህሪያት ተብለው ከሚጠቀሱት መካከል በቁጥር አናሳ የሆኑ ህዝቦች እንደ ሌሎቹ ማኅበረሰቦች በቋንቋቸው የመጠቀም፣ ታሪካቸውን የመግለፅ፣ ባህላቸውንና ልዩ መገለጫዎቻቸውን የማሳደግና የራሳቸውን ዕድል በራሳቸው የመወሰን መብት ማረጋገጡ ነው። በፌዴሬሽን ምክር ቤት ፍትሃዊ ውክልና የማግኘት መብታቸው ዋስትና አግኝቷል፡፡ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም ከ20 የማያንስ መቀመጫ እንዲኖራቸው በህገ መንግሥቱ ተደንግጓል፡፡ ይህ መብት በአሁኑ ጊዜ አናሳ ማኅበረሰቦች በተወካዮች ምክር ቤት በ23 መቀመጫ እንዲወከሉ አስችሏል፡፡ አናሳ ማኅበረሰቦችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የምጣኔ ሐብትና ማህበራዊ ዓላማዎች በህገ መንግሥቱ ላይ ሰፍረዋል፡፡ ይህም የሚያሳየው ፌዴራል ሥርዓቱ አናሳ ማኅበረሰቦች የመብት ጥያቄዎች እስኪያነሱ ድረስ ሳይጠበቅ ህገ መንግሥቱን ከጅምሩ ለፖለቲካዊ፣ ምጣኔ ሐብታዊና ማህበራዊ መብቶቻቸው የተሟላ መልስ መስጠቱ ነው፡፡ ይህ ነው የኢፌዴሪ ህገ መንግሥት ከሌሎች ተመራጭ ብቻ ሳይሆን የተለየ ነው ብሎ በድፍረት ለመናገር የሚቻለው።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy